በተቻለ አቅም የሰውነትዎን አጥንት የሚያጠነክሩና ጤንነታቸውንም የሚጠብቁ ምግቦችን መመገብ እንደሚያስፈልግ በተደጋጋሚ ጊዜ በጤና ባለሙያዎች ይመከራል። በተመሳሳይ ደግሞ አጥንትዎን ከሚጎዱ ምግቦችና መጠጦች ራስዎን እንዲያርቁም ባለሙያዎቹ አበክረው ይመክራሉ።
በተለይ ደግሞ በካልሺየም የበለፀጉና የአጥንት ጥንካሬን የሚጨምሩ ምግቦችን መመገብ እንዲሁም ‹‹ኦስቲዮፖረሰስ›› የተሰኙና አጥንትን የሚያዳክሙ በሽታዎችን ለመከላከል የሚረዱ የቫይታሚን ‹‹ዲ›› ምግቦችን ማዘውተር ለአጥንት ጤና ፍትሁ መድሃኒቶች ናቸው ይላሉ የጤና ባለሙያዎቹ። የሚከተሉት ሰባት ምግቦች ደግሞ አጥንትን የሚያዳክሙ ናቸው ሲሉ ይዘረዝራሉ።
1ኛ፡- ከፍተኛ የሶዲየም ያላቸው ምግቦች
የአጥንትዎን ጤንነት ለረጅም ጊዜ ማስቀጠል ከፈለጉ ጨው የበዛባቸው ምግቦችን ማስወገድ ይኖርብዎታል። ምክንያቱም ብዙ ጨው በተጠቀሙ ቁጥር በርከት ያለ ካለሺየም ከሰውነትዎ ስለሚያጡ ነው። ጨው የበዛባቸውን ምግቦች በብዛት የሚጠቀሙ ሰዎች በይበልጥ ‹‹ኦስቲዮፖረሰስ›› ለተሰኘውና የአጥንት መቀጨጨን ለሚያስከትለው በሽታ እንደሚጋለጡም በጥናት ተረጋግጧል።
2ኛ፡-‹‹ካፌይን››
ጥናቶች እንደሚያሳዩት ‹‹ካፌይን›› የተሰኘው ንጥረ ነገር /በብዛት በኮካ ኮላና መሰል የለስላሳ መጠጦች ውስጥ ይገኛል /በአጥንት ውስጥ የሚገኙ የካልሺየም ንጥረ ነገሮችን መምጠጥ የአጥንት ጥንካሬን ያሳጣል። የአጥንትዎን ጥንካሬ ለመጠበቅና ‹‹ኦስቲዮፖረሰስ›› ከተሰኘው በሽታ ለመከላከል ታዲያ ‹‹ካፌይን›› ከውሳጣቸው የወጣላቸውን ቡናና ሻይ እንዲጠጡ ይመከራሉ።
3ኛ፡- አልኮል
አልኮል በከፍተኛ ደረጃ በአጥንት ላይ ጉዳት ከሚያስከትሉ መጠጦች ውስጥ አንዱ ሲሆን በተለይ የአጥንት መሰንጠቅና በአጥንት መገጣጠሚያ አካባቢዎች ላይ ህመም በመፍጠር የአጥንትዎን ጤና ያቃውሳል። አልኮል በአጥንት ጤና ላይ የሚያስከትለው ጉዳትም ገና በለጋ እድሜ ላይ ሊንፀባረቅ የሚችል በመሆኑ አሁኑኑ ራስዎን ከአልኮል እንዲያርቁ በጤና ባለሙያዎቹ ይመከራሉ።
4ኛ፡- ጥራጥሬዎች
እንደ ባቄላ፣ አተርና ለውዝ የመሳሰሉ የጥራጥሬ ምግቦች በውስጣቸው ‹‹ፋይቴትስ›› የተሰኙና አጥንትን የሚገነቡ ካሊሺየሞችን መጠው የሚወስዱ ንጥረ ነገሮችን የያዙ ናቸው። ይሁንና ባቄላ በማግኒዢየም የበለፀገና ‹‹ኦስቲዮፖረሰስን›› ለመከላከል የሚረዳ ብሎም ለመላው የሰውነት ጤናም ጠቃሚ በመሆኑ ሙሉ በሙሉ ከምግብ ስርዓትዎ ውስጥ ማስወገድ አይኖርብዎትም።
ባቄላ በውስጡ የያዘውን የ‹‹ፋይቴትስ›› ንጥረ ነገር ለመቀነስ ከመመገብዎ በፊት ለተወሰኑ ሰዓታት በውሃ ውስጥ ቢዘፈዝፉትና አብስለው ቢመገቡት ተመራጭ መሆኑንም የጤና ባለሙያዎቹ ይጠቁምዎታል።
5ኛ፡- ቀይ ስጋ
ቀይ ስጋን ከልክ በላይ መመገብም በአጥንት ውስጥ ያሉትን የካልሺየም ንጥረ ነገሮችን በከፍተኛ ደረጃ ስለሚያጠፋ ከሚመገቡት ምግብ ውስጥ ሊቀነሱት ይገባል። በተለይ ደግሞ የአጥንት በሽታ ያለባቸው ሰዎች የቀይ ስጋ ፍጆታቸውን በመቀነስ በሳምንት ቢያንስ ሁለት ጊዜ ብቻ እንዲመገቡ የጤና ባለሙያዎች ይመክራሉ።
6ኛ፡- ጣፋጭ
ብስኩቶች ስኳር የአጥንትን ጤና የሚያዳክም እንደመሆኑ መጠን ስኳር የበዛባቸውን ብስኩቶችን መመገብም ለአጥንት ጉዳት የማጋለጥ ከፍተኛ አቅም አለው። የአጥንትዎን ጤና በዘላቂነት ለመጠበቅ ከፈለጉ ታዲያ ከመጠን ያለፈ ስኳር መጠቀምዎን ያቁሙ ሲሉ የጤና ባለሙያዎቹ ያሳስብዎታል።
7ኛ፡- ሶዳ
ሶዲየም ክሎራይድ በውስጣቸው የያዙና እንደ ኮካ ኮላ የመሰሉ የለስላሳ መጠጦችን በሳምንት ሰባትና ከዛ በላይ ብርጭቆ መጠጣት በአጥንት ውስጥ ያለውን የማዕድን ክምችት ከመቀነስ በዘለለ ለአጥንት መሰንጠቅና ተያያዥ ችግሮች ሊያጋልጥ እንደሚችል የዘርፉ ባለሙያዎች ያስጠነቅቃሉ።
ሶዳ አጥንትን ሊጎዳ የሚችል ከፍተኛ መጠን ያለው ስኳር በውስጡ መያዙንም እነዚሁ ባለሙያዎች ተናግረው፤ ለአጥንትዎ ጤና የሚያስቡ ከሆነ ማንኛውንም አይነት ስኳር የበዛባቸው የለስላሳ መጠጦች ከቀን ተቀን የምግብዎ ዝርዝር ውስጥ መሰረዝ እንደሚገባዎ ይጠቁማሉ።
ይህም ኮላ ኮላ ያልሆኑና ካፌይን የተሰኘው ንጥረ ነገር በውስጣቸው ያለና የሌለውን እንደሚያካትት ጠቅሰዋል። ምንጭ፡- ፍሊክሎድድ
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ጥር 7/2014