ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ በበጎ ገጽታ እንድትነሳ ከሚያደርጓት ጉዳዮች መካከል ቀዳሚው የአትሌቲክስ ስፖርት ነው። በዚህ ስፖርት ሃገሪቷ ስኬታማ ከሆኑ ሃገራት መካከል የምትጠቀስና በዓለም አቀፍ ደረጃ ዝነኛ የሆኑ በርካታ አትሌቶችን ያፈራች ብትሆንም አሁንም ድረስ ግን ስፖርቱ የሚከወነው በተለምዷዊ መንገድ ነው። ከስልጠና ጀምሮ እስከ ውድድር ባለው ሂደት የሃገር ውስጥ እንቅስቃሴዎች በሳይንሳዊና ዘመናዊ አሰራር ሳይሆን ኋላ ቀር በሆነ ሁኔታ እንደሚካሄድ እሙን ነው። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንም ይህንን ችግር በመቅረፍ ከሌላው ዓለም እኩል በዘመናዊ እና በቴክኖሎጂ እገዛ እንዲካሄድ የተለያዩ ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል።
በተያዘው ዓመትም ይህንኑ ተግባር ለማጠናከር ያቀደው ፌዴሬሽኑ፤ ውድድርን በቴክኖሎጂ እንዲደገፍ ለማድረግ የሚያስችሉ መሳሪያዎችን በግዢ ወደ ሃገር ውስጥ ማስገባቱን አስታውቋል። በሃዋሳ ከተማ በተካሄደው የፌዴሬሽኑ 25ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ በእቅዱ ላይ ገለጻ ባደረገበት ወቅት፤ ዘጠኝ ሚሊየን ብር የወጣባቸው መሳሪያዎችን ግዢ ፈጽሟል። በመሆኑም ከዚህ በኋላ ውድድሮችን እንደ ቀድሞ በሰዎችና ኋላ ቀር በሆኑ መሳሪያዎች እንዲመሩ ከማድረግ ይወጣል። በዚህም ምክንያት ከአትሌቱ የሚቀርበውን ቅሬታ እንዲሁም በሰዓት አያያዝ የሚገጥሙ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል መፍትሄ ነው። በቁጥር በርካታ እንደሆኑ የተጠቆሙት መሳሪያዎቹ ሌላው ዓለም በትልልቅ ውድድሮች ላይ የሚጠቀመው መሆኑን ተከትሎም ከዚህ ቀደም ለሰዓት ማሟያ በሚል ወደ ሌሎች ሃገራት የሚደረጉ ጉዞዎችን የመቅረፍ አቅም አለው።
የውድድር ማስጀመሪያ፣
በእርግጥ መሳሪያዎቹ በሚያስፈልጉት ልክ ሙሉ ለሙሉ ግዢ ያልተፈጸመባቸው ሲሆን፤ የሜዳ ተግባራት ግብዓት የሚሆኑ መሳሪያዎችና ሌሎችም በቀጣይ ወደ ሃገር ውስጥ ይገባሉ። ዳኞችም የመሳሪያውን አጠቃቀም ተረድተው ውድድሩን በአግባቡ መምራት እንዲችሉ ስልጠና እየተሰጣቸው ሲሆን፤ ለተጨማሪ ግንዛቤና ባለሙያዎችን ለማብቃት ከዛምቢያ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ኬንያ ባለሙያዎችን ለማምጣት ጥረት እየተደረገ ነው።
ከዚህ ቀደም ለሁለት ጊዜያት ሙከራ የተደረገባቸው ሲሆን፤ በቀጣይ በሚካሄደው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቻምፒዮናም በተሻለ ስልጠና መሳሪያዎቹ አገልግሎት ላይ እንደሚውሉም ፌዴሬሽኑ አስታውቋል። ይህም በውድድሮች የሚመዘገቡ ውጤቶችን አውቶማቲክ ስለሚያደርግ በቀጥታ በዓለም አትሌቲክስ ተቀባይነትን ያገኛሉ። ኢትዮጵያ በዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና እንዲሁም ሌሎች ውድድሮች ተሳታፊ ለመሆን በሌሎች ሃገራት የምታደርገውን የሰዓት ማሟያ ውድድርም በማስቀረት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንደሚሰጥ በእቅዱ ላይ ተመላክቷል።
በጠቅላላ ጉባኤው በሙሉ ድምጽ የጸደቀው እቅዱ፤የባለ ድርሻ አካላት ድጋፍን በማሳደግ፣ በመሰረተ ልማት፣ መሳሪያና ትጥቆች፣ የስልጠና ባለሙያዎችን ማሳደግ፣ የአገርና ዓለም አቀፍ ውድድሮችን በማዘጋጀትና በማሳተፍ እንዲሁም ውጤታማነትን ማረጋገጥም ከዕቅዶቹ መካከል ተጠቅሷል። በአገር አቀፍ ደረጃ ካሉት 4 የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከላት ባሻገር በኦሮሚያ ጎሬ፣ በደቡብ ክልል ጂንካ እንዲሁም በአማራ ክልል ተንታ አዳዲስ ማዕከላት መከፈታቸውን ተከትሎም ድጋፉን ማጠናከር ከፌዴሬሽኑ እቅዶች መካከል ተጠቃሏል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቻምፒዮናን በሚመለከትም የአዲስ አበባ ስታዲየም መምና ሜዳ በጥገና ላይ በመሆኑ፤ በተቀያሪነት ውድድር የሚካሄድበት የኢትዮጵያ ወጣቶች አካዳሚም ለውድድሩ አመቺ ባለመሆኑ ምክንያት ከአዲስ አበባ ውጪ ለማካሄድ መታቀዱም በዕቅዱ ተመላክቷል። ለዚህም የባህር ዳር እና ሃዋሳ ስታዲየሞች ታጭተዋል። በተመሳሳይ ሌሎች ውድድሮችን ለማድረግ አስገዳጅ ሁኔታዎች ሲገጥሙ ከአዲስ አበባ ውጪ ውድድሮች እንደሚካሄዱም ተጠቁሞ በጉባዬተኛው ጸድቋል።
በተመሳሳይ የ2013 ዓ.ም የፌዴሬሽኑ እቅድ አፈጻጸም የቀረበ ሲሆን፤ በእቅዱ መሰረት ያልተከናወኑና እንደ ክፍተት የተነሱ ጉዳዮች በእቅዱ እንዲካተቱ ተደርገዋል። ይኸውም የዘመናዊ ጂምናዚየም እና ህክምና ማዕከል ግንባታ፣ የለገዳዲ ለገጣፎ የጥርጊያ መሮጫ በተያዘው ጊዜ አለመጠናቀቅ፣ የአዲስ አበባ ስታዲየም መም በጫና ብዛት ጉዳት ማስተናገዱ፣ የመረጃ አያያዝ ስርዓት የተቀናጀ ባለመሆኑ ያለ እድሜ በውድድር ላይ የመካፈል ችግር፣ በታዳጊ ውድድሮች ላይ የአትሌቶች ተገቢነት እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮች በዓመቱ ትኩረት ተሰጥቶባቸው የሚሰሩ መሆናቸው ተመላክቷል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጥር 9/2014