አካል ጉዳትን መሠረት አድርገው ከሚካሄዱ ስፖርታዊ ውድድሮች መካከል አንዱ የዊልቼር ቅርጫት ኳስ ነው:: በየጊዜው ተወዳጅነቱ እየጨመረ የመጣው ይህ ስፖርት በዚህ ወቅት 100ሺ የሚሆኑ ለመዝናናት፣ በክለብ ደረጃ እንዲሁም በብሔራዊ ቡድን ደረጃ በታቀፉ አካል ጉዳተኞች እንደሚዘወተር የዓለም አቀፉ ዊልቸር ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን መረጃ ይጠቁማል::
የዓለም አቀፉ ፓራሊምፒክ ኮሚቴ አባል በመሆንም በየአራት ዓመቱ በሚካሄደው ትልቁ ፓራሊምፒክ ውድድር ላይ ይህ ስፖርት ፉክክር የሚደረግበት ነው:: በአፍሪካ እና በኢትዮጵያ ስፖርቱ ዘግይቶ ይተዋወቅ እንጂ የተሳታፊዎቹን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ በማሳደግ ላይ ያለ ተዘውታሪ ስፖርት እየሆነም ይገኛል::
ይህንንም ተከትሎ በኢትዮጵያ ከሁለት ዓመት በፊት በአሶሴሽን ደረጃ ከመቋቋምና ስፖርቱን በአገሪቷ ተዘውታሪ እንዲሆን ከማድረግ ባለፈ በአጭር ጊዜ የአፍሪካ እና የዓለም አቀፉ የዊልቼር ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን አባል ለመሆን ችሏል::
አሁን ደግሞ በአገር ውስጥ ዓመታዊ ውድድሮችን ከማስተናገድ ባለፈ አህጉር አቀፍ ሻምፒዮናም በኢትዮጵያ ለማካሄድ በቅቷል::
አሶሴሽኑ ባገኘው የአስተናጋጅነት ዕድል መሠረትም የአፍሪካ ዊልቼር ቅርጫት ኳስ ሻምፒዮና በአፍሪካ መቀመጫ በሆነችው አዲስ አበባ መጪው እሁድ ጥር 15/2014 ዓ.ም ጀምሮ የሚካሄድ ይሆናል:: በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚካሄደው ሻምፒዮና እንደ ማጣሪያ የሚያገለግለው ይህ ውድድር ለሰባት ቀናት የሚቆይ ይሆናል::
በሻምፒዮናው ላይ የተለያዩ ስምንት የአፍሪካ አገራት በወንድ ቡድኖቻቸው እንዲሁም ስድስት አገራት ደግሞ በሴት ቡድኖቻቸው ተካፋይ እንደሚሆኑም አሶሴሽኑ ጠቁሟል። ኢትዮጵያም በሁለቱም ጾታ ማጣሪያውን ስትሳተፍ፤ በሁለቱም ጾታ 12 ተጫዋቾች ተመርጠው ከወራት በፊት ወደ ዝግጅት እንዲገቡ ተደርጓል።
ለውድድሩ ሲደረግ ከቆየው ቅድመ ዝግጅት ባሻገር ኢትዮጵያን የሚወክለው ቡድን ውጤታማ እንዲሆንም የተለያዩ ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየቱም የሚታወስ ነው::
የአፍሪካ ዊልቼር ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ቻርለስ ሳውንደርስ እንዲሁም በፌዴሬሽኑ ሌሎች ባለሙያዎች የውድድሩን ቅድመ ዝግጅት ለመገምገም አዲስ አበባ ተገኝተው የመስክ ምልከታ አድርገዋል:: በዚህም ኢትዮጵያ ውድድሩን ለማስተናገድ የሚያስችል የማዘውተሪያ ስፍራዎች እንዲሁም ሌሎች ግብዓቶች እንዳሏት አረጋግጠዋል::
በኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር ከተደረገው የበጀት ድጋፍ ባለፈ ለአሶሴሽኑ ድጋፍ የሚውልና አንድ ሚሊዮን ብር የሚገመት 19 ዊልቼር እና የ250 ሺ ብር ድጋፍ በዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ መደረጉ ተጠቃሽ ነው።
የኢትዮጵያ ፖራሊምፒክ ኮሚቴም ለብሔራዊ ቡድኑ የትጥቅ ድጋፍ አበርክቷል። በዚህም ዝግጅቱ እንደተጠናቀቀ የተገለፀ ሲሆን፤ ውድድሩ በሚካሄድበት የራስ ኃይሉ ስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከል ምልከታ መደረጉን የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር አስታውቋል:: የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት፤ በቦታው ተገኝተው ምልከታ አድርገዋል::
ቡድኑ ጠንካራ ተወዳዳሪ እና አሸናፊ ሆኖ ማጣሪያውን በማለፍ በቀጣይ ኢትዮጵያን ወክሎ በዓለም አቀፍ የዊልቼር ቅርጫት ኳስ ውድድር ለመሳተፍ መትጋት እንዳለበትም መልዕክት አስተላልፈዋል ።
የኢትዮጵያ ዊልቼር ቅርጫት ኳስ አሶሴሽን ፕሬዚዳንት አቶ አባይነህ ጉጆ በበኩላቸው፤ መንግሥት ለፌደሬሽኑ እያደረገ ያለውን ድጋፍ በማድነቅ ውድድሩ የአገር ጉዳይ መሆን መቻሉ እንዳስደሰታቸውም የሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ መረጃ ያመለክታል::
በየአራት ዓመቱ የሚካሄደውና በስፖርቱ ትልቁ መድረክ የሆነው የዓለም ዊልቼር ቅርጫት ኳስ ሻምፒዮና በቀጣዩ ዓመት ለ14ኛ ጊዜ በዱባይ ይካሄዳል::
በዓለም አቀፉ የዊልቼር ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን አዘጋጅነት በሚካሄደው በዚህ ውድድር ላይም 16 የወንድ እና 12 የሴት ቡድኖች ተሳታፊዎች ናቸው:: አፍሪካም በውድድሩ ላይ በአንድ የወንድ እና በአንድ የሴት ቡድኖች ትወከላለች::
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጥር 10/2014