አዲስ አበባ:- በፍትህ ዘርፉ የሚስተዋሉ ብልሹ አሠራሮችን በመቅረፍ ሕብረተሰቡ የተፋጠነ የፍትህ አገልግሎት እንዲያገኝ በፍርድ ቤቶች የለውጥ ፍኖተ ካርታ ውስጥ ተካትቶ እየተሠራ እንደሚገኝ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገለጸ፡፡
በምክር ቤቱ የሕግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እጸገነት መንግስቱ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የፍትህ ሥርዓቱን በማዘመን፣ ሕዝቡ የሚፈልገውን የፍትህ ሥርዓት ዘመናዊና የተፋጠነ ለማድረግ እየተሠራ ነው፡፡
ሕዝቡ በአካባቢው ባሉ የፍትህ ተቋማት የተፋጠነ ፍትህ እንዲያገኝ፣ አቅም ያላቸው የፍትህ ተቋማት አመራሮች እና ባለሙያዎች እንዲፈጠሩ የለውጥ ፍኖተ ካርታው ውስጥ መካተቱንም አንስተዋል፡፡
በፍርድ ቤቶች ቴክኖሎጂን በመጠቀም ችሎቶችን ዲጂታላይዝድ በማድረግ ስማርት ኮርት የመፍጠር ተግባር ሰፋፊ ችግሮችን መቅረፍ የሚቻልበት መሆኑ ታምኖበታል ብለዋል፡፡
በፍርድ ቤቶች የግለሰብ ሰነዶች ባግባቡ መያዝ እንዳለባቸው እና የአንድ መዝገብ መጥፋት ቀላል ነገር እንዳልሆነ የገለጹት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢዋ፤ የዲጂታል ሥራ የተጀመረ በመሆኑ በቴክኖሎጂ ተደግፎ ከተሠራ ግለሰቦችን መጉዳትም ሆነ አላስፈላጊ ጥቅም ለማግኘት የሚቻልበት ሁኔታ አይኖርም ነው ያሉት፡፡
የፍርድ ቤቶች የለውጥ ፍኖተ ካርታ ውስጥ ከተካተቱ ሰባት ምሰሶዎች የፍርድ ቤቶች ነጻነትና ተጠያቂነት ይገኛል፡፡ ተጠያቂነትን ማስፈን የሚቻልበት ሁኔታ በስፋት የሚተነትን መፍትሔ ተቀምጧል ሲሉም አክለዋል፡፡
የዳኞች፣ የተቋም እና የፋይናንስ ነጻነት መኖሩን እንዲሁም በርካታ ዝርዝር ጉዳዮች መካተታቸውን ጠቁመው፤ ዳኛው ነጻነቱ ተጠብቆለት ያለማንም ጣልቃ ገብነት ኃላፊነቱን እንዲወጣ፣ የተሰጠ እንጂ ግለሰብ እንደፈለገ የሚጠቀምበት ሥርዓት የሚፈጥር አይደለም ብለዋል፡፡
እንደ እጸገነት ገለጻ፤ በየመዋቅሩ ያሉ ዳኞችን በማሰልጠን አቅማቸውን መገንባት ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ሕግን መሠረት በማድረግ የፍትህና የሕግ ኢንስቲትዩት ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት እንዲሆን እየተሠራ ይገኛል፡፡
አመራሩንና ዳኞችን የማጥራት ሥራ እንደሚሠራ የጠቆሙት ወይዘሮ እጸገነት፤ የአቅም ችግር ያለበት በሚመጥነው ቦታ እንዲሠራ፣ በስልጠና አቅሙ ዳብሮ መሥራት የሚችለው አቅሙ እንዲገነባ ማድረግም የለውጥ ፍኖተ ካርታው አካል ሆኖ እየተተገበረ ይገኛል ብለዋል፡፡
ክልሎች ሀገራዊ ሰነዱን መነሻ በማድረግ ከራሳቸው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በሚስማማ መልኩ ሰነዱን በማዘጋጀት ማቀዳቸውንም አመልክተዋል፡፡
አያይዘውም በፍርድ ቤቶችና በፍትህ ተቋማት ያለው ስብራት ሰፊ ጊዜና ብዙ ሥራ ይጠይቃል። በአንድ ጊዜ ውጤት ማምጣት የሚቻልበት ደረጃ ላይ አልተደረሰም፡፡ ተከራካሪዎች በፍርድ ቤት በሚሰጣቸው ውሳኔ ትክክል ነው ብለው የሚቀበሉበትን ሥርዓትም አልገነባንም ብለዋል፡፡
የሕዝቡን እርካታ ከፍ ማድረግ የሚቻለው በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በሳይንሳዊ ጥናት በመለየት በእያንዳንዱ የሥራ መዘርዝር ውስጥ ተካትቶ ሲሠራ መሆኑ ታምኖበት በእቅድ እየተከናወነ እንደሚገኝ እጸገነት ጠቁመዋል፡፡
ዘላለም ግዛው
አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 20 ቀን 2017 ዓ.ም