ኢትዮጵያውያን ከቀሪው ዓለም በተለየ መንገድ መገለጫ የሆኑ የባህል፣ የሃይማኖት፣ የተፈጥሮ እንዲሁም የታሪክ ባለቤቶች ነን። እነዚህን ሃብቶች የአንድነታችንና የማንነታችን መሰረቶች ሲሆኑ ደስታችን፣ ሃዘናችንም ሆነ ማናቸውንም ስሜቶቻችንን የምናንፀባርቅባቸው መንገዶቻችን ጭምር ናቸው።
ቀሪው ዓለም ደግሞ አዲስ ነገር የሚማርበት፣ የባህልና መሰል ሃብቶችን በመጎብኘት እውቀት የሚገበይበት ስጦታ ናቸው። አገራችን በርካታ የቱሪዝም መስህቦችን ለዓለም አበርክታለች። በዩኒስኮ የተመዘገቡ ቅርሶች፣ የማይዳሰሱ ሃብቶችና የተፈጥሮ ስፍራዎች ይገኙበታል።
ታዲያ በሚፈለገው መጠን የዓለም ኅብረተሰብ ወደነዚህ ውብና ታሪካዊ መዳረሻዎች መጥቶ እንዲጎበኝና ከዚያ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እንዲገኝ በቂ ስራ ተሰርቷል ማለት ባይቻልም የዓለም ማህበረሰብ እጁን በአፉ የሚያስጭን ኢትዮጵያ ግን አሁንም በዘርፉ በስስት ከሚታዩ አገራት መካከል ቀዳሚ እንደሆነች ምንም ጥርጥር አያሻም።
ከመስህብ እሴቶቻችን መካከል በቀዳሚነት የሚነሱት ሃይማኖታዊና ባህላዊ ይዘት ያላቸው ሃብቶቻችን ተጠቃሽ ናቸው። ከነዚህ ውስጥ ደግሞ የመስቀል፣ የጥምቀት፣ የጨምባላላ፣ የእሬቻ እና ሌሎች የአደባባይ ክብረ በዓላትን ማንሳት ይቻላል። በገና ወቅት በታሪካዊቷና በአስደናቂ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የምትታወቀው የላልይበላ ከተማ ላይ የሚደረገው ታላቁ የክርስቶስ የልደት በዓል ሌላኛው የኢትዮጵያውያን ድምቀትና የቱሪስቶች ተመራጭ ቀን ነው።
እንደሚታወቀው ያለፉት ጥቂት ዓመታት ኢትዮጵያ በትህነግ የሽብር ቡድን አገር የማፍረስ ግብ ግብ የተፈተነችበት ጊዜ ነው። ታዲያ በነዚህ ጊዜያት ውስጥ የሰላም መደፍረሱን ተከትሎ በነዚህ ክብረ በዓላትና መስህቡን ለመመልከት በሚመጡ ጎብኚዎች ላይ እክል ተፈጥሮ ነበር።
ያ የቱሪዝም ዘርፉን በእጅጉ ከማዳከሙም በላይ የክብረ በዓላቱ ታዳሚዎችና ምእመናን ስነ ስርዓቱን በአግባቡ እንዳይፈፅሙ በጠብ አጫሪዎች ሙከራ ተደርጓል። ይሁን እንጂ በመላው ኢትዮጵያውያን የሕልውና ትግል ሽብርተኛ ቡድኑ ከወረራቸው የአማራና የአፋር ክልል አካባቢዎች ተመቶ በመውጣቱ አሁን ሃይማኖታዊና የቱሪዝም መስህብ የሆኑ በዓላት ቀድሞ በነበረው መልኩ መከበርና እሴቶቹን መጠበቅ እየተቻለ ነው። ለዚህ ማሳያ የሚሆነው ከሳምንት በፊት በታላቅ ድምቀት የተከበረው “ገናን በላሊበላ” ክብረ በዓል አንዱ ነው።
ከፊታችን ማክሰኞ ጀምሮ በተከታታይ ቀናት በታላቅ ድምቀት መከበር የሚጀምረው የጥምቀት በዓልም የክርስትና እምነት ተከታይ የሆኑት ኢትዮጵያውያን የሚያሸበርቁበትና መላው ኢትዮጵያውያን የሚኮሩበት ሆኖ እንደሚያልፍ ይጠበቃል። በተለይ ይህ በከተራ በዓል በአማራ ክልል የታሩካዊቷ ጎንደር ከተማ በተለየ መንገድ እንዲከበር ዝግጅት ተደርጓል።
ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች በክልሉ የሚገኙ ታሪካዊ ባህላዊና ሌሎች የመስህብ ስፍራዎችን ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል። ጥር 11 የሚደረገውም ታላቁ የጥምቀት በዓል በተለይ በታሪካዊቷ የጎንደር ከተማ በድምቀት መከበሩን ተከትሎ እጅግ ብዙ ታዳሚያን ይገኛሉ ተብሎ ይታሰባል። ይህንን አስመልክቶ እንግዶችን ለመቀበል በቂ የሰላምና ጸጥታ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የአማራ ክልል ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቋል።
ቅድመ ዝግጀቱን እና በዝግጅቱ የሚኖሩትን መርሐ ግብሮች አስመልክቶ መግለጫ የሰጡት የአማራ ክልል ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ጣሂር መሃመድ በክልሉ የፀጥታ ስጋት እንዳይኖር በቂ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ተናግረው ነበር፡፡
“ከፌዴራል መንግስት እና ከክልሉ የፀጥታ ኃይሎች ጋር በጋራ በቂ የጸጥታ ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል” ያሉት ቢሮ ኃላፊው እንግዶች ያለምንም ስጋት በዓሉን በአገራቸው ያሳልፋሉ ነው ያሉት፡፡ የጥምቀት ልዩ ድምቀት በማይዳሰስ ቅርስነት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት «UNESCO» እንዲመዘገብ ሆኗል። የጥምቀት በዓል ከጊዜ ወደ ጊዜ የዓለም አቀፉን ኅብረተሰብ ቀልብ እየሳበ የመጣ ታላቅ ሃይማኖታዊ ክብረ በዓል ነው።
ኢትዮጵያ ጥምቀትን ከሚያከብሩ ጥቂት የዓለማችን አገሮች አንዷ እና ዋነኛዋ ናት። ይህ ታላቅ ሃይማኖታዊ በዓል ከሕዝቡ ባህል ጋር ጥብቅ ትስስር ያለው ስለሆነም ከሃይማኖታዊ በዓልነቱ ባሻገር ባሕላዊ ፋይዳውም አብሮ የሚሄድ ነው። ለዚህም ዳንሱ ጭፈራው ሎሚ ውርወራውና የፍቅር ጓደኛ መተዋወቁ ከጥምቀት በዓል ጋር ተያይዘው የሚታዩ በሥነ-ቃልም የሚገለፁ ክስተቶች ናቸው። በሁሉም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ የጥር ወር የሚታወሰው በዓለ ጥምቀት የሚከበርበት በመሆኑ ነው።
ጥር 10 ባሕር መጥረጊያ ወይም ከተራ ወይም ዋዜማ ተብሎ ይታወቃል። ጥር 11 በዓለ ጥምቀት የሚከበርበት ዕለት ነው። በሊቃውንት ስምምነት ጥር 12 ቃና ዘገሊላ፣ ጥር 15 ቂርቆስ፣ ጥር 18 ሰባር አፅሙ፣ ጥር 21 አስተርእዮ ማርያም፣ ጥር 24 ቤተልሄም፣ ጥር 25 መርቆርዮስ ሲሆኑ በእነዚሁ ቀናት እንደ ጥር 11 ቀን ሁሉ ታቦታቱን ወደ ጥምቀተ ባሕር በማውረድና ፀበል በመረጨት የዕድሜና የፆታ ልዩነት ሳይኖር ሁሉም በጋራ ያከብሩታል። ‹‹ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ” እንደሌሎች አካባቢዎች ሁሉ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎችም የጥምቀትን በዓል የሚጠባበቁት በጉጉት ነው። አዳዲስ ልብስና ጫማ ይገዛሉ። አዳዲስ ልብስና ጫማ መግዛት ያልቻሉም ያላቸውን አጥበውና ተኩሰው ብቅ ይላሉ። በተጨማሪም ሴቶች እጅና እግርን ለማቅላት የሚያገለግል እንሶስላ ይሞቃሉ። የተለያየ ዓይነት ቁንዳላ ይሰራሉ።
በበዓለ ጥምቀቱ የተገኙት እናቶች ለበዓሉ ብለው ፀጉራቸውን በተለያየ የሹርባ አሠራር ይሰራሉ። “አንዳንዶቻችን ዓይነቶች ምን ምን ናቸው?” የሚል ጥያቄ መጠየቃችሁ አይቀርም። በአካባቢው በባህላዊነታቸው የሚታወቁት የሹርባ ዓይነቶች አለባሶ (ድርብ)፣ ስንቅር፣ ግልብጭ (እልም ያለ ቀጭን)፣ ግጫ፣ ሳዱላ፣ ጋሜና ቁንጮ ናቸው። ከነዚህ ሌላ ሕዝብና መንግሥት፣ አሳ፣ ጨረቃ፣ አፖሎ የሚባሉ ዘመን የወለዳቸው የሹርባ ዓይነቶችም አሉ።
እንደ ሹሩባው ሁሉ የሚለብሱት የጥልፍ አይነት ይለያል። ለምሳሌ ያክል የሃገር ባህል፣ ስንዴ፣ ጉብጉብ፣ ፍቅር ቁርጥ፣ ላሊበላ፣ ፋኖ፣ (ቆለኛ ወይም ባለ ክታብ ተብሎም ይጠራል) ሳተላይት፣ ሞረድ፣ ተመሳሳይ፣ መጋዝ፣ ማርዳ፣ ጄትና አበባ ጨምሮ ሌሎችም በርካታ አይነት አልባሳት አሉ። ይህ ዝርዝር የራያ ጥልፍ ተብሎ የሚታወቀውን አይጨምርም። ፋኖ በሚባል የሚታወቀው የጥልፍ ዓይነት ሦስት የተለያየ መጠሪያ እንዳለው ሁሉ ማርዳ የሚባለው የጥልፍ ዓይነትም ቅጥያ እየተጨመረለት ጉርድ ማርዳ፣ ንቅስ ማርዳና ሸረሪት ማርዳ እየተባለ ይጠራል።
ሃይማኖታዊው ጎን በሊቀ ብርሃኑ እይታ ሊቀ ብርሃናት ኢሳይያስ ወንድምአገኘሁ የጥም ቀት (ከተራን) ሃይማኖታዊ ጎን እንደሚከተለው ያስቀምጡታል። ከዋናው ክብረ በዓል (ከሃይማኖቱ ውስጥ የሚቀዱ የተለያዩ የትውፊት፣ የስነ ቃልና ባህላዊ አልባሳትም የዚያው አካል እንደሆኑ ነው እንደሚከተለው የሚነግሩን። የጥምቀትን በዓል አከባበር ከሁሉም በዓላት ለየት ከሚያደርጉት ምክንያቶችና ሁኔታዎች ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡
ጥር 10 ቀን በዋዜማው ከተራ በሚል በሚታወቀው በዚሁ ዕለት ባሕረ ጥምቀት ከተዘጋጀ በኋላ በመላው ኢትዮጵያ በከተማም በገጠርም በመሐል አገርና በጠረፍ ጭምር ባሉት አብያተ ክርስቲያናት የሚገኙት ታቦታት ሁሉ ከመንበራቸው ተነሥተው ወደተዘጋጀው ባሕረ ጥምቀት በመውረድና በተዘጋጀላቸው ድንኳን ውስጥ በማደር በዚያው በአደሩበት ድንኳን ውስጥም ማኅሌቱና ሥርዓተ ቅዳሴው ከተከናወነ በኋላ ባሕረ ጥምቀቱ ተባርኮ ሕዝበ ክርስቲያኑ ሁሉ የበረከቱ ተሳታፊ ከመሆናቸውም በላይ በዓሉ ከዋዜማው (ከከተራው) ቀን ጀምሮ ታቦታቱ ወደየአብያተ ክርስቲያናቱ ተመልሰው በመንበራቸው ላይ እስኪያርፉ ድረስ ሁለት ቀን ሙሉ በየባሕረ ጥምቀቱና በየመንገዱ ሁሉ በድምቀት የሚከበር በዓል በመሆኑ ነው፡፡
ይህም “ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለማትን የፈጠረና ሁሉንም ያስገኘ ልዑል አምላክ ሲሆን ለእኛ አርአያና ምሳሌ ይሆን ዘንድ በተዋሐደው ሥጋ ትኅትናን ገንዘብ በማድረግ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ሄዶ በአገልጋዩ በዮሐንስ መጥምቅ እጅ የመጠመቁ ምሳሌ” መሆኑን ያስረዳል፡፡
በሁለተኛ ደረጃ የጥምቀትን በዓል ካህናቱ በማኅሌትና በመዝሙር፣ በቅዳሴና በልዩ ልዩ ውዳሴ፤ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች በተለያዩ መዝሙራትና ሽብሸባዎች ሕዝበ ክርስቲያኑ ደግሞ ወንድ ሴት ሽማግሌና ወጣት ሕፃናትም ሳይቀሩ ሀብት ያለው አዲስ ልብስ ገዝቶ፣ ዓቅም የሌለው ደግሞ በቤት ውስጥ ያለውን አጥቦና አጽድቶ፤ ነጭ በነጭ ለብሶና አሸብርቆ እጅግ በደመቀና ባማረ ሁኔታ ታቦታቱን በማጀብ በዝማሬ፣ በሆታና በእልልታ፣ በከበሮ፣ በበገናና በእምቢልታ በታላቅ ዝግጅትና ሰልፍ በባሕረ ጥምቀቱ አካባቢና ታቦታቱ በሚያልፉባቸው መንገዶች ሁሉ በታላቅ ድምቀት የሚያከብረው በዓል መሆኑ ነው፡፡
“ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ የሚለው ዘይቤም የሚያመለክተው ይህንኑ የጥምቀቱን በዓል ታላቅነት ነው” የሚሉት ሊቀ ብርሃናት ኢሳይያስ ወንድምአገኘሁ ነጭ በነጭ ተለብሶ የሚከበር በዓል መሆኑም በጥምቀት የሚገኘውን አዲስ ልደትና ከሃጢአት ቁራኝነት የመንፃትን ምሥጢር የሚያመለክት መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
ህዝበ ክርስቲያኑ ሁሉ በተለይም ወጣቱ ኅብረተሰብ ታቦታቱ በሚያርፉባቸው የባሕረ ጥምቀት ቦታዎች ከካህናቱ ጋር በማደርና ቀንም ታቦታቱ ወደ መንበራቸው እስኪመለሱ ድረስ ታቦታቱን አጅበው በመዋል፣ በልዩ ልዩ ዝማሬ፣ በጨዋታና በታላቅ ደስታ የሚያከብሩት ታላቅ በዓል ነው፡፡ በዓሉ በሁሉም አህጉረ ስብከት እጅግ በደመቀ ሁኔታ የሚከበር መሆኑ የሚታወቅ ቢሆንም በደቡብ ክፍላተ ሀገር የመስቀል በዓል ከሁሉም በዓላት በላይ እንደሚከበር ሁሉ በሰሜኑ ደግሞ የጥምቀት በዓል ከሁሉም በዓላት የበለጠ እንደሚከበር ይታወቃል፡ ፡
በአጽንኦት ለመናገር እንጂ የመስቀል በዓል በሰሜን፣ የጥምቀት በዓልም በደቡብ አይከበርም ማለት ግን አይደለም፡፡ የአከባበሩ ሁኔታ እንደሀገሩ የሚለያይ መሆኑን ለመግለጥ ያህል እንጂ ሁሉም በዓላት በሁሉም ቦታ እንደሚከበሩ የታወቀ ነው፡፡
በተለይም የጥር ወር በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ሰብል ተሰብስቦ የሚያበቃበትና ምርት የሚታፈስበት ከመሆኑም በላይ ለገበሬው ኅብረተሰብ የዕረፍት ጊዜ ስለሆነ በዚያውም ላይ ምርቱ በጎተራ ስለሚኖር በዓሉ በዘፈን በጨዋታ ብቻ ሳይሆን በመብል በመጠጥ፣ በተድላና በደስታ የሚከበር በዓል በመሆኑ ይህ በዓል በካህናትና በምእመናን ዘንድ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ዘንድ እጅግ ተወዳጅና ተናፋቂ፤ የሁሉንም ቀልብ የሚያስብና የሚማርክ ነው። በመሆኑም ፆታና ዕድሜ ሳይለይ ሁሉም በታላቅ ስሜትና ፍቅር ያከብረዋል።
እንደ መውጫ ሊቀ ብርሃናት ኢሳይያስ ወንድምአገኘሁ ከላይ እንደነገሩን የጥምቀት በዓል በመላው ኢትዮጵያ ይከበራል። ይሁን እንጂ በልዩ ሁኔታ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ጎልቶ የሚታይ ነው።
ለዚህም ይመስላል የአማራ ክልል በተለይ በታሪካዊቷ የጎንደር ከተማ “ጥምቀትን በጎንደር” በሚል መርህ ሁሉም የእምነቱ ተከታይ እንዲያከብረው ጥሪውን ያደረገው። ከዚህ በተጨማሪም የሽብርተኛውን ትህነግ ወረራ በተቀለበሰበት ማግስት ከዚህ ቀደም በዓሉ ሲከበርበት በነበረው መንፈስና ስነስርዓት ልክ ማክበር አስፈላጊ መሆኑን ታምኖበታል።
ለዚህ ደግሞ ነገ የሚጀምረውን የጥምቀት በዓል ምክንያት በማድረግ ስነስርዓቱን በጎንደር ከተማ ተገኝተው ለሚያከብሩ ታዳሚዎች ደህንነት የተጠበቀና ከሁሉም በላይ በሰላም እንዲጠናቀቅ በቂ ዝግጅት መደረጉን የአማራ ክልል የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ዋና ኃላፊ አቶ ጣሂር ሞሃመድ ይፋ አድርገዋል።
የጎንደር ከተማ አስተዳደርና ሕዝብም እንግዶቹን የፍቅር እጆቹን በመዘርጋት እንደ ሁልጊዜው ሁሉ ጥምቀቱን በደማቅ ሁኔታ በጋራ ለማክበር መዘጋጀቱን አስታውቋል።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ጥር 8/2014