እንደምን ሰነበታችሁ ልጆች፣ ስላም ናችሁ? በጣም ጥሩ ልጆች፣ በጣም ጥሩ!!! ልጆች ከሳምንት በፊት “ልጆችና መጻሕፍት” በሚል ርእስ ባስነበብኳችሁ ጽሑፍ መጻሕፍትን ማንበብ ለልጆች የሚሰጠውን ጥቅም፤ በአጠቃላይም የንባብን ፋይዳ ነግሬያችሁ ነበር።
እግረ መንገዴንም ጽሑፉ ከመውጣቱ ከአንድ ቀን በፊት ስለ ተመረቀው ግዙፉና ዘመናዊው አብርኈት ቤተመጻሕፍት አንዳንድ ሀሳቦችን አካፍያችኋለሁ።በተለይም ለቤተ መጻሕፍቱ ያለኝን አድናቆት ገልጬላችሁ እንደ ነበር አስታወሳችሁ አይደል? በጣም ጥሩ ልጆች፣ በጣም ጥሩ። ዛሬ ሙሉ ለሙሉ ስለዚሁ ቤተ መጻሕፍት አጫውታችኋለሁና ተከታተሉኝ።
በተለይም ለእናንተ ለልጆች ምን ምን ትሩፋቶችን ይዞ እንደ መጣ እነግራችኋለሁና ከእኔ እንዳትለዩ።
ዛሬ ስለ ዘመናዊው አብርኈት ቤተ መጻሕፍት እንድንጨዋወት የፈለኩት ስለዚህ ዘመናዊው ቤተ-መጻሕፍት በሚገባ ማወቅ፣ ማድነቅ፣ መጠቀም፣ መረዳትና ማስረዳት ስላለባችሁ ነው፤ እሺ ልጆች ግልፅ ነው? በጣም ጥሩ፤ አዎ ቤተመጻሕፍቱ ለሁሉም እንዲሆን ታስቦ የተገነባ በመሆኑ ሁሉንም ሰው እጁን ዘርግቶ በመጠባበቅ ላይ ሲሆን፤ የመጡለትንም እጁን ዘርግቶ እየተቀበለ ነው።
ልጆች፣ ይህ ቤተ-መጻሕፍት በአይነቱም ሆነ አደረጃጀቱ እንዲሁም በመስተንግዶው እስከ ዛሬዎቹ ለየት ይል ዘንድ ምክንያት የሆነው የእስከ ዛሬዎቹ የሌላቸውን እሱ ይዞ መገኘቱ ነው። በተለይ አንድ እራሱን የቻለ፣ ለዛውም የመጀመሪያው ወለል ላይ፣ የልጆች ዘመናዊው ቤተ-መጻሕፍትን አካትቶ ይገኛል።አዎ ልጆች፣ ገና ወደ ቤተ-መጻሕፍቱ ስትገቡ ፊት ለፊት ወደ ቀኝ ባደላ መልኩ የምታገኙት ዘመናዊውን “የልጆች ቤተመጻሕፍት” ነው።
ልጆች በዚህ ቤተ-መጻሕፍት ውስጥ ለልጆች የሚሆኑ፣ ለልጆች ታስበው የተሠሩ መገልገያ ቁሶች (ወንበር፣ ጠረጴዛ…) ተዘጋጅተው የምታገኙ ሲሆን፤ መጻሕፍቱም ለልጆች ብቻ ታስበው የተዘጋጁ፣ የተደረደሩ ናቸው።
ይህ ብቻ አይደለም ልጆች፣ የፈለጋችሁትን ለመሥራት (ለምሳሌ ሥዕል) ብትፈልጉ ምቹ ጠረጴዛዎች ከአስፈላጊ መሣያ ቁሶች ጋር ታገኛላችሁ።እውነትም ቦታው በትክክል “የልጆች ቤተ-መጻሕፍት” የሚያሰኙት በርካታ ነገሮችንም ይዟል ትላላችሁም። ልጆች፣ እሱ ብቻ አይደለም፤ የራሳችሁንም ቁሶች ይዛችሁ በመምጣት መጠቀም የምትችሉ መሆናችሁን ስነግራችሁ ደስ እንደሚላችሁ በመተማመን ነው።
ከእርሳስና እስኪሪቢቶ ጨምሮ ንፁህ ወረቀቶች ወዘተ ይዛችሁ በመምጣት መጠቀም ትችላላችሁ። ስለዚህ ይህንን ጽሑፍ ካነበባችሁበት ጊዜ ጀምሮ “ወዴት ልሂድ?” በተለይ እረፍት ስትሆኑ “የት ላሳልፍ?” የሚለው ጥያቄ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በምርቃት ሥነ ስርአቱ ላይ “ቤተ-መጻሕፍቱ ኢትዮጵያን የሚመጥን” ወዳሉለት ወደ “4 ኪሎ አብርኈት ቤተ-መጻሕፍት” የሚል መልስ አገኘ ማለት ነውና እንኳን ደስ አላችሁ!!! ልጆች ይህ በ19 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈውና ከአንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት ቤተ መጻሕፍቱ ዓለም አቀፍ ደረጃው የጠበቀና የሚያምር የኪነ-ህንጻ ጥበብ ያረፈበት ነው።በአንድ ጊዜ ከ2ሺህ በላይ ተጠቃሚዎችን ማስተናገድ የሚችል ሁለ-ገቡ አብርኈት ቤተ-መጻሕፍትም ነው።
በውስጡ “የልጆች ቤተ-መጻሕፍት”ን ብቻ አይደለም የያዘው።ቤተመጻሕፍቱ በውጪውም ለእናንተ ለልጆች ብቻ የሚሆን ተብሎ ጥሩ ጥሩ የእረፍት ማሳለፊያ ስፍራዎችን ተዘጋጅተዋል።ስትፈልጉ ዥዋዥዌ፣ ስትፈልጉ አባሮሽ፣ ስትፈልጉ … ሌሎች ብዙ ብዙ አይነት ጨዋታዎችን በግል አለያም በቡድን ልትጫወቱባቸው ትችላላችሁ።
ልጆች ይህንን ሁሉ የያዘና የእውቀት ማእድ የሆነው “የልጆች ቤተ-መጻሕፍት” ይዞላችሁ የመጣውን አገልግሎት ስነግራችሁ አንድ ያልነገርኳችሁ ነገር እንዳለ ልብ አላላችሁም? አዎ፣ ይህንን ሁሉ ስታደርጉ አንድ ከእናንተ፣ ከዛሬ አበባዎች የነገ ፍሬዎች ከሆናችሁት የሚጠበቅ ትልቅ ተግባር አለ። ይህም ተግባር በአጠቃላይ ስሙ “ሥነ-ምግባር” በመባል ይታወቃል። ልጆች ከማናቸውም ስፍራዎች በበለጠ፤ ከየትም ቦታ በተሻለ ቤተ-መጻሕፍት ከፍተኛ ፀጥታን ይፈልጋሉ።
መረበሽ ብሎ ነገር የለም፤ መጮህ የለም፣ መንጫጫት የለም፣ በአጠቃላይ ኮሽ ማለት የለም። በተለይ የሞባይል ጩኸትማ ኦኦኦ ….. የሚታሰብ ነገር አይደለም፤ ያስጠይቃል፣ ያስቀጣልም። ይህንን ጉዳይ በተመለከተ፣ ለምን ፀጥታ እንደሚያስፈልግ ቤተሰቦቻችሁን ጠይቃችሁ አታውቁም? አዎ ጠይቋቸው፤ በሚገባ፣ ዝርዝር አድርገው ያስረዷችኋል። ልጆች ስለ እናንተ ብቻ ሳወራ አሁንም አንድ ጉዳይ እረሳሁ።
“እንኳን ደስ ያላችሁ!!!” ያልኩት እናንተን ብቻ ነው አይደል? ጥሩ፤ ግን ሌሎች የሚቀሩኝ ሰዎች አሉ – ቤተሰቦቻችሁ። የልጆች መጠቀም፣ መደሰት፣ መጫወት፣ ማወቅ ወዘተ ጥቅሙም ሆነ ደስታው የልጆች ብቻ ሳይሆን የቤተሰብ፣ የማህበረሰብ፤ በአጠቃላይ የአገርም ነው።
እናም ቤተሰቦቻችሁንም “እንኳን ደስ አላችሁ!!!” ማለት ያስፈልጋል። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ልጄን፣ ልጆቼን የት ልውሰዳቸው፣ የት ያጥኑ ወዘተ የሚለው ነገር አያሳስባቸውም። በሉ እንግዲህ ልጆች፤ ከዛሬ ጀምሮ የማንበብ ባህልን ለማዳበር፣ የጥናትና ምርምር ሥራን ለማሳለጥና ማቀላጠፍ፣ ለአገሩና ወገኑ ተቆርቋሪ ትውልድ ለመፍጠር ወዘተረፈ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሎ ተስፋ ወደ ተጣለበት፤ በአራት ወለሎቹ (ፎቆች) ላይ ወጥታችሁ ምኞታችሁን አሳኩ።
1ነጥብ 4 ሚሊዮን መጻሕፍትን መያዝ የሚችሉ 1ነጥብ5 ኪሎሜትር መደርደሪያዎች ያሉት፤ በአፍሪካ ደረጃ ቀዳሚ ከሆኑት 10 ቤተመፃሕፍት መካከል አንዱ ወደሆነው፤ በአንድ ጊዜ 115 ተሽከርካሪዎችችን ለማቆም የሚያስችል የተሟላ የመኪና ማቆሚያ ስፍራ ወዳለው ወደ አብርኆት ቤተመጻሕፍት መሄድ የምን ግዜም ምርጫችሁ እንዲሆን ጋበዝኳችሁም።
መልካም ጥናት፣ መልካም የእውቀት ግብይት፣ መልካም መዝናናት፤ መልካም የትምህርት ዘመን ይሁንላችሁ!!!::
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ጥር 8/2014