በአትሌቲክስ ስፖርት ስኬታማ ሆነው ትልቅ ስምና ዝና ካገኙ አገራት መካከል የምትመደበው ኢትዮጵያ፤ በተለይ በረጅም ርቀት ሩጫዎች ስኬቷ በቀዳሚነት ትጠቀሳለች፡፡ ስፖርቱ ከሩጫ ባለፈ እርምጃ፣ ውርወራን እንዲሁም ዝላይን የሚያጠቃልል ቢሆንም ኢትዮጵያ የአጭር ርቀት ሩጫን ጨምሮ ወንዝ የተሻገረ የስኬት ታሪክ የላትም፡፡ ለስፖርቱ አመቺ ከሆነው መልከዓ ምድራዊ አቀማመጥ፣ የአየር ሁኔታ እና የአትሌቶች እምቅ አቅም አንጻር እንደ ረጅም ሩጫው ሁሉ በአጭርና የሜዳ ተግባራት ውድድሮች ውጤታማ የመሆን እድሉ ሰፊ ቢሆንም ውጤታማነቱ ተቃራኒ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በየጊዜው የተለያዩ ስልቶችን በመቀየስ እየሠራበት ይገኛል፡፡
በዚህ ረገድ የታዳጊ ወጣት ስፖርተኞች ምንጭ በሆኑት ፕሮጀክቶች ተተኪ አትሌቶች ማፍራት እንዲቻል፣ በአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከላት በስፖርቱ ስልጠናዎች እንዲሰጡ እንዲሁም ከአገር አቀፍ ቻምፒዮናዎች ውጪ እነዚህ ስፖርቶች ብቻ የሚካሄዱበት ውድድርን ማዘጋጀት በፌዴሬሽኑ ከተወሰዱ ርምጃዎች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ ይህ ዓመታዊ ውድድርም የኢትዮጵያ አጭር፣ መካከለኛ፣ 3ሺ መሰናክል፣ ርምጃና የሜዳ ተግባራት አትሌቲክስ ቻምፒዮና በሚል ይጠራል፡፡ የዚህ ውድድር ዋነኛ ዓላማም ተተኪና ውጤታማ ስፖርተኞችን ከማፍራት በተጓዳኝ የውድድር እድልን ለአትሌቶች መፍጠር ነው፡፡ በዚህም በስልጠና ላይ የቆዩ አትሌቶች ከአቻዎቻቸው ጋር በሚኖራቸው ፉክክር አቅማቸውን ለመለካት ያስችላቸዋል፡፡
ይህ ዓመታዊ ውድድር የዘንድሮ መርሃ ግብሩን በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ትናንት ማካሄዱን ጀምሯል፡፡ ለአምስት ቀናት በሚዘልቀው ፉክክርም ሁለት ክልሎች፣ አንድ ከተማ አስተዳደርና 22 ክለቦችና የማሰልጠኛ ተቋማትን ጨምሮ በድምሩ 25 ቡድኖች 707 አትሌቶቻቸውን እያካፈሉ እንደሚገኙ ከፌዴሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡ ከዚህ ቀደም ከተለመደው አንጻር የተሳትፎ ማነስ እንዲሁም በእድሳት ምክንያት ውድድሩ በአዲስ አበባ ስታዲየም ውጪ እየተደረገ ቢሆንም ድምቀቱ ሳይደበዝዝ እየተካሄደ እንደሚገኝ ለመታዘብ ተችሏል፡፡ በአትሌቶች መካከል ያለው ፉክክርም ከመነሻው ጀምሮ የተስተዋለ ሲሆን፤ በመክፈቻው ዕለት በተካሄዱ የፍጻሜ ውድድሮች ላይም በግልጽ ታይቷል፡፡
ትናንት ውድድሩ በተከፈተበት ዕለት የበርካታ ውድድሮች ማጣሪያ ሲደረግ፤ በሴቶች ምድብ ሦስት እንዲሁም በወንዶች ምድብ አንድ ውድድሮች ፍጻሜ አግኝተዋል፡፡ ከተጠናቀቁት ውድድሮች መካከል አንዱ በሆነው የሴቶች የርዝመት ዝላይ ውድድር የሰበታ ከተማ ክለብ አትሌቷ አስቴር ቶሎሳ ቀዳሚ በመሆን አጠናቃለች፡፡ አትሌቷ የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚነቷን ያረጋገጠችውም 5 ከ85 ሜትር በመዝለል ነው፡፡ ከፍተኛ ፉክክር በተደረገበት በዚህ ውድድር የመከላከያ ስፖርት ክለብ አትሌቷ ማርዋ ኪዶ እንዲሁም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አትሌቷ አሪያት ዲቦ ሁለተኛ እና ሦስተኛ በመሆን የብርና የነሐስ ሜዳሊያ ተሸላሚዎች ሆነዋል፡፡
በሴቶች ዲስከስ ውርወራ የፍጻሜ ውድድር ሲካሄድ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ስፖርት ክለብ አትሌቶች የሆኑት መርሃዊት ጸጋዬ እና አለሚቱ ተክለሥላሴ የወርቅና ብር ሜዳሊያ እንዲሁም ዙርጋ ኡስማን ከመከላከያ የሜዳሊያ ባለቤት ሆነዋል፡፡ በሴቶች የ3ሺ ሜትር መሰናክልም በተመሳሳይ ብርቱ ፉክር የተደረገ ሲሆን፤ አሸናፊዎቹ አትሌቶች በሰከንዶች ልዩነት ተለይተዋል፡፡ የመከላከያዎቹ ወርቅውሃ ጌታቸው እና አስማረች ነጋ አንደኛ እና ሁለተኛ ሆነዋል፡፡ ወርቅውሃ 9:53.23 በሆነ ሰዓት ርቀቱን ስታጠናቅቅ የክለብ አጋሯ ደግሞ በአራት ሰከንዶች ልዩነት ተከትላት ገብታለች፡፡ በተመሳሳይ ሰከንዶችን ዘግይታ የገባቸው የኦሮሚያ ደንና ዱር እንስሳት ድርጅት ክለብ አትሌቷ ሲምቦ አለማየሁም ሦስተኛ በመሆን የሜዳሊያ ሰንጠረዡን ተጋርታለች፡፡
ሌላኛው የፍጻሜ ውድድር የተደረገበት የወንዶች ዲስከስ ውርወራ የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ ገበየሁ ገብረየሱስ አሳማኝ የሆነ ብቃት በማሳየት አሸናፊ ሆኗል፡፡ ተቀራራቢ ነጥብ ያስመዘገቡት ሰይድ ሃምዳ ከቡራዩ ከተማ ተከታዩን ደረጃ ሲይዝ የመከላከያ ስፖርት ክለብ አትሌቱ ጸጋዬ ተመስገን ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ ውድድሩን አጠናቋል፡፡
ውድድሩ ዛሬ በሁለተኛ ቀን ውሎው በርካታ የፍጻሜ ውድድሮችን በማድረግ ለአሸናፊ አትሌቶች ሽልማት እንደሚያበረክትም በመርሃ ግብሩ ተጠቁሟል፡፡ በዚህም መሠረት በሁለቱም ጾታ የ100ሜትር፣ 400ሜትር፣ 800 ሜትር እና 4 በ1ሺ500 ሜትር ድብልቅ ውድድር ፍጻሜ ይካሄዳል፡፡ ሌሎች የፍጻሜ ውድድሮችም ሲካሄዱ፤ በሴቶች የከፍታ ዝላይ እና 100ሜትር መሰናክል እንዲሁም በወንዶች አሎሎ ውርወራ፣ ጦር ውርወራ እና 110 ሜትር መሰናክል የሽልማት ውድድሮች ይደረጋሉ፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 14/2014