በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከምንም በላይ የአገራቸውን ፍቅር በልባቸው ይዘው የሚኳትኑና በአካል ቢርቁም በመንፈስ ሁሌም ከኢትዮጵያ ጎን የሚቆሙ ናቸው:: አብዛኞቹም አገራቸውን የሚወዱ፣አገራቸው ተሻሽላና አድጋ ማየት የሚፈልጉና አንድ ጠንካራ ኢትዮጵያ እንድትኖር ከልብ የሚመኙ ፣ለዚያም የሚታገሉ ናቸው::
ይህ ስሜታቸውም በተለይ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አሕመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በግልፅ በአደባባይ እየታየ ይገኛል::
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድም በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ወደ አገር ቤት በመግባት በዓላቶችን እንዲያከብሩ ጥሪ ማቅረባቸውን ተከትሎም በርካታ ዲያስፖራዎች ወደ አገር ቤት ገብተዋል፤ በመግባትም ላይ ናቸው:: ‹‹the great Ethiopian home coming›› በሚል የቀረበውን አገራዊ ጥሪ ተቀብለው ወደ ኢትዮጵያ የመጡትም ሆነ የሚመጡትን ዜጎች ለመቀበል መንግሥትና ባለድርሻ አካላት በመተባበር መጠነ ሰፊ ዝግጅት አድርገዋል፤ እያደረጉም ይገኛሉ:: የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲም ዲያስፖራውን ከአገሩ ጋር ለማገናኘት የተቋቋመ ድልድይ ነው::
አዲስ ዘመን ጋዜጣም በአሁን ወቅት ያለው የዲያስፖራ ሁለንተናዊ ተሳትፎ እንዴት ይገለፃል? በተሰሩ ሥራዎች የተገኙ ውጤቶቹስ? የዲያስፖራውን መብትና ጥቅም በማስከበር ረገድ ምን እየተከናወነ ነው? የዲያስፖራውን አቅም አማጦ በመጠቀም ረገድ ፈተናዎች ምንድን ናቸው? ከአስፈፃሚ አካላትስ ምን ይጠበቃል? የሚሉ ጥያቄዎችን በማንሳት ከኤጀንሲው የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ወንድወሰን ግርማ ጋር ቆይታ አድርገናል:: ቆይታውንም እንደሚከተለው አሰናድተነዋል::
አዲስ ዘመን:- ከለውጡ በፊት የነበረውን የኢትዮጵያና የዲያስፖራዎች ቁርኝት እንዴት ያስታውሱታል?
አቶ ወንድወሰን:- ከለውጡ በፊት በነበሩ ዓመታት ዲያስፖራው ተቃዋሚ ነበር:: መንግሥትም ዲያስፖራውን የሚመለከተውና የሚለየው ደጋፊና ተቃዋሚ በሚል ከፍፋሎ ነው::ይህ አመለካከት ደግሞ አንዱን የማቅረብ አንዱን የመግፋት እድል ፈጥሯል:: በወቅቱ አብዛኛውን ጊዜ በኤምባሲዎችና የተለያዩ መድረኮች ላይ የሚጋበዙት ደጋፊ የሆኑ ዲያስፖራዎች ናቸው::
ዲያስፖራው የፈለገውን ሃሳብ ማራመድ፣ ማንፀባረቅ መወያየትና ሃሳብ ማቅረብ አይችልም:: አገሩን በፈለገው መልኩ ለመደገፍም ገደብ ይጣልበትም ነበር:: ዲያስፖራውም በአገር ውስጥ የሚፈልገው ለውጥ እንዲመጣ ከፍተኛ ተቃውሞ ሲያሰማም ቆይቷል:: በወቅቱ የመንግሥት አመራሮች ወደ ውጭ በሚወጡበት ወቅት ከዲያስፖራው የሚገጥማቸው ተቃውሞ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ሆኖ የሚታወስ ነው::
አዲስ ዘመን:- ከለውጡ በኋላስ ምን ተለወጠ? ለምን?
አቶ ወንድወሰን:- በዶክተር ዐቢይ አሕመድ የሚመራው የለውጥ መንግሥት እውን ከሆነ ጊዜ ጀምሮ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ከአገሩ ጋር ያለው ግንኙነት በእጅጉ ተለውጧል::
የለውጡ አመራርም ይህ እንዲሆን በአራት አህጉራት በመንቀሳቀስ ዲያስፖራውን አነጋግሯል:: በወቅቱም‹‹ ግንቡን እናፍርስ ድልድዩንም እንገንባ›› በሚል መርህ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ከዲያስፖራው ማኅበረሰብ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል::
በዚህም በአገር ቤት እና በዲያስፖራው መካከል ለዘመናት ተጋርዶ የነበረው ግንብ እንዲፈርስ ሆኗል:: ትስስሩ እንዲጠናከር ዲያስፖራው የአገሩ ባለቤትና ለውጡም ላይ ትልቅ አሻራ እንዳለው ከመግባባት ላይ ተደርሷል::
ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ሚሽነሪዎች ወይንም ኤምባሲዎችና በዲያስፖራው መካከል የነበረው መራራቅ እንዲወገድ ሆኗል:: ከለውጡ በኋላ ኢትዮጵያ የምትከተለው ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ መሆኑን የሚያረጋግጡ በርካታ ሥራዎች ተሰርተዋል::
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለተለያዩ ሥራዎች በተንቀሳቀሱባቸው አገራት በእስር ላይ የነበሩ ዜጎችን በማስፈታት በራሳቸው አውሮፕላን ሳይቀር በመጫን ወደ አገር ቤት መመለሳቸውም ሁሉም የሚያስታውሰው ነው:: በአሁን ወቅትም ዲያስፖራ ማለትም ኢትዮጵያ ውስጥ የማይኖር ኢትዮጵያዊ ነው::
በቦታ ብቻ ከአገሩ የተለየ ነው:: በአሁን ወቅት ደጋፊና ተቃዋሚ ዲያስፖራ የሚል ከፋፋይ እሳቤ የለም:: ዲያስፖራው የፈለገውን ሃሳብ ማራመድ፣ማንፀባረቅ መወያየትና ሃሳብ ማቅረብ ይችላል::
አገሩን ለመደገፍ ምንም ገደብ አይደረግበትም:: በአሁን ወቅት ዜግነቱን የቀየረውም ሆነ ዜግነቱን ያልቀየረው ሁሉንም አንድ የሚያደርጋቸው ነገር ሁሉም በአገራቸውን ጉዳይ ቀናዒ መሆናቸው ነው:: ሁሉም አገራቸውን በጣም ይወዳሉ:: በተለያዩ አገራት ዜግነት የወሰዱ አሉ::
ሁሉም ግን ከኢትዮጵያ ጎን ሲቆሙ አገራቸውን ሲያስቀድሙ መሸማቀቅ አይታይባቸውም:: ይህ አይነት እሳቤ ከዚህ ቀደም አልነበረም:: እነዚህ ሁሉ የሚናገሩት አንድ ነገር ቢኖር መንግሥት ለዲያስፖራው ልዩ ትኩረት መስጠቱን ነው:: ዲያስፖራውም ለኢትዮጵያዊ ወይንም ለዜጎቹ ትኩረት የሰጠ መንግሥት መሆኑን ከግንዛቤ በማስገባት አገራዊ ለውጡን እንደ ባለቤት በማየት ሁለንተናዊ ተሳትፎውን ከጊዜ ወደ ጊዜ አጎልብቷል::
አዲስ ዘመን:- ተሳትፎው ለመሻሻሉ ማሳያዎቹ ምንድን ናቸው?
አቶ ወንድወሰን:-በአሁን ወቅት ዲያስፖራው የለውጥና የአገር ባለቤትነት ስሜቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል::
በተለይም ለኢትዮጵያ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ሁሉ እየደገፈ ይገኛል:: የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ሚናውንም ከቅርቡ ማንሳት ይቻላል:: ከገጽታ ግንባታ ጋር ብንመለከት፣ዲያስፖራው በአሁን ወቅት ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው::
እንደሚታወሰው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ በተለይ በታላቁ የህዳሴ ግድብና ወቅታዊውን የሕልውና የሕግ ማስከበር ዘመቻ በሚመለከት ከአስር ጊዜ በላይ ለውይይት ተቀምጧል::
በእያንዳንዱ ስብሰባ ላይ ዲያስፖራው አስቀድሞ ሰልፍ በመውጣት የአገሩን ድምፅ አስተጋብቷል:: የበቃ /#Nomore/ ንቅናቄም ይበልጥ ገኖ ይታይ እንጂ ከዚህ ንቅናቄ በማይተናነስ መልኩ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ሁነቶች ከአገራቸው ጎን ቆመው ታይተዋል::
በመላው ዓለም የሚገኙ ዲያስፖራዎች ለእናት አገራችን ለኢትዮጵያ አናንስም፣ ባለን ሁሉ እንቆምላታለን ብለው ተነስተዋል:: በተለይ ኢትዮጵያ ላይ የተከፈቱ ወቅታዊ ሴራዎችን ለመቀልበስ ዓለም እውነቱን እንዲረዳ ድምጻቸውን በማሰማት ታላቅ ገድልን ፈፅመዋል::
‹‹ከኢትዮጵያ ላይ እጃችሁን አንሱ፣ ኢትዮጵያ የራሷን ችግር በራሷ መፍታት ትችላለች፣ የመረጥነውን መንግሥት መቀየር የምንችለው እኛው ራሳችን ኢትዮጵያውያን ነን፣ ችግራችንን ለራሳችን ተውሉን፤ የሚሉ ተቃውሞዎችን አሰምቷል::
በኢትዮጵያ ላይ የምታሳርፉትን ያልተገባ ጫና አቁሙ ብሏል:: በዚህ መልኩ በተካሄዱ ሰፊ የዲያስፖራ ንቅናቄዎችም አንዳንድ አገራትም ሆነ የፀጥታው ምክር ቤቱ የፈለጉት ኢትዮጵያ ምድር ላይ እንዳያሳካ ሆኗል::
በመደበኛ ዲፕሎማሲ መንግሥት ያከናወናቸውን ተግባራት ከዲያስፖራው ሚና ጋር መደመርም ለተገኘው ውጤት ሁነኛ ምክንያት ሆኖ የሚነሳ ነው:: በመንግሥት ከአገራት ጋር በተደረገ ውይይትና ግንኙነት በተለይ የቻይና እና ሩሲያ መንግሥታት ድምፅን በድምፅ በመሻር መብታቸውን በመጠቀም በኢትዮጵያ ላይ የታቀደው ሴራ እንዲከሽፍና ጫና እንዳይፈጠር ትልቅ እገዛ አድርጓል:: በውጤቱም ዲያስፖራው እንዳለው ኢትዮጵያ እንደ ትላንት ሁሉ ዛሬም የውስጥ ችግሯን በራሷ አቅም መፍታት እንደምትችል በግልጽ ታይቷል:: አዲስ አበባ ተከባለች ፣ኢትዮጵያ ልትፈርስ ነው የሚሉ ድምፆች በሙሉ ሐሰት መሆናቸው ተረጋግጧል::
ከዳር እዳር እጅ ለእጅ ተያይዘን በመሥራታችን ፣ በኢትዮጵያ ላይ ተደቅነው የነበሩ አደጋዎችን ሁሉ መቀልበስ ተችሏል:: ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረኮች ለመወከል የአገሩን መብትና ጥቅም ከመከላከል ባለፈ በአገር ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ጫናዎችን ማቃለል የሚችሉ ሬሚታንስ በመላክ በጎ አድራጎት ሥራዎች ላይ በመሳተፍ እያደረገ ያላቸው በርካታ ተግባራት አሉ::
ከፐብሊክ ዲፕሎማሲ ባሻገር ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው የዲያስፖራ አበርክቶዎችም ግዙፍና በርካታ ናቸው:: አንደኛው መገለጫው ውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሚልኩት ገንዘብ ወይንም (ሬሚታንስ) ነው::
የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ባለፈው ዓመት 3 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ወደ አገር ቤት ልኳል:: በዚህ ዓመት ባለፉት አምስት ወራት ከ 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወደ አገር ቤት ልኳል:: ይህ ገንዘብ በጣም ከፍተኛ መጠን ያለው ነው:: ዲያስፖራው በየዓመቱ ወደ አገር ቤት የሚልከው ገንዘብ፣ ኢትዮጵያ ከውጭ ምንዛሪ ከምታገኘው ገቢ ከፍተኛ ቦታ የሚወስድ ነው:: ከዚህ ባሻገር ዲያስፖራው አገር ውስጥ በከፈታቸው የባንክ ሂሳብ ቁጥሮች አማካኝነት የውጭ ምንዛሪ ተቀማጭ ያደርጋል::
በዚህም ባለፉት ስድስት ወር ብቻ ከአንድ ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ዶላር በላይ ተቀማጭ አድርጋል:: አካውንት በመክፈት ወይንም ሬሚታንስ በመላክ ብቻ ሳይሆን በኢንቨስትመንት ላይ ሰፊ ተሳትፎ እያደረገ ይገኛል:: ያለፈውን ዓመት ብቻ ብንመለከት 84 የሚሆኑ የዲያስፖራ ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ ገብተዋል::
እነዚህ የዲያስፖራ ፕሮጀክቶችም ከ10 ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥረዋል:: ከዚህ በተጨማሪ ዲያስፖራው በበጎ አድራጎቶች ሥራ ላይ በስፋት እየተሳተፈ ይገኛል:: ተሳትፎውም እጅግ በጣም የሚበረታታና ከዚህ ቀደም አይተነው የማናውቀው ነው:: በተለይ ከሕግ ማስከበር ዘመቻው በኋላ የዲያስፖራው ተሳትፎ እጅግ አስደናቂ እየሆነ መጥቷል::
ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ለመከላከያ ሠራዊት፣ ለተፈናቀሉ ወገኖች ለመደገፍና የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ልዩ ልዩ ድጋፍ አድርጓል:: ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ያደረገው ድጋፍ ብንመለከት ከግጭቱ በኋላ እንኳን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ነው::
ይህ ሁሉ የሚነግረን ዲያስፖራው በአሁን ወቅት ተጨባጭ የሆነ አገራዊ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ነው::ከለውጡ በፊት ዲያስፖራው በዋነኝነት ተቃውሞ ሲያሰማ የነበረው የሚፈልገው ዓይነት አገረ መንግሥት እየተገነባ አይደለም ብሎ ስላመነ ነው::
በአሁን ወቅት ለውጡን እየደገፈ ያለው ደግሞ የሚፈልገው አገረ መንግሥት እውን እየሆነ መምጣቱን በመረዳቱ ነው:: የለውጡ መንግሥት ኢትዮጵያን ትልቅ ለማድረግ በጋራ ክንድ መተጋገዝና መሥራት አለብን የሚል እሳቤና መልእክት ማጋራቱና ይህ እሳቤም ዲያስፖራውም ቀደም ባሉት ዓመታት ሲያስተጋባው የነበረ በመሆኑ በአሁን ወቅት በዲያስፖራውና በአገር መካከል ከመቼም ጊዜ በተለየ መቀራረብ የባለቤትነት ስሜት እንዲዳብር ሆኗል::
ዲያስፖራው በአሁን ወቅት በጋራ መቆም ከጉዳት እንደሚከላከል ተገንዝቧል:: በአገር ጉዳይ በጋራ መቆም እንዳለበት በእጅጉ ተምሯል:: በመሰብሰብና በመደመር ማሸነፍ እንደሚቻል ዲያስፖራው በተግባር እያስመሰከረ ይገኛል::
አዲስ ዘመን:- የዲያስፖራውን መብት ጥቅም በማስከበር ረገድ ምን እየተሠራ ነው?
አቶ ወንድወሰን:- የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ በዲያስፖራውና በአገር ቤት መካከል ድልድይ ሆኖ የማገልገል ኃላፊነት ተሰጥቶታል:: ከተቋቋመ ከሦስት ዓመት በላይ ያስቆጠረው ኤጀንሲው፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀትም የኢትዮጵያን የዲያስፖራ ፖሊሲና የኢትዮጵያ ዲያስፖራዎችን መብትና ጥቅም የማስጠበቅ ኃላፊነትም አለበት::
ኤጀንሲው ከተሰጡት ኃላፊነቶች አንደኛ እና ዋነኛው ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበርና በመመካከር የዲያስፖራውን መብት ጥቅም ማስከበር ነው:: ከዲያስፖራው መብት ጋር በተገናኘ በርካታ ጉዳዮች አሉ::
አብዛኛውን ጊዜ የዲያስፖራው መብት ጉዳዮች የሚነሱት መካከለኛው ምስራቅና አፍሪካ ላይ ነው::
ኤጀንሲውም በዚህ ጉዳይ ልዩ ትኩረት በመስጠት የዲያስፖራውን መብት እና ጥቅም የሚያስከብር አንድ ዲፓርትመንት አዋቅሯል:: በዚህም ለአብነት በሰው አገር በእስር ላይ የነበሩ ዜጎች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የማድረግ ሥራ ይሠራል::
በቅርቡም ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ ከ40 ሺ በላይ ዜጎች ወደ አገር ቤት እንዲመለሱ ተደርጓል:: በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ተለያዩ አገራት የገቡ ዜጎች ወደ ቤታቸው እንዲመለሱም እየተደረገ ነው:: ወደ አገር ቤት ከመመለስ ባሻገርም በሚኖሩበት አገር መብትና ጥቅማቸው ተከብሮ አስፈላጊው እንክብካቤ እንዲደረግላቸውና ሰብዓዊ መብታቸው እንዲከበር በማድረግ ረገድ ኤጀንሲያችን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ከሌሎችም የሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ጋር እየሠራ ነው:: አሁን ባለው ወቅታዊ የኢትዮጵያ ሁኔታና ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ሁኔታዎች አመቺ ባይሆኑም በችግር ውስጥ የሚገኙ ዜጎች በተወሰነ ቁጥርም ቢሆን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ እየተደረገ ይገኛል::
ከዚህ ባሻገር ሁኔታዎች እስኪመቻቹም በያሉበት አገር መብትና ጥቅማቸው ተከብሮ አስፈላጊ እንክብካቤ እንዲደረግላቸውና ሰብዓዊ መብታቸው እንዲከበርም ከሚመለከታቸው ጋር በቅርበት እየተሰራ ነው:: ይህም መንግሥት ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው::
አዲስ ዘመን:- ጥቁር ገበያ ኢትዮጵያ ከዲያስፖራው ማግኘት የሚገባትን የውጭ ምንዛሪ በማሳጣት ረገድ ምን ያህል ጫና አሳድሯል? ችግሩ በአሁን ወቅት ምን አይነት ቁመና ላይ ይገኛል?
አቶ ወንድወሰን:- መረጃዎች እንደሚያመላክቱት ወደ ኢትዮጵያ በመደበኛ መልክ እየገባ ያለው ገንዘብ ዝቅተኛ ነው:: ከአንድ ሶስተኛው የማይበልጥ ነው:: የዚህ አንደኛ እና ዋነኛ ምክንያት ጥቁር ገበያ ወይንም ብላክ ማርኬት ነው::
ኢትዮጵያ ችግሩን መከላከልና ማስቆም ባለመቻሏ ካላት የዲያስፖራ አቅሟ አንፃር ማግኘት የሚገባትን እያገኘች አይደለም::
በአሁን ወቅት እያገኘች ያለችው የውጭ ምንዛሪም የግብፅና የናይጄሪያ ገቢ አንፃር አንድ አራተኛ እንኳን አይሞላም:: ኢትዮጵያ ችግሩን ማስቆም ብትችል ግን ከባለፈው ዓመት ከተገኘው ማለትም ሶስት ነጥብ ስድስት ቢሊየን ዶላር ድርሻ አንፃር ሂሳቡ ቢሰራ እስከ 12 ቢሊዮን ዶላር ማግኘት ይቻላታል:: ችግሩ በተለያዩ መድረኮች ላይ ሁሌም ይነሳል::
ይሁንና መፍትሄ በመስጠት ረገድ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ማከናወን ይጠይቃል:: የአጭርና የረጅም ጊዜ መፍትሔ ማስቀመጥም የግድ ይላል:: ከአጭር ጊዜ አንፃር ዲያስፖራውም ሆነ ባንኮች የሚወስዷቸው አማራጮች አሉ::
በርካታ አገራት የተቀየሩትና ለእድገት የበቁት ዲያስፖራዎቻቸው በከፈሉት ዋጋ ነው:: በመሆኑም ዲያስፖራው በተለይ በአሁን ወቅት ዋጋ በመክፈል ገበያው እስኪረጋጋ ልዩነቱን በመተው በባለቤትነት፣ በኃላፊነት፣ ዋጋ በመክፈልና ለአገሬ ነው የማደርገው በሚል ስሜት በመደበኛው መንገድ ብቻ መቀጠል ይኖርበታል::
የፋይናንስ ተቋማት ደግሞ በአነስተኛ የአገልግሎት ክፍያ አማራጭ የገንዘብ ማስተላለፊያ መንገዶችን በተለይም በኤሌክትሮኒክስ ዘዴዎች ተግባራዊ ማድረግ እንዲችሉ ሰፊ ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው::
ይሁንና ተጨማሪ አማራጮች ይበልጡን መተዋወቅ አለባቸው:: ከዚህ በተጓዳኝ ዲያስፖራው ገንዘብ በሚልክበት ወቅት የመላኪያው ወጪ ባንኮች የሚጋሩበትን ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል:: ከዚህ በተጓዳኝ በመደበኛ መልኩ የሚልኩ ዲያስፖራዎችን ማበረታታት ያስፈልጋል:: ሽልማት መስጠትና የእውቅና መርሐ ግብሮችን ማዘጋጀት የግድ ይላል:: ይህን በማድረግ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ይቻላል::
ከረጅም ጊዜ መፍትሔነት አንፃር የምንዛሪ ተመንን አንድ በማድረግ ጥቁር እና ነጭ የሚባል ነገር ማጥፋት ነው:: ይህ ግን ከአገር ኢኮኖሚ ጋር የሚቆራኝ እንደመሆኑ የራሱን ጊዜ የሚወስድ ይሆናል:: አዲስ ዘመን:-መጪውን የገና እና የጥምቀት በዓል በመንተራስ ለዲያስፖራው የተዘጋጁ መርሐ ግብሮች ወይም ፓኬጆች ይኖሩ ይሆን፣ ምንስ አበርክቶ ይኖራቸዋል?
አቶ ወንደወሰን:-በተለያዩ ተቋማት ዲያስፖራውን ማገልገል የሚያስችሉ የተለያዩ ፓኬጆች እያስተዋወቁ ነው:: ዲያስፖራው በተለያዩ መስተጋብሮች ተሳታፊ ሲሆን ከኤርፖርት አንስቶ በየሂደቱ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር በተለይ የውጭ ምንዛሪ በቀላሉ ማግኘት እንዲችል ከባንኮች ጋር በመቀናጀት የተለያዩ ሥራዎች ተከናውነዋል::
ዲያስፖራው የሚሳተፍባቸው የተለያዩ መስተጋብሮችም ተመቻችተዋል:: ገናን በላሊበላ እና ጥምቀትን በጎንደር ከግዙፍ መርሐ ግብሮቹ መካከል ተቀዳሚ ተጠቃሽ ናቸው:: እነዚህ በዓላትና አካባቢዎችም ከፍተኛ የቱሪስት መስህብ ያለባቸው ናቸው:: ሁነቶቹም ዲያስፖራው ገንዘቡን ፈሰስ በማድረግ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዋልታ የሚሆንበትን አጋጣሚ የሚፈጥሩ ይሆናል::
አዲስ ዘመን:- በኢትዮጵያ የዲያስፖራውን በተለይ የኢንቨስመንት ሁለንተናዊ አቅም በመጠቀም ምቹ ከባቢን በመፍጠር ረገድ ቀደም ባሉት ዓመታት የአስፈፃሚ አካላት ድክመት ጎልቶ ሲነሳ ቆይቷል፣ ከዚህ በኋላ ይህን ታሪክ በመቀየር ረገድ ምን ሊደረግ ይገባል ይላሉ?
አቶ ወንድወሰን:- ኢትዮጵያ በአሁን ወቅት የንግድ ሥራ ምቹነት ከባቢያዊ ሁኔታን በማሻሻል‹‹ኢዝ ኦፍ ዱዊንግ ቢዝነስ ››እየተገበረች ትገኛለች:: በዚህ አሠራር ደግሞ አንድ ሰው ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት እስካለውና ማሟላት የሚገባውም መስፈርት እስካሟላ ድረስ እንቅፋት ሊኖርበት አይገባም::
የዓለም ታሪክ እንደሚያሳየን ለአብነት የቻይናን ተሞክሮ ብንወስድ በአገራቸው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ላይ ያላቸው ተሳትፎ እጅግ በጣም ከፍተኛ ነው:: በተለይ አገራቸው አስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ በነበረችባቸው ጊዜያት እስከ 80 በመቶ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ተሳትፎ እንደነበራቸው መረጃዎች ያመላክታሉ:: በኢትዮጵያም ዲያስፖራውን በመጠቀም ረገድ ከተሰራበት ዘርፈ ብዙ እምቅ አቅም አለ:: ከዚህም በላይ ማድረግ ይችላል:: በአሁን ወቅት በርካታ ዲያስፖራዎች ወደ አገር ቤት እየገቡ ናቸው::
ከእነዚህ ውስጥም በተለያዩ ዘርፎች የመሰማራት ፍላጎት ያላቸው በርካቶች ናቸው:: በርካታ ዲያስፖራዎች ወደ አገራቸው በሚመጡበት በዚህ ወቅት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ከወትሮው በተለየ ተገቢውን ክብካቤና ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ዲያስፖራው አጋር እንዲሆን መሥራት ይጠበቅባቸዋል:: አገልግሎት አሰጣጣቸውን ይበልጥ ማቀላጠፍ ይጠበቅባቸዋል:: ከዓመታት አስቀድሞ ቻይን እንደነበረችበት ሁሉ በአሁን ወቅትም ኢትዮጵያ ጫና ውስጥ ትገኛለች:: የኢትዮጵያ ዲያስፖራዎችም በሁሉ ረገድ ከአገራቸው ጎን ቆመው እየታዩ ናቸው:: የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ታዲያ ይህን የዲያስፖራ ፍላጎትና ተነሳሽነት ይበልጥ ሊጠቀሙበት የግድ ይላል:: ዲያስፖራው ለሚጠብቀው ምላሽና ለሚፈልገውም ምቹ አማራጭና ከባቢን ሊፈጥሩለት ይገባል::
የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲም በዚህ ረገድ በተለይም ዲያስፖራው ኢንቨስት ለማድረግ በሚፈልግበት ጊዜ እንቅፋቶች ሳይገጥሙት፣ በተቀላጠፈ መልኩ አገልግሎት እንዲያገኝ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የተለያዩ ተግባራት እያከናወነ ይገኛል:: ለዲያስፖራው ምቹ የኢንቨስትመት የተሳትፎ በሮች እንዲከፈቱለት እየሠራ ነው:: በአገር ውስጥ ከሃያ በላይ ባለድርሻ አካላት ጋር ይሠራል::
በክልል ደረጃም የዲያስፖራ ማስተባበሪያ ቅርንጫፎችና ጽሕፈት ቤቶች አሉ:: ዋነኛ ሥራቸውም ዲያስፖራውን በሚመለከት ኤጀንሲው የሚሠራቸውን ሥራዎች በመረከብ ምቹ ከባቢን መፍጠር ነው::
ኤጀንሲው ከባለድርሻ አካላቱ ጋር በየጊዜው የሥራ ግምገማ ያደርጋል:: ወቅታዊ የኢንቨስትመንት አማራጮችን በማስተዋወቅ ረገድም የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ናቸው::
በቅርቡም አንድ ሲምፖዚየም ይኖራል:: የኢንቨስትመንት ፎረም ነው:: የሚካሄደው ደግሞ ጥር 3 ቀን ነው:: አዘጋጁም የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ነው:: በዚህ መድረክም በኤጀንሲም ሆነ በሌሎች ባለድርሻ አካላት ኢትዮጵያ ውስጥ ምን አይነት አቅምና አማራጭ አለ የሚለው ይተዋወቃል:: በርካታ ዲያስፖራዎች የሚገኙበት እንደመሆኑም አጋጣሚው በጣም ጥሩ የሚባል ነው::
ይሁንና ዲያስፖራው ገንዘቡን፣ዕውቀቱንና ልምዱን አቀናጅቶ አገሩን የሚደግፍበት መደላድል እንዲፈጠር፣ መንግሥትን ጨምሮ የተለያዩ አካላት ጥረቶቻቸውን ይበልጥ ማስተባበር ይጠበቅባቸዋል:: ከተለመደው ጉዞ በተለየ፣ ወደፊት ኢትዮጵያ ውስጥ መሠረቱ የማይነቃነቅ አሻራ እንዲያሳርፉ ማድረግ ይገባል:: ዘመኑ ከደረሰበት ሥልጣኔ እኩል ለመራመድ የሚያስችላቸው አቅምና ክህሎት በመገንባት፣ የተቀላጠፈ አገልግሎት መስጠት የግድ ይላቸዋል::
አዲስ ዘመን:- ለሰጡን ሃሳብ ከልብ እናመሰግናለሁ፤
አቶ ወንድወሰን:- እኔም አመሰግናለሁ::
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 28/2014