በካሜሩን አስተናጋጅነት እየተካሄደ በሚገኘው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ፤ ከአዘጋጇ አገር ጋር በምድብ አንድ ተደልድሎ በማይበገሩት አንበሶች ሁለተኛ ሽንፈት የደረሰበት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) በውድድሩ ከምድቡ የማለፍ ተስፋው ከዜሮ በታች ሆኗል።
ዋልያዎቹ ከነገ በስቲያ ሶስተኛውን የምድባቸውን ጨዋታ ከቡርኪናፋሶ ጋር ቢያደርጉም ጥሩ ሶስተኛ ሆነው አስራ ስድስቱ ውስጥ የመግባታቸው ጉዳይ ያከተመለት ይመስላል። ከቡርኪናፋሶ ጋር የሚያደርገውን የመጨረሻውን የምድብ ጨዋታም ለክብርና መርሃግብር ማሟያ የሚጫወት ይሆናል።
ይህም የዋልያዎቹን ቀጣይ ጨዋታ አጓጊ አያደርገውም። ይልቁንም ካለፉት ጨዋታዎች ትምህርት ወስዶ ቡድኑ በቀጣይ የተሻለ እንዲሆንና በተደጋጋሚ በአፍሪካ ዋንጫ እንዲቀርብ ምን መደረግ አለበት የሚሉ ጉዳዮች ትኩረት የሚስቡ ናቸው።
ዋልያዎቹ ከካሜሩን ጋር በነበራቸው ጨዋታ ከመጀመሪያው የኬፕ ቨርዴ ፍልሚያ የተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ በማድረግ በመጀመሪያው አርባ አምስት መነቃቃት አሳይተዋል።
ይህም ገና በአራተኛው ደቂቃ በዳዋ ሆጤሳ አማካኝነት ግብ አስቆጥረው ደጋፊያቸውን በደስታ እስከ ማስፈንጠዝ የደረሰ ነበር። ብዙም ሳይቆይ ግን የማይበገሩት አንበሶች የአቻነቷን ግብ በቪንሰንት አቡበከር የግንባር ግብ በማስቆጠር ወደ ጨዋታው ተመልሰዋል። ዋልያዎቹ የአቻነቷ ግብ
ከተቆጠረችባቸው በኋላ ከዚህ በፊት እንደነበረው ሳይደናገጡና የመንፈስ መረበሽ ውስጥ ሳይገቡ በተሻለ የኳስ ቁጥጥር የመጀመሪያውን አርባ አምስት በጀብድና ልበ ሙሉነት አጠናቀዋል።
ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ግን ወትሮም ስጋት የነበረው የዋልያዎቹ የአካል ብቃት ጉዳይ ዋጋ ማስከፈሉ አልቀረም። እንደተፈራውም ዋልያዎቹ በመጀመሪያው አርባ አምስት ያሳዩትን ትግል የሚያስቀጥል የአካል ብቃት ማሳየት ተስኗቸው ሲብረከረኩ ታይተዋል። ከስልሳ ደቂቃ በላይ በብቃት የሚጫወቱበት የአካል ብቃት እንደሌላቸውም በግልጽ ታይቷል። ይህም ከማይበገሩት አንበሶች አንሰው እንዲታዩ አድርጓቸዋል።
በእርግጥም ይህ በትክለ ሰውነትም ሆነ በአካል ብቃት እንዲሁም በተጫዋች ጥራት ረገድ ዋልያዎቹ ከማይበገሩት አንበሶች ጋር ሊወዳደሩ እንደማይችሉ ሳይታለም የተፈታ ነበር።
ይህም ዋልያዎቹ እስከ ትናንት በስቲያ ድረስ በአፍሪካ ዋንጫው በአንድ ጨዋታ አራት፣ በሁለት ጨዋታ አምስት ግቦችን በማስተናገድ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ግብ እንዲያስተናግዱ አድርጓቸዋል።
ዋልያዎቹ ብዙ ግብ ተቆጥሮባቸው ጨዋታውን ቢደመድሙም፣ የተጫዋቾቹ ልምድ ማነስና ከእድሜያቸውም አንጻር ብዙ የሚያስደንቅና ሽንፈቱም የሚያሸማቅቅ ተደርጎ ሊወሰድ አይችልም።
ሽንፈት ባያኩራራም ዋልያዎቹ ለደጋፊያቸው የሚመጥን ብቃት በመጀመሪያ አጋማሽ አሳይተዋል። 90 ደቂቃ እና ከዚያም በላይ ወጥ በሆነ የአካል ብቃት ጨዋታን መቀጠል የማይችለው የአገራችን እግር ኳስ የአካል ብቃት ዝግጁነት እና የጨዋታ ትኩረት ግን የዋልያዎቹን ኮኮቦች ተደናቂ ልፋት ሁሌም ዋጋ እንደሚያስከፍል ሊሰመርበት ይገባል።
የሚጠበቅም እውነታ ነው። ይህም የአገሪቱ ሊግና የክለቦች ነጸብራቅ እንጂ ትናንት ለአፍሪካ ዋንጫ የተሰባሰቡት ዋልያዎቹና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ የፈጠሩት ችግር አይደለም።
የሆነው ሆኖ ዋልያዎቹ በመጀመሪያው አጋማሽ ከኬፕቨርዴው ጨዋታ ስህተት ፈጥነው መማርና መጫወት ከቻሉ እምቅ አቅማቸውን የመጠቀም ክህሎት የተቸራው እንደሆኑ ፍንጭ አሳይተዋል። በነፃነት ከማይጠቅሙ እንቅስቃሴዎች ተቆጥበው በህብረት መፋለም ከቻሉ ምን መሥራት እንደሚችሉ በተግባር ለሚሊዮኖች አረጋግጠዋል ።
የኦሌምቤ ስቴድየም የቩቩዜላ ጩኸትን ያቀዘቀዘ በሙከራ የታጀበ መልሶ በማጥቃት የተቃኘ ተደናቂ እንቅስቃሴ ውበቱ አባተ እና ልጆቹ በመጀመሪያው እረፍት በማሳየታቸው ሊበረታቱ ይገባል።
የሁለቱ ተመላላሾች ሱሌማን ሀሚድ እና ረመዳን የሱፍ ደካማ እንቅስቃሴ ግን ወትሮም የሜዳውን መሥመሮች ለሚጠቀመው ጉልበተኛው የማይበገሩት አንበሶች / ካሜሮኖች/ አጥቂ የቪሰንት አቡበከር የጎል መንገድ እንደሆነው ሁሉ በሰኞው ጨዋታ ትኩረት ተሰጥቶት ሊታረም ይገባል። ግብ ጠባቂው ተክለማርያም ሻንቆ እና ተከላካዩ አስቻለው ታመነ ከቡድን ጓደኞቻቸው ጋር የአቅማቸውን ጥግ በተደናቂ ብቃት በማሳየታቸው ምስጋና ሊነፈጋቸው አይገባም።
የዋልያዎቹን ብቸኛ ግብ ከመረብ ያሳረፈው ዳዋ ሆጤሳና አማካኙ መሡድ መሐመድና ሁለቱ አማኑኤሎች ሌሎቹ የቡድኑ ጠንካራ ጎኖች ስለነበሩም ምስጋና ሳይቸራቸው ቢታለፍ ንፉግነት ነው።
አሰልጣኝ ውበቱ አባተም ከጨዋታው በኋላ ከካፍ ዌብ ሳይት ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ በተጫዋቾቻቸው በተለይም የመጀመሪያ አርባ አምስት ደቂቃ እንቅስቃሴ መደሰታቸውን በመግለጽ ቢያንስ የአቻውን ውጤት አስጠብቆ ለመውጣት የተቻለውን ሁሉ ጥረት እንዳደረጉ ተናግረዋል።
በዋልያዎቹና በማይበገሩት አንበሶች መካከል የነበረው ትልቁ ልዩነትም የልምድ መሆኑን በመጥቀስ ዋልያዎቹ ልምድ የሚያዳብሩት በእንደዚህ አይነት ትልልቅ ጨዋታዎች እንደሆነ አስገንዝበዋል።
በአጠቃላይ ዋልያዎቹ በመጀመሪያዎቹ አርባ አምስት ደቂቃዎች በነበራቸው የራስ መተማመን ላይ የዳበረ የአካል ብቃት ለቀጣይ ጉዞ እንደ ማሣያ ተደርጎ መጠናከርም እንዳለበት በመጠቆም ቡድኑን ማበረታታት ተገቢ ይሆናል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጥር 7/2014