የአፍሪካ ትልቁ የእግር ኳስ ድግስ ትናንት የመካከለኛው አፍሪካ አገር በሆነችው ካሜሮን ተጀምሯል፡፡
በአውሮፓ ሊጎች የደመቁ የእግር ኳሱ ፈርጦችም በአህጉራቸው ተሰባስበው የአገራቸውን ስም በስኬት ለማስጠራት መፋለም ጀምረዋል። 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ኢትዮጵያ በተሳታፊነት፣ በዳኝነት እንዲሁም በካፍ የቴክኒክ ኮሚቴ ውስጥ መካተት የቻለችበትም ነው፡፡ የመጀመሪያው ምድብ ውስጥ የተደለደሉት ዋሊያዎቹ ትናንት ከኬፕ ቨርዴ ጋር ቀዳሚ ጨዋታቸውን አካሂደዋል፡፡
በዛሬው የአፍሪካ ዋንጫ ሁለተኛው ቀን መርሃ ግብር መሰረትም በሁለተኛውና በሶስተኛው ምድብ ሁለት ሁለት በጥቅሉ አራት ጨዋታዎች ይደረጋሉ፡፡
የመጀመሪያው ጨዋታ በሁለተኛው ምድብ የተደለደሉትን ቡድኖች፤ ሴናግልን ከዚምቧቡዌ እንዲሁም ጊኒን ከማላዊ ያገናኛል፡፡ በሶስተኛው ምድብ ደግሞ ሞሮኮ ከጋና ሲጫወቱ፤ ሌላኛው ጨዋታ ደግሞ ኮሞሮስ ከጋቦን ጋር ይደረጋል፡፡
ተጠባቂውና የመጀመሪያው ግጥሚያ የዘንድሮውን ዋንጫ የማንሳት አቅም እንዳለው የተገመተውን ጠንካራውን የሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን ከዚምቧቡዌ አቻው ጋር፤ በምዕራብ ካሜሮን በሚገኘው ኩዌኮንግ ስታዲየም የሚያፋልም ነው፡፡
በፊፋ የእግር ኳስ ደረጃ 20ኛ ላይ የሚገኙት የትራንጋ አናብስት፤ የሊቨርፑሉን ኮከብ ሳዲዮ ማኔን በአጥቂነት፣ የፒኤስጂውን እድሪሳ ጉዬን በመሐል ሜዳ፣ የቼልሲውን ኤድዋርድ መንዲ በግብ አዳኝነት፣ የናፖሊውን ካሊዱ ኮሊባሊን በተከላካይነትና በአምበልነት፣… እንዲሁም ሌሎች የአውሮፓ ሊግ ተጫዋቾች ያዋቀረ ቡድን ይዘው መቅረባቸው ይበልጥ አስፈሪ አድርጓቸዋል፡፡
በፊፋ የደረጃ ሰንጠረዥ 121ኛ ላይ የሚገኘው የዚምቧቡዌ ብሄራዊ ቡድንም በአውሮፓና ሌሎች ሊጎች የሚጫወቱ ተጫዋቾቹን በቡድኑ አካቶ ቀርቧል፡፡
ቀጣዩ ጨዋታ በእኩል ሰዓት በምድብ ሁለትና ሶስት የሚደረግ ሲሆን፤ ጠንካራዋ ጊኒ ደግሞ በአፍሪካ ዋንጫ ሶስተኛ ተሳትፎዋን ከምታደርገው ማላዊ ጋር ትጫወታለች፡፡
በያውንዴ ሌላኛው ስታዲየም አህማዱ አሂጆ ሌላ እጅግ አጓጊ ጨዋታ ይደረጋል። የአሸናፊነት ቅድመ ግምት ያገኘው የሞሮኮ ቡድን ከሌላኛው ጠንካራ ቡድን ጋና ጋር ሲገናኝ ከፍተኛ ፉክክር እንደሚስተናገድ ይጠበቃል፡፡
የአትላስ አናብስት በፊፋ የአገራት የእግር ኳስ ደረጃ 28ኛ ላይ ሲገኙ፤ ጥቋቁር ከዋክብቱ ደግሞ 52ኛ ናቸው፡፡ ይህ ከባድ ፍልሚያ የሚያስተናግድ ጨዋታ የእግር ኳስ ቤተሰቡ ትኩረት ነው፡፡ የመጨረሻው የዕለቱ ጨዋታ ደግሞ ጋቦንና ኮሞሮስን የሚያገናኝ ይሆናል፡፡
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ውድድሩን የሚካሄድበትን ወቅት እንዲሁም የተሳታፊዎችን ቁጥር ወደ 24 እንዲያድግ ካደረገ በኋላ ይህ የአፍሪካ ዋንጫ ሲካሄድ ለሁለተኛ ጊዜ ነው፡፡
ውድድሩን ለማካሄድ አስቸጋሪ ሁኔታዎች በመፈጠራቸው መራዘሙ የግድ ቢሆንም ኮንፌዴሬሽኑ የተለያዩ ማሻሻያዎችን በመተግበር እንዲሁም የዓለም ስጋት የሆነውን የኮቪድ 19 ወረርሽኝን እየተዋጋ አስጀምሮታል፡፡ ከማሻሻያዎቹ መካከል አንዱ በቪዲዮ የታገዘ የዳኝነት ስርዓት (ቫር) ሲሆን፤ በ52ቱም ጨዋታዎች ላይ የሚተገበር ይሆናል፡፡
ይህ የዳኝነት ስርዓት እአአ በ2019 ግብጽ ባስተናገደችው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየ ቢሆንም በተግባር የታየው ግን ከግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች ጀምሮ ነበር፡፡
አዲስ ዘመን ስሰኞ ፖርት ይህ ቦታ ለማስታወቂያ ክፍት ነው! የአህጉሪቷን እግር ኳስ በበላይነት የሚመራው ካፍ ለዚህ ውድድር ኢትዮጵያዊውን ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማን ጨምሮ 24 ዋና ዳኞችን እና 34 ረዳት ዳኞችን ከመመደቡ ባለፈ ለቪዲዮ ዳኝነቱ ስምንት ባለሙያዎችን መመደቡን አስታውቋል፡፡
አጠቃላይ ዳኞቹም ከ36 ሃገራት የተወጣጡ ሲሆን፤ አራቱ ከሌሎች ኮንፌዴሬሽኖች (ከሰሜንና መካከለኛው አፍሪካ እንዲሁም ከካረቢያን አገራት) የተገኙ እንዲሁም አራቱ ሴቶች መሆናቸውንም አስታውቋል።
ባወጣው መግለጫም በቪድዮ የታገዘ ዳኝነት ትግበራው፤ የዳኝነት ሂደቱን መልካም ገጽታ ለማሳየት ብቻ ታቅዶ ሳይሆን ዘመናዊና ወቅቱን የጠበቀ ውድድር በአፍሪካ ለማካሄድ መሆኑ ተቁሟል፡፡
በዚህ የአፍሪካ ዋንጫ ከታዩ ማሻሻያዎች መካከል አንዱ ለአሸናፊው ብሄራዊ ቡድን የሚበረከት የሽልማት ገንዘብ መጠን መሆኑንም ቢቢሲ በዘገባው ይጠቁማል። በዚህም መሰረት ዋንጫውን የሚያነሳው ቡድን 5ሚሊዮን ዶላር የሚበረከትለት ሲሆን፤ ይህም እአአ 2019 የአፍሪካ ዋንጫ የሽልማት ገንዘብ የ500ሺ ዶላር ብልጫ ያለው ነው፡፡
ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃን ይዘው ውድድሩን የሚያጠቃልሉ ቡድኖች 2 ነጥብ 75 ሚሊየን ዶላር፣ ለግማሽና ሩብ ፍጻሜ የደረሱት ደግሞ 2 ነጥብ 2ሚሊን ዶላር እንዲሁም 1ነጥብ 175 ሚሊዮን ዶላር ያገኛሉ፡፡ በአጠቃላይ ሲታይም ካፍ ለሽልማት ብቻ ካለፈው የአፍሪካ ዋንጫ 1 ነጥብ 85 ሚሊዮን ዶላር ጭማሪ አድርጓል፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጥር 2/2014