በአገር ውስጥ ልማትና ዕድገት ሊረጋገጥ የሚችለው ሁሉም ዜጋ በተሰማራበት መስክ ጠንክሮ ሲሰራ ነው። ታታሪነት ግን ብቻውን የአገርን ኢኮኖሚ ሊለውጥ አይችልም። ጥረት ሁሌም በእውቀት፣ ቴክኖሎጂና የስራ ፈጠራ ሊታገዝይገባል።
በተለይግዜው በድካም መስራት ሳይሆን በብልሃት ሰርቶ ውጤት ማምጣትን የሚጠይቅ በመሆኑ ይህን መንገድ መከተሉ ሀገርን በሁለንተናዊ መልኩ በፍጥነት ለመቀየር ያግዛል። እውቀት፣ የስራ ተነሳሽነት እና ብልሀት ለውጤት የሚያበቁ ጥምረቶች ናቸው።
በዋናነት ደግሞ አዳዲስ የፈጠራ ስራዎች ራስንና ወገንን ከመጥቀም ባለፈ የአገርንም ኢኮኖሚ በመለወጥ ረገድ ጉልህ ሚና ስለሚጫወቱ በበርካታ አገራት ትኩረት ተሰጥቶባቸው ይሰራባቸዋል። በኢትዮጵያም ከቅርብ አመታት ወዲህ ለስራ ፈጠራ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ይገኛል።
የኢፌዴሪ ስራ እድል ፈጠራ ኮሚሽን ከአንድ ዓመት በፊት ያዘጋጀውና በተለያዩ ዘርፎች ቁልፍ ችግሮችን ለመፍታትና የስራ እድሎችን ለመፍጠር የሚችሉ አዳዲስ ሀሳቦችን ያፈለቁ ሀያ ወጣቶችን የሸለመበት ፕሮግራምም ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው።
አሁን ደግሞ የኢትዮጵያ ኢንተርፕሪነርሺፕ ልማት ማእከል በሀገሪቱ ጎልቶ የሚታየውን የስራ አጥነት ችግር ለመቅረፍና የንግድ ስራ ፈጣሪነትን መንፈስ በኢትዮጵያ እንዲጎለብት ለማድረግ በርካታ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል።
ማእከሉ ለመጀመሪያ ግዜ የንግድ ፍቃድ ያላቸውና የምርት ናሙና በማምረት ደረጃ ላይ ያሉ ጀማሪ የንግድ ስራ ፈጣሪዎች የሚወዳደሩበት የኢንኩቤሽን ፕሮግራም በአገር አቀፍ ደረጃ በቅርቡ ይፋ አድርጓል።
በዚሁ መሰረትም ጀማሪ የንግድ ስራ ፈጣሪዎችን በተለያዩ ዘርፎች ሲያወዳድር ቆይቶ ከሰሞኑ ለመጨረሻው ዙር ያለፉ 6 ምርጥ አሸናፊዎችን ሸልሟል። ወጣት ቴዎድሮስ ማሞ በዚህ የስራ ፈጠራ ውድድር ቀርበው በማሸነፍ ለሽልማት ከበቁ ስድስት ተወዳዳሪዎች መካከል አንዱ ነው።
ትውልድና እድገቱ በሀረር ከተማ ሲሆን የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እዛው ሀረር ተከታትሏል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በመግባት በኬሚካል ኢንጂነሪንግ የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቷል። የሁለተኛ ዲግሪውን ደግሞ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢንቫይሮንሜንታል ኢንጂነሪንግ ተቀብሏል። ከዛም በኋላ የተወሰኑ መስሪያ ቤቶች ላይ በተማረባቸው ሞያዎች በቅጥር ሰርቷል። ከጀማሪ እስከ ከፍተኛ ሺፍት ኢንጂነርነት ደረጃ ድረስ በናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ ውስጥ ለሁለት ዓመታት ያህል በሞያው አገልግሏል።
ለአጭር ጊዚያቶች ደግሞ በሌሎች ስፖንጅ ፋብሪካዎችና ኬሚካል አስመጪ ድርጅቶች ውስጥ ተቀጥሯል። ከሀረር ወደ አዲስ አበባ ከመጣ ሰባት አመታት አካባቢ የሆነው ወጣት ቴዎድሮስ፤ በናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ ውስጥ ሲሰራ ጥሩ ደሞዝ ተከፋይ የነበረ ቢሆንም የራሱ ስራ እንዲኖረው ሁሌም ፍላጎቱ ነበር። የራሱን ቾክና ሳሙና ለማምረትም ተደጋጋሚ ሙከራዎችን አድርጓል። የፕላስቲክ ውጤቶችን ለማምረትም ሙከራ አድርጓል።
በመጨረሻ ግን አንዱ ለአንዱ ግብአት በመሆን ወደራሱ የፋይበር ግላስ ማምረት ሥራ ለመግባት ወሰነ። የፋይበር ግላስ ቴክኖሎጂ ለኢትዮጵያ ገና አዲስ እንደመሆኑ በተለይ ደግሞ ከቤት ውስጥ ፈርኒቸር ጀምሮ እስከ መኪና አካል ድረስ ጥቅም ላይ የሚውል በመሆኑ በዚህ ዘርፍ ላይ ቢሰማራ ውጤታማ እንደሚሆን አመነ። በመቀጠልም ከአንድ ዓመት በፊት በ5 ሺ ብር መነሻ ካፒታል ጀሞ መስታዎት ፋብሪካ አካባቢ ከመንግስት በተረከበው የማምረቻ ሼድ ውስጥ በመግባት የፋይበር ግላስና የአበባ መትከያዎችን ማምረት ጀመረ።
የኢትዮጵያ ኢንተርፕሪነርሺፕ ልማት ማእከል በቅርቡ ባዘጋጀው የንግድ ፍቃድ ያላቸውና የምርት ናሙና በማምረት ደረጃ ላይ ያሉ ጀማሪ የንግድ ስራ ፈጣሪዎች ውድድር የኢንኩቤሽን ፕሮግራም ላይ
ተሳተፈ። የአበባ መትከያን ከፋይበር ግላስ መስራት ከዚህ በፊት የነበረ ቢሆንም እርሱ ግን በፋይበር ግላስ በሚሰራው የአበባ መትከያ ላይ እሴት በመጨመር አዲስ ነገር ይዞ በውድድሩ ላይ ብቅ አለ። እርሱ ለውድድር ይዞት የቀረበው ከፋይበር ግላስ የሚዘጋጅአዲስ የአበባ መትከያ አትክልቱን ያለሰው ራሱን በራሱ የሚያጠጣ /self watering planter/ ሲሆን በዚህ ቴክኖሎጂ አማካኝነት አትክልቱን የሚያጠጣው ውሃ የተረፈው ወደ ውጪ ከመፍሰስ ይልቅ ከአፈሩ ስር በተዘጋጀለት ማስቀመጫ ይታቆራል።
አፈሩ እየደረቀ ሲመጣ የታቆረው ውሃ ውስጥ የተገጠመና በልዩ ሁኔታ የተዘጋጀ የጥጥ ክር ከአትክልቱ ስር ጋር እንዲገናኝ በማድረግ ክሩ በሚያገኘው እርጥበት አማካኝነት አትክልቱ የታቆረውን ውሃ መልሶ የሚጠጣበት ሁኔታ ይፈጠራል።
ይህም በተለይ አትክልቶችን ለማጠጣት ሰነፍ ለሆኑ እና የጊዜ እጥረት ለሚገጥማቸው ነገር ግን በቢሮዎቻቸው እና በመኖሪያ ቤታቸው አካባቢ አበባ እንዲኖራቸው ለሚፈልጉ ሰዎች ቴክኖሎጂውን ለመጠቀም ጥሩ አጋጣሚ ፈጥሯል። ከዚህ ባለፈ ደግሞ የፈጠራ ስራው ውሃ እንዳይባክንም አስችሏል። ወጣት ቴዎድሮስ ይህንኑ እሴት የተጨመረበት የስራ ፈጠራ ውጤት የኢትዮጵያ ኢንተርፕሪነርሺፕ ልማት ማእከል በቅርቡ ባዘጋጀው ውድድር ላይ ይዞ በመቅረብ በአገር አቀፍ ደረጃ ከተሳተፉ አራት መቶ ተወዳዳሪዎች ውስጥ የተለያዩ ዙሮችን በማጣሪያ ካለፉ ሀያ አራት የንግድ ስራ ፈጠራ ተወዳዳሪዎች አንዱ ለመሆን ችሏል።
አንድ አመት ከስድስት ወር በፈጀው በዚህ ውድድር ከነዚሁ ሀያ አራት ተወዳዳሪዎች መከካከል ለመጨረሻው ዙር ከደረሱ ስድስት ምርጥ የንግድ ስራ ፈጠራ ተወዳዳሪዎች መካከል አንዱ ለመሆን በቅቷል፡ በመጨረሻም ከስድስቱ ተወዳዳሪዎች ውስጥ ውድድሩን አምስተኛ ሆኖ በማጠናቀቁ የ125 ሺ ብር ተሸላሚ መሆን ችሏል። በቀጣይም የፈጠራ ስራውን ይበልጥ ለማበልፀግ ወደ ኢንኩቤሽን ፕሮግራም ገብቶ የሚሰራ መሆኑን ይናገራል።
የፈጠራ ስራውን ለማሳደግ ተጨማሪ የፋይናንስ ድጋፍ ከማእከሉ እንደሚያገኝ ይጠበቃል። በአሁኑ ጊዜ ቴዎድሮስ ማሞ የፕላስቲክ ውጤቶች ማምረቻ ኢንተርፕራይዝ ከተመሰረተ አንድ አመት ያስቆጠረ ሲሆን በዚሁ በፋይበር ግላስ ዘርፍ ገበያ ውስጥ ገብቶ ምርቶቹን ለሽያጭ እያቀረበ ይገኛል። በከተማዋ የፋይበር ምርቶችን ከሚያመርቱ ድርጅቶች ውስጥ ከአንድ እስከ አምስተኛ ደረጃ ካሉት ውስጥ አንዱ ለመሆን ችሏል።
‹‹ይሁንና ይህ እሴት የተጨመረበት የፈጠራ ስራ ለማህበረሰቡ አዲስ በመሆኑ በገበያ ውስጥ ይበልጥ ዘልቆ ለመግባትና ህብረተሰቡንም ለማለማመድ ትንሽ ግዜ ይፈልጋል›› ይላል የንግድ ስራ ፈጠራው አምንጪና የኢንተርፕራይዙ ባለቤት ወጣት ቴዎድሮስ ማሞ። የፈጠራ ስራው የኢንተርፕራይዙ አንዱ የፋይበር ግላስ ምርት ሽያጭ አማራጭ እንጂ እንደ ዋና ምርት የሚቆጠር እንዳልሆነም ይገልጻል።
ኢንተርፕራይዙ በአሁኑ ወቅት ሶስት ቋሚ ሰራተኞችን በመያዝና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ደግሞ ተጨማሪ ሰራተኞችን በኮንትራት ቀጥሮ ራሱን በራሱ የሚያጠጣ የአበባ ማስቀመጫን ጨምሮ ሌሎች የፋይበር ግላስ ምርቶችን ያመርታል። ሁሉንም አይነት የፋይበር ግላስ ምርቶችን የማምረትና ምርቶቹንም ያለገደብ ለገበያ የማቅረብ አቅም አለው። በመንግስትም ሆነ በግለሰብ ደረጃ የሚመጡ የትኞቹንም ትእዛዞች ተቀብሎ የማምረት አቅም ገንብቷል።
የፋይበር ግላስ ቴክኖሎጂ ብዙም ትላልቅ ማሽነሪዎችን የሚጠቀም ባለመሆኑ ኢንተርፕራይዙ ምርቶቹን ለማምረት ግራይንደር፣ ኮምሬሰርና ድሪል የመሳሰሉ አነስተኛ መሳሪያዎችን በመጠቀም ምርቶቹን ያመርታል።
ምርቱን ለማምረት የሚረዱ ጥሬ እቃዎችን ደግሞ ከአስመጪዎች ይረከባል። በአምስት ሺ ብር መነሻ ካፒታል ስራውን የጀመረው ኢንተርፕራይዙ በመሀል ከአዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም ተጨማሪ ገንዘብ በመበደርና በሂደትም ብድሩን በመክፈል በአሁኑ ግዜ ካፒታሉን ወደ 500 ሺ ብር አሳድጓል።
በቀጣይም ኢንተርፕራይዙ በፋይበር ግላስ ቴክኖሎጂ ላይ በስፋት ገብቶ የመስራትና http:// www.finefibertech.com በተሰኘው ድረ ገፁ አማካኝነት የማስተዋወቅ እቅድ አለው።
የሞተር ብስክሌት አካላቶችን፣ የመኪና መብራት ሽፋኖችንና ሌሎችንም የፋይበር ግላስ ውጤቶችን የማምረት ሃሳብም አለው። በተለያዩ የፋይበር ግላስ ዘርፎች ውስጥ ገብቶ የመስራትና ቴክኖሎጂውንም የማዳበርና የማዘመን ሰፊ እቅድ ነድፏል።
በተለይ ደግሞ ችግር ፈቺ የሆኑ፣ ማህረሰቡ የሚያጋጥመውን ተግዳሮት የሚፈቱና በቀላሉ ሊገኙ የሚችሉ የፋይበር ግላስ ማምረት ስራዎች ላይ አተኩሮ የመስራት ውጥንም ይዟል።
በተጨማሪም ኢንተርፕራይዙ የማምረቻ ቦታውን በማስፋት የምርት መጠኑን ማሳደግ፣ የሰራተኞቹን ቁጥር የመጨመር እንዲሁም ለመንግስትም ትልቅ ግብር ከፋይ የመሆን ራዕይ ሰንቆ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።
በምርት ሂደት የጥሬ እቃዎች አቅርቦት ችግር የለም የሚለው ወጣት ቴዎድሮስ ከተወሰነ ግዜ በኋላ ራሱ ኢንተርፕራይዙ ጥሬ እቃዎቹን ከውጪ አገር የሚያስገባበት እድል እንዳለ ይናገራል። ይሁንና የፋይናንስ እጥረትና የመሸጫ ቦታ አለማግኘት የኢንተርፕራይዙ ዋነኛ ፈተናዎች መሆናቸውን አልሸሸገም።
ወጣት ቴዎድሮስ ኢንተርፕራይዙ ከተቋቋመ ገና አንድ አመት ቢሆነውም ገና ሲቋቋም ከነበረው ሁኔታ ጋር ሲነፃፀር በካፒታል፣ በሰው ሀይልና በቁሳቁስ በርካታ ለውጦች የመጡ በመሆናቸው በቀጣይ ወደስኬት ለመንደርደር የሚያስችለውን መሰረት መጣሉን ይናገራል።
ገበያ ውስጥ መግባቱና ከዚህ ባለፈ ደግሞ በአገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደ የንግድ ስራ ፈጠራ ውድድር ላይ ቀርቦ ከምርጥ ስድስቶቹ አንዱ ሆኖ እውቅናና ሽልማት ማግኘት መቻሉም ኢንተርፕራይዙ ገና ከጅምሩ ያገኘው ትልቅ ስኬት መሆኑንም ይጠቁማል። ይሁን እንጂ ይህ ገና ጅምር እንጂ መጨረሻ እንዳልሆነ ያመለክታል።
ይህን ስኬት ማግኘት የቻለውም ጠንክሮ በመስራቱ፣ በተለይ ደግሞ ጭንቅላቱን ተጠቅሞ በብልሃት ስራዎችን በማከናወኑ መሆኑንም ወጣት ቴዎድሮስ ይጠቁማል። በዚህ ሂደት ታዲያ በርካታ ውጣውረዶች አጋጥመውታል። ችግሮችንም በብልሃትና በእውቀት በማለፍ አሁን ለደረሰበት ደረጃ ለመድረስ መቻሉን ይናገራል።
በተመሳሳይ ሌሎች ወጣቶችም ተቀጥሮ ከመስራት ይልቅ የራሳቸውን ስራ ፈጥረው እንዲሰሩና ራሳቸውን እንዲለውጡ በቅድሚያ ከምቾት ቀጠና መውጣት እንዳለባቸው ራሳቸውን ማሳመን ይገባቸዋል ይላል።
ከነገው የዛሬ መቸገር ይሻላል ብለው በድፍረት የራሳቸውን ቢዝነስ ለመጀመር ፍፁም ማመንታት እንደሌለባቸውም ይጠቁማል። ለዚህም ተደጋጋሚ ሙከራና ልፋት እንደሚጠይቅ ይመክራል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ጥር 7/2014