የአገራችን ሕዝቦች በሩቅም ሆነ በቅርብ ጠላት አንድነታቸው ሲፈተን “ሆ” ብሎ በደቦ ተነስቶ እኩያንን ማሳፈር ቀድሞም የነበረ ግብራቸው ነው።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ የኢትዮጵያውያን አንድነት፣ ማህበራዊ ትስስር፣ ኢኮኖሚያዊ መሰረት፣ መተሳሰብ፣ ባህል እንዲሁ በጉልህ መዝገብ ላይ የሰፈረው ታሪካቸው በእጅጉ የተፈተነበት ወቅት ነው። “ችግር ወዳጅና ጠላትን ለመለየት ይጠቅማል” ከሚሉት ብሂል ባለፈም የመከራ ግዜ ትብብርን፣ መደጋገፍን “አንተ ትብስ አንቺ ትብሽ” መባባልን እንደሚያሳይ አሁን መላው “አቢሲኒያውያን” እያለፉበት ያለው እንቅፋት የበዛበት ጠባብ የጭለማ መንገድ ጥሩ ማሳያ ነው።
የሚንደፋደፉት ጠላቶቻችን ጭርሱኑ ባይጥሉንም ለረጅም ግዜ የሚቆይ ስብራት ግን ጥለውብን አልፈዋል። ቁስላችን በቶሎ ባይሽርም እንደሚድን ግን አንዳች ጥርጥር የለንም። ለዚህ ደግሞ የሰሞኑ ቀፎው እንደ ተነካ ንብ ሆ ብሎ የአንድነት ድርና ማግ፣ የመረዳዳት አብዮቱን እያሳየን የሚገኘው ማኅበረሰብ ምስክራችን ነው።
ምዕራባውያን ኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ ያደረሰብን ኢኮኖሚያዊ ጫና ሳያንሰን “የጋሪ ፈረሳችንን ቤተመንግሥት ካላስገባችሁልን” በሚል እብሪት ዜጎቻቸው ከአገራችን ሙልጭ ብለው እንዲወጡ፣ ኢንቨስተሮቻቸው እንዲሸሹን፣ የልማትና የአጋርነት ትብብሮች እንዲቋረጡ ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም። በጥቅሉ ዳረጎታቸውን መልሰው ወደ ሰገባቸው በማጎር ሊያስፈራሩን ሞክረዋል።
በምዕራባውያኑና ሽብርተኛው ትህነግ በቅንጅት ባደረሱብን ጫና አያሌ የኢኮኖሚ መሠረቶች ተንደዋል። ከዚህ ውስጥ አገራችን ኢትዮጵያ የምትታወቅበት የታሪክ፣ የተፈጥሮ፣ የባህልና የተለያዩ ሥርዓቶችን ያቀፈው የቱሪዝም ዘርፉ አንዱ ነው። የብዝሃ፣ ሃይማኖት፣ ቅርስ፣ ትውፊት፣ ኪነ ጥበብ፣ ኪነ ሕንፃ እና አያሌ ሀብቶቻችን በጠላቶቻችን እብሪት ጉዳት ደርሶባቸዋል። እነዚህን መሠረት አድርጎ እንጀራውን ሲያበስል የነበረው የማኅበረሰብ ክፍልም ለግዜውም ቢሆን ጉሮሮው ተዘግቶ ከርሟል።
የሽብርተኛው ቡድንና የምዕራባውያኑ ማንነታችንን ጠቅልሎ የመሰልቀጥ ሙከራ ዳግም እንደ ጥንቱ በመላው ኢትዮጵያውያን ትብብር እየከሸፈ ይገኛል። ምዕራባውያኑ ቱሪስቶችን “በኢትዮጵያውያን ደጃፍ ድርሽ እንዳትሉ” በሚል ዛቻ ኢኮኖሚ መሠረታችንን ሊያደርቁ ቢጥሩም፤ ሽብርተኛው ቡድን የታሪክ የባህል ስፍራዎችን ለጠብ አጫሪ ዓላማው መርጦ ቢያወድማቸውም ኢትዮጵያውያን ግን ከያሉበት ተጠራርተው ወደ አገራቸው በመግባት ሊጥሉን ሲያንገዳግዱን የነበሩ እኩያኖችን ጭላንጭል ተስፋ ጭርሱኑ አምክነውታል።
ታዲያ እኛ ኢትዮጵያውያን በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይና በመንግስታቸው ጥሪ ወደ አገሩ ተምሞ የገባውን ዲያስፖራ ወንድማዊ ድጋፍ በምን መልኩ መጠቀምና ቁስላችንን ማሻር ይኖርብናል? በተለይ የተዳከመውን የቱሪዝም ዘርፍ ዳግም ለማነቃቃትና በእርሱ ላይ ኑሮውን የመሰረተው የማኅበረሰብ ክፍል ተስፋ እንዴት እናለምልመው? ዲያስፖራው በአገሩ ቆይታውን እንዲያደርግ፤ ባህል ታሪኩን፣ ተፈጥሮ ቅርሱን እንዳሻው እንዲመለከት (በተለይ) የኢትዮጵያ ቱሪስት አስጎብኚዎች ሚና ምን መሆን አለበት? ዲያስፖራውስ በአገሩ ቆይታ ሲያደርግ በተለይ የመስህብ ስፍራዎችን የሚያይበት ምን ምቹ አጋጣሚዎች አሉ? ይሄንና መሰል ወቅታዊ የቱሪዝም ዘርፉን ርዕሰ ጉዳይ እንደሚከተለው ለማየት እንሞክር።
አቶ ሄኖክ ፀጋዬ የኢትዮጵያ ቱሪስት አስጎብኚ ማኅበር ዋና ጸሐፊ ነው። በግልም ለ16 ዓመት ያክል የቱሪስት አስጎብኚ ሆኖ በአገር ውስጥ አገልግሏል። መንግሥት አንድ ሚሊዮን ዲያስፖራዎች ለአገራቸው አንድነትና ሉዓላዊነት መከበር በጋራ እንዲቆሙ ወደ አገራቸው ገብተው ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ መደረጉ ለቱሪዝም ዘርፉ እንደ መልካም አጋጣሚ እንደሚቆጠር ይገልፃል። በተለየ ንቅናቄ ወደ አገር ውስጥ እየገባ ያለው ትውልደ ኢትዮጵያዊና የኢትዮጵያ ወዳጅ ለአገሩ ክብር በአንድነት መቆሙን ከማሳየቱ በላይ በተጓዳኝ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን መስህቦች ጎብኝቶ ኢኮኖሚውንም በተዘዋዋሪ እንዲነቃቃ ይደግፋል የሚል እምነት እንዳለም ይገልፃል።
“የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎችን የማስጎብኘት ኃላፊነት ደግሞ የአስጎብኚ ድርጅቶችና ባለሙያዎች ነው” የሚለው ዋና ጸሐፊው ሄኖክ፤ ይሄ ስኬታማ እንዲሆን ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያንና የአገራችን ወዳጆችን ታሳቢ ያደረገ ልዩ ግብረ ኃይል እንደ ተቋቋመ ይገልፃል። በዚህ መሠረትም የተለያዩ የጉብኝት ወጪዎችን በቅናሽ ለማቅረብና አገራዊ መነቃቃቱን ለመደገፍ ከተለያዩ የዘርፉ ተጠሪ ተቋማት ጋር እየሠሩ መሆኑን ይናገራል።
በቱሪዝም ሚኒስቴር የሚመራው ግብረ ኃይል ዝግጅቱን አጠናቅቆ ጎብኚዎችን ለማስተናገድ ዝግጁ ይሁን እንጂ አጠቃላይ ጥሪ የተደረገለት ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ሙሉ ለሙሉ ገብተው የሚጠናቀቁት በዚህ ሁለት ቀናት ውስጥ ነው ብለን እናምናለን የሚሉት ዋና ጸሐፊው ወደ አገር የገባው ማኅበረሰብም የተለያዩ በአገራችን የሚገኙ የመስህብ ስፍራዎችን መጎብኘት የሚጀምረውና ውጤቱ መታየት የሚጀምረው በዚህ ሰሞን መሆኑን ይናገራሉ።
ከዲያስፖራው ምን ይጠበቃል
ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ወደ አገር ውስጥ ሲመጡ ለመላው ዓለም አንድነታችንንና አይበገሬነታችንን ከማሳየታቸው ባሻገር ኢኮኖሚውን ያነቃቃሉ ተብሎ ይታሰባል። ይህን ከሚያደርጉበት መንገድ አንዱ የቱሪዝም መስህብ ስፍራዎች ላይ በሚኖራቸው ቆይታ እንደሆነ ይገለፃል።
ይህንን አስመልክቶ አቶ ሄኖክ “የቱሪዝም ዘርፍ በኮቪድ ወቅት፣ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በተፈጠረ የሰላም መደፍረስ ምክንያት ተደራራቢ ችግር ገጥሞታል” በማለት ወደ አገር ጥሪ የተደረገላቸው ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ይህን ዘርፍ በማገዝ አጋርነታቸው ከማሳየታቸውም በላይ ለመላው ዓለም “ኢትዮጵያ ለጉዞ ምቹ አይደለችም” ብለው ለሚያስቡት ጭምር ትክክል አለመሆናቸውን ያሳያሉ የሚል እምነት አላቸው። ይህን ማድረግ የሚችሉት ዲያስፖራዎቹ ወደተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች እየተንቀሳቀሱ የመስህብ ስፍራዎቹን በመጎብኘት ማሳየት ሲችሉ መሆኑንም ይናገራሉ።
ሌላው አቶ ሄኖክ የሚያነሱት ጥሪ የተደረገላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች አንድ የመስህብ ስፍራ ላይ በተመሳሳይ ግዜና ሰዓት ከመገኘት ይልቅ በተለያየ ጊዜና ሰዓት ቢገኙ አገልግሎት አሰጣጡ የተቀላጠፈ እንዲሆን ከማስቻሉም በላይ ጎብኚዎችም በተጓደለ እንክብካቤ እንዳይሰላቹ መፍትሔ እንደሚሆን ይገልፃሉ። ኢትዮጵያ ሰፊና በርካታ መዳረሻ ስፍራዎች ያላት ከመሆኑ አንፃር በሰሜንም፣ በደቡብም፣ በምስራቅና በምዕራቡ ስፍራዎች በመጓዝ በዚያ የሚገኙ የመስህብ ስፍራዎችን ለዓለም ቢያሳዩ “ለካ ኢትዮጵያ ሰፊና በርካታ እሴቶች ያላት ነች” የሚለውን እሳቤ በግልፅ ማስተዋወቅና ገፅታዋን መልሶ መገንባት ይቻላል የሚል መልዕክት ያስተላልፋል።
አቶ ሄኖክ አሁን ያለው ወቅት በደቡብ ምዕራብና በምዕራቡ የኢትዮጵያ ከፍል ቡና የሚለቀምበት ሰዓት ከመሆኑ አንፃር በዚያ ያለውን መስህብ መመልከት፣ የማኅበረሰቡን ተፈጥሯዊ ሀብት ማየትና ለቀሪው ዓለም በማኅበራዊ ድረ ገፅ በማስተዋወቅ ዲያስፖራው ትልቁን ድርሻ መወጣት እንደሚቻል ይገልፃል። በተጨማሪ በነዚህ የመስህብ ስፍራዎች ሲሄዱ አስጎብኚ ባለሙያዎችን “ቱሪስት ጋይድ” ይዘው ቢሄዱ አስፈላጊውን መረጃና የመስህብ ስፍራ ከመልካም ጊዜ አጠቃቀም ጋር ማግኘት እንደሚችሉ ይገልፃል።
የአስጎብኚው ዝግጅት
“የኢትዮጵያ ቱሪስት አስጎብኚ ማኅበር ዋናው ዓላማ አገርን በእውቀት፣ ክህሎት፣ በታማኝነትና በተሟላ ስብዕና ማስጎብኘት አንዱ ነው” የሚለው ዋና ጸሐፊው አቶ ሄኖክ፤ ለማንኛውም ወደ አገሩ ለሚመጣ ኢትዮጵያዊ፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊና ወዳጆች ትክክለኛ፣ የተደራጀና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማቀበል ተዘጋጅተናል ይላል። ለዚህ ደግሞ በማኅበሩ ስር የሚገኙ ወደ 200 የሚጠጉ አስጎብኚዎች እራሳቸውን አዘጋጅተው እየጠበቁ መሆኑን ይናገራል። ከዚህ ውጪ በቱሪዝም ሚኒስቴር ስር የሚታወቁ 500 የአገር ውስጥ አስጎብኚዎች መኖራቸውንም ገልጿል። ከዚህ የተነሳ ወደ አገራቸው የሚመጡትን ዲያስፖራዎች በሚፈለገው ሙያዊ ስነምግባር ለማስተናገድ ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቋል። ይህን ቁርጠኝነታቸውን ደግሞ አገራዊውን ጥሪ ተቀብለው የገቡ ኢትዮጵያውያንን በአማካኝ 30 በመቶ ቅናሽ በማድረግ ለማገልገል መወሰናቸውን አሳይተዋል።
በመጨረሻው ወደ ኢትዮጵያ የመጡ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና ዲያስፖራዎች ወደ ኢትዮጵያ ቢገቡም ሁሉም የቱሪዝም መዳራዎችን ይጎበኛሉ ማለት ባይሆንም የአገራቸውን ጥሪ አክብረው በመምጣታቸው ሊመሰገኑ እንደሚገባ ይናገራል። ከመጡበት ዓላማ ጎን ለጎን ተጨማሪ ትልቅ ሥራ መሥራት የሚችሉት ግን ለአገራቸው ምጣኔ ሀብት መነቃቃት ጥቂት ድርሻ ሲወጡ ነው በማለት፤ የታችኛው ማኅበረሰብ የዲያስፖራውን መምጣት ዋጋውን እንዲረዳው ማድረግ (በትንሹ ጫማ በማስጠረግም ሆነ ቆሎ ገዝቶ በመብላት) ያስፈልጋል የሚል መልዕክት ያስተላልፋል።
የመንግሥት ዝግጅት ምን ይመስላል?
የኢትዮጵያ መንግሥት ለአንድ ሚሊዮን ዲያስፖራ ጥሪ ማድረጉን ተከትሎ እንግዶችን ተቀብሎ ለማስተናገድ በቂ ዝግጅት ማድረጉን በተደጋጋሚ እየገለፀ ይገኛል። ከዚህ ውስጥ በተለያዩ ዘርፎች ውስጥ የሚገኙ የመንግሥት ተቋማትም ይጠቀሳሉ። ከነዚህ ውስጥ የአማራ ክልል የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ይገኝበታል። ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች በክልሉ የሚገኙ ታሪካዊ ባህላዊና ሌሎች የመስህብ ስፍራዎችን ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል። የፊታችን ጥር 11 የሚደረገውም ታላቁ የጥምቀት በዓል በተለይ በታሪካዊቷ የጎንደር ከተማ በድምቀት መከበሩን ተከትሎ እጅግ ብዙ ታዳሚያን ይገኛሉ ተብሎ ይታሰባል። ይህንን አስመልክቶ እንግዶችን ለመቀበል በቂ የፀጥታ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የአማራ ክልል ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቋል።
ቅድመ ዝግጀቱን እና በዝግጅቱ የሚኖሩትን መርሐ ግብሮች አስመልክቶ መግለጫ የሰጡት የአማራ ክልል ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ጣሂር መሃመድ በክልሉ የፀጥታ ስጋት እንዳይኖር በቂ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል፡፡ “ከፌዴራል መንግስት እና ከክልሉ የፀጥታ ኃይሎች ጋር በጋራ በቂ የጸጥታ ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል” ያሉት ቢሮ ኃላፊው እንግዶች ያለምንም ስጋት በዓሉን በአገራቸው ያሳልፋሉ ነው ያሉት፡፡
“ጥምቀትን በጎንደር” ይከበራል ያሉት አቶ ጣሂር ከፀጥታ ኃይሎች በተጨማሪ ወጣቶች የአካባቢያቸውን ሰላም በመጠበቅ ተጨማሪ ጉልበት ይሆናሉ ፡፡ ኃላፊው የአማራ ሕዝብ በየአካባቢው ወገኖቻቸውን በተለመደው የእንግዳ ተቀባይነት ባህል በመቀበል እንዲያስተናግዱም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የሽብር ቡድኑ ወርሯቸው በነበሩ በርካታ አካባቢዎች የአገልግሎት ሰጭ ተቋማትን በማውደሙ የመልሶ ግንባታ ሥራዎችን ለመሥራት ጥረት መደረጉን ያወሱት ኃላፊው የኤሌክትሪክ ኃይል እና ሌሎች አገልግሎቶች ወደ ነበሩበት በፍጥነት ለመመለስ እየተሠራ መሆኑንም አንስተዋል፡፡ በቀሪ ጊዜያት ባለሃብቶች፣ የክልሉ ሕዝብ አጋሮች እና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሌሎቹን የአገልግሎት ሰጭ ተቋማት መልሶ ግንባታ በማፋጠን ለእንግዶች ምቹ ሁኔታዎችን እንዲፈጥሩም አቶ ጣሂር ጥሪ አቅርበዋል።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ጥር 1 / 2014