በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ለአንድ ዓመት የተራዘመው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ዛሬ በካሜሮን ይጀመራል። 60 ሺ ሰዎችን በወንበር በሚይዘው ኦሌምቤ ስታዲየም በሚደረገው የመክፈቻ ሥነሥርዓት የሚጀመረው ውድድሩ ለቀጣይ 30 ቀናት ይቀጥላል። የመክፈቻውን ጨዋታም አዘጋጇ ካሜሩን በምድብ አንድ የተደለደለችውን ሌላኛዋን አገር ቡርኪና ፋሶን በማስተናገድ የሚጀመር ሲሆን፤ የኢትዮጵያ (ዋሊያዎቹ) እና ኬፕቨርዴ ጨዋታም ቀጥሎ የሚደረግ ይሆናል።
አፍሪካ በእግር ኳስ ደረጃቸው የተሻሉ ከሚባሉት አገራት መካከል አንዷ የሆነችው የዚህ ውድድር አዘጋጅ ካሜሩን፤ ዋንጫውን ለአምስት ጊዜያት አንስታለች። እኤአ 1984 የመጀመሪያውን ዋንጫ ስታነሳ፤ እኤአ 1988፣2000፣2002 እና 2017 አሸናፊ በመሆን ተጨማሪ ዋንጫዎችን ሰብስባለች። ለሦሥት ጊዜያት ደግሞ የሜዳሊያ ተሸላሚ ለመሆን ችላለች። ከአስፈሪ ቡድኖች መካከል የሚመደቡት ‹‹የማይበገሩት አናብስት››፤ በተለይ በአውሮፓ ክለቦች የሚጫወቱት የአያክሱ ግብ ጠባቂ አንድሬ ኦናና፣ የፉልሃሙ የመሐል ሜዳ ተጫዋች አንድሬ ፍራንክ ዛምቦ የባየር ሙኒኩ አጥቂ ኤሪክ ማክሲም እንዲሁም የናፖሊው ኦንላን ደግሞ የማይበገሩትን አናብስት ይበልጥ እንደሚያጠናክሩትም ይጠበቃል።
ብሔራዊ ቡድኑ ዋንጫውን በአገሩ አፈር ለማስቀረት እንደሚጫወቱ ለቢቢሲ በዘገባው ይጠቁማል። ካሜሮናውያን ስድስተኛውን ዋንጫ ማንሳት ከቡድኑ የሚጠበቅ መሆኑን ፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ ቶኒ ኮንሴሳዎም ይስማሙበታል። ‹‹ሕዝቡ ውድድሩ በአገሩ በመዘጋጀቱ ምክንያት አሸናፊ ለመሆን እድል እንደሚሆን ከፍተኛ ተስፋ አሳድረዋል። ከዚህ ቀደም የነበረውን የአፍሪካ እና የዓለም ዋንጫ ተሳትፎ ታሪኮችንም እንደ ማሳያ ያነሳሉ። እኛ የስፖርቱ ባለሙያዎች ግን አሸናፊነት በዚህ መንገድ እንደማይገኝ እናውቃለን። ይልቁንም በስነልቦና ከተጠናከርን ለፍጻሜው እንደርሳለን›› ሲሉ እግር ኳስን አስቀድሞ መገመት እንደማይቻል አንጸባርቀዋል።
የቡርኪና ፋሶን እና ኬፕቨርዴን ጨዋታዎች መመልከታቸውን የሚያነሱት አሰልጣኙ በየጊዜው ለውጥ በማሳየት ላይ ያሉ ጥሩ ቡድኖች እንደሆኑ ገልጸዋል። የዛሬው ጨዋታ ከቡርኪና ፋሶ ጋር የሚካሄድ መሆኑን ተከትሎም ቡድኑን በማቅለል ብዙዎች ቅድመ ግምታቸውን ለካሜሮን ቢሰጡም እርሳቸው ግን በዚህ መልኩ እንደማያስቡ ገልጸዋል። በአፍሪካ ዋንጫ ከፍተኛ ውጤቷ ሶስተኛ ደረጃ የሆነው ቡርኪና ፋሶ በበኩሏ በወጣቶች የተዋቀረ ብሔራዊ ቡድን መገንባት ችላለች። ይህም ከምድቡ ወደ 16 የማለፍ ተስፋ እንዲጣልባት አድርጓል።
በበኩሏ እንደ ውድድር መስራችነቷ ጠንካራ ቡድን ሳትመሰርት ቆይታለች። በዚህ ተሳትፎ ግን ብሔራዊ ቡድኑ (ዋሊያዎቹ) ከምድባቸው አልፈው 16 ውስጥ መግባትን አልመዋል። የጨዋታ ቅድመ ግምቱን ያስቀመጠው ቢቢሲም ይህንኑ ሃሳብ የሚደግፈው ሲሆን የአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ቡድን ሳቢ የሆነ እግር ኳስ እንደሚጫወትም ጠቅሷል። በተለይ ሽመልስ በቀለ፣ ጌታነህ ከበደ እና አቡበከር ናስር የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋቾች መሆናቸውንም አያይዟል። አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ለካፍ ኦንላይን ዶት ኮም እንደገለጹት ከሆነም 99 ከመቶ የሚሆኑት የቡድኑ አባላት ከአገርውስጥ ሊጎች የተወጣጡ ሲሆን፤ ቡድናቸው በወጣትና ተስፋ ባላቸው ተጫዋቾች መገንባቱንም ገልጸዋል። ገጹ ከአሰልጣኙ አስተያየት ጋር አያይዞም አቡበከር ናስር፣ ጌታነህ ከበደ እና ሱራፌል ዳኛቸው የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋቾች መሆናቸውን ጠቁሟል።
አምበሉ ጌታነህ ከበደ በበኩሉ ‹‹እንደ አጥቂ ግቦችን እንድናስቆጥር ይጠበቅብናል፤ አፍሪካ ዋንጫ ላይም ይህ እጅግ አስፈላጊ ነው። በመሆኑም ቡድኔን ሊያግዙ የሚችሉና ወደ ቀጣዩ ዙር የሚያሸጋግሩ ግቦችን ማስቆጠር የግድ ነው›› ሲል ኃላፊነቱን ለመወጣት ያለውን ዝግጁነት ጠቁሟል። ስለ ኬፕቨርዴ ብሔራዊ ቡድን ሲጠየቅም ‹‹በእግር ኳስ ቀላል የሚባል ነገር የለም። እኛ ማድረግ የሚገባን በአግባቡ መዘጋጀት እንዲሁም በትኩረት እንደ ቡድን መጫወት ነው›› ብሏል። ተጫዋቹ አያይዞም ቡድኑ ኮትዲቯርን በማጣሪያው ማሸነፉን አስታውሶ፤ በአፍሪካ ዋንጫውም ትልልቅ ቡድኖችን መርታት እንደሚቻል በአስተያየቱ አንጸባርቋል።
ኬፕቨርዴም በዚህ የውድድር መድረክ እምብዛም የሚታወቅ ተሳትፎ የሌላት ስትሆን በመድረኩ ስትገኝ ይህ ሦስተኛ ጊዜዋ ነው። እኤአ ከ2013 ወዲህ በስፖርቱ ከፍተኛ መነቃቃት ያሳየው ብሔራዊ ቡድኗ በፊፋ የደረጃ ሰንጠረዥ 73ኛ ላይ ተቀምጧል። በመሆኑም ሰማያዊዎቹ ሻርኮች ከዋሊያዎቹ ጋር ጠንካራ ፉክክር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጥር 1 / 2014