መንፈስንም ጉልበትንም አዳሹ ልማት – በገላን አራብሳ

ዜና ሐተታ

“ድካም ብጤ ሲሰማኝ ጉልበቴንም መንፈሴንም ለማደስ በሁለት ኩሬዎች መካከል አረፍ እላለሁ።” ይላል ወጣቱ አርሶ አደር መስፍን ጠገና። መስፍን፤ በኩሬው ውስጥ ብቅ ጥልቅ የሚሉትን ዓሳ እና ከኩሬው በላይ ድምጽ እያሰሙ የሚያዝናኑትን ጅግራዎችን ማየት ጉልበቱን እንደሚያበረታለት ይናገራል።

በቅጥር ግቢያቸው የሚታዩት ኩሬዎቹ ብቻ አይደሉም፤ በርከት ያሉ የንብ ቀፎችም ጭምር እንጂ። በርከት ያሉ ባህላዊ የንብ ቀፎዎችና ከ40 በላይ የሚሆኑ ዘመናዊ የንብ ቀፎዎች በአግባቡ ተሰድረው ይስተዋላሉ። ጅግራዎቹም ቢሆኑ ከውበታቸው ባሻገር ኩሳቸው ለዓሳ ምግብነት፤ እንቁላላቸውና ስጋቸው ደግሞ ለሰው ምግብነት የሚሆን ነው።

ይህ በሸገር ከተማ አስተዳደር፣ በኮዬ ፈጬ ክፍለ ከተማ፣ በገላን አራብሳ ወረዳ ነዋሪ የሆነው ወጣት መስፍን፣ የዲፕሎማ ምሩቅ ነው። ይሁንና ተቀጥሮ መሥራትን አልመረጠም። በቤተሰብ ደረጃ በመደራጀት መንግሥት ባመቻቸላቸው መሠረት ወደዓሳና ንብ እርባታ መግባታቸውን ያስረዳል። በሁለቱ ሥራ ብቻ ሳይወሰኑ ሰንጋ በማደለብና በመስኖ ስንዴን በማልማት ላይም እንደሚገኙ ይገልጻል።

ወጣቱ አርሶ አደር፣ ብዙ ርቆ መሄድ ሳይጠበቅበት በቀዬው ሆኖ በደጃፉ የሚያስፈልገውን የገላንን ወንዝ በሞተር ታግዞ በመጥለፍ የቆፈሯቸውን ሁለት ጉድጓዶች ውሃ በመሙላት ወደ ዓሳ እርባታው በ2016 ዓ.ም መግባታቸውን ያስረዳል። በወቅቱም 400 ያህል የዓሳ ጫጩቶችንም ከሆለታ ግብርና ምርምር ማዕከል በወረዳቸው አማካይነት ማግኘታቸውን ያመለክታል።

“በእርግጥ በዓሳ ምርት ውጤት ይገኛል የሚል ሃሳብ አልነበረኝም ነበር። ነገር ግን በመስከረም የተጀመረው የዓሳ እርባታ ከስድስት ወር በኋላ ወደ 300 ያህል ዓሳ ለገበያ ማቅረብ አስችሎናል። ከአራት ወር በኋላ ደግሞ እንደ ሸገር ከተማ ክፍለ ከተማ በባዛር የዓሳ ምርት ይዘን ቀርበናል።” ይላል።

እርሱ እንደሚለው፤ ከዓመት በፊት ወደ ውሃው ኩሬ የገቡት 400 የዓሳ ጫጩቶች፤ ዛሬ በብዙ እየተሸጡም በእጥፍ ጨምረዋል። ስጋት የሆነን ግን የጉድጓዱ መጥበብ ነው። ከዚህ የተነሳ ከአንድ ወደ ሁለት፤ ከሁለት ደግሞ ወደሶስት የውሃ ጉድጓድ በመሸጋገር ላይ ይገኛሉ። በአንደኛው ጉድጓድ ወደ ሦስት ሺህ 500 ያህል ዓሳ፣ በሁለተኛው ጉድጓድ ደግሞ ወደ አምስት ሺህ ዓሳዎች ይገኛሉ። ሦስተኛው ጉድጓድም በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል።

ዓሳ፣ ከዚህ ቀደም በሌማታችን ውስጥ እምብዛም የማይካተት ነው፤ ዛሬ ግን ዋነኛ ምግብ ከመሆኑም በተጨማሪ ለሽያጭ በመጠቀም ውጤት እያገኘንበት ነው።

ይህን ያስተዋሉ የአካባቢው አርሶ አደሮችም ሆኑ ወጣቱ ወደግቢያቸው ጎራ እንደሚሉ ጠቅሶ፤ ዓሳ ማምረት እንደሚፈልጉና ተሞክሮውንም እንደሚቀስሙ ይገልጻል።

መስፍን እንደሚናገረው፤ ከዓሳ እርባታ በተጨማሪ ማርም በማምረት ላይ ናቸው፤ በዓመት ሁለቴ ይቆርጣሉ። ቀደም ሲል ከአንድ ባህላዊ ቀፎ የሚገኘው ግፋ ቢል ሁለትና ሦስት ኪሎ ቢበዛ ደግሞ አምስት ኪሎ ማር ነው። ከዘመናዊው ቀፎ ግን እስከ 20 ኪሎ መቁረጥ ይችላሉ። እስከ 40 ያህል ባህላዊ የንብ ቀፎ ቢኖረውም ውጤቱ ያን ያህል ነው። በአሁኑ ወቅት 45 ያህል ዘመናዊ ቀፎ አላቸው። ይህን በእጥፍ የማሳደግ እቅድም ይዘዋል።

ወጣቱ አርሶ አደር፣ በበጋ ወቅት የገላን ወንዝ የተፈለገውን ያህል ውሃ ሊሰጥ ስለማይችል የውሃ ችግር ስጋት እንደያዛቸው አስረድቷል። የዓሳ ምርቱንም ለማውጣት የሚያስችል መረብም ችግር እንደሆነባቸው ተናግሯል።

የገላን አራብሳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዲሱ በበኩላቸው፤ እንደ ገላን አራብሳ ወረዳ ያለው ኢኒሼቲቭ መልካም የሚባለው ነው ይላሉ። በተለይም የዓሳና የንብ ልማትን በተመለከተ ውጤታማ ሥራ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል። የክልሉ መንግሥት ባስቀመጠው ኢኒሼቲቭ መሰረት አርሶ አደሮች እንደየፍላጎታቸው በቤተሰብ ደረጃ ተደራጅተው ወደሥራ መግባታቸውን አስታውሰው፤ ጾሙን ያድር የነበረው መሬት ሁሉ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ጠቅሰዋል።

ኃላፊው እንደሚሉት፤ አርሶ አደሩ ወደሥራ ከመሰማራቱ በፊት የተለያዩ ስልጠናዎችን በመስጠት ሰፊ ግንዛቤ እንዲፈጠርለት ተደርጓል። ከዚህ የሥራ መስክ ውስጥ እንደወረዳው የዓሳና የማር ልማት ተጠቃሽ ሲሆን፤ በተለይም በዓሳ ምርት የወጣቱ ተሞክሮ ሌሎቹም ወጣቶችና አርሶ አደሮች እንዲያገኙ በማድረግ ወደሥራው እንዲገቡ በማበረታታት ላይ ይገኛሉ።

በሌላ በኩል ከማር ልማት ጋር በተያያዘ አርሶ አደሮቹ ባህላዊም ዘመናዊም የንብ ቀፎ አላቸው። ቀደም ሲል ያለው ባህላዊ ቀፎ ምንም አይነት ድጋፍ ሳይደረግለት የቆየ ነው። በአሁኑ ወቅት ባህላዊ የንብ ቀፎውንም ሙሉ ለሙሉ ሳያስወግዱ ወደዘመናዊ ቀፎ እንዲመጡ እያደረግን እንገኛለን። በተለይም በዘመናዊ ቀፎ እንዴት መስራት እንደሚቻል በቤተሰብ ደረጃ አደራጅተን አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያገኙ አድርገናል። ቀስ በቀስም በእንዲህ አይነት ሁኔታ ወደ ዘመናዊ ቀፎ እንዲሸጋገሩ እንፈልጋለን ብለዋል።

የገበያ ችግር አለመኖሩን የጠቀሱት አቶ አዲሱ፤ በባዛር ላይ ዓሳ እና ማር በማቅረብ ላይም እንደሚገኙ ተናግረዋል። እንደወረዳችን በማር ኢንሼቲቭ ላይ የተለያዩ አርሶ አደር ቤተሰቦች በማር ልማት እንዲደራጁ ተደርገው እየሠሩ ይገኛሉ። በዚህም ወደ 14 ያህል ማህበር መሰማራታቸውን አመልክተዋል።

የመረብ ችግር የተባለው አግባብነት ያለው ጥያቄ መሆኑን ጠቁመው፤ ብዙዎቹ አርሶ አደሮች ለተሞክሮ ወደወጣቱ አርሶ አደር ስለሚመጡ በዚህም የተሟላ ነገር ማየት አለባቸው ብለዋል። የዓሳዎችን ደረጃና አይነትም ለማሳየት ደግሞ ሁነኛ የሆነ መረብ አስፈላጊ እንደሆነ የሚታወቅ ነው። ይሁንና በአሁኑ ወቅት ባቱ አካባቢ ካሉ ዓሳ አምራች ማህበራት ጋር በመነጋገር ችግሩን ለመፍታት ከጫፍ ደርሰናል ሲሉ አስረድተዋል።

የውሃ ችግርን በተመለከተ የወንዙ ሁኔታ አሳሳቢ ቢሆንም፤ ወረዳችን ጥሩ የሆነ የከርሰ ምድር ውሃ አቅም ያለው እንደመሆኑ በዚህ ስጋት አይኖርም ብለዋል፤ ከዚህ ባለፈ ለበጋ መስኖ ልማት የሚሆን በቂ የሆነ ውሃ በመኖሩ ትንሽ ብቻ ቆፈር በማድረግ የጉድጓድ ውሃ በማውጣት ስንዴንም ማልማት የሚቻል ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ እንደ ወረዳችንም የተጀመረ ሥራ አለ። ስለዚህ ይህንኑ ሥራ እናሰፋለን ሲሉ መልሰዋል።

በሸገር ከተማ አስተዳደር ኮዬ ፈጬ ክፍለ ከተማ የኮዬ ፈጬ ክፍለ ከተማ የግብርና ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ዶክተር ናፍያድ ዓለሙ እንደሚገልጹት፤ በከተማችን ሰፋፊ ሥራዎች በመሠራት ላይ ይገኛሉ። እነዚህም ሥራዎች ውጤታማ መሆን የቻሉ ናቸው። ውጤታማ ከሆኑት ሥራዎች አንዱ የሌማት ትሩፋት ሲሆን፤ አርሶ አደሩ በአግባቡ እየሠራበት ይገኛል።

እንደሚታወቀው በከተማ አስተዳደር ውስጥ የነበሩ አርሶ አደሮች በተለይም ደግሞ በኮዬ ፈጬ ክፍለ ከተማ የነበሩ አርሶ አደሮች ከስፍራቸው በመፈናቀላቸው ሥነ ልቦናቸው የተጎዳ ነው። ስለዚህም ሥነ ልቦናቸው ከጉዳት እንዲወጣ በተለያዩ ቦታዎች ስልጠና ሰጥተናል። ስለዚህ ውጤት ማምጣት ተችሏል።

በአሁኑ ወቅት በየወረዳዎቹ ውጤታማ ልማት እየተካሔደ ሲሆን፤ በገላን አራብሳ የማር ልማትና የዓሳ ልማት አንዱ ተጠቃሽ ነው። በወረዳው ባለፈው ዓመት አመርቂ ሥራ ተሰርቶ ውጤት ተገኝቶበታል። የገበያ ሁኔታም ተመቻችቶላቸዋል ብለዋል። የዓሳ ልማቱን በተመለከተ ችግሩ በመረብ ብቻ ሳይሆን በቀፎ በኩልም እጥረት አለ። አስፈላጊ የሆኑ ግብዓት በሙላት ለማዳረስ እየተሠራ ነው። ለአርሶ አደሩ ተጨማሪ ስልጠናዎችንም የምንሰጥ ይሆናል። የዓሳም ሆነ የንብ ውጤትን ማስመዝገብ የሚቻለው በሂደት ነው ብለዋል።

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 20 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You