በ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በመሳተፍ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በሁለተኛው የምድብ ጨዋታ ዛሬ ከአዘጋጇ ካሜሮን ጋር ይጫወታል፡፡ በምድብ አንድ የተደለደለው ቡድኑ በውድድሩ መክፈቻ ዕለት የመጀመሪያ ጨዋታውን ከኬፕቨርዴ አቻው ጋር በማድረግ በአንድ ለባዶ ሽንፈት ማጠናቀቁ ይታወሳል፡፡
በዚህም ቡርኪና ፋሶን የረታችው ካሜሮን እና ኬፕ ቨርዴ በሶስት ነጥብ የደረጃ ሰንጠረዡን ሲመሩ ቡርኪና ፋሶ ሶስተኛ፤ ምንም ግብ እና ነጥብ ያላስመዘገበችው ኢትዮጵያ ደግሞ አራተኛ ሆነዋል፡፡
ዛሬ ምሽት አንድ ሰዓት ላይ በኦሌምቤ ስታዲየም በሚካሄደው ጨዋታም ዋሊያዎቹ የምድቡ ጠንካራ ቡድን የሆኑትን የማይበገሩት አናብስት / ካሜሮኖችን/ ይገጥማሉ፡፡ በዚህ ጨዋታ ላይም ቡድኑ ተጠናክሮ ነጥብ ለማስመዝገብ የሚሰለፍ ሲሆን፤ ከምድቡ ለማለፍ እንዲሁም ጥሩ ሶስተኛ ለመሆን ይህ ጨዋታ ወሳኝ ነው፡፡
ከስምንት ዓመታት በፊት በአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊ የነበረውና በአሁኑ ወቅት የቀድሞ ክለቡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን መሪ የሆነው አዳነ ግርማ፤ ቡድኑ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያው ካሳየው አቅም አንጻር ጥሩ ተፎካካሪ ይሆናል የሚል ግምት እንደነበረው በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ገልጿል፡፡ የዋሊያዎቹ ስብስብ በማጣሪያ ጨዋታዎች ከደቡብ አፍሪካ፣ ጋና እንዲሁም ከዚምቧቡዌ ጋር ሲጫወቱ፤ ጥሩ ኳስ የሚጫወት ቡድን መሆኑን ያሳየና የሚጠበቅም ነበር ያለው አዳነ፣ በአፍሪካ ዋንጫው የመጀመሪያው ጨዋታ በብዛት መደናገጥ ይታይበት እንደነበር ይናገራል፡፡
የዋሊያዎቹ ወሳኝ ጨዋታ ቡድኑ በዚህ ሁኔታ እያለ በቀይ ካርድ ምክንያት በጎዶሎ ተጫዋች መጫወት እንደሚከብድ ጠቅሶ፣ በቀጣይ ደቂቃዎች ቡድኑ ተረጋግቶ ወደ ተፎካካሪነት ይመለሳል የሚል ግምት ቢኖረውም ከዚያ በኋላም ተጫዋቾቹ አቅማቸውን አውጥተው ለመጫወት እንዳልቻሉ አዳነ ያስታውሳል፡፡
በጎዶሎ ቡድን ማጥቃት አዳጋች መሆኑን ጠቅሶ፣ ወደ ማጥቃት በመዞሩ ምክንያት ትክክለኛ የቡድኑን አቋም ለመመልከት አልተቻለም ይላል፡፡ በዛሬው ጨዋታ ቡድኑ በጣም መስራት እንደሚጠበቅበት አስገንዝቦ፣ ‹‹ካሜሮን ከአፍሪካ ታላላቅ ቡድኖች መካከል አንዱ ነው፤ በዚህ ላይ በአገሩ ላይ መጫወቱና ጥሩ ዝግጅት እንዳደረገ ይጠበቃል›› ሲል ያብራራል፡፡ ካሜሮኖች ለአውሮፓ ሊጎች የሚጫወቱ በርካታ ተጫዋቾች ያሏቸውና በዓለምና በአፍሪካ ጥሩ የእግር ኳስ ደረጃ ላይ የሚገኙ ቢሆኑም እግር ኳስ ግን የዕለት አቋምን ማዕከል ያደርጋል ያለው አዳነ፣ መፍራት ሳይሆን በትኩረት፣ በተጠናከረ የሕብረት ስሜት እና በጥንቃቄ መጫወት እንደሚገባ ተናግሯል፡፡
እነርሱ ካላቸው አቋምና ልምድ አንጻር የኢትዮጵያ ቡድን የቁጥር ብልጫ በማሳየት ተጠቃሚ መሆን ይችላል፤ ይኸውም የእነርሱ አንድ ተጫዋች ኳስ ሲይዝ ለሁለት በመያዝ ነው፡፡ ከምንም በላይ ጠንካራ ሕብረት ይዞ በመቅረብ እንዲሁም ሌሎች ክስተቶች እንዳይገጥሙ ጥንቃቄ በማድረግ በጨዋታው መካፈል አስፈላጊ መሆኑንም ያሳስባል፡፡
ሌላኛው በደቡብ አፍሪካ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊና የቡድኑ አማካይ የነበረው በኃይሉ አሰፋ (ቱሳ)፤ እግር ኳስ ቀድሞ የሚተነበይ ባይሆንም ይህ ቡድን ግን እነርሱ ከሄዱበት ርቀት አንድ ደረጃ የተሻለ ውጤት ያመጣል የሚል እምነት እንዳለው ይገልጻል፡፡
በተለይ ከኬፕ ቨርዴ ጋር በተደረገው የመጀመሪያ ጨዋታ ላይ ተስፋ አሳድሮ እንደነበር ጠቅሶ፣ የያሬድ ባየህ በቀይ ካርድ ከሜዳ መውጣት የቡድኑን የቁጥር ብልጫ በመውሰዱ እንደተጠበቀው ጥሩ ጨዋታ አልታየም ብሏል፡፡ የአፍሪካ ዋንጫው ከማጣሪያው ጀምሮ የነበረው ሁኔታ በእግር ኳሱ የተሻሉ እንደሆኑ የሚነገርላቸውን አገራት ጭምር አጣብቂኝ ውስጥ አስገብቶ ማለፉን ተጫዋቹ ይጠቁማል፡፡ ይህም ማለት አብዛኛዎቹ የአፍሪካ ቡድኖች አቅማቸው እየተቀራረበ መመጣቱን የሚያሳይ መሆኑን ጠቅሶ፣ ከዚህ ባለፈ ግን ከስምንት ዓመታት በፊትም ሆነ አሁን ያለው ቡድን ያሳየው የተለየ ለውጥ አለ ለማለት አያስደፍርም ሲል ያብራራል፡፡
በእርግጥ የኬፕቨርዴ አብዛኛዎቹ ተጫዋቾች በውጭ አገራት ሊጎች የሚጫወቱ መሆናቸውን አመልክቶ፣ በአንጻሩ የዋሊያዎቹ ተጫዋቾች ደግሞ በአገር ውስጥ ሊጎች የሚጫወቱ ናቸው፡፡ ሆኖም የቁጥር ብልጫው ተወስዶባቸውም ያስተናገዱት ግብ ጠባብ ነው ሲል ተናግሯል፡፡
የዛሬው ከካሜሩን ጋር የሚደረገው ጨዋታ በዚህ ልክ ቀላል ይሆናል ተብሎ አይጠበቅም ያለው በሀይሉ፣ አዘጋጇ ካሜሮን በደጋፊዋ ፊት የምትጫወት ከመሆኗም ባለፈ ከምድቡ ማለፏን የምታረጋግጥበት ጨዋታ እንደመሆኑ፤ ለኢትዮጵያም ጥሩ ሶስተኛ ቡድን በሚል ለማለፍ ወሳኝ ጨዋታ ነው ብሏል፡፡ ቀላል ጨዋታ እንደማይሆን ቢታወቅም በእግር ኳስ ምን እንደሚፈጠር ስለማይታወቅ ጥረትና ሙከራ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንም ተጫዋቹ አስገንዝቧል፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጥር 5/2014