ይህች ማህፀነ ለምለምዋ ምድር ኢትዮጵያ በየዘመናቱ ስለስዋ ሕልውና የሚዋደቁ ጀግኖች አፍርታለች። ለሕይወታቸው አንዳች ሳይሳሱ ስለአገራቸው ክብርና ነፃነት የተዋደቁ ትንታጎች ሳይሰለቻት አብቅላለች።
ለአገራቸው ክብርና አንድነት በፅናት ከታገሉ ስለአገራቸው ነፃነት እራሳቸውን ከሰጡ ጀግኖች መሀል አንዱን ከወርቃማው የታሪክ መዝገብ ላይ ገልጠን ልናይ ወደድን። አገሬን አሳልፌ አልሰጥም በሚል ስለ ኢትዮጵያ መሰዋት ከሆኑ ጀግኖች ተርታ ከፊት ተሰልፈው ይገኛሉ። አንድነት ሲነሳ በብዙ ይታወሳሉ። በመሳፍንት አገዛዝ ተከፋፍላ የነበረችውን ኢትዮጵያ ወደ አንድ ያመጡ ታላቅ መሪ ናቸው።
በአገዛዝ ዘመናቸው ኢትዮጵያን ነፃነትን መርጠው ባርነትን ተጸይፈው እራሳቸውን የሰው ኢትዮጵያዊ ንጉስ ናቸው ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ። ጥር 6 ቀን 1811 ዓ.ም ተወለዱ። በዛሬው የሳምንቱን በታሪክ አምዳችን እሳቸውን ለመዘከር ብዕራችንን አነሳን፤መልካም ንባብ። አፄ ቴዎድሮስ ከጎንደር ከተማ በስተምዕራብ ቋራ ውስጥ፣ ሻርጌ በተባለ ቦታ ተወለዱ። የክርስትና ስማቸውም ገብረኪዳን ተባለ።
ዋንኛ መጠሪያቸው የሆነው ስም “አጼ ቴዎድሮስ” በእናትና አባታቸው የወጣለችው ስም አይደለም። እናትና አባታቸው ያወጡላቸው ስም ካሳ ይባል ነበር። ንግሥናን እስኪቀበሉ ድረስም በዚሁ ስም እየተጠሩ ቆይተዋል። ስመ ብዙው አፄ ቴዎድሮስ በትውልድ ስማቸው ካሳ ኃይሉ ሲባሉ፣ በፈረስ ስማቸው አባ ታጠቅ፣ በወታደራዊ ስማቸው ደግሞ መይሳው ካሳ እና አንድ ለናቱ ተብለው የሚታወቁት አፄ ቴዎድሮስ የ19ኛ ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ ወታደርና ፖለቲከኛና ንጉስ ነበሩ።
ወቅቱም አገሪቷ በባላባቶች ተከፋፍላ የምትመራበትዘመነ መሳፍንት የሚባለው ወቅት ነበር። አባታቸው ደጃዝማች ኃይሉ ወልደ ጊዮርጊስ የቋራ ገዢ ነበሩ። አፄ ቴዎድሮስ የተወለዱበት ቋራ በኢትዮጵያና በሱዳን ድንበር የሚገኝ ሲሆን በዘመኑ ከሱዳኖችና ከግብፆች ዘንድ ብዙ ወረራ ይደርስበት የነበር አካባቢ ነው። ደጃዝማች ሃይሉ ወልደ ጊዮርጊስ ከሱዳን ጋር በተደረገ ጦርነት ሲያልፉ፣ በ1813 ዓ.ም ወይዘሮ አትጠገብ ህጻኑን ቴዎድሮስ ይዘው
ወደተወለዱበት ጎንደር ከተማ ተመለሱ። ወይዘሮ አትጠገብ በነበራቸው ገቢ መጠን ልጃቸውን በጥሩ ሁኔታ ማሳደግ ስላልቻሉ ክንፉ ሃይሉ ህጻኑን ቴዎድሮስ በጎንደርና በጣና ሃይቅ መካከል በሚገኘው ቸንከር በተባለ ቦታ የተክለ ሃይማኖት ገዳም ለትምህርት ላኩዋቸው።
አፄ ቴዎድሮስ የቄስ ትምህርት ተከታትለው ከጨረሱ በኋላ፣ የአጎታቸውን ጦር በኋላም ለጥቂት ጊዜ የጎጃሙን ጦር መሪ የነበሩት የጎሹ ዘውዴን ጦር ተቀላቀሉ። የውትድርና ዘመናቸው ከፍተኛ ችሎታን ማስመዝገብ ስለጀመሩና ዝናቸው ተስፋፋ። በወይዘሮ መነን ሊበን አምዴ አነሳሽነት የልጇን የራስ አሊ አሉላን ልጅ፣ ተዋበች አሊን ተዳሩ። ከዚያም በደጃዝማችነት ማዕረግ የቋራ አስተዳዳሪ ሆነው ተሾሙ። ደጃዝማች ሆነው ቋራን ሲመሩ ከቆዩ በኋላ የዘመነ መሳፍንት ሥርዓትን በመቃወም በሰሜን ባላባቶች ላይ ዘመቻ ጀመሩ።
በተከታታይ ዘመቻዎች የገጠሟቸውን ባላባቶች ማሸነፍ ቻሉ። ከዚያም መጀመሪያ የራስነት ማዕረግ በኋላም የንግስና ማዕረግን በአንድ ዓመት ውስጥ መቀዳጀት ቻሉ። ቆራጥ የጦር መሪና ተዋጊ የነበሩት አፄ ቴዎድሮስ በየጊዜው በሚያደርጉት የተሳካ ዘመቻ የዘመኑን ባላባቶች ኃይል በማሸነፍ የካቲት 11 ቀን 1947 ዓ.ም ንጉሥ ካሳ ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ተብለው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ሆኑ።
ብዙዎቻችን አፄ ተዎድሮስን በተለመዶ ቀይ ወደምንለው የቆዳ ቀለም የሚያደሉ ቢመስለንም አጼ ቴዎድሮስ ግን ጥቁር እንደነበሩ ጳውሎስ ኞኞ አጼ ቴዎድሮስ በሚለው መጽሐፉ በአካል ያዩዋቸውን ዱፍተን እና ዶ/ር ብላንክን ጠቅሶ “የቆዳ ቀለማቸው ወደ ጥቁር የሚያደላ ነበር።” በማለት አስረጂ ጠቅሷል።
ከዚህ ባለፈ አጼ ቴዎድሮስ ጀግና፣ እውነተኛ፣ ታማኝ፣ ጠቢብ፣ የማያወላውሉ ቆራጥ፣ ደፋር፣ የራሳቸውንና የአገራቸውን ክብር የማያስደፍሩ፣ ይቅርታን ለሚጠይቅ ምህረትን የሚያደርጉ፣ ለከዳተኞች ጠንካራ ፍርድን የሚያሳልፉ፣ ለነብሳቸው የማይሳሱ፣ ቅንጦት የማይወዱ፣ ራሳቸውን ከተራ ወታደር ለይተው የማያዩ ጀግና መሪ እንደነበሩ የታሪክ ድርሳናት ያመለክታሉ።
በንግስናቸው ወቅት ከእንግሊዝ ጋር በተፈጠረው ግጭት ምክንያትና በመረጃ ልውውጥ ላይ በተነሳው ችግር እንግሊዞች ለንጉሱ የላኩት ዛቻ መልስ ባለማግኘቱ ምክንያት ነሐሴ 1859 እንግሊዞች በሮበርት ናፒየር የሚመራ 32000 ጦር ሰራዊት በንጉሱ ላይ አዘመቱ። እንግሊዞቹ በዚህ ወቅት በኢትዮጵያ ስለሚሆነው ጉዳይ ጥልቅ መረጃ ነበራቸው።
ይህም በየአካባቢው እየተነሳ ስለነበር አመጽ ሙሉ መረጃ ነበራቸው። የቴዎድሮስ ሰራዊት በድሮ ጊዜ ወደ 100000 የሚጠጋ ሲሆን ንጉሰ ነገሥቱ የመጨረሻ ዘመቻቸውን ፈጽመው በጥቅምት 1860 ላይ መቅደላ ደረሱ፣ ይሄውም ከናፒየር ሰራዊት 2 ሳምንት ቀድሞ ነበር።
ሚያዚያ 6 ቀን 3 ሰዓት ላይ እንግሊዞች በመቅደላ ምሽግ ላይ ጥቃት አደረሱ። ንጉሱ፣ የሃይል ሚዛኑ ወደ እንግሊዞቹ ሙሉ በሙሉ እንዳጋደለ ስለተረዱ ለወታደሮቻቸው እንዲህ በማለት ተለይተው ሄዱ “ተፈጽሟል! ከርሱ እጅ ከምወድቅ ብሞት ይሻለኛል”። ወዲያውም ከንግስት ቪክቶሪያ የተላከላቸውን ሽጉጥ መዘው በመጉረስ በጀግንነት ተሰው።
ጳውሎስ ኞኞ የአጼ ቴዎድሮስን ታሪክ በፃፈበት መፅሃፉ የንጉሱን ሕይወት ከመነሻው እስከመድረሻው ያስቃኛል። እኛም ይሄንን ፅሁፍ ስናዘጋጅ ይህንን መፅሐፍና የተለያዩ ድህረ ገፆች በዋቢነት ተጠቅመናል።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ጥር 8/2014