የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ በተጓደሉ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ስፍራ ተተኪዎችን ሾሟል::
በዚህም መሰረት አቶ አበበ ገላጋይን ምክትል ሥራ አስፈጻሚ አድርጎ ሲሾም ወይዘሮ ሶፊያ አልማሙን ደግሞ ወደ ስራቸው እንዲመለሱ አድርጓል::
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን 13ኛ መደበኛ ጉባኤውን በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት በአርባ ምንጭ ከተማ አካሂዷል:: በጉባኤው ላይም በተለያዩ ምክንያቶች የተጓደሉ ሥራ አስፈጻሚ ቦታዎች ላይ የሚሰሩ የኮሚቴ አባላትን ሹመት አጽድቀዋል::
ከተጓደሉት አባላቱ መካከል የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንት ሲሆን፤ ኮሎኔል አወል አብዱራሂም ከወቅታዊው የአገሪቷ ሁኔታ ጋር ተያይዞ ላለፈው አንድ አመት እንደሌሎች ሥራ አስፈጻሚዎች በሥራ ላይ እንዳልነበሩ ተጠቁሟል::
በመሆኑም ፌዴሬሽኑ የመተዳደሪያ ደንቡን መሰረት አድርጎ በምትካቸው ሌላ ባለሙያ እንዲተኩ ለጠቅላላ ጉባኤው አቅርቧል:: በዚህም መሰረት ሥራ አስፈጻሚው ተወያይቶ ባቀረበው ፕሮፖዛል መሰረት አቶ አበበ ገላጋይ እንዲመረጡ ጥቆማ ሰጥቷል::
የጉባኤው አባላትም ግለሰቡ ለበርካታ ዓመታት በሥራ አስፈጻሚነት ሲያገለግሉ በመቆየታቸው በተቀረው ጊዜም ምክትል ፕሬዚዳንት እንዲሆኑ የቀረበውን ሃሳብ እንደሚደግፉ ሃሳባቸውን አንጸባርቀዋል:: ይህንንም ጉባኤተኛው በሙሉ ድምጽ አጽድቋል::
አቶ አበበ ገላጋይ ፌዴሬሽኑን በሥራ አስፈጻሚነት በመምራት ለረጅም ጊዜ የቆዩ ባለሙያ ሲሆኑ፤ በዚህ ወቅትም በካሜሮን የሚገኘውን የአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊ የሆነውን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በቡድን መሪነት እየመሩ መሆኑ ይታወቃል:: ሌላው ከሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ውጪ የቆዩት ወይዘሮ ሶፊያ አልማሙን እግዳቸው ተነስቶ ወደ ስራቸው እንዲመለሱ ተደርገዋል::
ከኮሚቴ አባልነታቸው ባሻገር የሴቶች ሊግ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩት ወይዘሮ ሶፊያ፣ ከኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ምርጫ ጋር ተያይዞ እንዲታገዱ መደረጋቸው የሚታወስ ነው:: ወይዘሮ ሶፊያ የመምረጥ ተቋማዊ ውክልና ከሥራ አስፈጻሚው ሳይሰጣቸው ከጽህፈት ቤቱ በወጣ ደብዳቤ በምርጫው ላይ ተካፍለው ድምጽ መስጠታቸው የእገዳቸው ምክንያት መሆኑን የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጂራ ለጠቅላላ ጉባኤው አስታውሰዋል::
አያይዘውም ግለሰቧ ይቅርታ ተደርጎላቸው ወደ ስራቸው እንዲመለሱ ጠቅላላ ጉባኤውን ጠይቀዋል:: በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን እንዲሰጡ የተደረገው ወይዘሮ ሶፊያ በበኩላቸው በተለይ በሴቶች ሊግ ሰብሳቢነታቸው በውድድሮች ላይ በርካታ መልካም ስራዎችን ሲያከናውኑ መቆየታቸውን አውስተው፣ ከስኬቶቻቸው መካከልም አንዱ ከ20 ዓመት በታች የሴካፋ አሸናፊ የሆነውን የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን እንደሆነ አሳውቀዋል::
በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ምርጫ ላይ የተገኙትም በፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ተወክለውና ዕውቅና ተሰጥቷቸው መሆኑን ገልጸዋል:: ቅጣቱ የማይገባቸው ቢሆንም እግር ኳስን ለመጉዳት እንዳላደረጉት እንዲታወቅላቸውም አስታውቀዋል:: ጠቅላላ ጉባኤውም በመድረኩ የቀረበውን ሃሳብ ተከትሎ በሰጠው ድምጽ መሰረት፤ ወይዘሮ ሶፊያ አልማሙን ሙሉ ድምጽ በማግኘት እገዳቸው ተነስቶ ወደ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነታቸው እንዲመለሱ ተደርጓል::
በፌዴሬሽኑ ካሉ ኮሚቴዎች መካከል ጉድለት በነበረበት ስፍራም ተተኪ ባለሙያ ተመርጠዋል:: ይኸውም የዲሲፕሊን ኮሚቴ ሰብሳቢ ሥራ ባዶ ሆኖ በመቆየቱ ፌዴሬሽኑ ባቀረበው ፕሮፖዛል መሰረት አቶ ዮሴፍ ካሳ በሙሉ ድምጽ ሊመረጡ ችለዋል:: ከአራት ዓመታት በፊት የተመረጠው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ኮሚቴ የሥራ ጊዜያቸውን ለማጠናቀቅ ስድስት ወራት ብቻ የሚቀሩት መሆኑ ይታወቃል::
በዚህም መሰረት በተጓደሉት ሥራ አስፈጻሚዎች ምትክ የተመረጡት አባላት ለወራት በሥራ ላይ ይቆያሉ:: በጉባኤው ማጠቃለያም ፌዴሬሽኑ በመጋቢት ወር /2014 ዓ.ም አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ የሚጠራ መሆኑን ሲያስታውቅ፤ የሥራ ዘመኑን በማጠናቀቅ ላይ በሚገኘው የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ምትክ ስለሚደረገው ምርጫ የሚወያይ መሆኑ ተጠቁሟል:: በመጪው ሰኔ ወር/2014 ዓ.ም ደግሞ ጠቅላላ ጉባኤው በጎንደር ከተማ ተካሂዶ አዳዲስ የፌዴሬሽኑ አመራሮች እንደሚመረጡ ይጠበቃል::
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 26/2014