የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በቀጣይ ዓመታት ለመስራት ካቀዳቸው መካከል አንዱ በታዳጊዎች እግር ኳስ ልማት ላይ መስራት ነው። በዚህም መሰረት የፓን አፍሪካን የትምህርት ቤቶች ውድድርን በአህጉር አቀፍ ደረጃ ለማካሄድ ሲሰራ ቆይቷል። ይህ ውድድር ዘንድሮ የሚካሄድ ሲሆን፣ ውድድሩን ለማዘጋጀትም የዴሞክራቲክ ኮንጎ ዋና ከተማ ኪንሻሳ ተመርጣለች። በብሄራዊ ደረጃ በተካሄዱ ውድድሮች የተሻለ አቅም ያላቸው ትምህርት ቤቶችም ሀገራቸውን ወክለው በመጪው መጋቢት ወር 2014ዓ.ም ውድድሩ ላይ የሚካፈሉ ይሆናል።
ውድድሩን አስመልክቶ ካፍ መግለጫ በሰጠበት ወቅትም የኮንፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ዶክተር ፓትሪስ ሞተሴፔ እንዳሉት፤ ውድድሩ በትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚካሄዱ የእግር ኳስ ውድድሮችን መሰረት አድርጎ የሚካሄድ ነው። ውድድሩም በታዳጊ ወጣቶች ውስጥ የእግር ኳስ በጎ አስተዋጽኦ እንዲያድር እንዲሁም ከጤና አኳያ ስፖርቱ የሚያስገኘው ጥቅም ተቋዳሽ እንዲሆኑ ያስችላል።
‹‹በአፍሪካ ለውጥ ለማምጣት ካስፈለገ በወጣቶች እድገት ላይ መስራት አስፈላጊ ነው። በአፍሪካ ደግሞ በዚህ ረገድ እግር ኳስ ቁጥር አንድ ነው። በርካታ ችግሮችን ለማለፍም ያለው ጠቀሜታ ይታወቃል›› ያሉ ሲሆን፤ በዚህ እሳቤ በመነሳት ውድድሩ እንደሚካሄድም አስታውቀዋል።
ይህንን ውድድር ተከትሎም የዓለም እግር ኳስን የሚመራው ፊፋ ዋና ጸሃፊ የሆኑት ፋቲማ ፋቲማ ሳሙራም ድጋፋቸውን ሰጥተዋል። ‹‹ፊፋ የአፍሪካን እግር ኳስ ለማሳደግ በአፍሪካ ህብረት እና ካፍ የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ ቁርጠኛ ነው። እግር ኳስ ከስፖርትም በላይ ነው፤ ታዳጊዎች ብቃታቸውን እንዲያሳድጉ ትምህርት ቤቶች ወሳኝ ናቸው›› በማለት ገልጸዋል።
በኢትዮጵያም በአህጉር አቀፍ ደረጃ የፓን አፍሪካን ትምህርት ቤቶች ውድድር ላይ ለመሳተፍ የሚያስችለው ውድድር የተካሄደ ሲሆን፤ ትናንት ፍጻሜውን አግኝቶ ኢትዮጵያን የሚወክሉት ተወዳዳሪዎችም ታውቀዋል። በደማቅ ሁኔታ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም የተጀመረው በዚህ ውድድር ለሶስት ቀናት ያህል ከየክልሉ በውስጥ ውድድሮቻቸው ውጤታማ የሆኑትን ሲያወዳድር ቆይቷል።
ውድድሩ በሁለቱም ጾታዎች የተደረገ ሲሆን፤ አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች፣ ኦሮሚያ፣ ሶማሌ፣ ሃረሪ እና ደቡብ ክልሎች ተወካዮቻቸውን አሳትፈዋል። ውድድሩ ዕድሜያቸው ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎችን የሚያሳትፍ በመሆኑ በስፖርቱ ተተኪ የሚሆኑ ስፖርተኞችን ለማፍራት እንደሚረዳ ይታመናል።
ከደቡብ የዱና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የማርያም ሰፈር አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና የጉሮቡቲጂ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ ከኦሮሚያ ክልል የአዋሮ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የእንጦጦ አምባ ትምህርት ቤት፣ ከሃረሪ የአቦኮር ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ የሶማሌ ክልል የወልወል አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በውድድሩ ተካፋይ ሆነዋል።
ትናንት በተካሄደው የፍጻሜ ውድድርም አሸናፊዎቹ ቡድኖች ተለይተዋል። በዚህም መሰረት የኦሮሚያ ክልሉ አዋሮ ትምህርት ቤት የደቡብ ክልሉን የዲላ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 5 ለ 0 በሆነ ውጤት በመርታት በፓን አፍሪካን ውድድር ተሳታፊ መሆኑን አረጋግጧል። በሴቶች ደግሞ ለፍጻሜ የደረሱት ደቡብ ክልሉ የዲላ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የኦሮሚያውን የአዋሮ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመለያ ምት 5 ለ4 በማሸነፍ በዴሞክራቲክ ኮንጎ ኢትዮጵያን የሚወክል ይሆናል።
ኢትዮጵያ የፓን አፍሪካን ሃሳብ ካመነጩት አገሮች መካከል አንዷ መሆኗ እንዲሁም ሃሳቡን በመደገፍ ተግራዊ ያደረገች አገር መሆኗ ይታወቃል። ለአፍሪካ አገሮች ነጻነትና እኩልነት የበኩሏን ድርሻ የተወጣች እንዲሁም የቀድሞ አፍሪካ አንድነት የአሁኑ አፍሪካ ሕብረት መስራች አገር እንደመሆኗ በዚህ ውድድር ላይ መሳተፏ ለዲፕሎማሲ ግንኙነት የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን በኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት ገልጸዋል።
የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮት ውድድሩን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ውድድሩ ተማሪዎች በትምህርት ቤት ውስጥ በንድፈ ሃሳብ ያገኙትን የስፖርት ሳይንስ ትምህርት በተግባር የሚያሳዩበት መሆኑን ጠቁመዋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጥር 6/2014