ብዙዎች በሕይወት ዘመናቸው ሊሆኑ የፈለጉትን ሳይሆኑ፤ የወደዱትን ማድረግ ሳይቻላቸው ይቀርና ምኞት ፍላጎቴ ይህ አልነበረም እንዲህ እሆናለሁ ብዬ አስቤም አላውቅም ወዘተ…ሲሉ ይደመጣል። በተቃራኒው ደግሞ ጥቂቶች በሕይወት ዘመናቸው ምኞታቸው ተሳክቶ የፍላጎታቸው ሞልቶ ሀሴት ሲያደርጉ ይስተዋላል። ይሁንና ብዙ ሰዎች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለውስጣዊው ስሜታቸው በማድላት ሀሳባቸው ሲሞላ እና በስኬታማነታቸው ሲደሰቱ ማየት የተለመደ ነው፡፡
ይህን ሀሳብ ያለምክንያት አላነሳነውም፤ የውስጥ ፍላጎቷን ለማሳካት ባላት አቅም ሁሉ ጥረት በማድረጓ ማንነቷን እንዳገኘች የተረዳች እንግዳ በማቅረባችን ነው። እንግዳችን ወይዘሮ አለምጸሐይ ሌሊሳ ትባላለች። የሽመና ሥራ ባለሙያ ናት። በሽመና ሥራዋ የተለያዩ ባህላዊ የአንገት ልብሶችን፣ የሶፋና የአልጋ ልብሶችን፣ መጋረጃዎችን እንዲሁም በአገሪቱ ብዙም ያልተለመዱ የሶፋ ሥር ምንጣፎችን፣ ከአልጋ ስር የሚነጠፉ ምንጣፎችን ለመታጠቢያ ቤት የሚሆኑ መረጋገጫዎችን በሽመና ሙያ በክር ትሠራለች። የሀገሯን ባህል የሚያስተዋውቁ ኢትዮጵያዊነትን የሚያጎሉ የእጅ ጥበብ ውጤቶችን ለገበያ ታቀርባለች።
ትውልድና ዕድገቷ ከሀዋሳ ከተማ የሆነችው አለምጸሐይ፤ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷንም በሀዋሳ ከተማ አጠናቃለች። የመምህርነት ስልጠናንም እንዲሁ ሀዋሳ በመምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጅ ትምህርቷን ተከታትላ ወደ አዲስ አበባ አቅንታለች። በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ትላልቅ በሚባሉ የተለያዩ የግል ትምህርት ቤቶች በመዘዋወር አገልግላለች።
ተቀጥሮ በመሥራት የሚገኘው ገቢ በተለይም ቤት መምራት ሲጀመርና ልጆች ሲመጡ በቂ እንደማይሆን የተረዳችው አለምጸሐይ ተጨማሪ ሥራ መሥራት እንዳለባት በማመን ከመደበኛው የመምህርነት ሥራዋ በተጨማሪ ተማሪዎችን በትርፍ ሰዓቷ በማስጠናት ገቢዋን ለማሳደግ በእጅጉ ተፍጨርጭራለች። ከዚህም ባለፈ የትምህርት ደረጃዋን ለማሻሻልም በማታው ክፍለጊዜ በህግ ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪ አግኝታለች። ታድያ በዚህ ወቅት የተጣበበ ጊዜ የነበራት አለምጸሐይ ምንም እንኳን ኑሮዋን ለማሻሻል ተደራራቢ ሥራዎች ብትሠራም ሕይወቷን በሽመና ሙያ ውስጥ አደርጋለሁ የሚል ሀሳብ አልነበራትም፡፡
ይሁን እንጂ ነብስ ካወቀች ጊዜ ጀምሮ የገበያ ቦታዎችን መጎብኘት የሚያስደስታት አለምጸሐይ፤ የምትገዛቸው ነገሮች እጅግ ጥቂት ሆነው ሳለ እሷ ግን በትላልቅ የገበያ ቦታዎች በተለይም ባዛሮችን እየፈለገች ትጎበኛለች። ይህ ከልጅነቷ ጀምሮ በውስጧ ላቆጠቆጠው ፍላጎቷ አቅሟ በፈቀደ መጠንና ባላት ጊዜ ሁሉ ወደ ባዛሮችና ሱፐርማርኬቶች በመሄድ ምላሽ ስትሰጥ ኖራለች። ባዛሮችን በምትጎበኝበት አንድ ወቅት ታድያ የመምህርነት ሙያዋን አስጥሎ ወደ ሽመና ሕይወት የሚወስዳት አጋጣሚ መፈጠሩን ታስታውሳለች።
አጋጣሚው በኤግዚብሽን ማዕከል የተፈጠረ ሲሆን እጆቿ በቀለም ተጨማልቀው የእጅ ሥራዎቿን ወደ ባዛሩ ይዛ ብቅ ያለችን አንዲት ወጣት ትተዋወቃለች። በወቅቱ አቡጀዲ ጨርቅ በቀለም ተነክሮ የሚሠራ የቻይና ጥለት መሳይ ሥራ ነበር። ይህን ምርት ታድያ ወጣቷ በቀለም በተጨማለቀ እጆቿ በቁጥር ለበዙ ደንበኞቿ በስፋት ስትሸጥ ትመለከታለች። ይህ ትዕይንትም የአለምጸሐይን እይታ በመቆጣጠር ወጣቷን ወደ ማድነቅ አደገ። አድናቆቷም በመጀመሪያ ሴት ከመሆኗ ሲነሳ በቀጣይነት እጆቿ እንደብዙዎቹ ሴቶች ንጹህና ውብ አለመሆኑ በራሱ ለወጣቷ የሰጠችውን ግምት በእጅጉ ከፍ አድርጎታል። ከዚህም ባለፈ ወጣቷ በአለምጸሐይ አእምሮ ውስጥ ቦታ አግኝታለች።
ስራዋን ብርታትና ጥነካሬዋን ከማድነቀም ባለፈ ወጣቷን ለማበረታታ በሚል የአንገት ልብስ ገዝታ በማድረግ በምታስተምርበት ትምህርት ቤት ወስዳ ለመሸጥና ለማስተዋወቅ ይሆን ዘንድ የወጣቷን ፈቃድ ጠየቀች። ወጣቷም በሀሳቧ ተስማምታ የተወሰኑትን እንድትሸጥላት በመተማመን ሰጠቻት። አንደኛው አለምጸሐይ እራሷ ለብሳ ወደ ሥራ ቦታዋ ስትገባ የተመለከቱት ጓደኞቿ ሁሉ ወደዱትና አድራሻዋን በመስጠት የገበያ ዕድል መፍጠር ቻለች። በምትሠራበት አሜሪካን ስኩል ውስጥ በሻይ ሰዓቷ በተለያዩ ክፍሎች በመዘዋወር አልባሳቱን መሸጥ ቀጠለች።
በአንድ ቀን ሶስት ሺ ብር በመሸጧ መደሰቷን ደግሞም ድንጋጤ ውስጥ መግባቷን ያስታወሰችው አለምጸሐይ፤ በዚህ ጊዜ እሷ ወር ጠብቃ ከምታገኘው ደምወዝ ጋር በማነጻጸር ቆም ብላ ለማሰብ በመገደዷ የቢዝነስ ሀሳቡ በውስጧ ቀረ። ያም ሆኖ የጀመረችውን የሽያጭ ሥራ በማጠናከር ከወጣቷ በ150 ብር የምትረከበውን አልባሳት በ200 ብር እና ከዛም በላይ በመሸጥ ገቢዋን መደጎም ጀመረች። በዚህ ሁኔታ ከተጀመረው ንግድ የሚገኘው ትርፍ በወቅቱ ትልቅ ዋጋ ያለውና አዋጭ ሆኖ አግኝታዋለች፡፡
‹‹እንዲህ እንዲህ እያለ የተጀመረው ሥራ በውስጤ የተለያዩ የቢዝነስ ሀሳቦች እንዲፈልቁ አድርጓል›› ትላለች። በተለይም የመምህርነት ሥራ ፋታ በሚገኝበት በክረምት ወቅት የተለያዩ የቢዝነስ ሀሳቦች በአእምሮዋ እየተመላለሰ አስጨንቆ ይይዛታል። በሀሳብ የዛለ አካላኗ ለማሳረፍ ወደ መኝታዋም ብታመራም በአዕምሮዋ የሚመላለሱትን የተለያዩ ሀሳቦች እየተነሳች መሞነጫጨር አንዱ ተግባሯ አድርጋው እንደነበር ታስታውሳለች። ከዛም መሰል ሀሳቦቿ ሲያይሉ ወደ ተግባር ለመግባት ጉዞ ጀመረች፡፡
በዚህ ጊዜ ታድያ ከምንም ነገር ተነስታ ሱቅ መክፈትን ቀዳሚ ሥራዋ ያደረገችው ወጣቷ፤ በሕይወቷ አንድ ነገር ከጀመረች ዳር ሳታደርስ የማታቆምና ሲበዛ ደፋር ስለመሆኗ ለራሷ ትመሰክራለች። ደፋር በመሆኗም ኃላፊነት ለመውሰድ ወደኃላ የምትል አይደለችምና ተወልዳ ባደገችበት ሀዋሳ ከተማ ያሉ እህቶቿን ሱቅ እንዲፈልጉላት በማድረግ የባህል አልባሳትን ለመሸጥ ወሰነች። ለዚህም ሪዞርቶች አካባቢ የተሻለ እንደሚሆን በማሰብ የሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ሪዞርት ውስጥ ሱቅ ተከራይታ መሥራት የምትችልበትን ዕድል በማመቻቸት ሰፊ ቦታ በተመጣጣኝ ዋጋ መከራየት ቻለች። ቦታውን ለማግኘት ታድያ የሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ባለቤት ወይዘሮ ዓለም ትልቅ ድርሻ የነበራት መሆኑን በማስታወስ ታመሰግናለች፡፡
ባዛር ውስጥ በቀለም ተጨማልቃ ባገኘቻት ወጣት ሴት መነሻነትና በውስጧ ባለው ፍላጎት እንዲሁም በድፍረት የተከፈተውን ሱቅ ለማስቀጠል ከታናሽ እህቷ 10 ሺ ብር ተበድራ ሥራውን ‹‹ሀ›› ብላ ቀጠለች። በወቅቱ ከወጣቷ ጋር የነበራት ግንኙነት የቀጠለ በመሆኑ ምርቶችን ከእሷ በመረከብ እንዲሁም በውስጧ ያለውን ተሰጥኦ ለማውጣት ጋቢዎችን በመጠቀም ቀለል ያሉ የተለያዩ አልባሳትን መሥራት ጀመረች።
‹‹የመምህርነት ሙያን ከልቤ ነው የምወደው›› የምትለው አለምጸሐይ፤ በመምህርነት ብቻ እንደማትቀጥልና መጨረሻዋም እንዳልሆነ ደጋግማ ለራሷ ነግራለች። በወቅቱ ታስተምር ከነበረበት ሳንፎርድ ትምህርት ቤት መልቀቂያ አስገብታ የመምህርነት ሥራዋን ስትሰናበት ምንም እንኳን ውሳኔዋ የውስጧ መሻት ቢሆንም በወቅቱ ፈታኝ የሆኑ ወቅቶችን አሳልፋለች። በመሆኑም ተሰናብታ ወደ ለቀቀቻቸው ትምህርት ቤት ደጅ በመጥናት በድጋሚ የማስተማር ዕድል አግኝታለች። በዚህ ጊዜ በከፈተችው ሱቅ ውስጥ እህቷን አሰማርታ ነበር፡፡
በድጋሚ የመምህርነት ሥራዋን ለመቀጠል አሜሪካን ስኩል ስትቀጠር የጥበብ ሥራዋን ይበልጥ የምታሳድግበት ዕድል ተፈጥሮላታል። ከውስጧ በሚመነጭ ፍላጎት ከምትሰራቸው የተለያዩ የአንገት ልብሶች በተጨማሪ መጋረጃዎችን እንድትሠራ አንድ የሥራ ባልደረባዋ ትጋብዛታለች። በዛው ቅጽበትም ባህላዊ የሆኑ የመጋረጃ ዲዛይኖችን ከድረ ገጽ በማፈላለግ ወደ ሥራው የገባችው አለምጸሐይ፤ በርካታ ቁጥር ያላቸው ደንበኞች በሯን ያንኳኩ ጀመር። የምትሠራቸው መጋረጃዎችም በተለይም ትላልቅ ሆቴሎችና ሎጆች ላይ በስፋት ተደራሽ መሆን ቻሉ። ከመጋረጃ በተጨማሪም የአልጋ እና የጠረጴዛ ልብሶችን ሠርታለች፡፡
በሥራው እጅጉን የተሳበችው አለምጸሐይ፤ በዚህ ጊዜ ደግሞ የሽመና ሙያን መማር ተመኘች ተመኝታም አልቀረች ባሰበችው ፍጥነት ከባድ ነው የምትለውን ሽመና ተማረች። በዚህ ጊዜ ከ10 ዓመት በላይ በመምህርነት የሥራ ልምድና በህግ የመጀመሪያ ዲግሪ ያላት በመሆኑ በዘርፉ የተሰማሩ በርካታ ሰዎችን በተለይም ሴቶችን ማበረታታት እንደሚቻል በማመን ሽመናን በትዕግስት ተምራ ጨረሰች። ሴቶች ውስጥ ሰፊ ዕውቀትና ዕምቅ አቅም እንዳለ ስለምታምን ፤ ለሴቶች አብዝታ የምታደላና በሴቶች የምትተማመን ናት፡፡
የሽመና ትምህርቷን አጠናቅቃ በመደራጀት የሽመና ቦታ ማግኘት ችላላች። ባገኘችው 40 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው ቦታ ላይ የሸማ ሥራዋን የሚያሳልጡ ማሽኖችንና የስፌት መኪና በመግዛት 10 ሠራተኞችን ቀጥራ ሥራዋን ቀጥላለች። ከሽመና ሥራዎቿ መካካል ያልተለመዱና አዳዲስ የኮሪደር ምንጣፎች፣ ከአልጋ ሥር የሚውሉ ምንጣፎች፣ ለመታጠቢያ ቤትና የሶፋ ሥር ምንጣፎችን ታመርታለች። ከዚህ በተጨማሪ የአልጋ ልብሶችና የተለያዩ መጋረጃዎችን በማምረት ለገበያ ታቀርባለች።
አዳዲስና ያልተለመዱ ሥራዎችን መሥራት የሚያስደስታት አለምጸሐይ፤ የምታመርታቸውን ምርቶች በተለያዩ ሱፐርማርኬቶች ተደራሽ በማድረግ የገበያ መዳረሻዋን አስፍታለች። ከምታከፋፍልባቸው ሱፐርማርኬቶቹ መካካልም ኩዊንስ፣ ጋራማርት፣ ባምቢስና ሌሎች ይገኙበታል። ምርቶቹ ከጥጥ የሚሰሩ በመሆናቸው ምቾት ያላቸው ናቸው። የምትጠቀማቸው ግብዓቶችም በሙሉ በአገር ውስጥ የሚገኙ ሲሆን በዋናነት ጥራት ያላቸውን ክሮች ትጠቀማለች።
በትምህር ቤት ውስጥ ለሥራ ባልደረቦቿ ከመሸጥ ጀምራ በትላልቅ ሱፐርማርኬቶች ምርቶቿን ተደራሽ እያደረገች ትገኛለች። በአሁን ወቅትም ገበያዋን ወደ ውጭ አገራት በማስፋት ኤክስፖርት ለማድረግ ዝግጅቷን አጠናቅቃ መላክም ጀምራለች። በቀጣይ ትልቁ ትኩረቴ የውጭ አገር ገበያን ሰብሮ መግባትነው። ለዚህም ጥራት የግድ አስፈላጊ ነው። በቅርቡም የተለያዩ የሽመና ምርቶቿን አሜሪካን አገር በመላክ መሸጥ ችላለች። በቀጣይም ይበልጥ ውጤታማ ለመሆን ጥራታቸውን የጠበቁና እጅግ ዘመናዊ የሆኑ የተለያዩ ምርቶችን በማምረት የውጭ ገበያውን በስፋት ለመቀላቀልና የኢትዮጵያን ምርቶች ጥራት ባላቸው አፈጻጸም አምርቶ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ማድረግና ማስተዋወቅ ትልቁና ዋነኛው ዕቅዷ ነው። በተለይም በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ እንደምትችል ሠርቶ በማሳየት ኢኮኖሚዋን መደገፍ እንደሚገባም አንስታለች።
በሕይወት ውስጥ ከባድ የሆኑ ውሳኔዎችን በድፍረት መወሰን ሁልጊዜ አደጋ ላይ የሚጥል አይሆንም፤ አንዳንድ ጊዜ ከነብስ ጥሪ ጋር ያገናኛል። ለዚህም እኔ ምሳሌ ነኝ የምትለው ወጣቷ፤ በወሰንኩት ውሳኔ ተጠቅሜያለሁ፤ ዕድለኛ ሆኜም በውስጤ ያለውን ችሎታ በማውጣት በምወደው ሥራ ተሠማርቼ ስኬታማ ሆኛለሁ። ስኬታማነትን ማጣጣም የሚቻለው ደግሞ አገር ሰላም ሲሆን ነውና ለአገሬ በምችለው አቅም ሁሉ ድጋፍ አደርጋለሁ ትላለች፡፡
ወይዘሮ አለምጸሐይ፤ ከሥራዋ በተጨማሪ ማሕበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት የተለያዩ ድጋፎችን የምታደርግ ሲሆን በተለይም ልጆች ላይ ትሠራለች። ለአብነትም ዱከም ከተማ ላይ ትምህርት ቤት ከፍታ መመገብና ማልበስ እንዲሁም መማር ያልቻሉ ህጻናትን ሰብስባ ታስተምራለች። በመሆኑም 36 ህጻናትን በነጻ መመገብና በመጠኑ ያገለገሉ አልባሳትን ከተለያዩ አካላት በማሰባሰብ ታለብሳለች ትምህርታቸውን እንዲከታተሉም ታደርጋለች። በጎ ሥራው ከተጀመረም ስድስት ዓመታትን አስቆጥሯል።
ከእህቷ 10 ሺ ብር ብድር ወስዳ በድፍረት ሱቅ የከፈተቸው አለምጸሐይ በአሁን ወቅት አምስት ሚሊዮን ካፒታል ላይ ደርሳለች። በቀጣይም ኢትዮጵያ ሰላም ትሁን እንጂ ጥራት ያላቸውን የአገር ውስጥ ምርቶች በስፋት ወደ ውጭ ገበያ በመላክ የውጭ ምንዛሪ ለአገሪቷ ማስገባት ከፍተኛ ፍላጎት አለኝ ትላለች። በተጨማሪም ከማግዛቸው 36 ህጻናት በተጨማሪ በርካታ ህጻናቶችን ለመደገፍ ሰፋፊ ዕቅዶች አሉኝ ትላለች። ማህበረሰቡን ለማገልገል ካላት ከፍተኛ ፍላጎት የተነሳ ከመንግሥት ቦታ ማግኘት እንደምትፈልግ ትናገራለች።
ሁሉም በየሞያው ጠንክሮ በመስራት፤ በአንድነት በመተባበር ሀገርን ከጥፋት ማዳን ይቻላል። በሀገር ላይ የመጣን ችግር በመረዳዳት፣ በመተሳሰብ፣ የተፈናቀሉትን በማቋቋም እና የወደሙ መሰረተ ልማቶችን ወደነበሩበት ለመመለስ ትብብር ማድረግ ከሁሉም ዜጋ ይጠበቃል። ሀገርን መደገፍ የሚቻለው በገንዘብ፣ በእውቀትና በጉልበት ጭምር ነው። እኔም ኢኮኖሚው ላይ የራሴን አስተዋጽኦ አደርጋለሁ። ዲያስፖራው ማህበረሰብ በሽመና ውጤቶች ሀገሩን የሚያስተዋውቅበት ለብሰውም የሚደሰቱበትን የሀገር ባህል ልብሶችን እናቀርባለን። በሕይወት ውስጥ ጨለማ እንዳለ ሁሉ ንጋት አለ። በኢትዮጵያም በአሁን ወቅት የጨለመ ቢመስልም ይነጋልና በዚህ ወቅት ሌሎች አማራጮችን ከመውሰድ ይልቅ በችግርም ይሁን በደስታ ጊዜ ከአገር ጎን በመቆም የሚጠበቅብንን ሁሉ እናድርግ የመጨረሻ መልእክቷ ነው።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 23/2014