ኢትዮጵያ ያለችበትን የሰላም ችግር ከግምት በማስገባት “ለኢትዮጵያ ሰላም እሮጣለሁ” በሚል መሪ ቃል የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር ነገ በቢሾፍቱ ከተማ ይካሄዳል። ውድድሩን ያዘጋጀው የኢትዮጵያ አትሌቶች ማህበር ትናንት በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መሰብሰቢያ አዳራሽ በሰጠው መግለጫ፣ ውድድሩ የተዘጋጀው በአገራችን የሚገኙ አትሌቶች ለሰላም የድርሻቸውን እንዲወጡ ለማድረግ መሆኑን ገልጿል። አትሌቲክስ ወዳዱን ማህበረሰብ በውድድሩ ላይ ተሳታፊ ማድረግም የውድድሩ አላማ መሆኑ ተጠቁሟል።
ማህበሩ ውድድሩን ያዘጋጀው ኢትዮጵያ ያቀረበችውን ጥሪ በመቀበል እንዲሁም የተከሰተውን ጦርነትና የሰላም እጦት ችግር ምክንያት በማድረግ መሆኑ ተገልጿል። ውድድሩ የህይወት መስዋዕትነት እየከፈለ ላለው የመከላከያ ሰራዊት እንዲሁም በጦርነቱ ሳቢያ ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ ለማድረግ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ አትሌቶች ማህበር ፕሬዚዳንት ኮማንደር አትሌት ማርቆስ ገነቴ በመግለጫው ላይ ተናግሯል።
“ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ታሪክ አትሌቶች ከ60 ዓመት በላይ ጀምሮ በአህጉርና በዓለም አደባባይ ኢትዮጵያን በማስተዋወቅ ላይ እንደሚገኙ ለሁላችንም ግልጽ ነው” ያለው ኮማንደር አትሌት ማርቆስ፣ በርካታ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተለያዩ ታላላቅ ውድድሮች ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ የአገራቸው ሰንደቅ አላማ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብና ብሔራዊ መዝሙሩ በክብር እንዲዘመር ከማድረጋቸው በላይ ኢትዮጵያ በዓለም ህዝብ ዘንድ በአሸናፊነት መንፈስ እንድትታወቅ የጎላ አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ አስታውሷል። የኢትዮጵያን በጎ ገጽታ በመገንባትም አትሌቶች ትልቅ ሚና እየተጫወቱ እንደሚገኙ ጠቁሟል።
ውድድሩን ለማካሄድ ቅድመ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ከተለያዩ የአገራችን ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች አትሌቶችና ሌሎች እንግዶች ተጋባዥ እንደሚሆኑ ታውቋል። በዚህም ከ15 ሺህ በላይ ህዝብ በውድድሩ ይሳተፋል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን በርካታ የማናጀርና የክለብ አትሌቶች እንዲሳተፉ ጥሪ ተደርጎላቸው ዝግጅት እያደረጉ እንደሚገኙ ኮማንደር አትሌት ማርቆስ አብራርቷል። መነሻውን በቢሾፍቱ ቱሪስት ሆቴል በሚያደርገው ውድድር ነባርና ታዋቂ አትሌቶች በስፍራው ተገኝተው የውድድሩ ድምቀት እንደሚሆኑ ተጠቁሟል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተሳትፎና ውድድር ዳይሬክተር አቶ አስፋው ዳኜ ውድድሩን በመምራት ሂደት ከ150 በላይ የሰው ሃይል ዝግጁ መሆኑን ጠቅሰው፣ የኢትዮጵያ አትሌቶች አገር ካለችበት ችግር አኳያ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማድረግ መወሰናቸውን ተናግረዋል። የአትሌቶች ማህበር ፕሬዚዳንቱ ኮማንደር አትሌት ማርቆስና ሌሎችም ግንባር ድረስ በመሄድ ለአገር አለኝታ መሆናቸውን በማስታወስም ምስጋና እንደሚገባቸው ገልጸዋል።
በውድድሩ የተለያየ ደረጃ ይዘው ለሚያጠናቅቁ አትሌቶች ከፍተኛ የገንዘብ ሽልማት መዘጋጀቱን የገለጹት አቶ አስፋው በሁለቱም ጾታ ከአንድ እስከ ስምንት ባለው ደረጃ የሚያጠናቅቁ አትሌቶች ከ 50ሺ እስከ 7 ሺ ብር ተሸላሚ እንደሚሆኑ አስረድተዋል። አንጋፋ አትሌቶች በሁለት የእድሜ ደረጃ ተከፍለው የሚወዳደሩ ሲሆን ከሃምሳ ዓመት በላይና በታች የሚወዳደሩ ይሆናል። ከአንድ እስከ ሶስት ባለው ደረጃ የሚያጠናቅቁም ከአራት እስከ ሁለት ሺ ብር ተሸላሚ እንደሚሆኑ ታውቋል። በአጠቃላይም 318 ሺ ብር ለሽልማት መዘጋጀቱ ተጠቁሟል።
የውድድሩ መሮጫ ቲሸርት በከፍተኛ ደረጃ እየተሸጠ እንደሚገኝ የተጠቆመ ሲሆን አትሌቶች ቲሸርቶችንና የመሮጫ ቁጥር ተመዝግበው እስካላገኙ ድረስ በውድድሩ አሸናፊ ቢሆኑም ውጤታቸው ዋጋ እንደማይኖረው አዘጋጆቹ አሳውቀዋል። ዛሬ የመሮጫ ቲሸርቱን በመግዛት በውድድሩ መሳተፍ ለሚፈልጉም ጉርድ ሾላ በሚገኘው የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ህንጻ፣ መገናኛ ደራርቱ ቱሉ ህንጻ ላይ በሚገኘው የአዲስ አበባ ከተማ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እንዲሁም በቢሾፍቱ ወጣቶችና ስፖርት ጽህፈት ቤት ማግኘት እንደሚቻል ተገልጿል።
ለውድድሩ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንና የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በገንዘብና የሰው ሃይል በማቅረብ ድጋፍ እንዳደረጉም ለማወቅ ተችሏል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 23/2014