በአሸባሪ ቡድኑ ከወደሙ የመሰረተ ልማት አውታሮች ውስጥ የጤና ተቋማት በዋናነት ይጠቀሳሉ። ከነዚህ ውስጥ ደግሞ ለህክምና አገልግሎት እንደ ዋና ሞተር ሆነው የሚያገለግሉት የመድኃኒት ማከማቻዎች ይገኙበታል። በተለይ ቡድኑ በደሴ በቆየባቸው ጊዜያት ውስጥ ካወደማቸው የመድኃኒት ማከማቻዎች ውስጥ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት አገልግሎት ዋናው ቅርንጫፍ አንዱ ነው።
በዚህ ቅርንጫፍ በክምችት የነበሩ የመድኃኒትና ሌሎች የህክምና ግብዓቶች በአሸባሪ ቡድኑ በከፍተኛ ደረጃ ወድመዋል፤ ተዘርፈዋል። ቅርንጫፉ በከፍተኛ መሰረተ ልማት የተደራጀና በአካባቢው ለ27 ሆስፒታሎች፣ ለ303 ጤና ጣቢያዎችና ለ60 ወረዳዎች አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል።
ቅርንጫፉ ከህግ ማስከበር ዘመቻ እስከ ህልውና ዘመቻው ድረስ በከፍተኛ ደረጃ የመድኃኒትና ሌሎች የህክምና ግብአት በማቅረብ አገልግሎት እየሰጠ የነበረ ሲሆን፤ በክምችት ከነበረ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸውን መድኃኒቶች፣ የህክምና ቁሳቁስና ሁሉንም የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን ከጥፋት ቡድኑ ለማዳን ቢቻልም ቡድኑ በተቀሩት መድኃኒትና የህክምና ግብአቶች ላይ ዘረፋና ውድመት ፈፅሟል። ከዚህም ጋር በተያያዘ በምስራቅ አማራና አጎራባች ክልሎች የሚገኙ ሁሉም የጤና ተቋማት ጉሮሮ ተዘግቷል።
የጥፋት ቡድኑ ውድመት በከፍተኛ መዋእለ ንዋይ የተገነባ ግዙፍ የእናቶችና ህፃናት ክትባት ግበዓት ማከማቻ የማቀዝቀዣ ሰንሰለት መጋዘንን /cold room/፣ ዋና መጋዘንን /main warehose/፣ ቢሮዎችን፣ የማከማቻ መሰረተ ልማትን፣ ፎርክ ሊፍቶችን፣ የደህንነት መቆጣጠሪያ ሥርዓቶችን፣ የቢሮ መሳሪያዎችንና ሌሎች ንብረቶችን ያካትታል።
ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት አገልግሎት በአጠቃላይ በቅርንጫፉ ላይ የደረሰውን ውድመት የሚያጠና ቡድን አቋቁሞ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ እንደሚሉት፤ አገልግሎቱ በደቡብ ወሎ ዞን ካሉት አስራ ዘጠኝ ቅርንጫፎች ውስጥ ደሴ ቅርንጫፍ ዋናው ሲሆን ምስራቅ አማራንና አፋርን ጭምር ሲያገለግል ቆይቷል። 8 ነጥብ 7 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብም ሲገለገልበት ነበር። ለ27 ሆስፒታሎችም በቀጥታ መድኃኒቶችን የሚያቀርብና 303 ለሚሆኑ ጤና ጣቢያዎች እንዲሁም ለኤች አይ ቪ እና ለቲቢ ወባና ሌሎች የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት የሚውሉ መድኃኒቶችን ጭምር ለ60 ወረዳዎች በቀጥታ የሚያቀርብ ነበር።
ይህ ቅርንጫፍ በወራሪው የሕወሓት ቡድን ከፍተኛ ዝርፊያና ውድመት ደርሶበታል። ቡድኑ ትልቁን የመድኃኒት ማከማቻ መጋዘን አውድሟል። በውስጥ የነበሩትን መድኃኒቶችንም ዘርፏል። ከቅርንጫፉ ውጪ ያሉትንም በተመሳሳይ ከጥቅም ውጪ አድርጓል። ሌሎች የቢሮ እቃዎችንም አጥፍቷል። በተለየ ሁኔታ ደግሞ ቡድኑ የሴቶችና የህፃናት ክትባት ማቀዝቀዣዎችን ያለርህራሄ አውድሟቸዋል።
ይሁንና የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት አገልግሎት ከሌሎች ቅርንጫፎች ጋር በመተባበር በጣም ወሳኝ የተባሉ መድኃኒቶችን፣ 160 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው የመድኃኒቶችንና የህክምና ቁሳቁሶችን አሸባሪ ቡድኑ ሳይደርስ አስቀድሞ ማውጣት ተችሏል። ወደ 33 የሚሆኑ የተቋሙን ተሳቢ ተሽከርካሪዎችንም በተመሳሳይ አስቅድመው እንዲወጡ አድርጓል። ሌሎችንም ተሽከርካሪዎች ማዳን ተችሏል።
ነገር ግን ሁሉንም ማትረፍ ስላልተቻለ አሸባሪ ቡድኑ ቅርንጫፉ ላይ ደርሶ አውድሞታል፤ የቻለውንም ዘርፏል። በዚህም በቅርንጫፉ አካባቢ የሚገኘው ህዝብ መድኃኒቱን እንዳያገኝ አድርጓል።
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ የጥፋት ቡድኑ በደሴ ቅርንጫፍ ያደረሰው ጉዳት ምን ያህል እንደሆነ ለማወቅ በአገልግሎቱ በኩል የጥናት ቡድን ተቋቁሞ እያንዳንዱን ውድመት በተለያዩ ዘርፎች በመከፋፈል እያጠና ይገኛል። ይህ ጥናት እንደተጠናቀቀም የጉዳቱ መጠን በቀጣይ ለሚዲያ አካላት የሚገለፅ ይሆናል።
በአሁኑ ጊዜም በአካል ቦታው ድረስ በመገኝት ግብረ ሃይል ተቋቁሞ ከወደሙ አስራ ስምንት ቅርንጫፎች ውስጥ ግማሽ ያህሉን መልሶ ለማቋቋም ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ። እያንዳንዱ ቅርንጫፍም ከራሱ ላይ አዋጥቶ መድኃኒቶችንና ሌሎች የቢሮ እቃዎችን የወደሙ ቅርንጫፎች ሥራ መጀመር የሚችሉበት አሰራርም ተዘርግቷል።
ለአብነትም ደሴ ከአሸባሪው ወራሪው ሃይል ነፃ እንደሆነ በሁለት ቀናት ውስጥ ለሆስፒታሎች መድኃኒት እንዲደርስ ተደርጓል። በተመሳሳይ ለኮምቦልቻ ሆስፒታልም መድኃኒት እንዲደርስ ተደርጓል። የሀይቅ ሆስፒታልም ድጋፍ እየተደረገለት ይገኛል። በሌሎች ሆስፒታሎችም በዛው ልክ መድኃኒቶች እንዲደርሱ እየተደረገ ነው።
ይህም ሆስፒታሎች ከቅርንጫፎች የሚያገኟቸውን መድኃኒቶችና የህክምና መሳሪያዎች በቀጥታ እየደረሰላቸው ይገኛል። ከዚሁ ጎን ለጎንም ቅርንጫፎች እንዲቋቋሙና በፍጥነት ሥራ እንዲጀምሩ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ። በዋናነት ደግሞ ማህበረሰቡ በስፋት የሚጠብቃቸው መድኃኒቶች ለአብነትም የኤች አይ ቪ፣ የቲቢ፣ የወባ፣ የደም ግፊትና የስኳር መድኒቶች በቶሎ የተለቀቁ ቦታዎች ላይ ለማድረስ በሆስፒታሎቹ፣ በጤና ጣቢያዎች፣ እየተሰራ ነው። እስካሁን ባለው ሁኔታም በርካታ መድኃኒቶች እንዲደርሱ ተደርጓል።
ዋናው የደሴ መድኃኒት ማከማቻ ቅርንጫፍ በቶሎ ስራ መጀመር ያለበትና መድኃኒት ጊዜ የማይሰጥ ጉዳይ በመሆኑ በፍጥነት ቅርንጫፉን ወደነበረበት ለመመለስ አሁን ያለውን ክምችት በቦታው በማድረስና ቅርንጫፉን ጎን ለጎን ሥራ በማስጀመር ብሎም መድኃኒቶችን ለሆስፒታሎችና ለጤና ጣቢያዎች ቀጥታ በማድረስ ችግሩ እንዳይብስ ስራዎች ሌት ተቀን እየተሰሩ ይገኛሉ።
ለአብነትም ሰመራ ከሚገኘው ቅርንጫፍ አገልግሎት እንዲሰጥ አዲስ አበባ ላይ የሚገኙ ሁለት አብይ ቅርንጫፎችም ቁጥር አንዱ ደሴ፣ ኮምቦልቻ፣ ድረስ እንዲሁም ቁጥር ሁለቱ እስከ ደብረ ብርሃንና መሀል ሜዳ ድረስ እንዲያደርስ በማድረግ ማህበረሰቡ መድኃኒት እንዲያገኝ እየተደረገ ነው እንደሆነ ዋና ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።
በአጠቃላይ አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ወረራ በፈፀመባቸው የአማራ ክልል በሚገኙ አካባቢዎች የጤና መሰረተ ልማቶችን በዋናነት ሆስፒታሎችን፣ ጤና ጣቢያዎችን፣ ጤና ኬላዎችንና የመድኃኒት ማከማቻ መጋዘኖችን አውድሟል፤ የቻለውንም ያህል ዘርፏል። በመሆኑም የወደሙ መድሐኒቶችንና የህክምና መሳሪያዎችን መልሶ ለማቅረብ ጥረት እየተደረገ ነው።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 16/2014 ዓ.ም