የዋልያዎቹ ዋና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ከትናንት በስቲያ አመሻሽ ላይ ወደ አፍሪካ ዋንጫው የሚያመሩ ሃያ አምስት ተጫዋቾቻቸውን ዝርዝር ይፋ አድርገዋል፤ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ከግብ ጠባቂ አንስቶ እስከ አጥቂ መስመር የተመረጡት ተጫዋቾች በአፍሪካ ዋንጫው ማጣሪያና በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ብሔራዊ ቡድኑን ሲያገለግሉ የቆዩ ናቸው።
አሰልጣኙ ይፋ ካደረጉት የተጫዋቾች ስብስብ መካከል በጥሩ ብቃት ላይ የሚገኙ የተወሰኑ ተጫዋቾች በስነምግባር ጉድለት አልተካተቱም፤ በተለያዩ የአውሮፓና ሌሎች አገራት ሊጎች የሚጫወቱ ትውልደ ኢትዮጵያውያንም ሳይካተቱ ቀርተዋል።
ይህም በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ የመወያያ ርእስ ሆኗል፤ አሰልጣኙ በተለይም ለትውልደ ኢትዮጵያውያን እድል ቢሰጡ ብሔራዊ ቡድኑን ለማጠናከር እንደሚጠቅም አስተያየቶች ሲሰነዘሩ ሰንብተዋል። በሌላም በኩል ተጫዋቾችን የመምረጥ መብቱ የአሰልጣኙ እንደመሆኑ የመሰላቸውን የማካተት ነፃነት ሊሰጣቸው እንደሚገባ አስተያየት እየተሰጠ ነው።
በተለያዩ የአውሮፓና ሌሎች አገራት ሊጎች የሚጫወቱና ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመጫወት ፍላጎት ያላቸውን ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾችን በመለየት እንዲሁም አድራሻቸውን ይዞ ግንኙነት በመፍጠር ትውልደ ኢትዮጵያዊው የቀድሞ የብሔራዊ ቡድንና የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋች ዴቪድ በሻህ ባለፉት አመታት ትልቅ ጥረት አድርጓል። ይሁን እንጂ ዴቪድ በሻህ የሚሰማው ሳያገኝ ቆይቷል።
በ2021 የአፍሪካ ዋንጫ የሚሳተፈውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አስመልክቶ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ትናንት በኢሊሊ ሆቴል ባዘጋጀው የፓናል ውይይት ላይ አሰልጣኝ ውበቱ በዚህ ጉዳይ ላይ ለሚነሳው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል። ዋና ፀሐፊው አቶ ባሕሩ ጥላሁን ለውድድሩ እየተደረገ ስለሚገኘው ቅድመ ዝግጅት ገለፃ ካደረጉ በኋላ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጂራ የመክፈቻ ንግግር በይፋ የተከፈተው መርሐ ግብሩ፣ በብሔራዊ ቡድናችን ዋና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ቡድኑ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ስላለበት ሒደትና ስለ ውድድሩ እቅድ ዝርዝር ማብራሪያ ሰጥተዋል።
አሰልጣኝ ውበቱ በፓናል ውይይቱ ዴቪድ በሻህ ባለፉት አራት አመታት ትልቅ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን በማስታወስ ሃሳቡ ሰሚ አጥቶ ተስፋ እስከ መቁረጥ እንደደረሰ ተናግረዋል። ይሁን እንጂ እሳቸው ብሔራዊ ቡድኑን ማሰልጠን ከጀመሩ ወዲህ ዴቪድ በሻህ ተደጋጋሚ ጥያቄ በማቅረብ ከፌዴሬሽኑ ጋር አብሮ የሚሰራበት ሁኔታ ተፈጥሯል።
እንዳሰልጣኝ ውበቱ ገለጻ፣ ዴቪድ በሻህ እሳቸው በሚያቀርቡለት ጥያቄ መሠረት ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾችን እንዲያቀርብ ፌዴሬሽኑ እውቅና ሰጥቶታል። በዚህም ካለፈው መስከረም ጀምሮ ወደ ሥራ ገብቷል። የተወሰኑ ተጫዋቾችን በቪዲዮ የተደገፈ እንቅስቃሴም አቅርቦም ውይይት አድርገዋል።
ከረዳት አሰልጣኞቻቸው ጋር በጉዳዩ ዙሪያ ከተወያዩ በኋላም ዴቪድ ያቀረባቸውን ተጫዋቾች ካለው አጭር ጊዜ አኳያ ለአፍሪካ ዋንጫው መጠቀም ከግብአቱ ይልቅ ክፍተቱ ስለሚበዛ ወደ ፊት መመልከት ይሻላል ብለው ወስነዋል።
አሰልጣኝ ውበቱ ለዴቪድ በጀርመን ሦስተኛ ዲቪዚዮን የሚጫወተውን ኬቪን ሪዶንዶንና በኖርዌይ ሊግ የሚጫወተውን የግብ ጠባቂው ዳንኤልን ተጨማሪ እንቅስቃሴ የሚያሳይ ቪዲዮ እንዲልክላቸው መጠየቃቸውን በማስታወስ ሌላ ዝርዝር ጉዳይ ውስጥ መግባት እንደማይፈልጉ ገልጸው የዴቪድ ፍላጎት እሱ ያቀረባቸው ተጫዋቾች በአፍሪካ ዋንጫው እንዲሰለፉ መሆኑን አብራርተዋል።
«እዚህ ጋ ነው የተላለፍነው፣ የተላኩት ቪዲዮዎች የአራት የአምስት ደቂቃ ይሆናሉ፣ ኢትዮጵያ የመቶ ሚሊዮን ሕዝብ አገር ናት፣ ለእነዚያ ደቂቃዎች ቪዲዮ ብቻ ተጫዋቾቹን አፍሪካ ዋንጫ ላይ እንዳሰልፍ ከሆነ ፍላጎቱ ይህ ለእኛ ስድብ ነው፣ ልክም አይደለም›› ብለዋል፡፡
‹‹የተላከው ቪዲዮ በራሱ ጥራት የለውም፣ ተጨማሪ ቪዲዮ እንዲልክ ጠይቄ ነበር፣ በተላኩት ተንቀሳቃሽ ምስሎች ጥሩ ነገር አስተውያለሁ፣ ግብ ጠባቂው ኖርዌይ የሚጫወት ቢሆንም ተጠባባቂ ነው፣ ተጫዋች በዚህ መልኩ መምረጥ ተገቢ አይደለም» በማለት አሰልጣኝ ውበቱ ከዴቪድ ጋር ስለነበረው ጉዳይና ሂደት አስረድተዋል።
ዴቪድ የሚለፋው ለአገር መሆኑን የገለጹት አሰልጣኝ ውበቱ፣ ሁሉም ለአገር የሚለፋ እስከሆነ ድረስ የሚያስመሰግን ነገር መስራት ተገቢ እንደሚሆን ተናግረዋል። ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ ተጫዋቾች በዚህ አጭር ጊዜ ብሔራዊ ቡድኑን ቢቀላቀሉ ከቡድናቸው ጋር አዋህደው ውጤታማ ለመሆን አይደለም «ስማቸውን እንኳን ለመያዝ አይቻልም» በማለትም በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 15/2014