ሁለት እግር አለኝ ተብሎ ሁለት ዛፍ ላይ አይወጣም ይላሉ አባቶች፤ የምርጫን የግድነት ለማመልከት ነው፡፡ ልክ አሁን እኛ እንደ አገር ካለንበት ሁኔታ ላይ ሲደርስ የሚተረት ነው፡፡ እንደ አገር ሰላምን እንፈልጋለን። እንደገና እንደ አገር ሙሉ ወታደራዊ ድልንም እንፈልጋለን። ምኞቱ ምንም ክፋት የለውም፡፡ አገርን ከመውደድ እና አዋጪው ዘላቂው መንገድ ይህ ነው ብሎ ከማሰብ ነው፡፡ ችግሩ ሁለቱንም በእኩል ሰዓት ማግኘት አለመቻሉ ላይ ነው። ዘላቂ ሰላምን ከፈለግን ለጊዜውም ቢሆን የጦር ሜዳ ፍጹማዊ ድል ፍላጎታችንን ልንገታው ይገባል፡፡
ብዙዎች ሠራዊቱ ወደ ትግራይ ክልል ዘልቆ ባለመግባቱ ቅር ተሰኝቷል፡፡ ስጋታቸው ግልጽ ነው፡፡ አሸባሪው ኃይል በድጋሚ ትንፋሹን ሰብስቦ ተደራጅቶ ሌላ ችግር እንዳይፈጥር ከመስጋት ነው፡፡ ይህ ቅሬታ እያለ ደግሞ መንግሥት ሌላ እርምጃ ወሰደ፡፡ በተለያዩ ወንጀሎች በመጠርጠር ክስ ከመሰረተባቸው የትህነግ የፖለቲካ አመራሮች አንዳንዶቹን ፈታ፡፡
ይህ ሁኔታ በቀደመው ውሳኔ ቅር ተሰኝተው ለነበሩ ሰዎች በሙሉ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ የሚባለውን ስሜት ፈጠረባቸው፡፡ ምናልባት ከዚህ በኋላም የሚመጡ ውሳኔዎች የእነዚህን ሰዎች ስሜት ጨርሶ ሊረብሹት ይችላሉ፡፡ ሊታወቅ የሚገባው ጉዳይ ይሄ ሁሉ የሚደረገው ሕዝብን ለማስከፋት ወይም ለማስደሰት ተብሎ አለመሆኑ ነው፤ የአገርን ጥቅም ለዘለቄታው ማስከበር ሲባል የተደረገ መሆኑ ነው፡፡
ነፍሳቸውን ይማረውና ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ኢትዮጵያ ውስጥ የአገር የሕዝብ እና የመንግሥት ፍላጎት ተመሳስለው አያውቁም ብለው ነበር፡፡ እውነታቸውንም ነው፡፡ መቅደም የነበረበት የአገር ጥቅም ነው፡፡ ያለፉት መንግሥታት ግን ከዚህ በተቃራኒው የመጨረሻው ፍላጎት የሆነውን የመንግሥት ፍላጎት ሲያስቀድሙ ኖረዋል፡፡
በዚህም የተነሳ ሁሌም ሕዝብ እንደ ተማረረ አገርም እንደተጎዳች ኖረዋል፡፡ በሌላ መልኩ መሪዎች የሕዝበኝነት ባህሪ ሲያይልባቸው የሕዝብን ፍላጎት ለማሟላት የሚያደርጓቸው ጥረቶች ለዘለቄታው አገርን የሚጎዱ ሆነው ይገኛሉ፡፡ ልባም መሪዎች ግን ተለዋዋጭ ከሆነው የሕዝብ ፍላጎት እንዲሁም ከማይጠረቃው የመንግሥት ፍላጎት ይልቅ ዘላቂውን የአገር ጥቅም ያስቀድማሉ። ይህ እርምጃ ለጊዜው ቢወቀሱበትም በዘለቄታው ግን የሚመሰገኑበት ተግባር ይሆናል፡፡
ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆኑ ታሪኮችን ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመከላከያ ሠራዊቱን ዋና መምሪያ አዲስ ሕንጻ በመረቁበት ወቅት በብዙ ቀደምት ታሪኮች አመላክተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጠቀሷቸው የቀደምት መሪዎች ዛሬ ላይ በታሪክ የታወሱት በጊዜው የነበረባቸውን ጫና ተቋቁመው ከራሳቸው ስልጣንም ሆነ ከሕዝባቸው ጊዜያዊ መሻት ባለፈ ለአገር የሚጠቅመውን ውሳኔ በመወሰናቸው ነው፡፡
ነገር ግን አሁን ዘመኑ ተቀይሯል፡፡ ፖለቲካዊ ውሳኔዎችን ከግለሰብ በጎ ስሜት ጋር የማያያዝ እና ግለሰቡን የማሞገስ ጊዜው አልፏል፡፡ ውሳኔዎች የጋራ እና ሕዝባዊ የመሆን ግዴታን የሚጠይቅ ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡ ይህም ማለት የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ እና የፓርቲያቸው ውሳኔ ብቻ ሳይሆን የሕዝብ ውሳኔም አስፈላጊ የሚሆንበት ወቅት ነው፡፡
ሕዝብ ምን ይወስን? ታዲያ እንግዲህ ሕዝብ መወሰን ያለበት ለጊዜው ካለበት የቅሬታ ስሜት ይልቅ ዘላቂውን የአገሩን ጥቅም አስቀድሞ አንዳንድ መስዋዕትነቶችን ሊከፍል ዝግጁ መሆን አለበት፡፡ የሚተላለፍ ውሳኔ የመሪ ሳይሆን የትውልድ ውሳኔ መሆን አለበት፡፡ ይህ ትውልድ ሁለት እግር አለኝ ብሎ ሁለት ዛፍ ላይ የመውጣት ፍላጎትን ትቶ አዋጪውን እና ዘላቂውን ውሳኔ በማሳለፍ ለቀጣይ ትውልዶች የቤት ስራውን ማቅለል አለበት፡፡
ይህ መስዋዕትነት የመክፈል ታሪክ እኛ የጀመርነው አይደለም፡፡ ከዚህ ቀደም በሌሎች አገራትም የተሄደበት እና ያዋጣ ነው፡፡ ለዚህ በተለይ ጥሩ ምሳሌ መሆን የምትችለው ደቡብ አፍሪካ ናት፡፡ በአፓርታይድ መውደቅ ወቅት የነበረው የደቡብ አፍሪካ ትውልድ እንዲወስን የተገደደው ለብዙ መቶ ዓመታት በነበረው የቀደምቶቹ ጥያቄ እና ቅሬታ ላይ ነበር፡፡ ያ የደቡብ አፍሪካ ትውልድ አባቶቹ ያላጋጠማቸውን እድል ነው ያጋጠመው፡፡ አባቶቹ በባርነት ወድቀው ሲማቅቁ ስለኖሩ ይህን የነጻነት እድል እና የመወሰን መብት አላገኙም ፡፡
እሱ ያንን እድል ሲያገኝ የአባቶቹን በደል ለማወራረድ እድል አግኝቶ ነበር፡፡ ብዙዎችም የጠበቁት ያንን እንዲያደርግ ነበር፡፡ ነገር ግን ያንን አላደረገም፡፡ ይልቁንም በውስጡ ያለውን የበቀል ስሜት ዋጥ አድርጎ ለከርሞው አገሪቱን የሚራምዳትን ውሳኔ አሳለፈ፡፡ በባርነት ሲረግጡት ከነበሩ ሰዎች ጋር ለመመካከር በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀመጠ፤ መከረም፡፡
አንዳንድ መስጠት የማይፈልገውን ነገርም ሰጠ፤ አንዳንድ መቀበል የሚፈልገውንም ነገር ተቀበለ፡፡ ማንም በተለይ አላተረፈም፤ ማንም የባሰ አልከሰረም፡፡ ደቡብ አፍሪካ ግን እንደ አገር አተረፈች፡፡ እነሆ ደቡብ አፍሪካ የአፍሪካ መሪ እንደሆነች ሶስተኛ አስር ዓመቷ ላይ እየተቃረበች ነው፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን እንዲህ አይነት ተግባርን በኢትዮጵያዊ ወግ ለኢትዮጵያ በሚመች መልኩ እንድንከውነው ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ሲባል ለጊዜውም ቢሆን አፈሙዝን ዝቅ ማድረግ ፤ አንዳንድ አደገኛ ሀሳብ ያላቸው የሚመስሉንን ሰዎች ወደ ጠረጴዛው ማምጣት ያስፈልጋል፡፡
ፍጹም ልንደራደርባቸው አንችልም የምንላቸው ጉዳዮችን ለመስማት ጆሮአችንን ማዘጋጀት አለብን፡፡ ይሄ ለሰላም የሚከፈል ዋጋ ነው፡፡ ይሄ እንደ ሕዝብ የሚከፈል መስዋዕትነት የሠራዊታችንን ወታደራዊ ድል ፖለቲካዊ መሠረት ለማስያዝ ይጠቅማል፡፡
ይህ መስዋዕትነት የአገርን ሉዓላዊነት እና አንድነት ለማስጠበቅ ያስፈልጋል፤ ይሄ መስዋዕትነት ታሪካዊ ቁርሾዎችን ለመፍታት እና ያመረቀዙ ቁስሎችን ለማከም ይበጃል፤ ይህ መስዋዕትነት ባለፉት ዓመታት በመንግሥትም በተቃዋሚዎችም የተደረጉ የፖለቲካ ስሌት ስህተቶችን ማስተካከያ እድል ይፈጥራል፤ ይህ መስዋዕትነት የኢትዮጵያ ጠላቶች ገብተው የሚፈተፍቱበትን የክፋት እጅ ይቆርጣል፤ ይህ መስዋዕትነት ወዳጆቻችን ሊደግፉበት የሚችሉትን ትክክለኛውን አቅጣጫ ይጠቁማቸዋል፤ ከሁሉም በላይ ይህ መስዋዕትነት ባለፉት ጥቂት ዓመታት የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዝቶ ሲናፍቀው የነበረውን ዘላቂ ሰላም ለማግኘት በር ይከፍታል፡፡
ይህ ሁሉ መስዋዕትነት ሲፈጸም በደንብ ሊታሰብ የሚገባው ነገር አለ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጦሩ ወደ ትግራይ እንዳይገባም ሆነ የእስረኞች ክስ እንዲቋረጥ ሲያደርግ የውሳኔው መሠረት ሉዓላዊነት ፤ ብሔራዊ ጥቅም እና አገራዊ ክብር እንደሆነ ገልጸዋል፤ መልካም ነው፡፡ ሕዝብም ቀጣይ መስዋዕትነት ሊከፍል ሲነሳ እነዚህን መሠረታዊ ነገሮች ማሰብ ይኖርበታል፡፡
ማንኛውም የብሔር ስሜት ፤ የቡድን ጉድኝት ፤ የጥቅም ትስስር ፤ ዝምድና ፤ የሃይማኖት መመሳሰል ከሉዓላዊነት ከብሔራዊ ጥቅም እና አገራዊ ክብር በላይ የሚሆን ቦታ ሊሰጣቸው አይገባም፡፡ ሁሉም ነገር ለኢትዮጵያ አንድነት ፤ ክብር እና ሰላም በሚመጥን መልኩ ብቻ መካሄድ አለበት፡፡ ቀጣይ የሚካሄደው ድርድር እና ውይይትም ጊዜያዊ የሆነ መፍትሔ ለማምጣት ፤ አንድን ቡድን ለማስደሰት ፤ የመንግስትን ሥልጣን ለማደላደል ወይም ለሌሎች ምክንያቶች ሳይሆን፣ ለዘለቄታው አገራችንን በጽኑ መሠረት ላይ ለማስቀመጥ ብቻ መሆን ይኖርበታል፡፡
ከዚያ ባለፈ ዘላቂ ሰላምም ፈልጎ ጦርነቱም እንዳይቆም ፈልጎ ፤ አንድነትም ፈልጎ ድርድርንም ጠልቶ አይሆንም፡፡ ሆደ ሰፊ መሆን ያስፈልጋል፡፡ አሁን ጊዜው ሁለት ዛፍ ላይ መንጠላጠያ ሳይሆን የዘላቂ ሰላምን ዛፍ የምናለመልምበት ነው፡፡
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን ጥር 11/2014