ሳዑዲ አረቢያ በአገሪቱ መንግሥት ላይ ትችትና ተቃውሞ የሚሰነዝሩ ግለሰቦችን በፀረሽብር ሕግ ሽፋን እያፈነችና መብታቸውንም እየጣሰች ነው፣ ሲል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተቃውሞ አቅርቦባታል፡፡ የድርጅቱ የሰብዓዊ መብቶች ካውንስል (UN Human Rights Council) ሰሞኑን በጄኔቫ ባካሄደው ጉባዔ የባህረ ሰላጤዋ አገር ድርጊት ሃሳብን በነፃነት ስለመግለፅ የወጡ ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችን የሚጥስ እንደሆነ ገልጿል፡፡
ፊዮኑላ አዎላይን የተባሉ የድርጅቱ የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ባለሙያ የበርካታ አገራት የፀረ-ሽብር ሕግጋት ግራ የሚያጋቡና በግልፅ ያልተቀመጡ በመሆናቸው በፀረ-ሽብር ዘመቻ ሰበብ የግለሰቦችን ሰብዓዊ መብቶች ለመድፈር ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥሩ ተናግረዋል፡፡
‹‹እነዚህ ሕግጋት የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን፤ ምሁራንን፤ ጋዜጠኞችን፤ ደራሲያንን፤ የሃይማኖት መሪዎችንና ሌሎች በማኅበረሰቡ ዘንድ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑ ግለሰቦችን መብት ለማፈን በጥቅም ላይ የሚውሉ ናቸው›› ብለዋል፡፡ ማይክል ፎርስት የተባሉ ሌላኛው የድርጅቱ የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ባለሙያ በበኩላቸው፣ የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት በአገሪቱ ዜጎች ላይ ስለሚፈፅመው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ክትትል ሲያደርጉ እንደነበር ጠቅሰው፣ ‹‹ጉዳዩን የበለጠ አሳሳቢ ያደረገው ደግሞ ሴት የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ከሁሉም የከፋ የመብት ጥሰትእየተፈጸመባቸው መሆኑ ነው›› ብለዋል። ከዚህ በተጨማሪም፣ በመንግሥት ኃይሎች ቁጥጥር ስር የዋሉት ሁሉም ግለሰቦች የት እንደሚገኙ እንደማይታወቅም ገልጸዋል፡፡
በጉባዔው ላይ የተገኙ የሳዑዲ አረቢያና የሌሎች አገራት የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በበኩላቸው፣ የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት በቁጥጥር ስር ያዋላቸውን የመብት ተሟጋቾች እንዲለቅ ጠይቀዋል፡፡ የባህረ ሰላጤው የሰብዓዊ መብቶች ማዕከል (Gulf Centre for Human Rights) ባልደረባ የሆኑት ዘይነብ አልካዋጃ፤ የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት በቁጥጥር ስር ካዋላቸው የመብት ተሟጋቾች መካከል አንዳንዶቹ በአገሪቱ ያለውን ተባዕታይ አገዛዝ የሚቃወሙና ለፆታ እኩልነት የሚታገሉ ስመጥር ግለሰቦች በመሆናቸው እርምጃው የግለሰቦቹን እንቅስቃሴ ለመግታት የታለመ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ ማዕከሉ የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት በግለሰቦቹ ላይ የሚፈፅማቸውን የመብት ጥሰቶች በዝርዝር የሚያሳይ ሪፖርት ይፋ ማድረጉንም ዘይነብ አልካዋጃ ገልጸዋል፡፡
ኦማይማ አል-ናጃር የተባለች በስደት የምትኖር ሳዑዲ አረቢያዊት ጦማሪ፤ ሴቶች መኪና የማሽከርከር መብት እንዲኖራቸው ሲታገሉ የነበሩ ሴቶች ትግላቸው ከግብ ቢደርስም እነርሱ ግን እስካሁን ድረስ በእስራት ላይ እንደሚገኙ ጠቁማለች፡፡
‹‹ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ግፊት ካላደረገ በስተቀር እነዚህ ሴቶች ቀሪውን ዕድሜያቸውን በእስራት እንደሚያሳልፉ ግልፅ ነው›› ብላለች፡፡የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት በዜጎች ላይ እንዲህ ዓይነት እርምጃዎችን የሚወስደው ግለሰቦቹ በመንግሥት አሰራር ላይ ጥያቄ ስላነሱና ትችት ስላቀረቡ ብቻ እንደሆነ የሚናገሩት ደግሞ አርሳላን ኢፍቲቅሃር የተባሉ የሕግ ባለሙያ ናቸው፡፡ እንደባለሙያው ማብራሪያ፣ የአገሪቱ ባለስልጣናት ‹‹የፀረሽብር ሕግ›› ብለው የደነገጓቸውን ሕግጋት የሚጠቀሙባቸው የመብት ተሟጋቾችን፣ የሃይማኖት መሪዎችንና ጋዜጠኞችን ለማጥቃት ነው፡፡
‹‹ሳዑዲ አረቢያ ‹ግልፅነት ያለው የመንግሥት አሰራር እየተከተለችና በለውጥ ጎዳና እየተራመደች ነው› በሚባልበት ወቅት አገሪቱ ግን የኋልዮሽ እየተጓዘች እንደሆነመዘንጋት የለበትም›› በማለት ለአልጀዚራ ተናግረዋል፡፡ የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት የፀረ-ሽብር ርምጃዎች አሜሪካ ከመስከረም 11 ጥቃት በኋላ የወሰደቻቸውን የፀረ-ሽብር ተግባራት ያስታውሳሉ፡፡ የአሜሪካ መንግሥት በወቅቱ የወሰዳቸው ርምጃዎች በሙስሊሞች፣ በአረቦችና በደቡብ እስያ አገራት ዜጎች ላይ ያነጣጠሩ ነበሩ›› ይላሉ፡፡
እጅግ ሲበዛ አፋኝ የሕግ ስርዓት ባላት አገር ቅንጣት ታክል ገለልተኛነትና ነፃነት ይኖራቸዋል ተብለው በማይታሰቡ ፍርድ ቤቶች የሚቀርቡ የመንግሥትን አሰራር የሚነቅፉ የዚያች አገር ዜጎች ምን ዓይነት ፍርድ ሊገጥማቸው እንደሚችል ማሰብ እንደማይከብድም የሕግ ባለሙያው አርሳላን ኢፍቲቅሃር ይናገራሉ፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጄኔቫ ጽሕፈት ቤት የሳዑዲ አረቢያ አምባሳደር አብዱላዚዝ ሞ አልዋሲል፤ የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት የሚወስዳቸው ሁሉም ርምጃዎች ከሰብዓዊ መብት ጋር ተያያዥነት ካላቸው ዓለም አቀፍና ብሔራዊ ድንጋጌዎች ጋር የተጣጣሙ እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡ በሰብዓዊ መብት ጥበቃ ላይ አተኩረው የሚሰሩ ትልልቅ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና የመብት ተሟጋች ግለሰቦች ሳዑዲ አረቢያ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደምትፈፅም በተደጋጋሚ ሲገልፁ ይስተዋላል፡፡
ከወራት በፊት በቱርክ በሚገኘው የሳዑዲ አረቢያ ቆንስላ ጽሕፈት ቤት ውስጥ የተፈፀመው የጋዜጠኛ ጀማል ኻሾግጂ ግድያ የታዘዘውና የተቀነባበረው በሳዑዲ አረቢያ ከፍተኛ ባለስልጣናት ነው የሚል ሪፖርት መውጣቱ የአገሪቱ መንግሥት በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ ከባድ ተቃውሞና ውግዘት እንዲገጥመው አድርጎታል፡፡ የአሜሪካ ማዕከላዊ የስለላና የደኅንነት ተቋም (CIA) በግድያው የአልጋ ወራሹ መሐመድ ቢን ሰልማን እጅ እንዳለበት መረጃዎቼ ይጠቁማሉ ሲል፤ የሴኔቱ አባላት የሳዑዲ መንግሥት ሌሎችም አምባገነኖች መቀጣጫ የሆነ ቅጣት መቀጣት አለበት የሚል ጠንካራ አቋም ይዘዋል፡፡ ይሁን እንጂ፤ ‹‹አልጋ ወራሹ ከደሙ ንጹህ ነው›› ያሉት ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከሴናተሮቹ ጋር ውዝግብ ውስጥ በመግባታቸው የኻሾግጂ ግድያ አሁንም አነጋጋሪ እንደሆነ ቀጥሏል፡፡
ወጣቱ የሳዑዲ ንጉሳዊ መንግሥት አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ሰልማን፤ ሳዑዲ አረቢያ ካለፉት ጊዜያት የተሻለ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ምኅዳር እንዲኖራት አድርጋለሁ ብለው ቃል ከገቡ በኋላ፤ ሴቶች መኪና እንዲያሽከረክሩና ከዚህ ቀደም ተከልክለው በቆዩባቸው አንዳንድ እንቅስቃሴዎች ውስጥ እንዲሳተፉ አድርገዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም፣ ሳዑዲ አረቢያ በነዳጅ ላይ ጥገኛ ከሆነ ምጣኔ ሀብት እንድትላቀቅ የሚያስችሉ ርምጃዎችን መውሰድ መጀመራቸው ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ፤ ወትሮም ቢሆን ከሰብዓዊ መብት ጥበቃ ጋር ስሟ በበጎ የማይነሳው ሳዑዲ አረቢያ ዛሬም በመስኩ መሻሻል አላሳየችም ተብላ ክፉኛ እየተብጠለጠለች ነው፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 27/2011
በአንተነህ ቸሬ