ባለፈው ሳምንት የመጨረሻ ቀናት በኢትዮጵያ ያልተጠበቀ ክስተት ተስተናግዷል። በተለያዩ ወንጀሎች ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩ ፖለቲከኞች ክሳቸው ተቋርጦ ከእስር ተለቀዋል። መንግስት ቀደም ብሎ ማብራሪያ ሳይሰጥ የፖለቲከኞቹን ክስ ማቋረጡ በብዙዎች ዘንድ ግርታን መፍጠሩ አልቀረም።
በተለይም የሕወሓት መስራቾች ከእስር መለቀቅ ለብዙዎች ዱብዳ ሆኖ ነበር። ጉዳዩ በብዙዎች ዘንድ ግርታን መፍጠሩ እና ጥያቄዎችን ማስነሳቱ አይደንቅም። ሕዝቡ የመረጠው መንግስት የሚወስናቸው ውሳኔዎች ዙሪያ ጥያቄ የማንሳት መብትና ስልጣን አለው። ሆኖም ሕዝቡ ሊረዳ የሚገባው አንድ ቁልፍ ጉዳይ አለ ብዬ አምናለሁ።
ሁሉንም ነገር መንግስት በቅድሚያ ለሕዝቡ ይፋ ካደረገ በኋላ ሊፈጽም አይችልም። መንግስት ለአገርና ለሕዝብ ይጠቅማል ብሎ ሲያስብ ቀድሞ ለሕዝቡ ይፋ ሳያደርግ የሚያስተላልፋቸው ውሳኔዎች እንደሚኖሩ ሕዝቡ ሊረዳ ይገባል፡፡
መንግስት የወሰደው እርምጃ ተገቢና ወቅታዊ እንደነበር ከአሁኑ ውጤቶች መታየት ጀምረዋል። የኢትዮጵያ መንግስት የወሰደው ቆራጥ እርምጃ በኢትዮጵያ ላይ አደገኛ አጀንዳ ቀርጸው ሲንቀሳቀሱ የቆዩትን አካላት አጀንዳ እያሳጣቸው ይገኛል።
የኢትዮጵያን ስም ከዘር ማጥፋት፣ ከጦር ወንጀል እና ሰብዓዊነት ላይ ከሚፈጸም ወንጀል ጋር አያይዘው ደጋግመው ሲያነሱ የነበሩ አካላት በመጠኑም ቢሆን ጋብ ማለት ጀምረዋል። የኢትዮጵያ እጅ ለመጠምዘዝ ሲሞክሩ የነበሩ ኃይሎች ጫናቸውን መቀነስ ጀምረዋል። የተለያዩ አይነት ማዕቀቦችን ለማስጣል ጥረት ሲያደርጉ የነበሩ አካላትም አካሄዳቸውን ቆም ብለው እንዲመለከቱ አድርጓል፡፡ የሕወሓት መሪዎች እና ተከታዮቹ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት ላይ እንዲሁም በአማራ እና አፋር ክልል ሕዝቦች ላይ የፈጸሙትን እኩይ ተግባር ማንም አልካደም።
ሊክድም አይችልም። ሁሌም መወገዝ ያለበት ተግባር ነው። ይሁን እንጂ መንግስት የኢትዮጵያን ችግሮች በሰላማዊና በዘላቂነት ለመፍታት ጥፋትንና በቀልን በብሔራዊ ውይይት ለመፍታት በማለም ውሳኔ ላይ ደርሷል። ይህ ደግሞ የአገሪቱን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ብቸኛው አማራጭ ነው።
በሰላማዊ መንገድ ያልተቋጨ ግጭት ሁሌም ዋጋ እያስከፈለ መቀጠሉ አይቀሬ ነው። ከግጭት አዙሪት መውጣት የሚቻለው አገሪቱ አሁን ለገባችበት ጦርነት ዘላቂና ሰላማዊ መፍትሄ መስጠት ሲቻል ነው፡፡ መንግስት ከሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር አገራዊ ምክክር እና ውይይት በማድረግ የአገሪቱን ቀጣይ እጣ ፈንታ ወደ መልካም አቅጣጫ ሊያመራ የሚችል ውሳኔዎችን አሳልፏል።
የአገሪቱ የዘመናት የፖለቲካ አለመግባባቶችን መፍታት የሚቻለው በጦርነት ሳይሆን ሁሉን ባሳተፈ ብሄራዊ ውይይት ነው። ይህ በራሱ ለአገር የወደፊት እጣ ፋንታ ከሚጨነቅ ቆራጥ መንግስት የሚጠበቅ ቆራጥ እርምጃ ነው።
የመንግስትን ቆራጥ እርምጃ መሬት ለማስያዝ ግን ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች መሳተፍ አለባቸው። ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በውይይት መድረክ ላይ ካልተሳተፉ ብሄራዊ ውይይቱ ውጤታማ ሊሆን አይችልም። ሁሉ የፖለቲካ ኃይሎች ያልተሳተፉበት ድርድርና ውይይት ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት እንደማያስችል ሌሎች አገራትን እንደ ማሳያ ማንሳት አይጠበቅብንም።
ኢትዮጵያ ራሷ ጥሩ ማሳያ ነች። የደርግ ስርዓት መገርሰስን ተከትሎ በ1983 ዓ.ም የተደረገው ውይይትና ምክክር አገሪቱ በወቅቱ ከነበረችበት ችግር ያስወጣት ቢመስልም የአገሪቱን ችግር በዘላቂነት ሊፈታ አልቻለም። አገሪቱን የአንድ ቡድን መፈንጫ ከማድረጉ ባሻገር ለሌላ ዙር ጦርነት ነው የዳረጋት። መንግስት አገሪቱ ከዚህ ቀደም ካለፈችበት መንገድ ትምህርት መውሰዱን አመላካች ነው። በመሆኑም የሰሞኑ እስረኞቹን የመፍታት ፖለቲካዊ ውሳኔው ወቅታዊ እና ተገቢ ነው የሚል እምነት አለኝ።
እዚህ ጋር አንድ መረሳት የሌለበት ከአገራችን ባህል አኳያ በዳይና ተበዳይ ይቅር መባባል ይቅርታን መቀበል መስጠት የተለመደ ጥንታዊ ባህላችን ነው። ተበዳይ ለዘለቄታ አብሮ ለመኖር ቂም በቀልን ትቶ በዳይን ይቅር ብሎ በሽምግልና ችግርንም መፍታት ለአገር ልማት በጋራ ለመኖር እና ለመስራት ታላቅ መፍትሄ መሆኑ የሚታወቅ ነው። ይቅርታ ማለት በአንተ ላይ የደረሰውን ጉዳት መርሳት ወይም ማመካኘት ወይም ጉዳቱን ካደረሰው ሰው ጋር መስማማት ማለት አይደለም።
እዚህ ላይ መንግስት ትኩረት አድርጎ መስራት ያለበት ጉዳይ ያለ ይመስለኛል። መንግስት ለአገር ይበጃል ብሎ የወሰነው ውሳኔ ሕዝቡ ለፍትሕ እና ለፍትሕ ተቋማት ያለው አመለካከት ላይ ጥላ እንደያጠላ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል። መንግስት ሕግና ስርዓት የማስከበር አቅም እንደሌለው ተደርጎ እንዳይወሰድ የመንግስት ውሳኔ ለሕዝቡ በአግባቡ ሊብራራ ይገባል።
በዚህ ረገድ የብዙሃን መገናኛዎች በስፋት ሊሰሩበት ይገባል። የመንግስት ውሳኔ ለአገሪቱ ዘላቂ ሰላም ወሳኝ መሆኑን በቅድሚያ የሚዲያው ባለሙያ እና አመራር እንዲገነዘብ አስፈላጊው ማብራሪያ ሊሰጥ ይገባል። የሚዲያ ባለሙያው እና አመራር ከዚያ በመቀጠል ለሕዝቡ ሊያሰርጽ ይገባል የሚል እምነት አለኝ፡፡
በእርግጠኝነት፣ ስለ ይቅርታ ባህል ጠቃሚ ትምህርቶችን ከቅድመ አያቶቻችን ወስደን ሌሎችንም አስተምረናል። በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጉት ንግግር እንዳብራሩት ምኒልክ የሸዋ ንጉሥ በነበሩበት ወቅት ከጎጃሙ ገዥ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ጋር እንባቦ በተባለ ቦታ ላይ ትልቅ ጦርነት ገጥመው ንጉስ ተክለ ሃይማኖት ተሸንፈው የተማረኩ ቢሆንም ንጉስ ተክለ ሃይማኖት ወደ ጎጃም ገዥነታቸው ነው የመለሷቸው።
አያቶቻችን ይቅርታን እንደ ዋነኛ መሳሪያ እየተጠቀሙ ነው አገሪቱን እዚህ ያደረሷት። በመሰረቱ ይቅርታ የሚያስፈልጋቸውን ይቅር ማለት ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ካለው ፋይዳ ባሻገር እፎይታን የሚሰጥ ነገር ነው።
ስለዚህ “ሌሎችን ይቅር በላቸው ይቅርታ ስለሚገባቸው ሳይሆን ሰላም ይገባሃል” የሚለው አባባል የኢትዮጵያ መንግስት ቀደም ሲል ያሳለፈው ውሳኔ የሚክስ ውጤት ለማምጣት ትልቅ አስተዋፅዖ እንደሚኖረው አያጠራጥርም።
በእርግጥም በርካታ ኢትዮጵያውያን የአገራቸውን ሰላምና መረጋጋት ለማስጠበቅ ሕይወት ከፍለዋል። በርካቶች አጥንታቸውን ከስክሰዋል፤ ደማቸውን አፍሰዋል። የቀን ሀሩር፤ የሌሊት ቁር ሳይበግራቸው ተዋድቀዋል።
ይህ ሁሉ መስዋዕትነት የተከፈለው የአገር አንድነትንና ሉዓላዊነትን ለማስቀጠል ነው። ይቅርታው ደግሞ የአገር ሉዓላዊነትን እና አንድነትን ለማስቀጠል የላቀ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡ “በእኔ እምነት ይቅርታ ምንም አያስከፍለንም።
መንግስት የወሰነው ውሳኔ ኢትዮጵያ ድል እንድታጭድ ይረዳታል። ስለሆነም መላው ኢትዮጵያውያን ይህንን ውሳኔ ለአገራችሁ ክብርና ድል ስትሉ እንድትቀበሉ በትህትና እጠይቃለሁ።
መንግስት የአንዳንድ ተጠርጣሪዎች ክስ የማቋረጥ አላማ የኢትዮጵያን ጠላቶች ማቃለል፣ ሀብት ማሰባሰብ እና ወንጀለኞች ወደ ጥፋት ጎዳና እንዳይመለሱ ለማድረግ ያለመ ነው” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጉዳዩን አስመልክተው በቅርቡ ባደረጉት ንግግር አብራርተዋል። ለኢትዮጵያ ክብርና ድል ሲባል የተወሰነው ውሳኔ መላው ኢትዮጵያዊያን በበጎ ተመልክተው ሊቀበሉት ይገባል ባይ ነኝ፡፡
የለውጥ መንግስት ይቅርታ ምህረት እና ክስ ማቋረጥ አሁን አይደለም የጀመረው። ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ተግባራዊ የተደረገው ይቅርታና ምህረት የኢትዮጵያ መንግስትን ለሌሎች የአፍሪካ መንግስታት አርዓያ ሊሆን የሚችል ነው።
ኢትዮጵያ ለችግሮቿ የራሷን መፍትሄ አሰጣጥ ዘዴ እንዳላትም ለዓለም ያስመሰከረ ነው። ሌሎች የአፍሪካ አገራትም ውስጣዊ ችግሮቻቸውን መፍትሄ ለመስጠት ሊጠቀሙበት የሚገባ መንገድ ነው።
መንግስት እና ገዥው ፓርቲ አገሪቱን ከጥፋት በመታደግ ወደ ብልጽግናና ሰላም መንገድ ለመመለስ እያደረገ ያለውን ጥረት ሌሎች ፓርቲዎችም ሊደግፉት ይገባል። የፖለቲካ ኃይሎቹ እየተፈጠረ ያለውን ምቹ ሁኔታ በአግባቡ መጠቀም አለባቸው። መንግስት እየወሰደ ያለው መልካም እርምጃዎችን ለማስቀጠል ቁርጠኛ ሊሆኑ ይገባል። መንግስት ለሰላም የዘረገው እጅ እንዳይታጠፍ የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል።
መንግስት የወሰነው አይነት ለሰላም የሚበጁ ውሳኔዎች ከፓርቲዎችም በኩል ይጠበቃል። በቀጣይ የሚካሄደው የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይትም ፍሬ እንዲያፈራ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጨዋነት በተሞላበት መንገድ ሊንቀሳቀሱ ይገባል።
የዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ ከኢትዮጵያ መንግስት ጎን በመሆን መንግስት ችግሩን በውይይት ለመፍታት እያደረገ ያለው ጥረት ውጤት እንዲያፈራ አስፈላጊውን እገዛ ሊያደርግ ይገባል።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ጥር 7/2014