የስፖርት ውርርድና አቋማሪዎች ወደ ኢትዮጵያ ከገቡ ወዲህ በጥቅሙና ጉዳቱ ላይ የተለያዩ ክርክሮች አሁንም ድረስ ይነሳሉ። የስፖርት ውርርድ በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የእግር ኳስ ደረጃቸው ዝቅተኛ በሆኑ አገራት ጥቅም እንዳለው ሁሉ ጉዳቱም የዚያኑ ያህል እንደሆነ ፍንጮች መታየት ጀምረዋል። የስፖርት ውርርድ በአጠቃላይ በአንድ ማህበረሰብ ላይ ከሚያደርሰው ጉዳት በዘለለ የአንድን አገር ስፖርት የሚጠቅምበት አጋጣሚ እንዳለ መካድ አይቻልም። ለምሳሌ ያህል ለዘመናት የስያሜ ስፖንሰር ኖሮት የማያውቀው የኢትዮጵያ ፕሪሚየርሊግ ስያሜውን ቤትኪንግ ለተባለው አቋማሪ ድርጅት ሸጦ ገንዘብ በማግኘት ሊጉም ሆነ ክለቦች በገንዘብ ተጠቃሚ ማድረጉን መካድ አይቻልም። በክለብ ደረጃም አቋማሪ ድርጅቶች ስፖንሰር በመሆን የፋይናንስ ችግሮቻቸውን መደገፍ ጀምረዋል። ይህ በሌሎች አገራትም የሚሰራበትና አቋማሪ ድርጅቶች ስፖርቱን ከገንዘብ አኳያ በመደገፍ የሚያበረክቱት አንድ ጥቅም ነው። ይሁን እንጂ የስፖርት ውርርድ ከማህበረሰቡ አልፎ በስፖርቱ ቀጥተኛ ተዋናዮች የሚከወን ከሆነ አደጋው የከፋ ነው። አቋማሪ ድርጅቶች ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡም የተፈራው ነገር ይህ ነበር። የተፈራውም አልቀረም የስፖርት ውርርድ ክፉ ጎን በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ላይ ተጽዕኖውን ማሳረፉ ከፍንጭ ባለፈ ተጨባጭ ጉዳት ማድረስ መጀመሩ እየታየ ነው።
ባለፈው ሳምንት ኢትዮጵያ ቡና ይሸነፋል ብሎ በማስያዙ ኢትዮጵያ ቡና የክለቡን ተጫዋች ናትናኤል በርሄን ማሰናበቱ ታውቋል። ኢትዮጵያ ቡና በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በሀዋሳ ከተማ በነበረው ቆይታ ካደረጋቸው ጨዋታዎች መካከል፤ ከአንዱ ጨዋታ አስቀድሞ በስፖርታዊ ውርርድ ኢትዮጵያ ቡና ይሸነፋል በማለት አንድ ተጫዋች መወራረዱ ታውቋል። ይህን ድርጊት ፈፅሟል የተባለው ተጫዋች ናትናኤል በርሄ ሲሆን በቡድን መሪውና አሰልጣኞቹ አማካኝነት ድርጊቱን ስለመፈፀሙ የሰነድ ማረጋገጫ ከመቅረቡ ባሻገር ራሱ ተጫዋቹ ሁኔታውን አምኖ የእምነት ቃሉን ሰጥቷል።
በዚህም መሠረት ክለቡ ካስቀመጠው የተጫዋቾች የሥነ-ምግባር መመርያ ውጭ እምነት አጉድሏል በማለት ቀሪ ኮንትራት እያለው ክለቡ ተጫዋቹን አሰናብቶታል። ከዚህ በተጨማሪም የኢትዮጵያ እግርኳስ የበላይ አካል በሆነው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን መመርያ መሠረት ድርጊቱ ለሁለት ዓመት ከማንኛውም እግረኳሳዊ እንቅስቃሴ የሚያሳግደው በመሆኑ ፌዴሬሽኑ ህጉን ተግባራዊ እንዲያደርግ ክለቡ በደብዳቤ መጠየቁ ታውቋል።
ኢትዮጵያ ቡና ይህን ጉዳይ ይፋ አደረገ እንጂ በተለያዩ ክለቦች መሰል ጉዳዮች ሊኖሩ እንደሚችሉ የበርካቶች እምነት ነው። ኢትዮጵያ ቡና ይህን ጉዳይ ይፋ ካደረገ በኋላ የሚወጡ ተመሳሳይ ወሬዎችም ችግሩ በበርካታ ክለብ ተጫዋቾች ስር ሳይሰድ እንዳልቀረ የሚያሳዩ ናቸው። አንድ አንድ ተጫዋቾች መኪናቸውን ጭምር እያስያዙ ይህን ቁማር ስራዬ ብለው መያያዛቸው እየተነገረ ነው። ይህ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ እዚህ ግባ የማይባል የእግር ኳስ ደረጃ ላላቸው አገራት ከስጋትም በዘለለ ለማደግ ዳዴ የሚለውን እግር ኳስ በአጭሩ ሊቀጭ የሚችል አደጋ መሆኑ አስደንጋጭ ነው።
ይህን ችግር የሚፈጥሩት ራሳቸው ተጫዋቾች እንጂ አቋማሪ ድርጅቶች የሚጠየቁበት አግባብ ሊኖር አይችልም። የየትኛውም ክለብ ተጫዋቾች ከዚህ ድርጊት ራሳቸውን ማራቅ ካልቻሉ ከራሳቸው አልፈው ክለባቸውን፣ ከዚያም አገርን ሊጎዱ እንደሚችሉ ማወቅ አለባቸው። የተጫዋቾች መሰል ድርጊት ከራሳቸው አልፎ ጉዳቱ የት ድረስ እንደሚዘልቅ አንድ ቀላል ምሳሌ ማንሳት ተገቢ ነው። ለአብነት ያህል ኢትዮጵያ ቡና ያሰናበተው ተጫዋች በመቆመሩ ምክንያት ካገኘው ነገር ያጣውና ወደ ፊት የሚያጣው ነገር ተዘርዝሮ አያልቅም። ተጫዋቹ ሆን ብሎ በመቆመሩ ምክንያት ክለቡን ውጤት አላሳጣም ተብሎ በየዋህነት ቢታሰብ እንኳን ከክለቡ በመሰናበቱ ራሱ ተጫዋቹም ክለቡም ተጎጂዎች ናቸው። በዚህ ወቅት ይህን ድርጊት የፈጸመውና የተሰናበተው የብሔራዊ ቡድን ወሳኝ ተጫዋች ቢሆንስ? አገር ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት ማሰብ ይቻላል።
በእንግሊዝ የፕሮፌሽናል ተጫዋቾች ፌዴሬሽን በዚህ ጉዳይ ከ350 የእግር ኳስና ክሪኬት ተጫዋቾች ላይ ያደረገውን የጥናት ግኝት ጠቅሶ ቢ.ቢ.ሲ በአንድ ወቅት የሰራው ዘገባ ላይ እንደሰፈረው፣ በስፖርቱ ቀጥተኛ ተሳታፊ ካልሆነው ማህበረሰብ በላይ ተጫዋቾች በሶስት እጥፍ የስፖርት ውርርድ ሱስ ውስጥ ይገባሉ። ከ170 ኳስ ተጫዋቾችም ስድስት በመቶ ያህሉ የዚህ ችግር ሰለባ መሆናቸውን ሲያምኑ በርካቶቹ የሚደርስባቸውን አደጋ በመስጋት ዝምታን እንደሚመርጡም የጥናቱ ግኝት ያስቀምጣል። በጥናቱ ቃለመጠይቅ ከተደረገላቸው አስር ስፖርተኞች አንዱ በጨዋታዎች ላይ ብቁ ሆኖ ለመገኘት እንደሚቆምር ሲናገር፣ ከአራቱ አንዱ በሌሎች የክለቡ ተጫዋቾች ወደ ውርርድ እንዲገባ መበረታታቱን ይናገራል። ከሶስቱ አንዱ ደግሞ ክለቦች ራሳቸው ከቁማሩ ኢንዱስትሪ ጋር ግንኙነት እንዳላቸውና ተጫዋቾችም ወደዚሁ እንዲገቡ እንደሚያበረታቷቸው ምላሽ ሰጥተዋል።
እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት ሊጎች፤ የተጫዋቾችና አሰልጣኞች እንዲሁም የክለቦች የፕሮፌሽናሊዝም ደረጃና አስተሳሰብ ይህ ችግር ገዝፎ እንጂ አንሶ እንደማይገኝ ጥናት ማድረግ ሳያስፈልግ መናገር ይቻላል። ስለዚህም ይህ ችግር የበለጠ ስር ሳይሰድ ፌዴሬሽኑም ይሁን ክለቦች ለተጫዋቾቻቸው አበረታች ንጥረነገር ተጠቃሚነትን ቀድሞ ለመከላከል እንደሚሰጡት የግንዛቤ ማስጨበጫና ትምህርት ሁሉ የስፖርት ውርርድ የሚያስከትለውን አደጋና ይዞ ከሚመጣው ጦስ ጋር በተያያዘ ሊያስቡበት እንደሚገባ ማስታወስ ያስፈልጋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 25 ቀን 2014 ዓ.ም