በድሮ የጦር ስልት ድልን በመናፈቅ ዳግም አራት ኪሎን ስታልም በሩቅ እንኳን ማተራምስ ከአራት ኪሎ ዳግም ከመቀሌም መዋል ሆኖሃል የቀን ህልም! የሰው ልጅ ሊያስገድለው እና ሊግድለው የሚችለው «የሚወደው» ነገር ነው ፡፡
ሲኦል መግባትን እና አገር ማፍረስን የሚወድ ሰው የሚሞተው ሲኦል ለመግባት እና አገርን ለማፍረስ ሲጥር ነው ፡፡ ሰላም እና እድገትን የሚሻም ሰው የሚሞተው ለሰላም እና ለእድገት ሲኳትን ነው፡፡ ነገር ግን ሲኦል ለመግባት እና አገር ለማፍረስ የሚጥር ሰው እና ሰላም አንድነትን ለማምጣት የሚታትር ሰው ሲሞት የሚሰጠው ክብር ለየቅል ነው፡፡ ለምሳሌ አፓርታይድን ይሰብኩ የነበሩ ግብዝ ነጮች እና አፓርታይድን የተፋለሙት ኔልሰን ማንዴላ የሚወዱት ነገር የተለያየ ነበር፡፡ አሁን ላይ በደቡብ አፍሪካ ታሪክ አፓርታይድን ሲያራምዱ የነበሩ ግብዝ ነጮች እና እኩልነትን ለማስፈን የተጋጋጠው ማንዴላ የሚነሱበት አውድ ፈጽሞ የተለያየ ነው ፡፡ እነ አይተ ጭሬ ልድፋው እና ከአይተ ጭሬ ልድፋው ጋር የረከሰ ጋብቻ የፈጸመችው ኦቦ ጫካ ሱሱ እና ለጥፋታቸው መሳካት እርዳታ እያደረገች ያለችው አሜሪካ የሚወዱት ነገር ቢኖር አባቶቻችን ጠብቀው ያቆዩትን እድራችንን መበተን ነው፡፡ እኛ ደግሞ የምንወደው አሉ የንታ ፍሬው ፤ አባቶቻችን ያስረከቡን እድር ጠብቀን ማቆየት ነው፡፡ ወደ ፊት በታሪክ የምንወሳበት አውድ ግን ለእኛ ኩራት ሲሆን ለእነሱ ግን የሃፍረት መሆኑን አልጠራጠርም፡፡ ምክንያቱም የእኛ እያንዳንዷ እርምጃችን የእድራችን ህልውና ለማስቀጠል በሚያስችሉ እና ተለክተው በተቆረጡ ህጎች እና መርሆዎች የተከሉ ናቸው፡፡ አሜሪካ የአይተ ጭሬ ልድፋውን እና የኦቦ ጫካ ሱሱን የረከሰ ጋብቻ ለመደገፍ የምታደርገውን መላላጥ አንድ እርኩስ መንፈስ የተጠናወተውን ሃኪም አስታወሰኝ፡፡ በአንድ ወቅት እርኩስ መንፈስ የሰፈረበት ሃኪም ነኝ ባይ ሰው ነበር ፡፡ በአንድ ሰፈር ውስጥ የኖሩ ሰዎችን ሰብስቦ የአይን ሃኪም እንደሆነ ነገራቸው ፡፡ አይናቸው ማየት የተሳነቸውን ሰዎች ማየት እንዲችሉ ማድረግ እንደሚችል እና ማየት የሚችሉትንም የእይታ አድማሳቸውን እንደሚያሰፋላቸው አስረዳቸው። ሰዎችም በሃኪሙ ብቃት እጅጉን ተገርመው አይናቸውን በቀዶ ጥገና እንዲቀይርላቸው ጠየቁት፡፡ ሃኪሙም ጤነኞችን እና አይነ ስውራንን በአንድ ላይ በተመሳሳይ መልኩ በቀዶ ጥገና አይን ቀየረላቸው ፡፡ ከቀዶ ጥገናው በኋላም አይናቸው አየ ፡፡ ሁሉም ደስ አላቸው ፡፡ ሃኪሙንም ማየት ቻልን! ማየት ቻልን !እናመስግናለን! እያሉ አቀፉት፡፡ ሃኪሙም «ምን ይታያችኋል ? » ሲል ሰዎችን ጠየቀ ፡፡ ሰዎችም በአንድ ድምጽ «ቁጥራቸው እጅግ በርካታ የሆኑ አይጦች »ብለው መለሱ፡፡ ምክንያቱም ተንኮለኛው ሃኪም ለሰዎቹ የቀየራለቸው የሰው አይን ሳይሆን የድመት ነበርና ነው ፡፡ አይተ ጭሬ ልድፋው እና የኦቦ ጫካ ሱሱን ጋብቻ የጥፋት የጫጉላ ጊዜ ወጭ እየሸፈነች ያለችው አሜሪካም የምትሰራው ስራ የተንኮለኛውን ሃኪም አይነት ነው ፡፡ አሜሪካ እና መሰል የጥፋት ጌቶች አይተ ጭሬ ልድፋውን እና ኦቦ ጫካ ሱሱን ከጥንት ጀምሮ በፈጠሩት የተንሸዋረረ እይታ እንዲያዩ በማድረግ በሰውነት ደረጃው ሰው ማየት ሲገባቸው ከሰውነት ደረጃ ወርደው አይጥ ብቻ እንዲያዩ እያደረጓቸው ይገኛሉ፡፡ ይህን የተገነዘቡት የንታ ፍሬው አንድ ቀን የእድራችንን አባላት በሰፈራችን ከሚገኘው ዋርካ ጥላ ስር ሰብስበው እድሩ የተቋቋመበትን አላማ እና የሚታደርበትን ህግ እና መርህ እያንዳንዱ የእድሩ አባል ለሴኮንድም ቢሆን መርሳት እንደሌለበት ያስተምራሉ፡፡ የእድሩ አባላትም የንታ ፍሬውን ምክር እየሰሙ ተመስጠዋል፡፡ ከመመሰጣቸው የተነሳ ሰው ቢጎትታቸው እንኳን የሚሰሙ አይመስሉም፡፡ የንታ ፍሬው ስለመርህ ሲያስተምሩ እንዲህ አሉ «በድንጋይ ወፍጮ እህል መፍጨት አይቻልም፡፡ የድንጋይ ወፍጮ ድንጋይን የሚያህል ጠንካራ ነገር ስላደቀቀ ብቻ እህል ይፈጫል ማለት አይደለም፡፡ በእህል ወፍጮም ድንጋይን መፍጨት አይቻልም ፡፡ እህል ስለፈጨ
ድንጋይን ይፈጫል ማለት አይደለም ፡፡ ለሁሉም ነገር የራሱ ነገር አሰራር እና ሂደት አለው ፡፡ በስሜት ሊሆን የሚችል ነገር የለም ፡፡ » ራስን መግዛት እና መቆጣጠር የመርህ እና የአላማ ጽናት መጀመሪያው «ሀሁ» ነው ፡፡
የአይተ ጭሬ ልድፋው አላማው አገርን ማጥፋት ነው፡፡ ይህን አላማውን ለማሳካት የሚከተለው መርሁ ደግሞ መነሻው እና መድረሻው አጥፍቶ መጥፋት ነው። የሚገርመው ከራሱም ወገን ሆነ ከተቃራኒው ሰው ቢሞት ንብረት ቢወድም ደንታው አይደለም፡፡
ባህሪን ፖሊሲ ወይም መርህ ሊገዛው አይችልም፡፡ ሊሞርደው ሊጠግነው ይችላል ፡፡ ግን ችሎ በተፈለገው ልክ አያስተካክለውም ፡፡ አይተ ጭሬ ለድፋውና ኦቦ ጫካ ሱሱ መርህ አለን ቢሉም የጠፍቶ ማጥፋት ጠባያቸው አገርሽቶባቸው ሊያወድሙን የረከሰ ጋብቻ ፈጽመው ነበር፡፡ በዘር ሊያቧድኑን ፈለጉ፡፡ አልቻሉም።
በነገራችን ላይ ከየትኛውም ዘር ብትሆን ፤ ምንም ምክንያት ብትሰጠው ዘረኝነትን የሰበክ ዕለት በጉንዳን ጉድጓድ ገብቶ እንደመተኛት ወይም ንብን ከቀፎዋ ድረስ ሂዶ ለመግደል እንደመሞከር ነው ፡፡ ወይም በደነበረ ፈረስ ላይ ተቀምጦ የደነበረውን ፈረስ ለማስቆም በደነበረው ፈረስ የነበረን ገመድ አንገትን እንደማጥለቅ ነው ፡፡ ወይም በበርሜል በሚፈላ ዘይት ውስጥ እንደመዘፍዘፍ ነው ፡፡ ምክንያቱም የዘር ጥላቻ አንድ ሰብዓዊ ፍጡር ለሌላው ሰብዓዊ ፍጡር ሊኖረው የሚገባውን ሐዘኔታና ርህራሄ ከሰው ልብ ፈልቅቆ አውጥቶ ከአውሬ በባሰ ጭካኔ ይተካዋል፡፡በዚህ ጊዜ የተፈጠረው ጥላቻ ሁሉንም ሳይመርጥ እኩል መብላቱ የማይቀር ነው ፡፡ የንታ ፍሬው አሁንም ንግግራቸውን እንደቀጠሉ ናቸው፡፡
አላማ እና መርህ አልባው አይተ ጭሬ ልድፋው ወደ ማህል አገር ዘልቆ የሰው ህይወት በቀጠፈበት እና ንብረት ሲያወደም የአይተ ጭሬ ልድፋውን ጥፋት የሚመክት ሃይል ያለን አይመስልም ነበር፡፡ ነገር ግን የሰፈራችን ሰዎች በአጭር ጊዜ ተደራጅተው ለረጅም ዓመታት ለጥፋት ሲዘጋጅ የነበረውን ሃይል አፈር ድሜ ማብላት ተችሏል፡፡ አብዛኛው ሃይሉ ማህል አገር ተገድሎበታል፡፡ ግማሹ ተማርኮበታል ፡፡ ጥቂት ሃይሉ ደግሞ ይዞ የመጣውን ንብረት ጥሎ ፈረጠጠ፡፡ ከመሀል አገር ተሸንፎ እግሬ አውጭ ያለው አይተ ጭሬ ልድፋው ለጥፉት ጌቶቹ ለሁለተኛ ጊዜ የዘር ማጥፋት ወንጀል ሊፈጸምብኝ ነው አድኑኝ ሲል ለመነ ፡፡
በመርህ እና በህግ የሚመሩት የንታ ፍሬው በሰከነ አእምሮአቸው ግራ እና ቀኝ እንዲሁም ፊት እና ኋላቸውን ቃኝተው እነ አይተ ጭሬ ልድፋውን ስላሸነፍኩ ብቻ እነአይተ ጭሬ ልድፋው መንደር አሁን ላይ አልገባም ሲሉ ተደመጡ፡፡
ይህን የሰማው አይተ ጭሬ ልድፋው ያለምንም አላማ ባስገደላቸው የሰፈሩ ልጆች የሰፈሩ ነዋሪዎች ጥያቄ እንዳያነሱበት እና እንዳያምጹበት በመስጋት ምንም ቢል ጥሩ ነው «የየንታ ፍሬው የጦር ሃይል ሰፈራችን እገባለሁ ካለ እዚሁ እንቀብረዋለን! ፡፡ይህን ለማድረግ እንዲቻል ከዚህ ቀደም አድርገን ከነበረው የበለጠ መዘጋጀት አለብን» ሲል ደሰኮረ፡፡ በዚህ ጊዜ ነበር አንድ ከሃሺሽ ጡዘቱ የነቃ ተሰብሳቢ ከስብሰባው መካከል ተነስቶ የንታ ፍሬው ለሁለተኛ ጊዜ የዘር ማጥፋት ሊፈጽምብን ነው ስትሉ እንዳልቆያችሁ ሁሉ ለምንጊዜው ተገልብጣችሁ የየንታ ፍሬው የጦር ሃይል ሰፈራችን ቢገባ እዚሁ እንቀብረዋለን ልትሉ ቻላችሁ? ብሎ ጠየቀ ፡፡
አይተ ጭሬ ልድፋው « እንደሚታወቀው እኛ ከማህል አገር ስንወጣ ስልታዊ ማፈግፈግ ነው ያደረግነው፡፡ ይህንንም ስልታዊ ማፈግፈግ ያደረግነው ገናን በላሊበላ ጥምቀትን በጎንደር ለማክበር ወደ አገራቸው የሚመጡ ዲያስፖራዎች ምቾት እንዲሰማቸው በማሰብ ነው!» በማለት መለሰ፡፡
የአይተ ጭሬ ልድፋው መልስ ያልተዋጠለት ከሃሺሹ ድንዛዜ የወጣው ልጅ «እነ የንታ ፍሬው ሰፈር ገብተን ህይወት ስናጠፋ እና ንብረት ስናወድም በነበርንበት ጊዜ ዲያስፖራዎችን በውጭ የሚያደርጉትን ተፅዕኖ የማያቆሙ ከሆነ ውጭም ቢሆን ሂደን እንጨርሳቸዋለን፡፡ ለዚህም ደግሞ ሙሉ ዝግጅት ተደርጎ ተጠናቋል ስትሉ አልነበር እንዴት ዛሬ ደግሞ ስለእነሱ ምቾት ተጨነቃችሁ ?»ብሎ ደግሞ ጠየቀ ፡፡ ይህን ጥያቄ የጠየቀው ሰው በተሰብሳቢዎች ሰርጎ ገብ ነው ተብሎ ተፈረጀ፡፡
በዓልን በሲኦል እንዲያከብርም የአስቸኳይ ቪዛ ተቆርጦለት ወደ ሲኦል ተላከ፡፡ ሌላው ከሃሽሽ ድንዛዜ የወጣው ሰው ከተሰብሳቢዎች መካከል ተነስቶ ዴሞክራሲን ለህዝባቸው በመንፈግ የሚያስተዳደሩ አምባገነን መንግስታት ሁልጊዜም እጣፋንታቸው የስልጣን ዘመናቸውን የሚያጠናቅቁት በሃይል እና በሁከት ነው፡፡
ወንድሞቻችንን እናቶቻችንን፣ እህቶቻችንን ፣ አባቶቻችን እና ልጆቻቸውን ምክንያት በሌለው፤ በውሸት እና በጉራ ህዝቡን እያነሳሳችሁ ጦርነት በማዝመት እንዲሞቱ ስታደርጉ ለምን ያለምክንያት ይሞታሉ ብለን ስንጠየቅ ለጠየቅነው ጥያቄ መልስ መመለስ ሲሳናችሁ ታፍኑናለችሁ ።
ትገድሉናላችሁ። እንዴት እንታፈናለን? እንዴትስ እንደወንጀለኛ ተቆጥረን እንገደላለን ፤እንታሰራለን? ፡፡ ሞሶሎኒም በእብሪት ተወጥሮ ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት በመያዝ የአደዋውን ሽንፈት ተበቅየ አሳያችኋለሁ ባለ ጊዜ ሃብት ያለው ጣሊያናዊ ሃብቱን ሰጠ፡፡
ሃብት የሌለው ደግሞ የጋብቻ ቀለበቱን ሳይቀር ሰጠ፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው ሞሶሎኒ በፈጠረው አጉል ውሸት እና ጉራ የጣሊያን ህዝብ ተታሎ ነበር ፡፡ የኋላ ኋላ ግን የሞሰሎኒ ውሸት የገባቸው ጣሊያናዊያን ከማንም በፊት ሞሰሎኒን በሚዘገንን መልኩ በጎረረበት አደባባይ የገደሉት ጣሊያናዊያን ናቸው፡፡
የእናንተም እጣ ፋንታ የሞሶሎኒ አይነት ነው የሚሆነው ሲል ሁሉም ተሰብሳቢዎች በአንድ ድምጽ ሲኦል ጠብቀን አሉ፡፡ የንታ ፍሬው ለእድርተኛው ያስተላለፉትን የመጨረሻው መልዕክት ልንገራችሁ እና እንሰናበት፡፡ የንታ ፍሬው ግንባራቸውን ቁጥር ፈታ እያደረጉ ወገኖቼ ፍትህን በምልጃ ከምታገኙ የበደል ችንካር ውስጥ ታስራችሁ ቆዩ! ፡፡ አሜሪካ እና አጋሮቿ እውነታቸው ሳይጠፋቸው ፍትህን ነፈጉን፡፡
ፍትህን በምልጃ ካልሆነ በስተቀር እውነትን ስለተከተልን ብቻ እንደማይሰጡን ነገሩን፡፡ ነገር ግን እኛ በምልጃ እንዲሰጡን በፍጹም አንፈልግም !፡፡ ፍትህ እስከምናገኝ ተጨቁነን ብንቆይ ይሻል እንጂ ፍትህን ለማግኘት አሜሪካን እና አጋሮቿን አንለማመጥም፡፡ ይህም የአባቶቻችን ያወረሱን ታሪክ አይደለም ፡፡
ስለሆነም አሜሪካ እና አጋሮቿ እኛን ጠልፈው ለመጣል የሚያደርጉትን ሙከራ ለማክሸፍ እስከዛሬ ከምናደርገው በበለጠ እጅ ለእጅ ተያይዘን ልንቆም ይገባል፡፡ በብዙ አገራት የሰው ልጅ በዘሩ እየደራጀ ሲጋጭና ሲጫረስ ኖሯል፡፡ ከተፈጸሙት እልቂቶች በመጠነሰፊነቱ ቀዳሚው አስራ ሶስት ሚሊዮን የአሜሪካ ቀደምት ሕዝቦች (ሬድ ኢንዲያንስ) በአውሮፓውያን መጤዎች የተገደሉበት ነው፡፡
በቤልጅየሙ ንጉሥ ሊኦፖልድ ዳግማዊ ትዕዛዝ አስር ሚሊዮን ኮንጓውያን በየተወለዱበት ቀዬ የተጨፈጨፉበት ይከተላል። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ደግሞ ስድስት ሚሊዮን ይሁዲዎች በናዚ ጀርመኖች በመግደያ ጣቢያዎች በጅምላ እንዲያልቁ ተደርገዋል፡፡እንዴት እነኝህ አገራት ስለሰው ልጅ ክብር ደፍረው ሊነግሩን ይሞክራሉ፡፡
ይሄን የእነ አሜሪካ አካሄድ በምሳሌ ለማስረዳት ያህል የአንድ ዝንጀሮ ታሪክ መመልከቱ ተገቢ ነው፡፡ አንድ ቀን አንድ ዝንጀሮ ከጫካ ወጥታ ባጋጣሚ ከተማ መሀል ትከሰታለች ፡፡ መልኳንም በመስታወት ትመለከተዋች ፡፡ ነገር ግን ያየችው ምስል የሌላ ዝንጀሮ እንጅ የራሷ አልመሰላትም፡፡
በመስታወቱ የተመለከተችው ምስል መቀመጫው ላይ ያለውን መላጣ ነው ፡፡ እናም ዝንጀሮዋ ምን ብትል ጥሩ ነው! «እኔ እንደዚህ መላጣ ብሆን ታንቄ ነበር የምሞት።» አሜሪካም ለአንድ ቀንም ራሷ አክብራቸው የማታውቃቸውን የተለያዩ ህግጋት ሌሎች አገራትን ለምን አታከብሩትም እያለች ስተጮህ የተመለከተ ማንም ሰው ራሷን ማን እንደሆነች የዘነጋችውን ዝንጀሮ ማስታወሱ የማይቀር ነው ፡፡ የተነፈግነውን ፍትህ ለማስመለስ መለማመጥ ሳይሆን ጠንክረን መገኘት አለብን፡፡
ጠንክረን ለመገኘት ደግሞ የመከላከያ ኃይላችንን ማጠናከር አለብን፡፡ ስለሆነም እያንዳንዱ የእድራችን አባላት የመከላከያ ተቋምን ከዛሬ ጀምረህ ተቀላቀል ተብለሃል። በእንዝላልነት በየሰፈሩ ተደብቀህ የምትቀምጥ ግን ነጻነትህን ሰዎች እንዲሰጡህ እየጠበክ መሆኑን ለአፍታም መዘንጋት የለብህም፡፡
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 28/2014