ለረጅም ዓመታት የኢትዮጵያን ስፖርታዊ ውድድሮች በብቸኝነት በማስተናገድ አንጋፋነትን የተቀዳጀው የአዲስ አበባ ስታዲየም በእድሳት ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል። የስታዲየሙ እግር ኳስ መጫወቻ ሜዳ ደረጃውን የጠበቀ ባለመሆኑ አህጉር አቀፍ ጨዋታዎችን እንዳያካሂድ መታገዱ ለእድሳቱ ምክንያት ሲሆን፤ አሁን የደረሰበት ሁኔታም በኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር አመራሮች እንዲሁም የኢትዮጵያ እግር ኳስ እና አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ጉብኝት ተደርጎበታል።
ትናንት ከተካሄደው ጉብኝትም አራት የተጫዋቾች መልበሻ ክፍል፣ የዳኞች ማረፊያ እንዲሁም ሌሎች አገልግሎት ሰጪ የስታዲየሙ ክፍሎች እድሳት እየተጠናቀቀ እንደሚገኝ ለመረዳት ተችሏል። የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በዋናነት ትኩረት የሚያደርግበት የእግር ኳስ መጫወቻ ሜዳ ግንባታውም በመፋጠን ላይ ይገኛል።
በጉብኝቱ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ፤ በየጊዜው ከሚያደርጉት ጉብኝት አንጻር የመልበሻ ክፍሎች እድሳቱ በተያዘለት ጊዜ እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመዋል። ከመጫወቻ ሜዳው የሳር ተከላ ጋር በተያያዘ እድሳቱን በማከናወን ላይ የሚገኘው ተቋራጭ ልምድ እንደሌለው ተናግረዋል። ስታዲየሞች ጨዋታ ከማስተናገድ እንዲታገዱ ያደረገው ዋነኛው ችግርም ይህ መሆኑን ጠቅሰው፣ ጉዳዩ ትኩረት ሊደረግበት እንደሚገባም አሳስበዋል። የሳር ተከላው እንዴት መከናወን ይኖርበታል በሚለው እንዲሁም ሳር በመትከሉ ሂደትም ልምድ ያለው አካል በምን መልኩ መግባት ይኖርበታል በሚለው ላይ መፍትሄ ማስቀመጥ እንደሚያስፈልግ ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል።
ከዚህ ቀደም በተካሄደው ጉብኝት እንደ ፌዴሬሽን ይህንን ሥራ ሊያከናውኑ የሚችሉ ባለሙያዎች እንዲገኙ ጉብኝት እንዲያደርጉ ተብሎ እንደነበር አስታውሰው፤ ከአገሪቷ ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር ተጋባዡ ካምፓኒ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ በፈረንሳይ መንግሥት በመከልከሉ ጉብኝቱ መቅረቱን አስታውቋል። ባለሙያዎቹ አገሪቷ ያለችበትን ሁኔታ በሂደት በመረዳት ላይ የሚገኙ መሆኑን ተከትሎ የመምጣት እድላቸው የሰፋ መሆኑን ተናግረዋል። ካምፓኒው የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅ የሆነችውን ካሜሩን አብዛኛዎቹን ሜዳዎች የሠራ መሆኑን የሚያነሱት ፕሬዚዳንቱ በድጋሚ ስህተት ላለመስራት እንደሚሰራ አመልክተዋል።
‹‹የአዲስ አበባ ስታዲየምን ሜዳ ለሌሎች ስታዲየሞች ተምሳሌት ለመሆን በሚችልበት ሁኔታ በጥንቃቄ መስራት ተገቢ ነው›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ የስታዲየሙ እድሳት አብዛኛው ሥራ እየተጠናቀቀ መሆኑን ተከትሎ እንዲሁም ካምፓኒው የሚመጣ ከሆነም በእድሳቱ እቅድ እንደተመላከተው በውድድር ዓመቱ የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊግ የመጨረሻ ጨዋታን ለማስተናገድ የመድረስ እድል እንደሚኖረው ጠቁመዋል።
በጉብኝቱ ወቅት በስታዲየሙ ተገኝተው ሃሳባቸውን የሰጡት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ባለሙያም ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል የሚሏቸውን ጉዳዮች አመላክተዋል። በዚህም እንደ እግር ኳስ ስፖርት ሁሉ አገሪቷ ዘመናዊና ምቹ መም የሌላት በመሆኑ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ለማስተናገድ አልተቻለም ብለዋል። በመሆኑም ለመሮጫ መም ግንባታ፣ ፌዴሬሽኑ የሚገለገልባቸውን ዘመናዊ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች እንዲሁም የሜዳ ተግባራት ቁሳቁስን ታሳቢ ባደረገ መልክ እድሳቱ መካሄድ እንደሚገባው አስገንዝበዋል።
የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ ቀጄላ መርዳሳ የስታዲየሙ የመጀመሪያ ዙር ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን ገልጸዋል። በዚህ ወቅት የግንባታ ደረጃው 40 ከመቶ ላይ የደረሰ ሲሆን፤ በ100 ቀናት ውስጥ እንዲጠናቀቅ በተያዘው እቅድ መሰረት እየተጓዘ ነው።
ስታዲየሙ ቅርስ መሆኑንም ጭምር በመገንዘብ ባለበት ሁኔታ ተጠብቆ በጥራት እድሳቱ በመካሄድ ላይ መሆኑም ተመላክቷል። በዚህም ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ለማስተናገድ የሚችልና ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን እየተሰራ ቢሆንም ከውጭ መምጣት ያለባቸው ቁሳቁስን ማስገባት እንደሚጠይቅ አስረድተዋል።
በቀጣይም በስታዲየሙ የተመልካቾች መገኛ አካባቢ የሚታዩና ረጅም ዓመታትን ያስቆጠሩ እንዲሁም ያረጁ ወንበሮችና መሰል ቁሳቁስ በአዲስ የሚተኩ መሆኑንም ሚኒስትሩ ይገልጻሉ። እድሳቱ በዚህ ወቅት በፍጥነት እየተከናወነ መሆኑን ተከትሎም በዚሁ ከቀጠለ በዚህ አንድ ዓመት ይጠናቀቃል የሚል እምነት እንዳላቸው አስታውቀዋል።
ባልተጠበቀ ሁኔታ የጊዜ መራዘም ቢኖርም በእቅድ ከተቀመጠው ጊዜ ውጪ ከሦስት ወር በላይ አይራዘምም ሲሉም ተናግረዋል። መሠረታዊ የሆኑ ጉዳዮች መሬት የያዙ መሆኑን ተከትሎ ከዚህ በኋላ የሚቀረው ስድስት አሊያም ሰባት ወራት በመሆኑ በእነዚህ ጊዜያት እንደሚጠናቀቅም ይጠበቃል። ከእድሳቱ ፍጥነት ጋር ተያይዞ ጥራት ላይ ችግር እንዳይከሰትም ከፌዴሬሽኖች ጋር በጋራ መስራት ላይ እንደሚገኝም ሚኒስትሩ ይገልጻሉ።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 16/2014 ዓ.ም