የኢትዮጵያ ስፖርት ከዕድሜው አንጻር ውጤታማ አለመሆኑን ተከትሎ በጥናት ላይ ተመስርቶ የተዘጋጀው የስፖርት ፍኖተ ካርታ በርካታ ጉዳዮችን አመላክቷል።ከእነዚህ መካከል አንዱ የብሄራዊ ስፖርት ማህበራት (ፌዴሬሽኖች) ድክመት ሲሆን፤ ለዚህም በዋናነት አደረጃጀቱን ጠቁሟል።የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴርም በጥናት ላይ ተመስርቶ ማህበራቱን መልሶ በማቋቋምና በማደራጀት ላይ አተኩሮ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።
በአገሪቷ 31 የሚሆኑ የስፖርት ማህበራት፣ ኮሚቴዎችና አሶሴሽኖች እንደመኖራቸው በአግባቡና በሕጋዊ መንገድ ከመደራጀት አንጻር ችግሮች ሲስተዋሉ ቆይተዋል።የጥራት እና ሰፊውን ሕዝብ የማሳተፍ ችግርም በተመሳሳይ የሚንጸባረቅ እንደመሆኑ ዓለምአቀፍና አገር አቀፍ መስፈርት አሟልተው እንዲደራጁና እንዲመዘገቡ ለማድረግ ዕቅድ ተይዞ እንቅስቃሴዎች ሲደረጉ ቆይቷል።
ማሕበራቱን መልሶ ለማቋቋም የሚያስችለው መመሪያ በብሄራዊ የስፖርት ምክር ቤቱ የጸደቀ ቢሆንም፣ አዲሱ አመራር ወደ ሥራ በመምጣቱ ጉዳዩ በድጋሚ እንዲታይ መደረጉን የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዲኤታ አምሳደር መስፍን ቸርነት በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ገልጸዋል።በመመሪያው ላይ የህግ አስተያየቶች እንደተሰጠበት ጠቅሰው፣ በአሁኑ ወቅትም ወደ ተግባር ለመግባት የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ይገኛል ይላሉ።
እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ፤ የስፖርት ማሕበራቱ በተለይ እንደ ክፍተት ከሚነሳባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ በገቢ ራሳቸውን ችለው ከመንግሥት እገዛ አለመላቀቃቸውን ነው።ካሉት ማሕበራት መካከል ከመንግሥት በጀት ተላቀው የገቢ ምንጮችን በመፍጠር እየተንቀሳቀሱ ያሉት የኢትዮጵያ እግር ኳስ እና አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ብቻ መሆናቸውም ይታወቃል።
በእርግጥ በኢትዮጵያ ካለው አቅምና ስፖርቱ ካለበት አጠቃላይ ሁኔታ አንጻር ያሉት የስፖርት ማሕበራት በቁጥር በርካታ ሊባሉ የሚችሉ ናቸው።ይህ ቁጥር እንደ ችግር ባይነሳም፤ ያሉት ማሕበራት ግን ከጥራት አኳያ፣ በገቢ አቅም ራስን በመቻል፣ ስፖርቱን በማልማትና በሕብረተሰቡ ዘንድ ተደራሽ በመሆን፣ በመልካም አስተዳደር፣ … ሲታይ አሁንም የመንግሥት ጥገኞች ናቸው።በመሆኑም ይህን ችግር ለመፍታት ቁልፍ የሆነው ጉዳይ አሰራሩን ማስተካከል መሆኑን ሚኒስትር ዲኤታው ይጠቁማሉ።
ማሕበራቱ ሲደራጁ የመጀመሪያው ጉዳይ ዓለም አቀፍ እውቅናን ለማግኘት በኢትዮጵያ የስፖርት ማሕበራት ሕግ መደራጀት አለባቸው ያሉት አምባሳደር መስፍን፣ ስለዚህም የስፖርት ማሕበራት መመሪያ ቁጥር ስድስት የነበረው በአዲስ መልክ ተከልሶ ጥራትና ብቃት ያላቸው ሕዝባዊ የሆኑ የስፖርት ማሕበራት እንዲኖሩ በሚያስችል መልኩ እየተዋቀረ እንደሚገኝ ይጠቁማሉ።ይህ መመሪያ ከጸደቀ ጊዜ ጀምሮም የስፖርት ማሕበራት በዚህ መልኩ የመመራት ግዴታና ኃላፊነት ይኖርባቸዋል።በዚህም ቁመናቸውን፣ ጥራታቸውን ሕዝባዊነታቸውን፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮቻቸውን እየፈቱ እንዲሄዱ መንግሥትም ድጋፍ ያደርጋል፤ ራሳቸውም የሚያስተካክሉበትን እድል ይፈጠርላቸዋል ሲሉ ያብራራሉ።
በዚህ ወቅት በአንጻራዊነት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እና ኦሊምፒክ ኮሚቴ በስፖንሰርና በተለያየ መልኩ ራሳቸውን የሚችሉ ማሕበራት ናቸው።የተቀሩት ሌሎቹ በመንግሥት የሚደገፉ ናቸው።ይሁንና ስፖርት በኢትዮጵያ መሆን ያለበት ሕዝባዊ ነው።አዲሱ የአስፈጻሚ አካላት ሥልጣን ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 1263 ለኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት የተሰጠው አንዱ ትኩረት የስፖርት ማሕበራት ራሳቸውን እንዲችሉ ማብቃት ነው።ይኸውም የስፖርት ፈንድ እንዲቋቋም ማድረግ ሲሆን፤ በስፖርት ፍኖተ ካርታውም ከተመላከቱ ጉዳዮች መካከል አንዱ ይሄው ነው።ለዚህም ጥናት ተካሂዶና አደረጃጀት ተሰርቶ ደምብም ከተዘጋጀለት በኋላ ወደ ሚኒስትሮች ምክር ቤት የሚላክ ይሆናል ብለዋል።
የስፖርት ፈንድ ዓላማውም ስፖርት በመንግሥት ብቻ እንዲደገፍ ሳይሆን፤ ስፖርቱን የሚደግፉ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት (መንግሥት፣ ሕዝብ፣ የግሉ ዘርፍ እና ሌሎች ድጋፍ የሚያደርጉ) በሚዘጋጀው አንድ ቋት ድጋፍ እንዲያደርጉበት ነው።የራሱ የሆነ አደረጃጀትና ጽህፈት ቤት ኖሮት የሚተዳደርበት፤ የስፖርት ማሕበራቱም በመመሪያው መሰረት የሚደገፉበት ሥርዓት ይሆናል።ሌላኛው መንገድ የስፖርት ማሕበራት ዘላቂና አስተማማኝ በሆነ ገቢ ራሳቸውን የሚችሉበትን መንገድ ፈጥረው ከመንግሥት ድጋፍ ደረጃ በደረጃ የሚላቀቁበት ሁኔታ የሚፈጠርበት ነው።ይህንንም ወደ ተግባር ለማስገባት በተያዘው ዓመት ለመስራት በዕቅድ ከተያዙ ጉዳዮች መካከል መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታው ያስረዳሉ።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጥር 4/2014