ከስምንት ዓመታ በኋላ ኢትዮጵያ መስራች ወደሆነችበት የአህጉሪቷ ትልቁ የእግር ኳስ ውድድር፤ የአፍሪካ ዋንጫ በድጋሚ ተመልሳ ባደረገችው የመጀመሪያው የምድብ ጨዋታዋ ሽንፈት ማስተናገዷ ይታወቃል። ጨዋታው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) ከፍተኛ ዋጋ ሊያስከፍሉ የሚችሉ ስህተቶችን መስራት መቀጠሉ የታየበት ሲሆን፤ ከአስተናጋጇ አገር ካሜሮን ጋር የሚደረገው ቀጣዩ ጨዋታም በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ ከወዲሁ ስጋት የሚያሳድር ሆኗል።
ኢትዮጵያ ከኬፕቨርዴ (ሰማያዊዎቹ ሻርኮች) በተደረገው ጨዋታ፤ ቡድኑ እንደተለመደው በስህተት ምክንያን ዋጋ የከፈለ ሲሆን፤ ተከላካዩ ያሬድ ባየህ በቀይ ካርድ ጨዋታው በተጀመረ ጥቂት ደቂቃ ውስጥ ከሜዳ እንዲሰናበት መደረጉ የጨዋታውን ቅርጽ እንዲለወጥ አስገዳጅ ሆኗል። ተጫዋቹ ምናልባትም ቡድኑ ግብ እንዳይቆጠርበት የታደገበት መንገድ ተቃራኒ ተጫዋች ላይ ጥፋት መስራት መሆኑ ቢጫ ካርድ ቢያሰጠውም፤ በቪዲዮ በታገዘው ዳኝነት ግን ቀይ ካርድ እንደሚገባው ለዳኛው ጥቆማ በመሰጠቱ ከሜዳ እንዲወጣ ተደርጓል። ይህም ተቃራኒ ቡድን በዋሊያዎቹ ላይ ጫና ወስዶ ለመጫወት ያስቻለው ሲሆን፤ የግብ አጋጣሚዎችንም መፍጠር ችሏል።
በአንጻሩ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የጨዋታ ሚዛኑን በመከላከል ላይ እንዲያተኩር በማድረጉ በማጥቃት በኩል የነበረው እንቅስቃሴ እጅግ አናሳ ከመሆኑ ባለፈ ሙከራዎቹም የተሳኩ ነበሩ ለማለትም
አያስደፍርም። በአማካዩ መስኡድ መሃመድ ተተክቶ የገባው ምኞት ደበበም በራሱ መረብ ላይ ግብ ሊያስቆጥር የሚችልበት አጋጣሚ መፈጠሩም ሌላኛው በቡድኑ የታየው አስደንጋጭ ሁኔታ ነበር። በርካታ ድራማዊ ክስተቶች በተስተናገዱበት የጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ የተጨመሩት ደቂቃዎች ኬፕቨርዴዎች ግብ በማስቆጠር ብልጫውን ለመውሰድ ችለዋል። ዋሊያዎቹ በሁለተኛው አጋማሽ በተሻለ እንቅስቃሴ እንደሚመለሱ ቢጠበቅም፤ ቡድኑ አንድ ለምንም በሆነ ሽንፈት የመጀመሪያውን ጨዋታ ሊያጠቃልል ችሏል።
በእርግጥ ቡድኑ ሊበረታታ የሚገባው የተለያዩ መልካም ጎኖቹንም ያሳየበት ጨዋታ መሆኑን መሸሸግ አይቻልም። ጨዋታው ከመጀመሩ የቀይ ካርድ ሰለባ መሆን በራሱ የስነልቦና ጫና እንደሚፈጥር እሙን ነው። ይህን የተቋቋሙት ዋሊያዎቹ በጎዶሎ ተጫዋች ክፍተትን ሸፍኖ ለመጫወት ያደረጉት ጥረት ይበል የሚያሰኝ ነው። ሌላው የቡድኑ መልካም ጎን ኢትዮጵያ ወደ ውድድሩ ለመመለስ ረጅም ዓመታት የፈጀባት መሆኑን ተከትሎ የቡድኑ አባላት ከአምበሉ ጌታነህ ከበደ በቀር (ሽመልስ በቀለ እና ጀማል ጣሰው በጨዋታው ላይ አለመሳተፋቸውን ልብ ይለዋል) አዳዲስና ወጣት ተጫዋቾች በመሆናቸው ነው። ተጫዋቾቹ ይህን በመሰለ ትልቅ መድረክ ተካፍለው ባያውቁም በቻሉት መጠን መልካም የሚባል ጥረት አሳይተዋል።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነው በርካታ ግቦችን እንዳያስተናግዱ ያደረጉት ጥረትም በእርግጥም ቡድኑን ከተጨማሪ ጭንቀት ታድጎታል። አጥቂዎቹ ጌታነህ ከበደ እና አቡበከር ናስርም በተቻለ መጠን የግብ ሙከራዎችን የመፍጠር ጥረት አሳይተዋል። በተለይ በጨዋታው ትልቅ መሻሻል በማሳየት ቡድኑ ከአንድ በላይ ግብ እንዳይቆጠርበት አበረታች እንቅስቃሴ ያሳየው ግብ ጠባቂው ኃይለማርያም ሻንቆ ነው።
የጨዋታው ክፍተቶችና መልካም ጎኖች ቢኖሩትም፤ ከቅድመ ውድድር ዝግጅት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ግን አሁንም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ራሱን እንዲመለከት የሚያደርጉ ሁኔታዎችን ማጤን አስፈላጊ ነው። የኬፕቨርዴ (ሰማያዊዎቹ ሻርኮች) ቡድን አባላት በርካታዎቹ በኮቪድ 19 በመያዛቸው በጨዋታው ላይ የተሳተፉት በጠንካራ ተጫዋቾቻቸው ተጠናክረው አልነበረም። የዳኝነት ችግር እንዳለ ቢሆንም ይህ ለዋሊያዎቹ ነጥብ ይዘው የሚወጡበት ወርቃማ እድል ቢሆንም ሊጠቀሙበት ግን አልቻሉም።
በመሆኑም ከጠንካራ ቡድኖች ተርታ ከሚሰለፉትና ዋንጫውንም በአገራቸው ለማስቀረት ካቀዱት የካሜሮን ቡድን ጋር የሚኖራቸው ግጥሚያ ጠንካራ ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ መገመት ይቻላል። ጥቃቅን የሚመስሉ ነገር ግን ጨዋታን የመቀየር አቅም ያላቸው ስህተቶችንና ጥፋቶችን ማስቀረት የቡድኑ ትልቅ የቤት ስራ ሊሆን ይገባዋል። ይሁንና ቡድኑ በጎዶሎ ተጫዋች ያሳየውን ጥረት ሊደግም ከቻለ የስፖርት ቤተሰቡን ስጋት በመቅረፍ ከምድብ የማለፍ እድሉን ማስፋት ይችላል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጥር 3/2014