ኢትዮጵያ የአፍሪካ እግር ኳስ የመሰረት ድንጋይ ያኖረች አገር እንደመሆኗ መጠን የመድረኩን ጣፋጭ ድል ለአንድ ጊዜም ቢሆን መጎንጨት ችላለች። ኢትዮጵያ በወርቃማ የእግር ኳስ ዘመኗ የአፍሪካ ዋንጫን ከስድስት አስርት ዓመታት በፊት ማንሳት ስትችል አዲስ ዘመን ጋዜጣ ኢትዮጵያ አዘጋጅ አገር እንደመሆኗ መጠን ከመስተንግዶው ጀምሮ እስከ ዋንጫው ፍፃሜ ዘገባዎችን ለአንባብያን ሲያደርስ የነበረ ግንባር ቀደም የህትመት ውጤት ነበር። ጥር 6 ቀን 1954 የአፍሪካ ዋንጫ አስተናጋጇ ኢትዮጵያ የመክፈቻ ጨዋታውን ከቱኒዚያ ጋር ያደረገችውን ጨዋታ እውቁ የስፖርት ጋዜጠኛ ሰለሞን ተሰማ ጥር 9 ቀን 1954 ለአንባቢያን በበቃው አዲስ ዘመን ጋዜጣ የስፖርት አምድ ላይ ያቀረበው ዘገባ የሚከተለውን ይመስል ነበር።
«የሦስተኛው ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ የፉትቦል ውድድር ጥር 6 ቀን 1954 ዓ.ም ከቀትር በኋላ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ስታዲየም ላይ በኢትዮጵያና ቱኒዚያ ብሔራዊ ቡድን መካከል ተጀምሮ የኢትዮጵያ ቡድን 4ለ2 ማሸነፉን ከጨዋታው ስፍራ በመገኘትና በራዲዮን በመስማት ሴት ወንዱ፤ ልጆችና ሽማግሌዎች ተባብለው ሳይከፋፈሉ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ከልብ የተደሰተ በመሆኑ ሰሞኑን በመስሪያ፤ በመኖሪያ፤ በሆቴልና በቡና ቤቶች፤ በገበያና ንግድ ሱቆች፤ በሴይቼንቶና በአውቶብስ ውስጥ እንዲሁም በልዩ ልዩ አደባባዮች የሚወራው ወሬ አንዳችም ጣልቃ ሳይገባበት የኢትዮጵያን ቡድን አድናቆት የተመልካችን ሁኔታና ይኼንኑ የመሳሰሉ ወሬዎች ብቻ ናቸው »።
ሰለሞን የጨዋታውን መክፈቻ በእዚህ መልኩ ካካተተ ከቀናት በኋላ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በተመሳሳይ ውጤት ግብፅን በፍፃሜ ጨዋታ በመርታት እስካሁን የምንጠቅሰውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ትልቅ ስኬት ማስቀረት ችሏል። በወቅቱም አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጥር 15 ቀን 1954 ዓ.ም ባወጣው እትሙ የፊት ገፅ ላይ « ቀልጣፋው የኢትዮጵያ ምርጥ ቡድን የግብፅን ቡድን 4ለ2 አሸነፈ» በሚል ርፅስ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ለቡድኑ አምበል ሉቺያኖ ቫሳሎ የአፍሪካ ዋንጫውን ሲያበረክቱ የሚያሳይ ፎቶ ግራፍ ይዞ ወጥቷል።
የዘገባው መግቢያም የሚከተለውን ይመስል ነበር « ለ3ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የሚደረገው የእግር ኳስ ውድድር ጥር 13 ቀን 1954 ዓ.ም ባለፈው እሁድ ቁጥሩ ከ5o ሺህ የማያንስ ህዝብ በተሰበሰበበት በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ስታድዮም ተደርጎ ፤ የኢትዮጵያ ምርጥ ቡድን የግብፅን ብሔራዊ ቡድን 4ለ2 አሸንፎ የአፍሪካን ዋንጫ ወስዷል።
በሁለቱ አፍሪካዊ ቡድኖች መካከል የሚደረገውን ውድድር ለማየት በስታዲየሙ ውጭና ግቢ አሰፍስፎ ይጠብቅ የነበረው ተመልካች ታሪካዊ አቀባበል የሚመሳሰል ነበር። ውድድሩ ከመጀመሩ በፊት ግርማዊ ንጉሰ ነገስት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት መንግስት ወራሽ ልዑል መርዕድ አዝማችን፤ አስፋ ወሰንን፤ ልዑል ራስ እምሩንና ሌሎችንም የክብር ተከታዮቻቸውን አስከትለው በፖሊስ ሰራዊት ሞተር ብስክሌተኞች ታጅበው ከስታዲየም ደረሱ»።
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ከፍተኛ ንቅናቄን በፈጠረው የ2o13 የደቡብ አፍሪካ ዋንጫም አዲስ ዘመን ከዘመኑ ጋር ተጉዞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሰላሳ አንድ ዓመት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ሲመለስ በርካታ ጨዋታዎችን ተከታትሎ ዘገባዎችን ለአንባቢ አቅርቧል። በአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው እየተመራ ቤኒንን ከእዚያም ሱዳንን በመጨረሻ የማጣሪያ ጨዋታ በደርሶ መልስ ውጤት ዋልያዎቹ ድል አድርገው ወደ አፍሪካ ዋንጫ ሲመለሱ ጥቅምት 3 ቀን 2oo5 ዓ.ም ይዞት በወጣው እትሙ በፊት ገፁና በስፖርት ባለቀለም ገፁ የአሰልጣኞች፤ ተጫዋቾችና ደጋፊዎች ስሜትን የሚገልፁና በቃለ መጠይቅ የዳበሩ በርካታ ዘገባዎችን ማቅረብ ችሏል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 24/2014