
ለወልድያ ጠቅላላ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ካደረግነው የቁሳቁስና መድሃኒት ድጋፍ በላይ ትርጉም የሚሰጠን አንድነታችንን የመዝረፍ እሳቤን በማፍረስ አንድነታችንን ማሳየት መቻላችን ነው፤ ሲሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶክተር አንዷለም ደነቀ ገለጹ። የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ስድስት ነጥብ አራት ሚሊዬን ብር የሚገመት ቁሳቁስና መድኃኒት ድጋፍ አድርጓል።
ዶክተር አንዷለም፣ በስፍራው ለሚገኘው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የጋዜጠኞች ቡድን እንደተናገሩት፤ በአሸባሪው የሕወሓት ወራሪ ኃይል ዘረፋና ውድመት ለተፈጸመበት የወልድያ ጠቅላላ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከተደረገው ድጋፍ በላይ አንድነትን የመዝረፍ እሳቤ በማፍረስ በአንድ ላይ መቆም ማሳየት መቻሉ ሊሆን ይገባል። በአንድነት ሲቆም ደግሞ የጠፋውን ተክቶ፤ የጎደለውን ሞልቶ ሆስፒታሉን በሁለትና ሦስት ወራት ውስጥ ቀድሞ ይሰጥ የነበረውን መደበኛ አገልግሎት በሙሉ እንዲሰጥ በማድረግ ማሳየት ይቻላል።
እንደ ዶክተር አንዷለም ገለጻ፤ ሆስፒታሉ ብዙ የሕክምና እቃዎች ተዘርፈውበታል። ብዙ መድኃኒቶች ወድመውበታል። አገልግሎቱም ለአምስት ወራት ያህል ተቋርጦ ቆይቷል። ስለዚህ ይሄንን ሆስፒታል ለማስጀመር እና ወደነበረበት ሁኔታ ለመመለስ የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በጤና ሳይንስ ኮሌጁ ስር ያለው ኃላፊነቱን ወስዶ ከወልድያ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ጋር እየሠራ ይገኛል። ይሄንን ከማድረግ አኳያ የተለያዩ ግብዓቶችን እንዲሁም የሰው ኃይል ይዘው ሄደዋል።
ዶክተር አንዷለም እንደተናገሩት በተጨማሪ በሰው ኃይል ደረጃ የቀዶ ሕክምና ስፔሻሊስት፣ የአጥንት ሕክምና ስፔሻሊስት፣ የሰመመን ሰጪ ሕክምና ስፔሻሊስት እና አንስቴቲስት፣ ሚድ ዋይፍ፣ የድንገተኛ ሕክምና ባለሙያዎች፣ እንዲሁም የኦፕራሲዮን ክፍል ነርሶችን ይዘን እንደ ቡድን መስርተው ነው ወልድያ ገብተዋል። እነዚህም በሁሉም ቦታ እየተንቀሳቀሱ ውጤታማ ሆነዋል። በሚቀጥሉት ጊዜያትም በጥቁር አንበሳ ውስጥ የሚገኙ ከፍተኛ ባለሙያዎችን ስፔሻሊስትና ሰብ ስፔሻሊስቶችን ጨምሮ ሌሎች ባለሙያዎችን ለማምጣትና ሕክምናውን ለማስቀጠል እየተዘጋጁ ይገኛል።
ዶክተር አንዷለም እንደሚሉት፤ በውጤታማ ጅማራቸው የድንገተኛ ሕክምና፣ የተመላላሽ ሕክምና እንዲሁም የድንገተኛ ቀዶ ሕክምና አገልግሎት ክፍሎች ስራ ጀምረዋል። እነዚህ ደግሞ በጣም ተስፋ ሰጪ ናቸው። ከዚህ አኳያ በሚቀጥሉት ሁለትና ሦስት ወራት የወልድያ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ቀድሞ የሚሰጠውን ሁሉንም መደበኛ አገልግሎት ወይም ከዛ በተሻለ ሁኔታ ተደራጅቶ ሕብረተሰቡን የሚያገለግልበት ሁኔታን ለመፍጠር እየተሰራ ነው።
ይሁን እንጂ ችግሩ ቀላል የሚቻል አይደለም። ይሄን ሆስፒታል ለማደራጀት ዓመታት ወስዷል። በዓመታት ውስጥ የተደራጀውን ሆስፒታል በጥቂት ወራት ውስጥ ከፍተኛ የሚባል ዝርፊያ ተፈጽሞበታል። የጽኑ ሕክምና ማሽኖችና መሳሪያዎች ተወስደዋል፤ የሕመምተኛ ቁጥጥር የሚደረግባቸው ሞሚተሮች ተወስደዋል፤ የአልትራ ሳውንድ ማሽኖች ተወስደዋል፤ ተንቀሳቃሽ ኤክስሬይ ማሽን ተወስዷል፤ መውሰድ ያልተቻለው ደግሞ ወድሟል፤ ሜዳ ላይ ተዝረክርኮ ቆሻሻ ሆኗል።
ወንድወሰን ሽመልስ (ወልድያ)
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 23/2014