ብዙ ተሰጥዖ ያላቸው ወጣቶች ዕድል በማጣት ችሎታቸው ተቀብሮ ቀርቷል። ያ ተሰጧቸው በልምድ መዳበር ሲገባው እንዲረሱትና ወደ ሌላ አልባሌ ነገር እንዲገቡ ተደርገዋል። በተለይም በገጠራማው የአገራችን ክፍል ተሰጥዖን ከግብ ማድረሻ ዕድሎች የሉም።
የብዙ ወጣቶች የሥነ ጽሑፍና የድምጽ ተሰጥዖ ባክኖ ቀርቷል። የተሰጥዖን ከግብ ማድረሻ ዕድል አለመኖር የእነዚህን ሰዎች ወጣቶች ችሎታ ቀብሮ ማስቀረቱ ብቻ አይደለም ችግሩ። የፈጠራ ሥራ የሌላቸውና የኩረጃ ሥራዎች እንዲስፋፉ ዕድል መክፈቱ ነው።
ዕድሉን አገኘን በሚል ያለምንም ችሎታ የሌሎችን ሥራዎች አበለሻሽተው ያቀርባሉ። ይህም በኪነ ጥበብ ኢንደስትሪው ላይ የምናየውና የምንሰማው አይነት ወቀሳ እንድንሰራ ያደርጋል ማለት ነው።
የዘላቂነቱ ነገር በይደር ይቆይና (እዚህ አገር ብዙ ነገሮች ተጀምረው ስለሚጠፉ) የሚዘልቅ ከሆነ አንድ አዲስ መላ የተገኘ ይመስላል። ይሄውም ‹‹አዲስ ዓድዋ የዜማና ግጥም ውድድር›› የሚባል ሊጀመር ነው መባሉ ነው። አዘጋጁ ጃዝ አምባ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ሲሆን ከፈንድቃ የባህል ማዕከል፣ ከላፍቶ ሞል እና ከጁቢሊ የሁነት አዘጋጅ (event organizer) ጋር በመሆን ነው። ጃዝ አምባ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ለረጅም ዓመታት የቆየና በርካታ የሙዚቃ ባለሙያዎች ያሉበት ነው።
ተባባሪ አካላትም ለኪነ ጥበብ ቅርበት ያላቸው የባህልና ጥበብ አካል ናቸው። ዋና ዓላማቸውም የኢትዮጵያን የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ከፍ ማድረግ እንደሆነ ተናግረዋል። ከጃዝ አምባ የሙዚቃ ትምህርት ቤት መሥራቾች አንዱ የሆነውና የሙዚቃ ባለሙያው አቢይ ወልደማርያም እንደሚለው፤ የዚህ የግጥምና ዜማ ውድድር ዋና ዓላማ ከ18 እስከ 35 ዓመት ዕድሜ ውስጥ ያሉና ዕድል ያላገኙ ወጣቶችን ሥራዎች ወደ ሕዝብ ማድረስ ነው።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ያለችበትን አገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ በጥበብ ሥራዎች ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማስተዋወቅ ነው። ለዚህም ነው ውድድሩ ‹‹አዲሱ ዓድዋ›› የሚል ስያሜ የተሰጠው። እንደ ሙዚቃ ባለሙያው አቢይ ማብራሪያ፤ አዲስ ዓድዋ የዜማና ግጥም ድርሰት ውድድር አዲስ የፈጠራ ሥራዎችን የያዘ መሆን አለበት። ከሌላ ቦታ የተኮረጀ ወይም የተገለበጠ በፍፁም ተቀባይነት አይኖረውም። ለዚህም የሚመረጡ ዳኞች ለረጅም ጊዜ የሙዚቃ ሥራዎች ላይ የዳበረ ልምድ ያላቸውና ብዙ ባለሙያዎች ናቸው። የሚቀርቡት ሥራዎችም እንደ ስያሜያቸው ዓድዋን የሚያስተዋውቁ መሆን አለባቸው።
የዓድዋ ታሪክን አሁን ላለው ወጣት ትውልድ ለማስተዋወቅና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ለማድረስ ነው። ተወዳዳሪ ወጣቶች የፈጠራ ሥራዎቻቸውን በምን መንገድ ማቅረብ እንዳለባቸውም ባለሙያው ተናግረዋል። ጃዝ አምባ የሙዚቃ ትምህርት ቤት(Jazz Amba School of Art) ድረ ገጽ እና አዲስ ዓድዋ የዜማና ግጥም ውድድር (The New ADWA Song Writing Competition) የፌስቡክ ገጽ ላይ ሥራዎቻቸውን መላክ አለባቸው ተብሏል።
ሥራዎቻቸውን ማቅረብ የሚችሉት ከጥር 12 ቀን 2014 ዓ.ም (January 20, 2022) ጀምሮ ሲሆን የሚላኩ ሥራዎች በቪዲዮ ጭምር መሆን አለባቸው ተብሏል። የሚላኩ ሥራዎች እስከ የካቲት ሰባት ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ በባለሙያዎች ታይተውና ተገምግመው ይለያሉ። በባለሙያ የተለዩ ሥራዎች በዓድዋ በዓል መዳረሻ የካቲት 19 ቀን 2014 ዓ.ም በልዩ ዝግጅት ይፋ ይደረጋሉ። እንደ ባለሙያው አቢይ ገለጻ፤ የሚቀርብ የትኛውም ሥራ ወጥ እና ያልተኮረጀ የራስ ፈጠራ እስከሆነ ድረስ ባለቤትነቱ ሙሉ በሙሉ የደራሲው ነው። የሚጠራውም በባለቤቱ ስም ነው።
የአዘጋጆቹ ሚና የፕሮዳክሽንና የሙያ ድጋፎችን አድርጎ ሥራው ለሕዝብ እንዲቀርብ ማድረግ ነው። እንደ አዘጋጆቹ ገለጻ፤ ለዚህ ሀሳብ ያነሳሳቸው ኢትዮጵያ ካለፈው አንድ ዓመት በላይ በቆየችበት ጦርነት ውስጥ ባለው ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴ ነው። በቅርቡ የተጀመረው የ‹‹በቃ!›› እንቅስቃሴ በጎዳናዎች መፈክር ብቻ ሳይሆን ዘላቂ በሆኑ የኪነ ጥበብ ሥራዎች እንደ ዓድዋ ያሉ የኢትዮጵያን ገናናነት ለማሳየት ነው። ለዚህም ነው ስያሜውም በዓድዋ የሆነው፤ የሚቀርብበት ጊዜም የዓድዋ ሰሞን እንዲሆን የተደረገው፡፡
እንደ አቢይ ገለጻ፤ ለውድድር የሚላኩት ሥራዎች፤ አንድነትን፣ ፍቅርን፣ መቻቻልንና አብሮነትን የሚገልጽ መሆን አለባቸው። ዓላማቸውም በጥበብ ሥራዎች ዘላቂ ፍቅርና ሰላምን መገንባት ነው። እንደ ዓድዋ ያሉ የኢትዮጵያ አኩሪ ገድሎችን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ መንገር ነው። ሥራዎቹ ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ በየትኛውም ቋንቋ መቅረብ ይችላሉ፤ ዳሩ ግን ለውድድር ሲላኩ በአማርኛ፣ በእንግሊዘኛ ወይም በፈረንሳይኛ በጽሑፍ ተተርጉመው መቅረብ አለባቸው ተብሏል።
በነገራችን ላይ በእነዚህ ቋንቋዎች መተርጎሙም ሆነ ሥራው በየትኛውም ቋንቋ እንዲቀርብ መደረጉ ዓድዋን የበለጠ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ እንዲታወቅ ያደርገዋል። ይህም የኢትዮጵያን ገናናነት ያሳያል ማለት ነው። በተለይም አዲስ አበባ ውስጥ ብዙ ኢትዮጵያዊ የሆኑ ወጣቶች በእነዚህ ዓለም አቀፍ ቋንቋዎች የመዝፈን ችሎታ እንዳላቸው በተለያዩ የተሰጥዖ ውድድሮች የምናየው ነው። በተለይም የግል ትምህርት ቤት ውስጥ በእንግሊዘኛና በሌሎችም ቋንቋዎች የሚዘፍኑ ብዙ ወጣቶች እንደሚኖሩ ነው።
የውጭ ሙዚቃዎችንና ፊልሞችን መከታተል የውጭ ናፋቂ ለመሆን ብቻ ሳይሆን እንዲህ አገርን ለማስተዋወቅም መዋል አለበት። ሥራዎቹ አዲስ መሆን አለባቸው ሲባል የግድ አዲስ ዘፋኝ ማለት ብቻ እንዳልሆነ ባለሙያው አቢይ ተናግሯል። ሥራው ነው አዲስ እንዲሆን የተፈለገው። ከዚህ በፊት ዘፈን የነበረው ሰው ከሆነ አሁን የሚያመጣው ዘፈን በእሱም ሆነ በሌላ ዘፋኝ ከዚህ በፊት ያልተሠራ ሥራ ነው መሆን ያለበት።
ዕድሜ እስከ 35 ዓመት የተባለበት ምክንያት ግን ያን ያህል አስገዳጅ ባይሆንም ወጣቶችንና ዓድዋን ለማስተዋወቅ ተብሎ ነው። የጉዞ ዓድዋ የእግር ጉዞ እንቅስቃሴ የተጀመረው በወጣቶች ነበር። አሁንም ዓድዋ ላይ የሚንቀሳቀሰውም ሆነ የሚወቀሰው ወጣቱ ስለሆነ ወጣቶችን ዓድዋ ላይ ለማሠራት ነው። በአጭሩ ከማበረታታት አንፃር ነው ተብሏል።
ያም ሆኖ ግን ያን ያህል አስገዳጅ አይደለም፤ ከ35 ዓመት በላይ ያለ ሰው ጥሩና አዲስ የፈጠራ ሥራ ይዞ ከመጣ ባለሙያዎች ሊወያዩበት ይችላሉ ተብሏል። ‹‹ዓድዋ ለዓለም ምሳሌ የሚሆን የሰው ልጅ የፍትሕ ምሳሌ ነው›› ያለው የፈንድቃ የባህል ማዕከል ባለቤት መላኩ በላይ፤ ዓድዋ በእንዲህ አይነት የኪነ ጥበብ ሥራዎች መተዋወቅ አለበት ብሏል። የ‹‹በቃ!›› እንቅስቃሴ ጊዜያዊና ወቅታዊ መልዕክት ቢሆንም በጥበብ ሥራዎች ግን የኢትዮጵያን ምንነት በዘላቂነት ማስተዋወቅ ያስፈልጋል።
ዓድዋ የሰው ልጅ የፍትሕ ምሳሌ ነው። በ‹‹በቃ!›› እንቅስቃሴ ሲገለጽ የነበረውም ፍትሕ ነው። ስለዚህ ‹‹በቃ›› የሚለው እንቅስቃሴ በጽሑፍ መፈክር የሚነገርበት ጊዜ ቢቆምም በጥበብ ግን እንደ ዓድዋ ያሉ የሰው ልጅ የፍትሕ ማሳያዎችን ማሳወቅ እንደሚገባ ተናግሯል። በዝርዝር መግለጫው ላይ እንደተጠቀሰው፤ ሥራዎችን በግለሰብ ደረጃ ማቅረብ ይቻላል፣ በቡድን ወይም በባንድ ማቅረብ ይቻላል።
ዓድዋ የኢትዮጵያ ኩራት መሆኑንና የበቃ እንቅስቃሴ የኢትዮጵያ የፍትሕ ጥያቄ መሆኑን ይግለጽ ከኢትዮጵያም ይሁን ከየትኛውም ዓለም ያለ አካል ሥራውን ማቅረብ ይችላል። በአንድ ዘፈን ውስጥ በተለያዩ ቋንቋዎች መልዕክት የሚያስተላልፍ ቢሆን ይመረጣል ተብሏል።
እንግዲህ የዚህ ውድድር ዋናውና ለብዙ ተቋማት ምሳሌ ሊሆን የሚገባው ዓላማው ከሙዚቃው የሚገኘው ትርፍ በጦርነቱ ለወደሙ ትምህርት ቤቶች ድጋፍ የሚውል መሆኑ ነው። ሥራዎቹ በ‹‹ዩ ቲዩብ››ም ሆነ በሲዲ ሽያጭ የሚገኘው ትርፍ ለትምህርት ቤቶች ማሠሪያ ድጋፍ የሚደረግ ነው ተብሏል። የጥበብ ሥራዎች ለእንዲህ ዓይነት ዓላማዎች መዋላቸው ሌሎችንም ያበረታታል። ዓድዋ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ትኩረት እያገኘና ትኩረት እየተሰጠው ነው።
በተለይም በእንዲህ አይነት የጥበብ ሥራዎች የኢትዮጵያን ምንነት በዓለም አቀፍ ደረጃ ማሳወቃቸው፣ ዕድል አጥተው ተደብቀው የቀሩ የጥበብ ሥራዎቻን ወደ ታዳሚ እንዲደርሱ ማድረጋቸው እና በተለያዩ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ችግሮች ለሚደርሱ አደጋዎች ድጋፍ የሚያደርጉ መሆናቸው ይበል የሚያሰኝ ነው። ጥበብ የሕዝብ መሆኑንም የሚያስመሰክር ነውና ሊበረታታ ይገባል፤ በጅምር እንዳይቀር ግን አዘጋጆቹ ከወዲሁ ጠንክረው መሥራት ይኖርባቸዋል።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ጥር 5/2014