የኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በስኬት ላይ ስኬት እየደረበ ጉዞውን ቀጥሏል። የመካከለኛውና ምሥራቅ አፍሪካ አገራት(ሴካፋ) ዋንጫን ከስድስት ሳምንታት በፊት ዩጋንዳ ላይ በማንሳት በኢትዮጵያ ሴቶች እግር ኳስ ታሪክ የመጀመሪያ ድል ያሳካው ብሔራዊ ቡድኑ ባገኘው ስኬት ሳይዘናጋ ፊቱን ወደ ዓለም ዋንጫ ማጣሪያ በማዞር በሌላ የስኬት ጉዞ መረማመዱን ቀጥሏል።
ከሁለት ሳምንት በፊት ኮስታሪካ በ2022 ለምታስተናግደው የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ሦስተኛ ዙር ጨዋታ ቦትስዋናን በሜዳዋ የገጠሙት የሉሲዎቹ ተተኪዎች 3ለ1በሆነ ውጤት በማሸነፍ ወደ አራተኛው ዙር ማጣሪያ የሚያልፉበትን እድል አስፍተው መመለሳቸው ይታወቃል።
ባለፈው አርብም የመልሱን ጨዋታ በአበበ ቢቂላ ስቴድየም አድርገው እንደተጠበቀው በሰፊ ውጤት ተጋጣሚያቸውን በመርታት የአራተኛው ዙር ማጣሪያ ተፋላሚ የሚያደርጋቸውን አስተማማኝ ውጤት አሳክተዋል።
የሉሲዎቹ ተተኪዎች የመልሱን ጨዋታ 5ለ1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ በአጠቃላይ 8ለ2 በሆነ ድምር ውጤት ስድስት ቡድኖች ወደ ሚፋለሙበት ቀጣዩ የማጣሪያ ጨዋታ አልፈዋል። የሴካፋን ዋንጫ በማንሳታቸው በትልቅ የራስ መተማመን ላይ የሚገኙት የሉሲዎቹ ተተኪዎች በዓለም ዋንጫ ማጣሪያም ድል እየቀናቸው በመሆኑ በቀሪዎቹ ሁለት የማጣሪያ ጨዋታዎች አዲስ ታሪክ ሊጽፉ እንደሚችሉ ይጠበቃል።
በቀጣዩ ማጣሪያም የታንዛኒያ አቻቸውን እንደሚገጥሙ ተረጋግጧል። ታንዛኒያ ቡሩንዲን በሜዳዋ ገጥማ 1ለ1 በሆነ አቻ ውጤት የመልሱን ጨዋታ ብታጠናቅቅም በድምር ውጤት 4ለ3 አሸንፋ ለቀጣዩ ማጣሪያ ደርሳለች።
የሉሲዎቹ ተተኪዎች በሴካፋ ዋንጫ አምስት ጨዋታዎችን አሸንፈው ቻምፒዮን ሲሆኑ፣ ታንዛኒያን 2ለ1 እና ቡሩንዲን 1ለ0 ማሸነፋቸው ይታወሳል። ይህም በቀጣዩና አራተኛው ማጣሪያ ታንዛኒያን አሸንፈው ወደ ቀጣዩና የመጨረሻው ማጣሪያ ጨዋታ የማለፍ እድል እንደሚኖራቸው ከተጋጣሚያቸው አንገጻር ሲታይ የተሻለ ግምት አሰጥቷቸዋል። የኢትዮጵያ እና ታንዛኒያ ጨዋታ በአዲሱ የፈረንጆች ዓመት ወደፊት በሚገለፅ ቀን ይከናወናል።
የሁለቱ አገራት አሸናፊ የጋና እና ዩጋንዳ አሸናፊን የሚገጥም ሲሆን ይህን ጨዋታ ማሸነፍም ወደ ዓለም ዋንጫ የማለፊያውን እድል የሚያስገኝ ይሆናል። የኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል ባለፈው አርብ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ «በውጤቱ ተደስቻለሁ፣ ጨዋታውንም እንዳያችሁት የተሻለ ነገር ማሳየት ችለናል። ነገር ግን በአጨራረስ ረገድ አሁንም ማሻሻል ያለብን ነገሮች አሉ፤ ያው ታዳጊዎችም ስለሆኑ በሥራ የሚሻሻል እና የሚስተካከል ይሆናል።» በማለት አስተያየቱን ሰጥቷል።
«በምንፈልገው መንገድ መጫወታችንም ቡድኑ ምን ዓይነት መንገድ ይዞ እየተጓዘ እንዳለ እያስመለከተን ነው ብዬ አስባለሁ።
ሌላኛው በዛሬው ጨዋታ /ባለፈው አርብ ከቦትስዋና ጋር ያደረጉትን ጨዋታ ነው/ ላይ ከሜዳችን ውጪ ከነበረን በተለየ መልኩ ታዳጊዎቻችንን ቀይረን ወደ ሜዳ በማስገባት የኢንተርናሽናል ጨዋታ ልምድ እንዲያገኙ አድርገናል። ጨዋታው 11ኛ ጨዋታቸው መሆኑን ተናግሮ፣ እስከ አሁን አንድም ሽንፈት እንዳልገጠማቸው አስታውቋል፡፡ ‹‹ይሄ በጣም ጥሩ ልምድ እንድናገኝ ረድቶናል።» ያለው አሰልጣኝ ፍሬው፣ ‹‹“ዕቅዳችን ኮስታሪካ መሄድ ነው፣ ለዓለም ዋንጫው ለማለፍ ጥረት እያደረግን ነው›› ሲል ጠቁሟል፡፡
በተጫዋቾቹ ሙሉ ዕምነት እንዳለውና በፌዴሬሽኑ በኩልም ጥሩ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን ጠቅሶ፣ ሕዝብም እስከ አሁን ሲያደርግ እንደቆየው ሁሉ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቋል፡፡
ሁለት አገራት ብቻ ከአፍሪካ በሚያልፉበት የኮስታሪካ ከ20 አመት በታች የሴቶች የዓለም ዋንጫ ጨዋታ ኢትዮጵያን ጨምሮ ስድስት አገራት ወደ ቀጣዩ ዙር ማጣሪያ ማለፋቸውን አረጋግጠዋል። ሞሮኮ ጋምቢያን በድምር ውጤት 9ለ1 በማሸነፍ ማለፏን አረጋግጣለች፤ አገሪቱን ተጋጣሚዋን በሰፊ የግብ ልዩነት በማሸነፍ ቀዳሚውን ደረጃ ይዛለች።
በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ሁለተኛ ስትሆን፣ በሴካፋው ዋንጫ ፍጻሜ በኢትዮጵያ በሜዳዋ የተሸነፈችው ዩጋንዳ ደቡብ አፍሪካን 1ለ0 በሆነ ድምር ውጤት አሸንፋ የቀጣዩ ማጣሪያ ተፋላሚ መሆኗን አረጋግጣለች።
ጋናም በተመሳሳይ ዛምቢያን በድምር ውጤት 1ለ0 ረታ የአራተኛው ማጣሪያ ተፋላሚ ነች። ሴኔጋልም ከጊኒ ጋር በድምር ውጤት 3ለ3 ብትለያይም ከሜዳ ውጪ ብዙ ግብ ባስቆጠረ ሕግ ወደ ቀጣዩ ዙር አልፋለች።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 12/2014