መስቀል- በሶዶ ክስታኔ ቤተ-ጉራጌ

ወርሃ መስከረም መስኩ በልምላሜ በአደይ አበባ የምታሸበርቅበት፣ ወንዙ ጅረቱ የሚጠራበት፣ ዝናብና ጉሙ አልፎ፣ ጭቃው ጠፎ፣ ነፋሻ አየር የሚነፍስበትና ጸሀይ የምትደምቅበት ወቅት ነው። የክረምቱ ወቅት የሚወጣበትና የበጋው ወቅት መግባት የሚጀምርበት፣ አዝመራው የሚያብብበት፣ ስሜት በደስታ የሚሞላበት እንደመሆኑም በልዩ ሁኔታ ይታያል፡፡

በዚህ ወቅት በርካታ ሃይማኖታዊ ባህላዊ ይዘት ያላቸው በዓላት የሚከናወኑበት መሆኑ ብዙዎች ወሩን የደስታና የፌሽታ አድርገው ያስቡታል፤ በናፍቆት የሚጠብቁትም ነው። በድምቀት ከሚከበሩ ሃይማኖታዊ በዓላት አንዱ ደግሞ የመስቀል በዓል ነው። በእርግጥ! መስቀል የአካባበሩ ሁኔታ ይለያይ እንጂ በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እንደየባህላቸው፤ ታሪካቸውና ቋንቋቸው በተለየ መንገድ ያከብሩታል። በርካታ ባህላዊ እሴት ያላቸው ክዋኔዎች ያሉበት መሆኑ ደግሞ የተለየ ያደርገዋል፡፡

መስቀል በድምቀትና በበርካታ ክዋኔዎች ከሚያከበሩ የሃገሪቱ ብሔር ብሔረሰቦች መካከል የጉራጌ ብሄረሰብ አንዱ ነው። መስቀል በሁሉም ቤተ-ጉራጌ ብሄረሰብ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው፤ ከሃይማታዊ ይዘቱ በተጨማሪ ባህላዊና ማህበራዊ መስተጋብሩ የላቀ በመሆኑ ተወላጆቹን ብቻ ሳይሆን የሌላ አካባቢ ነዋሪዎችም ጭምር ቦታው ድረስ ሄደው እንዲያከብሩት የሚያጓጓና የሚያስናፍቅ በዓል ነው። እኛም በዛሬው ሃገርኛ አምዳችን የሶዶ ክስታኔ (ሶዶ ጉራጌን) የመስቀል በአል አካባበርና ባህላዊ ኩዋኔዎችን እናስቃኛችኋለን፡፡

የመስቀል በዓል አጀማመር የእየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት ግማደ መስቀል ከማግኘት ጋር ተያይዞ የተጀመረ ሲሆን እያንዳንዱ የክርስትና እምነት ተከታይ/ በተለይ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች/ በዓሉን የሚያከብሩት እንደ ሕዝቡ ባሕል አኗኗርና ወግ በመሆኑ ከሃይማኖታዊ ስርዓት ባሻገር ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ ፋይዳው የጎላ ስለመሆኑ ይገለጻል። የመስቀል በዓል የተጣላ የሚታረቅበት፣ የተራራቁ የሚቀራረቡበት፣ ወጣቶች የሚተጫጩበት፣ ጋብቻ የሚመሰርቱበት፣ በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖረው የብሄረሰቡ አባል ያለውን ይዞ ወደ ትውልድ ቀየው በመሄድ ለአባት ለእናቱ ለጎረቤቱ በመስጠት የሚመረቅበት፣ ለመጪው ዓመት የሚታቀድበት፣ በሰላም ላደረሳቸውና ለፈጣሪያቸው ምስጋና፤ ለወዳጆቻቸው ምኞታቸውን የሚገልጹበት በዓል ነው።

ወይዘሮ ማሜ ጌታቸው የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልሉ የምስራቅ ጉራጌ ዞን የቡኢ ከተማ አስተዳደር ባሕልና ቱሪዝም ፅህፈት ቤት ኃላፊ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ በሶዶ ክስታኔ ማሕበረሰብ መስቀል በዓመት ከሚከበሩ አንዱና ትልቁ በዓል ነው። መስቀል ከሌሎች ሃይማኖታዊና ባሕላዊ በዓላት ለየት የሚያደርገው በዋናነት የተራራቁ ቤተሰቦችን የሚያቀራርብ፤ የተጣሉ የሚታረቁበትና የተለያዩ ክዋኔዎች የሚከናወኑበት መሆኑ ነው። መስቀል ለክስታኔ ሕዝብ ዓመቱን ሙሉ በተለያዩ ዝግጅቶች በጉጉት የሚጠበቅ ሲሆን፣ በተለይ ከነሐሴ ወር ጀምሮ ደመራ በማዘጋጀትና የተለያዩ ለበዓሉ ድምቀት የሚውሉ ስራዎችን የሚሰሩበት መሆኑ የተለየ ያደርገዋል።

የክስታኔ ሕዝብ ዓመቱን ሙሉ በጉጉት ሲጠብቀውና ሲዘጋጅበት የሚቆይበት ይሁን እንጂ በተለይም ከመስከረም 12 እስከ ጥቅምት 5 ድረስ በተለያዩ ባሕላዊና ሃይማኖታዊ ይዘት ባላቸው ክዋኔዎች በድምቀት የሚከበር መሆኑን ያነሳሉ። ‹‹የሶዶ ክስታኔ ቤተ-ጉራጌ የመስቀል በዓልን የበዓሎች ሁሉ አውራ አድርጎ ሲያከብር ኖሯል፤ ለእዚህ አከባበርም አስቀድሞ ሰፊ ቅድመ ዝግጅት ያደርጋል፤ በዓሉን ከመስከረም 12 እስከ ጥቅምት አምስት ድረስ እየጨፈረና ለበዓሉ ተብሎ የተዘጋጁ ምግብ አይነቶችን እየተመገበ ያከብራል›› ሲሉም ይገልጻሉ። በእያንዳንዱ ቀን ስለሚከናወነው ተግባርም ኃላፊዋ አብራርተዋል፡፡

መስከረም 12 ቀን ‹‹ሌማት ያወርድቦማይ››

እንደ ወይዘሮ ማሜ ማብራሪያ፤ መስከረም 12 በሶዶ ክስታኔ ማሕበረሰብ የመስቀል በዓል ለምግብ ማቅረቢያነት የሚውሉ ቁሳቁስ ከተሰቀሉበት ስፍራ የሚወርዱበት ቀን ነው። በዚህ እለት ከማጀት እስከ ደጅ ድረስ የፅዳት ስራ ይካሄዳል፤ ግድግዳ በተለያዩ ቀለማት እንዲደምቅ ይደረጋል።

መስከረም 12 በሶዶ ክስታኔ ማሕበረሰብ ‹‹ሌማት ያወርድቦማይ›› ይባላል። በዚህ እለት የተለየዩ የቤት እቃዎች ጽዳት የሚደረግበት ቀን ነው። በእዚህ ቀን ቁሳቁስ በጥንቃቄ ታጥበውና ፀድተው እስከ ጥቅምት 5 ድረስ ለምግብ ማቅረቢያነት አገልግሎት እንዲውሉ ይደረጋሉ።

መስከረም 13 – ‹‹ዎልቀነ››

መላው ክስታኔ በእዚህ ወር ‹‹ማኛም በኬር አሰላንህም፤ አሰላነ›› እያለ የእንኳን አደረሰን መልእክት ይለዋወጣል፤ መስከረም 13 ቀን ግን ሴቶች በተለየ መልኩ የሚከበሩበት እለትና የተለየ ክዋኔ የሚደረግበት ነው። ይህ ቀን በሶዶ ክስታኔ ማሕበረሰብ ‹‹ዎልቀነ›› ተብሎ ይጠራል፤ በዚህ እለት ጎመን ከማሳ ካለ የሚለቀምበት፤ ከሌለ ደግሞ ከገበያ ተገዝቶ በትልቅ እንስራ ተቀቅሎ፤ ልክ እንደ ክትፎ ሁሉ ደቆ ተክትፎና በቂቤ፤ በኮረሪማና በሌሎችም ቅመማቅመሞች ታሽቶና ተዋዝቶ ይዘጋጃል።

የመስቀል በዓል ዝግጅቶች የሚያጠናቅቁበት እለትም ነው። ለመስቀል ተብለው በተዘጋጁት በሁሉም የምግብ ዓይነቶች ላይ የሙከራ ቅምሻ የሚደረግበት (የሚበላበት) እና የጎመን ቀን እየተባለ በተለምዶ የተሰየመ እለት ነው። በተጨማሪም በዕለቱ ‹‹ኸቆት›› አይብ መጠኑ ከጎመን የሚያንስበት አይነት ምግብ ተዘጋጅቶ የሚበላበትና ሴቶች በሚገባ እንዲመገቡ የሚደረግበት ነው።

ወይዘሮ ማሜ እንደሚሉትም፤ እንደ ዓለም የሴቶች ቀን (ማርች ኤይት) ሁሉ ሴቶች በዚህ ቀን ጎልተው ይታያሉ፤ ይደምቃሉ፤ ይደመጣሉ፤ የፈለጉትን ሁሉ እንደልባቸው ያከናውና። በዚህ ቀን ሴቷ ምንም አይነት ጥፋት ብትሰራ ማንም ቀና ብሎ እንደማያያት እንደማይናገራት ኃላፊዋ አስገንዝበዋል።

‹‹ዎልቀነ ዎልቀነ

ምሽት ይገራቦ ቀነ

ታምብል ይጋም ኮነ..›› እየተባለ በዚህ ቀን ሴቶች በተለየ መልኩ ስማቸው እየተነሳ ይጨፈራል።

ኃላፊዋ የዚህን ባሕላዊ ዜማ ትርጓሜ ሲያስረዱ ‹‹በዕለቱ ምንም መበያ የሚሆናት ነገር ብታጣ ብታጣ የጎመን ውሃ አታጣም ማለት ነው›› ይላሉ። በእዚህ እለት ማንኛውም የሶዶ ክስታኔ ሴት እሷም ከሰራችውና ቤት ካፈራው የምትበላበትና የምትጠግብበት በደስታ የምታከብርበት ቀን ነው። ይህም በመሆኑ እለቱ ‘የሴቶች ቀን’ ወይም ‹‹ዎልቀነ›› እየተባለ እንደሚጠራ ያመለክታሉ። የአካባቢው ተወላጆችም ለመመረቅ እጃቸውን ያፈራውን ለእናት አባቶቻቸው እና ለጎረቤትም ጭምር ይዘው እንደሚሄዱም ተናግረዋል።

መስከረም 14 ቀን ‹‹ደንጌሳት››

በሶዶ ክስታኔ መስቀል በድምቀት ከሚከበርባቸው ቀናት አንዱ መስከረም 14 ቀን ይጠቀሳል። ይህ እለት በማሕበረሰቡ ዘንድ ‹‹ደንጌሳት›› በመባል ይጠራል፤ ትርጉሙም ደስታ ወይም ፍሰሀ ማለት ነው። በዚህ ቀን ማምሻ ያላገቡ ወጣቶችና ዕድሜያቸው ከዚያ በታች ያሉ የልጆች ደመራ የሚያቃጥሉበት ሲሆን፣ በማሕበረሰቡ አጠራር የልጆች እሳት ወይም ዳመራ ‹‹የባዮች ኸሳት›› ይባላል።

በእለቱ ለሁሉም የቤተሰብ አባል የተዘጋጀለትን ‹‹ደንጋሳ›› የጎመን ክትፎ እና አይብ የሚበላበት፤ በተለይ እናት ለልጆች እንደየድርሻቻው ጎመን በአይብ የምትሰጥበት ቀን ነው። ቀኑ የሴቶች ድርሻ ጎልቶ የሚታይበት በመሆኑ እናቶችም ሙሉ ዝግጅት ማድረጋቸውንና የቤት አባወራ እንዲገኝላቸው ብቻ ለማመላከት ለማሕረሰቡ በስንኝ ቋጠሮ ይገጥሙታል።

‹‹በርበሬም ዎቀጥኩም

ጥወም አቅላለጥኩም

አምበልም አረጥኩም

ጉንስም አልባበጥኩም

አናቀርብሆኖ የጌ አቢ ቀበጥኩም…›› እየተባለ የሚዜምበትና የሚጨፈርበት ቀን መሆኑን ወይዘሮ ማሜ ይናገራሉ። ይህም በርበሬ መወቀጡን፤ ቂቤ መነጠሩን፤ ጎመኑም መከተፉን፤ ቆጮም መጋገሩን እንዲሁም ለበዓሉ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ሁሉ ስንዱ መሆናቸውንና ለማቅረብ አባወራ እንደሚጠብቁ ለማንፀባረቅ የሚዜም ማራኪ ዜማ ነው።

በአንፃሩ ደግሞ በቂ ዝግጅት ያላደረገች እመቤት ‹‹የደንጌሳቲማይ ቃዬሲ ባያንሴ

አዮዲ ትሙትም ሀዘንኪ የባሴ›› በሚል የስንኝ ቋጠሮ የምትችበት ሁኔታ እንዳለም ገልጸዋል፤ ይህንንም ትችት በመፍራት ሁሉም የክስታኔ ሴቶች አስቀድመው ዝግጅታቸውን ለማጠናቀቅ እንደሚታትሩም ያመለክታሉ።

መስከረም 15 ቀን ‹‹የእርድማይ››

መስከረም 15 በሶዶ ክስታኔ ቤተ ጉራጌ ጨርቆስ ወይም ‹‹የእርድማይ›› ተብሎ ይጠራል፤ በዚህ ቀን የአባወራዎች ተግባር ጎልቶ ይታያል። ስለሆነም አስፈላጊውን ዝግጅት ለአንድ ዓመት ሙሉ ቆጥበው በሬ ገዝተው የሚያርዱበት ቀን መሆኑን ወይዘሮ ማሜ ያስረዳሉ። ሆኖም በዚህ ቀን አባወራው ያረደው ሰንጋ የደለበ ካልሆነ ሴቶች በግጥም ይተቹታል።

‹‹ጬሮደም ኸጭንን

ቅብዲም ነስጭን

የመናጊ ጠብጠት ንቶናም በጨበር

ደናኛ ንዥንን…›› በማለት ይወርፉታል። ይህም ማለት ‹‹ስጋውንም ብላው፤ ቂቤውዬንም ልጠጣው፤ በማግስቱ ጠዋት ፀሀይ ላይ ቁጭ ብለን መልካችን እንየው›› በማለት የተሻለው የማነው በማለት ዝግጅቱ በቂ ያለመሆኑን የሚያስረዱበት ሁኔታ መኖሩን ይጠቅሳሉ፡፡

በተጨማሪም ‹‹በሰርደ የጣየ

ጂለል በገባየ

ምን ነይዝም ነውጣየ

አዚ የደነገጥኩን በደኽ የግባየ›› በማለት ባሎቻቸውን በዜማው የሚወርፉ መሆናቸውን ኃላፊዋ ይገልፃሉ። ይህም ማለት ‹‹ስጋው የበግ ኩሽና ብገባም ይዤ የምወጣው ስላጣው ደነገጥኩኝ፤ ድንጋጤዬ የአንተ ይሁን›› የሚል ይዘት ያለው መሆኑን ያስረዳሉ።

በአንፃሩ ደግሞ የአባወራው የተሻለ ሆኖ የእማወራ ካነሰ ‹‹ቅብደሽ የሀምሌ ነሀሴ

ልብለበው የባሴ›› በሚል የአሹሙር ይዘት ባለው ቅኔ ይወርፏታል። ይህም ማለት ቅቤሽ ለጋ ስለሆነ ቃር አስቸግሮኛል የሚል ትርጓሜ ያለው መሆኑን ያባራራሉ።

በሌላ በኩል ግን በዚህ እለት ስጋ ያልገባላት ከሆነች በማህበረሰቡ ዘንድ የተፈታች ተደርጎ ታሳቢ ይደረጋል። ባል የሞተባት ከሆነች ደግሞ ዘመድ አዝማዱ ተሰባስቦ ስጋ ያስገባላታል፤ ምክንያቱም ባሏን አስባ እንዳታዝን በማሰብ እንደሆነ ይናገራሉ። ‹‹ባል የሞተባት ሚስት እስከ አንድ ዓመት ስጋ ሳትበላ የምትቆይበት ስርአት ጎጂ ልማድ በመሆኑ ከ 40 ቀን በምንም መልኩ መብለጥ እንደሌለበት የሶዶ ጎርደና ሴራ ያስቀምጣል›› ሲሉም ያክላሉ።

መስከረም 16 ቀን ‹‹የኸሳትማይ››

በማሕብረሰቡ መስከረም 16 ቀን ‹‹የኸሳትማይ›› በመባል ይጠራል፤ ቀኑ ዋናው ዳመራ የሚበራበት ነው። ከነሐሴ 12 ጀምሮ የተደመረውን ዳመራ በዚህ እለት የአካባቢው ማሕበረሰብ ተሰባስቦ ያበራል። በአብዛኛው ሃይማኖታዊ ክዋኔ የሚደረግበት ቀን ሲሆን፣ ከቤተ-ክርስቲያን መልስ ሁሉም በየአካባቢው የተዘጋጀ ደመራ በማቃጠል ክትፎ በቆጮ (ብርንዶ በአልበበጫት) ቀርቦ የሚበላበት፤ የሚጨፈርበት ቀን መሆኑንም ያመለክታሉ።

በዚሁ ወቅትም አባቶች ልጆችንም ሆነ መላው የአካባቢውን ሕዝብ የሚመርቁበት ስርዓትም እንደሚከናወን ይጠቅሳሉ። ከባሕላዊ ክዋኔዎች ጎን ለጎን ሃይማኖታዊ ይዘት ያላቸው ስርዓቶች እንደሚካሄዱ አስታውሰዋል። በዚህ እለትም ጎልቶ ከሚታወቁትና በስፋት ከሚዜሙት የቀየው ባሕላዊ ዘፈኖች መካከል ‹‹ብርንዶ በወጨት ይቄኖት

ቅብም ይስግቦት

አልበበጫት ይፈርሙም

በሌማት ያቀርቡም

ዚሆም ይደንቅቦትን

ነግዳ ይቂበልቦትን

የማንም ተሻልሙ

ክስታኔ ዝወርሙ

ስም ይነንትን ሶዶ

ድሮም በብርንዶ…›› በማለት በእለቱ ክትፎ የመብላት ሂደትንና የአቀራረብ ስርዓቱን የሚያሳዩ ዘፈኖች እየተዘፈኑ ፤ በጭፍራ ሌቱ የሚነጋበት ሁኔታ እንዳለም ነው ያመለከቱት።

መስከረም 17 ቀን መስቀል

ይህ ቀን ልክ በተለይ የግማደ መስቀሉ መገኘትን ምክንያት በማድረግ በልዩ ሁኔታ የሚከበርበት ሲሆን፣ በዚህ እለትም የብሔረሰቡ መታወቂያ የሆነውን ክትፎን ጨምሮ ቁርጥና ሌሎች ባሕላዊ ምግቦች በስፋት ይበላሉ። ከዚሁ በተጓዳኝ የተነፋፈቀ ዘመድ አዝማድ ይወያያል፤ ይመራረቃል፤ ይጠያየቃል።

አዳብና

አዳብና በሶዶ ክስታኔ ማሕበረሰብ መስቀልን ተገን አድርገው ከሚከናወኑ ባሕላዊ ክዋኔዎች ዋነኛው ነው። ይህም ወጣት ወንዶችና ሴቶች በተለይ ገበያ ባለባቸው ቦታዎች ላይ የሚያካሂዷቸው ባሕላዊ ጫወታዎች እና ጭፈራዎች የሚከናወንበት ስርዓት መሆኑን ያስረዳሉ። ይህም ባሕላዊ ክዋኔ ከመስከረም 16 የሚጀምር ሲሆን፣ እስከ ጥቅምት አምስት ድረስ ገበያ ባለባቸው ቦታዎች ይቀጥላል። ወንዱ የሚፈልጋትን የሚመርጥበትና የሚያጭበት ወቅትም መሆኑን ጠቅሰው፤ ሌላውን የሰርግ ስርዓት ደግሞ ቤተሰብ የሚጨርስበት ሁኔታ መኖሩን ያብራራሉ፡፡

መስቀል ለክስታኔ ቤተ ጉራጌ የሁሉም ነገር መገለጫ መሆኑን ኃላፊዋ ጠቅሰው፤ በተለይም በመላ ሃገሪቱ የሚኖረው ይህ ማሕበረሰብ ዓመቱን ሙሉ ለፍቶ ያገኘውን ከቤተሰቡ ጋር የሚቋደስበት፤ ስጦታ የሚለዋወጥበት፤ የሚተጫጭበት መሆኑ የተለየ እንደሚያደርገው ይገልፃሉ።

የትኛውም የብሔረሰቡ ተወላጅ በዚህ ወቅት ትውልድ አካባቢው የመግባት ግዴታ እንዳለበት መሆኑን ይናገራሉ። ገንዘብ ባይኖረውም እንኳን የወላጆቹን እርግማን በመፈራትና ከእነሱ የሚያገኘውን ምርቃት ታሳቢ በማድረግ በምንም ሁኔታ ውስጥ ቢሆን ለመስቀል ሃገሩ የሚገባበት ሁኔታ መኖሩን ያመለክታሉ። ይህም የጉራጌ ማሕበረሰብ ለወላጆችና ሆነ ለምርቃት ያለውን ከፍ ያለ ስፍራ እንደሚያሳይ ይናገራሉ፡፡

‹‹ማሕበረሰቡ በተለይ ለታላላቆችና ለአባቶች ትልቅ ክብር ይሰጣል፤ በምንም ሁኔታ ውስጥ ቢሆን እነሱን ተሻግሮ የሚሄድ አንድም ሰው የለም›› የሚሉት ወይዘሮ ማሜ፤ ይህ የመከባበርና የመቻቻል መሰረቱ ቤተሰብ መሆኑን እንደሚያመላክት ያስረዳሉ። ‹‹ ይህም እየተመናመነ የመጣው የመከባበርና የመቻቻል እሴት እንዲያንሰራራ ጥሩ ተምሳሌት ይሆናል›› ይላሉ። እንዲህ አይነቱን የመደማመጥና የመከባበር እሴት በማዳበር ሁሉም ለዘላቂ የሃገር ሰላም የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

ማህሌት አብዱል

አዲስ ዘመን መስከረም 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You