በበርካቶች ዘንድ ባህላዊ ስፖርቶች የዘመናዊ ስፖርት መሰረት መሆናቸው ይታወቃል:: ሆኖም በርካታ ባህላዊ የስፖርት ሀብቶች የሆነችው ኢትዮጵያ የህብረተሰቡ ተሳታፊነት አነስተኛ በመሆኑ ተጠቃሚ ለመሆን አልቻለችም:: በመሆኑም ስፖርቱን ለማሳደግ ዓመታዊ ውድድሮች አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ይካሄዳሉ::
ዘንድሮም የአዲስ አበባ ከተማ አቀፍ ባህል ስፖርቶች ውድድርና ፌስቲቫል ለ12ኛ ጊዜ ከዛሬ ጀምሮ በጃንሜዳ የስፖርት ማዕከል መካሄድ ይጀምራል::
‹‹ባህላዊ እሴቶቻችን መጎልበት፤ ለጠንካራ አገራዊ አንድነት›› በሚል መርህ የሚካሄደው ውድድሩ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ እና በባህል፣ ቱሪዝምና ኪነ-ጥበባት ቢሮ ጋር በመሆን የተዘጋጀ ነው:: በአራዳ ክፍለ ከተማ አስተናጋጅነት አስራ አንዱንም ክፍለ ከተሞች ተሳታፊ በማድረግ የሚካሄደው ውድድሩ ከትግል በቀር በ10 ስፖርቶች ፉክክር ይደረጋል::
የትግል ውድድርም አካላዊ ቀረቤታንና ንክኪን የሚጠይቅ መሆኑ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ፕሮቶኮል ክልከላ ምክንያት አይካሄድም:: የመክፈቻ ስነስርዓቱ ትናንት በደማቅ ሁኔታ በጃንሜዳ ሲካሄድ፤ ዳያስፖራዎች፣ የኪነጥበብ እና የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የታደሙበት ሲሆን፤ ውድድሩ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ጥር 7ቀን2014 ዓ.ም ድረስ ቀጥሎ ይደረጋል::
የባህል ስፖርት ዓይነቶች በሕብረተሰቡ ዘንድ ይበልጥ እንዲታወቅም በባዛር መልክ የተዘጋጀ ሲሆን፤ ስለ ውድድሩ መረጃ እንዲኖረውም ገለጻ ሲደረግ ነበር:: በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት
ቢሮ ኃላፊ አብርሃም ታደሰ፤ ኢትዮጵያ የብዙ ባህሎችና ቱፊቶች ባለቤት መሆኗን ንግግር ባደረጉበት ወቅት ጠቁመዋል:: ‹‹ይሁን እንጂ ባለፉት ዓመታት ባህሎቻችንና እሴቶቻችን ተገቢው ጥበቃና ድጋፍ ስላልተደረገላቸው በሚፈለገው መጠን ሊጎለብቱ አልቻሉም:: በመሆኑም የባህል ስፖርት እንቅስቃሴውን ለማጠናከርና በአገር አቀፍ ደረጃ ለሚካሄደው ውድድር የተሻሉ አቅም ያላቸውን ተወዳዳሪዎች ለማፍራት እንዲቻል ውድድሩ ተዘጋጅቷል::
ባህሎቻችንና እሴቶቻችን ሲጎለብቱ ኢትዮጵያዊ ማንነታችን ከፍ ይላል:: ይህም ለአንድነታችንና ህብረታችን ወሳኝ ነው::
አንድነታችንና ህብረታችን በባህላዊ እሴታችን ተደግፎ ሲቀጥል ደግሞ ትውልዱም በባህሉ የሚኮራ፣ በራሱ የሚተማመንና ለሌላው ዓለምም ባህሉን የሚያስተላልፍ እንዲሆን ትልቅ አቅም ይፈጥራል›› ብለዋል::
ባህል ቱሪዝምና ኪነጥበባት ቢሮ ኃላፊዋ ዶክተር ሂሩት ካሳው በበኩላቸው፤ ስፖርት ለማህበራዊ ትስስር መሰረት የሆነ እንቅስቃሴ መሆኑ አንጸባርቀዋል:: አሁን ላሉ ስፖርቶች መነሻ የሆኑት ባህላዊ የስፖርት እንቅስቃሴዎች ከሰው ልጆች እድገት ጋር እያደጉና እየዘመኑ አካልና አእምሮ ማጎልበት ባሻገር ማህበረሰቡን በማቀራረብ ወደር የማይገኝለት ዘርፍ ነው:: ሌሎች ሃገራት የዘመናዊ ስፖርት መሰረት ከሆኑት ባህላዊ ስፖርቶች ተጠቃሚ ሆነዋል::
ኢትዮጵያም በዘርፉ ሰፊ የሆነ እምቅ አቅም ያላት ብትሆንም በተለያዩ ምክንያቶች አስፈላጊው ትኩረት ባለመሰጠቱ ተወዳዳሪነቷ ዝቅተኛ ነው:: ስለሆነም በተጠናና በታቀደ መልኩ ይህ ሁኔታ ሊለወጥ እንደሚገባ አሳስበዋል::
ይህ ዓይነቱ ውድድር ኢትዮጵያዊነትን ለመግለጽ የሚያስችል መሆኑን የሚገልጹት ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃኑ አድማሱ ናቸው:: ባህሉን የሚያውቅ ትውልድ ለመፍጠር የገና በዓልን መነሻ በማድረግ ውድድሩ በየዓመቱ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ይካሄዳል::
ውድድሩ ከሚካሄድባቸው ዓላማዎች መካከል በቅርቡ በሚካሄደው አገር አቀፍ ውድድር ላይ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን ወክለው በውድድሩ ላይ የሚካፈሉ ምርጥ ስፖርተኞችን ለመምረጥ ያስችላል::
የስፖርቱ ባለቤት ህብረተሰቡ እንደመሆኑ የሚገናኝበትና ልምድ የሚለዋወጡበት ነው፤ አንዴ ታይቶ የሚጠፋ እንዳይሆን የመንግሥት አካላትም ሆኑ ባለሀብቶች ተሳታፊ መሆን ይገባዋቸል::
በዓመት አንዴ ብቻ የሚካሄድ ሳይሆን በትምህርት ቤቶች እንዲሁም በሌሎች አካላት ዘንድም ተደራሽ እንዲሆንም ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ፕሬዚዳንቱ ይጠቁማሉ:: ከዚህ ጎን ለጎንም ውድድሩ በጦርነቱ የተጎዱ ወገኖች የሚታሰቡበት እንዲሁም ለኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትም እገዛ የሚደረግበትም ነው::
እንዲሁም አጠቃላይ ፌስቲቫሉ ከተማዋ ሰላም የሰፈነባት ስለመሆኗ ለተቀረው ዓለም የሚንጸባረቅበት ምቹ አጋጣሚ እንደሚሆንም ጠቁመዋል::
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 28/2014