በበርካታ ባህል የበለጸገችው ኢትዮጵያ ከእሴቶቿ መካከል ባህላዊ የስፖርት ጨዋታዎችና ፉክክሮች ይጠቀሳሉ። በተለይ በዓላትን ተገን አድርገው፤ መንደር ከመንደር፣ ደብር ከደብር፣ ላይ አምባ ከታች አምባ፣… ከሚፎካከሩባቸው ውድድሮች መካከል የገና ጨዋታ አንዱ ነው።
ይህንን ጨዋታ ወጣቶች ተሰባስበው መኸር በተሰበሰበበት ለጥ ያለ ሜዳ ከታህሳስ ወር ጀምሮ በጥር፣ በሚያዚያ እስከ ክረምቱ መግቢያ ድረስ የሚጫወቱት መሆኑንም በኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን የተዘጋጀ ሰነድ ይጠቁማል።
ዛሬ የሚከበረውን የገና በዓል ምክንያት አድርገውም የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ከመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ጋር የቡድን አባቶቻቸውን ይዘው በመቅረብ እንደ ወጉ ‹‹ነብሮ›› እና ‹‹አምበስ›› በሚል ተሰይመው በጃንሜዳ ውድድራቸውን አድርገዋል።
በባህል ልብሶች አሸብርቀው ከጫፉ ቀለስ ባለው የገና ዱላ ሩሯን(ጥንግ) እየለጉ ቢፎካከሩም መሸናነፍ ባለመቻላቸው በመለያ ምት የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ረተው የበግ ተሸላሚ ሆነዋል።
በመጨረሻም ሁለቱም ቡድኖች ‹‹አሲና በል አሲና ገናዬ›› እያሉ በመዝፈን ተለያይተዋል። የኪነጥበብ ባለሙያዎችን ወክለው በጨዋታው ከተሳተፉት መካከል አንዱ አንጋፋው አርቲስት ፋንቱ ማንዶዬ ናቸው። ገናን እየተጫወቱ ያደጉ ሲሆን፤ ጨዋታው የባህል መገለጫ እንደመሆኑ ሊጠናከር እንደሚገባው ያሳስባሉ።
ሽልማት ያላቸው ውድድሮችን በየአካባቢው በማዘጋጀት ማስፋፋት እንደሚቻልም ይጠቁማሉ። ሌላኛው አንጋፋ አርቲስት ችሮታው ከልካይ በበኩላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን የውጭ አገራት ነዋሪዎች (ዲያስፖራዎች) በተጠሩበት በዚህ ወቅት ባህልንእንዲሁም አገሪቷ ያለችበትን ሁኔታ ማሳየት መልካም እድል እንደሆነ ይገልጻሉ።
‹‹በዚህ ውድድር ላይ መሳተፍ ለሌላው አርዓያ ከመሆን ባለፈ ለዲያስፖራው ማህበረሰብ ኢትዮጵያ ከእነ እሴቶቿ እንዳለች ለማሳየት፣ የውሸት ፕሮፓጋንዳውም ተጨባጭ ያልሆነ መሆኑን እንዲረዱ የሚያግዝ ነው። ስለ አዲስ አበባ ከተማ አሉታዊ መረጃ ሲያስተላልፉ ለቆዩትም ጥሩ ማሳያ ይሆናል።
በቀጣይም መሰል ውድድሮችን በወጣቶችም ሆነ በባህልና ቱሪዝም ቢሮ በማዘጋጀት ስፖርቱን ማሳደግ አስፈላጊ ነው›› ሲሉም አሳስበዋል። የጋዜጠኞች ቡድንን በአምበልነት የመራው ጋዜጠኛ ነዋይ ይመር፤ የገና ጨዋታ አስደናቂ ህግ ያለውና አስደሳች የሆነ ጨዋታ መሆኑን ይጠቁማል።
ገናን ጨምሮ የባህል ስፖርቶች በሚፈለገው ልክ እንዲያድጉ የሁሉም ኃላፊነት ሲሆን፤ የመገናኛ ብዙሃን ግን ከሙያቸው አንጻር ከፍተኛ ስራ መስራት አለባቸው። ስፖርቱን የሚመሩት አካላትም ህብረተሰቡ ጋር ተደራሽ የሚሆንበትን ሁኔታ መፍጠር ይገባቸዋል። ‹‹በርካታ ስፖርቶችን ከውጭ እንደመዋሳችን እኛም ለውጪዎች ልንሰጣቸው የምንችላቸው ስፖርቶች አሉ።
በመሆኑም ስፖርቱን በማበልጸግ ወደ ተሻለ ደረጃ ማሸጋገር አስፈላጊ ነው›› ብሏል። ሌላኛው ጋዜጠኛ አንተነህ ሲሳይ በበኩሉ፤ በልጅነት የሚያውቀውን የገና ጨዋታን ለረጅም ጊዜ ሳይጫወት መቆየቱን ያስታውሳል። ህግ ተዘጋጅቶለት በዚህ መልክ መካሄዱም እጅግ ደስ የሚል ነው። በርካታ ባህላዊ ስፖርቶች በኢትዮጵያ ቢኖሩም ውድድር ለማካሄድ
ገናን መጠበቅ የለበትም። ከገና ጋር ተመሳሳይ የሆነው የፈረንጆቹ ‹‹ሆኪ›› ህግና ደንብ ተዘጋጅቶለት በመካሄዱ ታዋቂ ስፖርት ሆኗል።
ራሳቸውን ከማስተዋወቅ ባለፈም በገቢ ተጠቃሚ ሆነውበታል። በመሆኑም እንደ ገና ያሉ የባህል ስፖርቶችን በማሳደግና በማስተዋወቅ ከፍተኛ ስራ መስራት የግድ ነው፤ ለሌሎች ስፖርቶች የሚሰጠውን ያህል ትኩረት መስጠትም ያሻል። የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች፣ አንጋፋ ሰዎች እንዲሁም ባለሃብቶችም ስፖርቱን ማስተዋወቅ እና ማገዝ ይገባቸዋል ሲልም መልዕክቱን አስተላልፏል።
ማስተር ሄኖክ መገርሳ ለሁለት አስርት ዓመታት አሜሪካን ጨምሮ በተለያዩ አገራት የኖሩ ዲያስፖራ ናቸው። ገናን ልጅ ሆነው መጫወታቸውን አስታውሰው ይህንን መሰል ውድድር ማካሄድም ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እንዳለው ይጠቁማሉ።
ይህ ጨዋታ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተወራረሰ መቀጠሉን በመመልከታቸው መደሰታቸውን ጠቅሰው፤ ዓለም አቀፍ ፌስቲቫል እንዲሆን መሰራት ይገባዋል። ዲያስፖራው ማህበረሰብም ባህሉን እንዲያውቅ ለማድረግ የተለያዩ ስራዎችን ማከናወን እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃኑ አድማሱ፤ ትውልዱ ባህሉን እንዲያውቅ ትምህርት ቤቶች ላይ መሰረት በመጣል በፕሮጀክቶች ታቅፎ ታዳጊዎች እንዲሳተፉበት እየተሰራ መሆኑን ይገልጻሉ።
በከተማዋ 11ዱም ክፍለ ከተሞች ፕሮጀክቶች የተመሰረቱ ሲሆን፤ የአገሪቷን እሴት የማስተዋወቅ ስራ እንደመሆኑ ትምህርት ቢሮ እንዲሁም የባህልና ቱሪዝም ቢሮ በዚህ ረገድ ከፍተኛ ትኩረትና እገዛ ሊያደርግ ይገባዋል። ስፖርት ቢሮውም የተለያዩ መርሃ ግብሮችን ማዘጋጀት እንደሚገባውም ጠቁመዋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 29/2014