አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በከፈተው ጦርነት ከሰው ሕይወት ባሻገር በንብረት ላይም ጉዳት ደርሷል። በተለይ በጤና ተቋማት ላይ ያደረሰው ጉዳት መጠነ ሰፊ እንደነበር ሁሉም የሚያውቀው ነው። ከጉዳቱም በላይ ወደ ትግራይ ተጭኖ የተወሰደው የሕክምና ቁሳቁስ ቀላል አልነበረም፡፡ ሕወሓት መከላከያ ሲደርስበትና ጭኖ ለመሄድ ሳያመቸው ሲቀርም ቢሆን ከተቋሙ ጋር በእሳት ያጋየው የህክምና መሳሪያ ብዙ ነበር፡፡ በዚህም የአማራና የአፋር ክልሎች ብዙ ዋጋ እንዲከፍሉ ሆነዋል፡፡
ክልሎቹ በአሸባሪው ኃይል ከደረሰባቸው ውድመት አንጻር ዕድገታቸውን ከ30 እስከ 40 ዓመታት ለሚፈጅ ጊዜ ሊጎትተው እንደሚችል በጥናት የተደገፉ መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡ ቡድኑ ለእኩይ ዓላማ ሲጠቀምባቸው የነበሩና ከሕዝብ የተዘረፉ ተቋሞችን ወደ ክልሎቹ በማዞር የክልሎቹን ዕድገት የሚጎትተውን ሂደት ለማሳጠር መሞከር አይነተኛ አማራጭ መሆኑን አንዳንድ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ሲጠቁሙም ይሰማል። ይሄ በጊዜ ሂደት መሆኑ ባይቀርም አሁን ላይ የጤና ተቋማቱን መልሶ ወደ ሥራ ለማስገባት መፍትሄ የሚሆነው የተጀመረውን እርስ በእርስ የመደጋገፍ ባህል ማጠናከር ነው።
ጉዳቱ መጠነ ሰፊ በመሆኑም፤ የግልም የመንግስትም ተቋማት የድጋፍ ርብርብ ቀጣይነት እንዲኖረው ማድረግ አስፈላጊ ነው። በቅርቡ የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደገለፁት፤ በአማራና በአፋር ክልሎች በጁንታው ምክንያት ከ2 ሺህ 500 በላይ የሚሆኑ ተቋማት ከጉዳት ባሻገር በቡድኑ ተዘርፈዋል፡፡ ከ1 ሺህ 500 በላይ የሚሆኑት የጤና ተቋማት ደግሞ እጅግ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡
አሸባሪ ቡድኑ ምሽጉን ሰሜን ኢትዮጵያ ውስጥ አድርጎ በሠላማዊ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ወረራ በማካሄድ፣ ጦርነት በመቀስቀስና በመክፈት በአማራ ክልል ብቻ በዘረፋና በጉዳት ምክንያት 20 ሆስፒታሎች እና 277 ጤና ጣቢያዎች አገልግሎታቸውን እንዲያቋርጡ ማድረጉንም ሚኒስትሯ በመግለጫቸው አመላክተዋል፡፡ አሁንም ከዚሁ ከአማራ ክልል ሳንወጣ 14 ሆስፒታሎች እንዲሁም 153 ጤና ጣቢያዎች በተጨማሪም 642 ጤና ኬላዎች ላይ ከፍተኛ ዘረፋ ተፈጽሟል ብለዋል። በአፋር ክልል ላይም ተመሳሳይ ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል፡፡
የአፋር ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ያሲን ሐቢብ በጉብኝቱ ወቅት እንደተናገሩት፤ ቡድኑ የጤና ተቋማትን ሙሉ በሙሉ አንኮታኩቷል። የጤና ተቋማቱን ግንባታ አፈራርሰዋል። በርና መስኮቶቻቸውን ሳይቀር ሰባብረዋል። መድኃኒትና የሕክምና መሳርያዎችንም ቢሆን እንዲሁ ዘርፎ ወስዷል። የቀረውንም ያቃጠለበትና አገልግሎት እንዳይሰጥበት አድርጓል፡፡ ጭፍራ፣ አደአር፣ ጉሊና፣ እዋ፣ አዉራ ወረዳዎች ደግሞ ጉዳቱ ከፍተኛ የሆነባቸው ቦታዎች ናቸው፡፡
አንድ ሆስፒታል፣ 17 የጤና ጣቢያዎች፣ 42 የጤና ኬላዎች ከአገልግሎት ውጭ በመሆናቸው የተነሳ እናቶች ልጆቻቸውን ዛፍ ሥር ለመውለድ ተገድደዋል ያሉት ኃላፊው፤ አንድ ሆስፒታል፣ 10 ጤና ጣቢያዎች እና 38 የጤና ኬላዎች ላይ የተፈፀመው ዘረፋና በተለይ ጉዳቱ በሦስት ከፍተኛ ተገልጋይ ባለባቸው ዞኖች የፈጠረው ክፍተት በቃላት ከሚገለፀው በላይ እንደሆነባቸውም አስረድተዋል።
የጦርነት ቀጠና በነበሩትና በአዋሳኝ አከባቢዎች በሚገኙት ጭፍራ ከተማ፣ በርሃሌ እና መጋሎ ወረዳዎች ላይ ያለው ችግር የባሰ እንደነበረም ጠቁመዋል። በጦርነቱ ምክንያት ተፈናቅለው በተለያዩ አካባቢዎች ለሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች ሕክምና በተለይም፤ ሲሰጥ የነበረውን የኮቪድ ክትባት እንኳን መሰጠት ሳይችል መቆየቱንም ጠቅሰዋል።
ሕብረተሰቡ የሕክምና አገልግሎት እንዳያገኝ በብዙ መንገድ መደረጉን ያስረዱት ኃላፊው፤ ይህ ሆኖም ክልሉ በሚደረግለት እገዛ መሻሻሎች እየታዩበት መሆኑን አስታውሰዋል፡፡ በተለይም በጤና ሚኒስቴር አስተባባሪነት እየተደረጉ ያሉ ድጋፎች የጤና ተቋማቱን መልሶ ወደ ሥራ የማስገባት ሥራ ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡ ለማሳያነትም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የጤና ሚኒስቴርና አምሪኤፍ ሄልዝ አፍሪካን አማካኝነት ባሳለፍነው ሳምንት የተደረገውን ድጋፍ አንስተዋል፡፡ ውድመትና ዘረፋ ለተፈፀመባቸው የጤና ተቋማት ከ8 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የሕክምና መሣሪያዎችና መድኃኒቶች ድጋፍ ብዙ ነገራቸውን እንደሚለውጠውም ተናግረዋል፡፡
‹‹አሸባሪው ቡድን በክልሉ በቆየባቸው ጊዜያት በጤና ተቋማት መሠረተ ልማቶች ላይ ውድመትና ዘረፋ በመፈፀሙ የሕክምና አገልግሎት ተቋርጦ ቆይቷል›› ያሉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ፤ የሕክምና አገልግሎቱን ለማስቀጠል የሚያስችለውን ድጋፍም አስረክበዋል። ከተማ አስተዳደሩ ድጋፉን ለክልሉ ጤና ተቋማት ያደረገው በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ሥር የሚገኙ ስድስቱን ሆስፒታሎች በማስተባበር መሆኑንም በመርሐ ግብሩ ላይ ገልጸዋል።
ዓላማው ተቋማቱ ወደ ሥራ በመመለስ ለሕብረተሰቡ የሚሰጡትን አገልግሎት እንዲቀጥሉ ማስቻል መሆኑንም ጠቁመዋል። ድጋፉን አሸባሪው ቡድን ጉዳት አድርሶባቸው ሥራ አቁመው ከነበሩ ጤና ተቋማት መካከል በማዋል የተወሰኑትን ሥራ ማስጀመር እንደሚያስችልም ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ከእነዚህ በክልሉ ከሚገኙ ጤና ተቋማት መካከል፤ ስድስቱን ጤና ጣቢያዎች በኃላፊነት ተረክቦ ዕድሳትና አስፈላጊውን ግብዓት በማሟላት ሥራ ለማስጀመር እየሰራ የሚገኝ መሆኑንም ከንቲባዋ አዳነች አቤቤ አብራርተዋል።
የሕክምና ግብዓቶቹን ያስረከቡት የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አየለ ተሾመ በመርሐ ግብሩ ላይ እንደተናገሩትም፤ አሸባሪው ቡድን ጤና ተቋማቱ አገልግሎት እንዳይሰጡ አድርጎ አውድሟቸዋል። አሁን ላይ ጤና ተቋማቱን በማደስና የሕክምና ግብዓቶችን በማሟላት ወደ ሥራ ለማስገባት በቂ ዝግጅት እየተደረገ ነው።
ተቋማቱን ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ለማስገባት በሚደረገው ርብርብ የሁሉም ማኅበረሰብና ባለድርሻ አካላት ድጋፍና አስተዋጽዖ ያስፈልጋል። ‹‹የሽብር ቡድኑ ባደረሰው ውድመትና ዘረፋ ሳንሸነፍ ጠንካራ የሆነ ሥራ አከናውነን የሕክምና አገልግሎቱን እናስጀምራለን›› በማለትም ሀሳባቸውን አሳርገዋል። እኛም አገርን መልሶ በመገንባቱ ዙሪያ የበኩላችንን ጠጠር ለመወርውር “ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” በጤና ተቋማት መልሶ ግንባታ ልንተገብረው ይገባል በማለት አበቃን፡፡ ሰላም!
ሠላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 23/2014