የኔታ ፍሬው የእድራችንን ህልውና ለማስቀጠል የማይፈነቅሉት ድንጋይ፤ የማይገቡበት ጉራንጉር የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም። የሚገቡባቸው ቦታዎች ከመብዛታቸው የተነሳ ብዙ ነገሮችን የሚያዩበት አተያይ እጅጉን የሰፋ ነው። አንዳንዴ የሚያራምዷቸው አስተሳሰቦች በስፋታቸው እና ጥልቀታቸው ምክንያት የእድራችን ነዋሪዎች ሊገነዘቧቸው የሚችሏቸው አይደሉም።
በዚህ ሳቢያም አንዳንዴ የንታ ፍሬው የሚወስኗቸው ውሳኔዎች ከላይ ከላይ የሚመለከቱ ተራ የእድራችን አባላቶቻችንን የሚያስደነግጡም ናቸው ። ብዙ ውዝግቦችንም ሲያስነሱ ይስተዋላሉ። ከሰሞኑ ያስተዋልነውስ ይሄን አይደል። ከሰሞኑ ከተላለፉ ውሳኔዎች ጋር ተያይዞ የንታ ፍሬው የእድራችንን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴዎችን ሰብስበው ስለውሳኔው አጠቃላይ ነገር ሲያስረዱ የእድር መሪዎች የሚመሯቸውን እድሮች ህልውና በጸና መሰረት ላይ እንዲቀመጥ በመጀመሪያ ደረጃ እድሮች ሁነኛ አላማ ሊኖራቸው ይገባል። አላማውም በመርህ ሊመራ ግድ ነው።
አንዳንድ ጊዜ መርህ ደግሞ አላማን ለማሳካት መራራም ሊሆን ይችላል። የብዙ እድሮች ተሞክሮ ይሄንን በግልጽ የሚያሳይ ነው። የእኛ ሰፈር እድር በብዙ ነገሩ ከሰፈራችንም ባለፈ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ እና ተጽዕኖ ፈጣሪም ነው ። በዚህ ሳቢያ የሰፈራችን ሰዎች እንደ አይናቸው ብሌን ቢጠብቁትም የውጩ ዓለም እና የሰፈራችን አንዳንድ እኩይ ተልዕኮ ይዘው የሚንቀሳቀሱ ሃይላት የእድራችንን ህልውና ሲፈታተኑት እያየን ነው ።
አይተ ጭሬ ልድፋው እና የጥፋት ግብሩ አስፈጻሚው ኦቦ ጫካ ፍቅሩ የእድራችንን ህልውና በተደጋጋሚ ለመፈተን ሲጥሩ እያያን ነው። ስለዚህ ለእድራችን ህልውና ሲባል ወጣ ገባውን እያየን ውሳኔዎችን ማስተላለፍ ያስፈልጋል። በአንድ ቦታ ላይ እንደ ጅብራ ተቸክሎ ከዚህ በፊት ያልነው ካልሆነ በስተቀር ሞቼ እገኛለሁ ማለት ተገቢ አይደለም!።
ውሳኔዎችን ለመወሰን ከሁኔታዎች መነሳት እንደሚገባ ሲያስረዱ ውሃን እና እሳትን በምሳሌነት አነሱ። ሰው ውሃን በሕወይት ለመኖር ሁነኛ ነገር አድርጎ ይወስደዋል። መቼ ? ቢባል ፤ ለመጠጥ ግልጋሎት ሲያውለው ፣ አሳ አስግሮ ለምግብነት ሲጠቀመው እና ያጠመደውን አሳ በመሸጥ የገቢ ምንጭ ሲደርገው ፣ ለመዝናኛነት ሲጠቀምበት ፣ ለመጸዳጃ ሲያውለው ወዘተ።
አንዳንዴ ደግሞ ውሃን ከጠላታችን በላይ አድርገን ልንጠላው እንችላለን ። መቼ? ቢባል ፤ ጎርፍ ሆኖ ሲያጥለቀልቀን ፣ ማዕበል ፈጥሮ ሰፋራችንን ጠራርጎ ሲወስድ ስናይ ። ሕይወታችንን ሲያሳጣን።
እሳትም ምግባችንን ለማብሰል እና በብርድም ወቅት ለመሞቅ በተጠቀምነው ጊዜ እንወደዋለን ። ነገር ግን ሰደድ ቃጠሎ ተነስቶ ሰፈራችንን «ነበር» ሲያደርገው እጅጉን እንጠላዋለን። ስለሚያጠፋን ብለን ግን ውሃ እና እሳትን በቤታችን እንዳናየው ብለን ከቤታችን ድራሻቸውን አናጠፋቸውም። እዚህ ላይ አንድ ነገር ልንገነዘብ ይገባል ! አንድ ሃይል ጠላት ቢሆንም እንኳን ወቅቶች እና ሁኔታዎች በሚያስገድዱን ጊዜ ጠላትን ልንወደው እና ያደረሰብንን በደል በውስጣችን ይዘን ይቅር ብለን በአንድ ቤት ከመኖር ባለፈ በአንድ መሶብ አብረን ለመብላት ልንገደድ እንችላለን። ስለዚህ ነገሮችን ማሰብ የሚገባን ከዚህ አንጻር ነው ሲሉ ተሰብሳቢውን አስረዱ። ይህን ተከትሎ የእድራችን ጸሃፊ የየንታ ፍሬውን ሃሳብን ገዢ እንደሆነ ለማሳየት ሲሉ የአጼ የምኒሊክን ስራዎች በምሳሌነት አቀረቡ።
በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ መሪ የነበሩት አጼ ምኒሊክ ያደረጉትን ይቅር ባይነት ለኢትየጵያ መረጋገት እና ህልውናዋ በጽናት መሰረት ላይ እንዲቀመጥ ለማስቻል የራሱ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደነበረው አስረዱ። አጼ ምኒሊክ የጦር ጄኔራላቸው ከነበረው ጎበና ዳጪ ጋር መጀመሪያ ላይ ከፍተኛ ውጊያ አድርገው ነበር።
ጎበና ዳጪ ብዙ የሰው ሃላይቸውን እና ንብረታቸውን ቢያወድምባቸውም ጎበና የሚመራውን ህዝብ በሃገረ መንግሥት ግንባታ በማካተት ሃገረ መንግሥቱን የጸና ለማድረግ ጎበና ዳጪን ጄነራላቸው አድርገው ሾሙት። ይህም የአገሪቱን ሰላም እና እድገት መሰረት እንዲጸናበማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል። በአንድ ወቅት አጼ ምኒሊክ ከወላይታው ካዎ ጦና ጋር ከፍተኛ የሆነ ጦርነት አደረጉ። በሁለቱም ወገን ከፍተኛ የሆነ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ኪሰራ ደረሰ። ነገር ግን ከፍተኛ ሰብኣዊ እና ቁሳዊ ኪሳራ ደረሰ ብለው ካዎ ጦናን አልገደሉትም። ርስቱንም አልነጠቁትም።
እየመረራቸውም ቢሆን ለኢትዮጵያ ሃገረ መንግሥት መጽናት ሲሉ ሁሉን ነገር ይቅር ለእግዜር ብለው የካዎ ጦናን ርስት ሳይነጥቁ የወላይታ ገዢ አድርገውት ነበር። ወደ አድዋ ጦርነት ሲዘመቱም የማህሉን አገር እንዲጠብቅ አደራ ሰጥተውት የዘመቱት ለካዎ ጦና ነበር። በዚህም የወላይታን ግዛት ከኢትዮጵያ ግዛት ጋር በሰላም እንዲቀላቀል በማድረግ ሃገረ መንግሥቱ እንዲጸና አደረጉት። አሁን ላይ የወላይታ ሕዝብ ስለኢትዮጵያ ይሞታል። በማንኛውም ረገድ ኢትዮጵያን ከጠላቶቿ ለመጠበቅ ግንባር ቀደም በመሆን ከፊት ሲሰለፍ በተለያዩ አጋጣሚዎች ተመልክተናል። ለዚህ ዋነኛው ምክንያት ይቅርባይነት እንደሆነ ልብ ይሏል። ይህ ሲሆን ግን በርካታ ቁጥር ያላቸው የእምየ ዘማች ወታደር ቤተሰቦች እና ወታደሮች ልባቸው በፈላ ዘይት ውስጥ እንደተጨመረ ድንች እርር ድብን ማለቱ አልቀረም።
እውነቱ ግን የሞቱት ለሀገራችው ህልውና እስከሆነ ድረስ ከካዎ ጦና ጋር ለሰላም እጃቸውን መዘርጋቱ ሲመኙት የነበረው የጸና ሀገረ መንግሥት በመመስረት በኩል ከፍተኛ ዋጋ እንደነበረው አብራርተው ተቀመጡ። ይህ በእንዲህ እያለ በሕዝብ ግንኙነት ስራ ላይ የሚሰራው አስናቀ የተባለው ኮሚቴ ከተሰብሳቢዎች መካከል ተነስቶ እንዲህ አለ፡- በነገራችን ላይ አዲስ የሆነን ነገር ለአንድ ሕዝብ ለማልመድ የሚያመጣ ሰው እጅግ ከባድ ፈተና እንደሚገጥመው ይታወቃል። ለምሳሌ እየሱስ ክርስቶስ መጽሃፍ ቅዱስን በሚያስተምርበት ጊዜ የደረሰበትን በደል የምናውቀው ነው። ክፉ ነገር የሰበከ እና ያስተማረ ይመስል ተደብድቦ በወንበዴዎች መከካል እንዲሰቀል ተፈረደበት ። ነብዩ መሐመድም ቅዱስ ቁራንን ለማስተማር በተንቀሳቀሱበት ጊዜም የደረሰባቸውን እንግልት የምናውቀው ነው። መጀመሪያ ተቃውሞ የተነሳባቸውም ከሰፈራቸው ነው። በአገራችንም በዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግሥት የተከሰተው ይሄው ነው።
ዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ ለወታደሮቻቸው ደመወዝ ለመክፈል እንደተዘጋጁ በአዋጅ አስነገሩ ። አዋጁ ከመውጣቱ በፊት የኢትዮጵያ ወታደር እየዘረፈ እና የፈለገውን ሴት እየደፈረ ይኖር ነበር ። ይሄም ለወታደሩ እንደ ደመወዙ ይቆጠርለት ነበር። በዚህም ብዙ ሕዝብ ለከፋ በደል እና ስቃይ ተዳርጎ ቆይቷል። ይህን ተከትሎ ዳግማዊ አጼ ቴወድሮስ ደምወዝ ለወታደራቸው እከፍላለሁ! ስለዚህ አንድም ወታደር ከአሁን በኋላ ሕዝቤን ቢዘርፍ እና ሴቶችን ቢደፍር ከባድ ቅጣት እቀጣለሁ ብለው ጥብቅ መልዕክት ለወታደሮቻቸው ነገሩ። ነገር ግን ከመንግሥት ደመወዝ ተከፍሎት የማያውቀው ወታደር ከመንግሥት ደመወዝ መከፈሉን በደል እንደተፈጸመበት ቆጥሮት ነገሩን በክፋት አይኑ ይመለከለተው ነበር ።
በዚህም የአጼ ቴዎድሮስ ወታደሮች አጼ ቴዎድሮስን በተደጋጋሚ ይከዱ ነበር። የሕዝብ ግንኙነቱ አስናቀ ንግግሩን ቀጥሎም ከሰሞኑ የንታ ፍሬው በሰፈራችን የማይጠበቅ አዲስ ነገር አሰሙን ። በእርግጥ ዜናው ጆሮ ጭውውው ያደርጋል። ምክንያቱም የእድራችንን ድንኳን ቀዳድዶ ለመጣል በድንጋይም ቢሆን ተወግሬ የእድሩን ድንኳን መቅደድ እስከቻልኩ ድረስ በድንጋይ መወገሬን እንደ ጽድቅ እቆጥረዋለሁ ብሎ የእዳራችንን ድንኳን ለመቅደድ በማሰብ የእድራችንን ድንኳን ጠባቂ «ቅራቶች» በተኙበት የመግደል ወንጀል የፈጸሙት የአይተ ጭሬ ልድፋው ወገኖች «ይገደላሉ! የሞት ፍርድ ፈረድባቸዋል !» ብሎ የእድራችን አባላት ሲጠብቁ ወንጀለኞች ክሳቸው ተቋርጦ ተፈቱ። የንታ ፍሬው መሪ አይደሉ ! እነኝህ ሰዎችን በሞት ፍርድ ከመቅጣት እና መፈታት ለሰፈራችን የትኛው ይጠቅማል የሚለውን ግራ እና ቀኝ አይተው እና ዙሪያ ገባውን ገምግመው እስረኞቹ ቢፈቱ እንደሚሻል በማሰብ የአይተ ጭሬ ልድፋውን ቤተሰቦች ከእስር ፈቱ። «እኛ ሰዎች በተደጋጋሚ የምናደርገው ነገር ነን።» እንዳለው አሪስቶትል ከዚህ በፊት የእድራችንን ህግ የተላለፈ ማንኛውም ሰው ፤ ለዚያውም ድንኳናችንን የሚጠብቀውን ቅራት በመግደል ድንኳናችንን ሊቀድ የተነሳን ቡድን በእድሜ ልክ እስራት ወይም የሞት ቅጣት እንደሚበየንበት ይታወቃል።
በእድራችን የተለመደው እና በተደጋጋሚ የተደረገው ይሄ ነው። ነገር ግን የንታ ፍሬው ይህን ቅጣታ መቅጣቱ ለእድራችን ሊያመጣለት የሚችለውን ትርፍ እና ኪሳራ አመዛዝነው ስለፈቷቸው የእድራችን አባላት አብዝተው በየንታ ፍሬው አዘኑ። «የንታ ፍሬውን አብደዋል እንዴ! » ሲሉ መጠየቃቸው አልቀረም ብሎ ተቀመጠ። በቅጽል ስሙ ማርሽ ቀያሪው የተባለው የእድራችን የሕግ ጉዳዮች ባለሙያ ስብሰባውን ለሚመሩት የንታ ፍሬው የሚናገረው ነገር እንዳለው ለማሳየት እየጣረ እጁን ከፍ አደረገ። የንታ ፍሬው እድል ሰጡት።
ማርሽ ቀያሪው ንግግሩን ቀጠለ ፤ የእድራችን ህልውና በጽኑ መሰረት ላይ ለማስቀመጥ የአይተ ጭሬ ልድፋው ዘመዶች መፈታታቸው ጥሩ ነው። ነገር ግን አሁን ጊዜውን ያልጠበቀ ሊሆን ይችላል። የትኛውንም ጉዳይ ውጤታማ ለማድረግ አስፈላጊውን ነገር በተገቢው ጊዜ መጠቀሙ አስፈላጊ ነው። ትልቅ ዛፍ ለመቁረጥ መጥረቢያን እንጂ ማጭድን አንጠቀምም ትርፉ ድካም ነው። ሳር እና ሰብል ለማጨድም ማጭድን እንጂ መጥረቢያን አንጠቀምም። በተመሳሳይ በክረምት ወቅት አዝእርት እንዘራን እንጂ አናጭድም ።
በበጋም የደረሰ ሰብላችንን እንሰበስባለን እንጂ አዝዕርት አንዘራም። ይሁን እንጂ አንዳንዴ ለእድራችን ህልውና መጽናት ሲባል በመስኖም ቢሆን ሰብል ዘርተን በክረምት ለመሰብሰብ ልንገደድ እንችል ይሆናል ብሎ ተቀመጠ። ውይይቱ እንዲህ ተጧጡፎ ለሰዓታት ከቀጠለ በኋላ የንታ ፍሬው የማጠቃለያ ንግግር አደረጉ። የማጠቃለያ ንግግራቸውን በፈላስፎች አባባል ጀመሩ። ከፈላስፎች አንዱ ንጉስ አይወድህም አሉት። አዎ! ንጉስ ሊያጠፋው የሚችልን አካል አይወድም አለ።
ንጉስ የሚያጠፋውን ቀድሞ ያስራል !ይገድላል። ነገር ግን ንጉስ ጠላቱን ካሸነፈው በኋላ ለቀቀው ማለት ትርጉሙ የተሸነፈው ጠላቱ ደካማ እንደሆነ ማሳያ ነው። ስለዚህ ሊያጠፋ የማይችልን ሰው መፍራት ዝንጀሮ በለሌበት ማሳ ዙሪያ ዝንጀሮ ለመጠበቅ መቀመጥ አይነት ነው። ነገር ግን ጠላትህ አስፈሪ ሆኖ እያለ መከላከል አለመቻል ደግሞ ዝንጀሮ ባለበት የተዘራን ሰብል በአግባቡ መጠበቅ የማይችል ሰው ሰብሉን ዝንጀሮ ባለበት አካባቢ ዘርቶ ማሳውን ፈጣሪ ይጠብቀው ብሎ ጥሎ እንደመተኛት ነው።
ይህ አካሄድ ያልተፈለገ ዋጋ ያስከፍላል። የንታ ፍሬው በምሳሌ የተናገሩት ንግግር ቅኔ ሁሉንም ተሰብሳቢዎች ስለገባቸው ሁሉም ተሰብሳቢ ድጋፉን በጭብጨባ ገለጸ። የንታ ፍሬው ንግግራቸውን ቀጠሉ ፤ በሕይወት ጎዳና ላይ ስትጓዙ አይናችሁን ከግባችሁ ላይ አትንቀሉ። አይናችሁ ከቦንቦሊኖው እንጂ ከቦንቦሊኖው ቀዳዳ ላይ መሆን የለበትም ! ሁሌም ማተኮር ያለባችሁ ከአላማችሁ ላይ ነው። ሁሌም አሸናፊዎች ዓላማቸውን ያያሉ።
ተሸናፊዎች ደግሞ መሰናክሎችን ይመለከታሉ። አሸናፊዎች ዓላማቸውን ያያሉ ሲባል ዓላማቸውን ለማሳካት የትኛውንም ያህል መሰናክል ቢያጋጥማቸው እንኳን ዓላማቸውን እየተመለከቱ መሰናክሎቻቸውን በጥበብ ለማለፍ ይደክማሉ እንጂ መሰናክሎችን እያሰቡ አርፈው ይቀመጣሉ ማት አይደለም።
ተሸናፊዎች ደግሞ መሰናክሎቻቸውን ይመለከታሉ ሲባል አንድ እቅድ ያቅዱና ወደ ተግባር ከመግባታቸው ቀድመው ስለመሰናክሎቻቸው ያስባሉ። ራሳቸውንም ያደክማሉ። ቀድመው ይሸነፋሉ። መሰናክሎችን እያሰቡ በግባቸው ላይ የስንፍና ፍሊት ይረጩበታል። ሃሞታቸውን ያፈሱታል። ይሄ ትክክል አይደለም ።
እናም አሸናፊዎች ዓላማቸውን ለማሳካት በሚያደርጉት እንቅስቃሴ መካከል መሰናክሎቻቸውን ለማለፍ የተለያዩ ውሳኔዎችን ሊወስኑ ይችላሉ። እነኚህ ውሳኔዎች በተሸናፊዎች ምናልባትም እንደ ችግር ሊቆጠሩ ይችላሉ። ለዚም ነው «ሄነሪ ፎርድ » መሰናክሎች አይናችሁን ከግባችሁ በነቀላችሁ ጊዜ የምታዩዋቸው አስፈሪ ነገሮች ናቸው ማለቱ። ስለዚህ በእድራችን አመራሮች እስረኞቹ እንዲለቀቁ የተወሰነው ውሳኔ ከምንፈልገው ዓላማ ያርቀናል ወይ? የሚለውን ጉዳይ በውል መመርመር ይጠበቅብናል። ከግባችን የሚጻረር ከሆነ እውነትም ተሳስተናል። ነገር ግን እኛ ግራ ቀኙን አይተንና ገምግመን ነው ውሳኔውን የወሰንነው። ምክንያቱም የወሰንነው ውሳኔ ከግባችን አንድም ኢንች ፈቀቅ ስለማያደርገን ነው።
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ጥር 5/2014