የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከዚህ ቀደም ከነበረበት አካሄድ በተሻለ መልኩ እየተጓዘ እንደሚገኝ ተገለፀ።
ፌዴሬሽኑ 13ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በአርባ ምንጭ ከተማ ሲያካሂድ የ2013ዓ.ም የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርቱን ያቀረበ ሲሆን፣ በቀረበው ሪፖርት ላይ አስተያየት የሰጡት የጉባኤው አባላትም ፌዴሬሽኑ ከዚህ ቀደም ይወቀስባቸው የነበሩ ጉዳዮች ላይ ለውጥ በማሳየት የተሻለ ሥራ እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ፌዴሬሽኑ ባለፈው ዓመት በታዳጊና ወጣት እግር ኳስ ልማት ዙሪያ በተለያዩ የዕድሜ ገደቦች በርካታ ስራዎች ማከናወኑ በማሳያነት የተጠቀሰ ሲሆን፣ በዚህም መሰረት ከ15 ዓመት በታች የስልጠና መርሃ ግብር 10 ጣቢያዎችን በመክፈት ለ600 ታዳጊዎች ስልጠና እንዲያገኙ ተደርጓል።
ከ17ዓመት በታች የተለያዩ ብሄራዊ ቡድን ውድድሮችን በማካሄድ በርካታ ታዳጊዎች ለብሄራዊ ቡድን እንዲመለመሉ አስችሏል።
ከእስራኤል 17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ጋርም አብሮ በመስራት ልምድ ልውውጥ ማድረጉ እንደጥንካሬ ተነስቷል። ፌዴሬሽኑ በክለብ ላይሰንሲንግና በመተዳደሪያ ደንብ ማሻሻያዎች ላይ እየተሰራ የሚገኝ ሲሆን፤ ፊፋ ባስቀመጠው አቅጣጫ እና በባለሙያ እገዛ መሰረት ማሻሻያው እየተደረገ ይገኛል።
ከስፖርት ባለሙያዎች ልማት ጋር በተያያዘም 50 የውድድር ዳኞች፣ 21 ኢንተርናሽናል ዳኞችና 13 ኤሊት ዳኞችን በዓመቱ ማፍራት ተችሏል። ከዚሁ ጎን ለጎንም የአቅም ማጎልመሻና የአካል ብቃት ምዘና ሰጥቷል።
ካፍ ላለፉት ስድስት ዓመታት አግዶት የቆየው የአሰልጣኝነት ስልጠና ለማስቀጠል ኮንቬንሽን በማዘጋጀቱ ኢትዮጵያም ይህንኑ ተፈራርማ ስልጠናውን ጀምራለች። የ‹‹ኤ›› እና ‹‹ቢ›› ላይሰንሲንግ ስልጠናውም አስፈላጊው ግብዓት ሲሟላ የሚጀመር እንደሚሆን ታውቋል።
ፌዴሬሽኑ ውድድሮችን በሚመለከትም ባዘጋጀው የኮቪድ 19 ፕሮቶኮል መሰረት ሰባት ውድድሮችን በአስቸጋሪ ወቅት ውስጥ ሆኖ ሲያካሂድ ቆይቷል። በዓለም አቀፍ ተሳትፎም የኢትዮጵያ ወንዶች ብሄራዊ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፉ እንደስኬት የሚነሳ መሆኑ ተገልፃል።
ከዚህ ጎን ለጎን ፌዴሬሽኑ ከተለመደው ውጪ በአገር ውስጥና በውጭ አገራት በርካታ የወዳጅነት ጨዋታዎችን አዘጋጅቷል። በዓመቱ ከ15 እና 17 ዓመት በታች ቡድኖች ውጪ ሁሉም ብሄራዊ ቡድኖች በተለያዩ ውድድሮች ተሳትፈዋል።
ለ11 ዓመታት ያለ ስራ ተቀምጦ የቆየውን የካፍ የልህቀት ማዕከልን ከተቋሙ ጋር በመነጋገር የወረቀት ስራዎች ባይጠናቀቁም አገልግሎት ላይ ማዋል ተችሏል። በዚህም የብሄራዊ ቡድኖች ማረፊያ መደረጉ ከፍተኛ ወጪን ቀንሷል።
ከገንዘብ ጋር በተያያዘም በዓመቱ ከፊፋ፣ ከካፍ፣ ከመንግሥት እንዲሁም ከሌሎች ገቢዎች 124 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ሲገኝ 121 ሚሊየን ወጪ አዲስ ዘመን ስረቡዕ ፖርት ይህ ቦታ ለማስታወቂያ ክፍት ነው! በማድረግ 3 ሚሊየን ብር ትርፍ ተገኝቷል።
ፌዴሬሽኑ በከፍተኛ ሁኔታ ከሚታማባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ የባለሙያዎች እጥረት ነው፤ ነገር ግን በርካታ ባለሙያዎችን ከመቅጠር ባለፈ እንደ ህክምና ያሉ ክፍሎችን ለመጀመሪያ ጊዜ አደራጅቷል።
የስልጠና ቡድኖችንም በተለያዩ ባለሙያዎች ያሰባጠረ ሲሆን፤ የስነ ልቦና፣ የአካል ብቃት እና የጨዋታ ተንታኝ (በተንቀሳቃሽ ምስል) ማሟላት ችሏል። የፌዴሬሽኑን የገንዘብ አቅም ከማጠናከር አኳያ በዓመት ከሁለት ተቋማት (አንዱ የህክምና ተቋም)ጋር አብሮ ለመስራት ተፈራርሟል።
ፌዴሬሽኑ በተለይ በዓመቱ እንደ ውስንነት ካነሳቸው ጉዳዮች መካከል ዋነኛው የክለቦች አስተዳደራዊ ሁኔታ ውስንነትና የደመወዝ አከፋፈልን ነው።
ሌላው ፌዴሬሽኑ በስሩ ስምንት ብሄራዊ ቡድኖች ያሉት ሲሆን ፤ የሁሉንም ወጪ መሸፈኑን ነው። ስፖንሰሮች የወንዶች ብሄራዊ ቡድንን (ዋሊያዎቹን) የሚመርጡ መሆኑ ጫና ያሳደረበት መሆኑም ተጠቁሟል።
የስታዲየሞች በካፍ መታገድ እንዲሁም በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ደጋፊ ወደ ስታዲየም እንዳይገባ መደረጉም ገቢውን በመቀነስ በኩል እንደ ክፍተት ሊነሳ የሚችል ጉዳይ መሆኑም ተገልጿል።
ሪፖርቱ ከተደመጠ በኋላ አስተያየታቸውን ያንጸባረቁት የጠቅላላ ጉባኤው አባላትም፤ ፌዴሬሽኑ በርካታ አዳዲስና አበረታች የሚባሉ ስራዎችን እንዳከናወነ ጠቁመዋል። ይሁንና አሁንም ፌዴሬሽኑ በተቋም ደረጃ ራሱን ችሎ እንዲቆም አዳዲስ ስልቶችን ሊከተል እንደሚገባ ተጠቁሟል።
ከዚህ ጎን ለጎን ግን የክለብ አደረጃጀትን በሚመለከት ከፍተኛ ሥራ ማከናወን እንደሚጠበቅበት ተመላክቷል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 27/2014