በጉጉት የሚጠበቀውና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋልያዎቹ ከስምንት ዓመት በኋላ የሚሳተፉበት የ2022 የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ ሊራዘም ወይም ሊሰረዝ የሚችልበት እድል ስለመኖሩ የተለያዩ ዘገባዎች ሲወጡ ከርመዋል። ካሜሩን የምታዘጋጀው ይህ 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ምእራብ አፍሪካዊቷ አገር ዝግጅቷን በጊዜ ባለማጠናቀቋ የተነሳ ውድድሩ ሊሰረዝ ወይም ከአፍሪካ ውጪ ሊካሄድ እንደሚችል ስጋት ማደሩ ይታወቃል።
ይህንን ከዝግጅት መጓተት ጋር የተያያዘ ስጋት ለመቅረፍ ካፍና ፊፋ እየተረባረቡ በሚገኙበት በዚህ ወቅት ግን ውድድሩ ሊሰረዝ ወይም ሊራዘም የሚችልበት ሌላ አዲስ ስጋት ተከስቷል። ይህም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ አዲስ ዝርያ የሆነው ‹‹ኦሚክሮን›› የተባለው ወረርሽኝ ከመስፋፋቱ ጋር ተያይዞ ሲሆን የአፍሪካ ዋንጫ በዚህ የተነሳ እንዲሰረዝ የተለያዩ አካላት ግፊት እያደረጉ ይገኛሉ።
ካፍ ከትናንት በስቲያ በቃል አቀባዩ በኩል ውድድሩ በታቀደለት ጊዜ መሰረት በካሜሩን እንደሚካሄድ ቢገልጽም፣ በዚሁ ጉዳይ ላይ የተደመደመ ውሳኔ ላይ አልተደረሰም። ሰሞኑን እየወጡ የሚገኙ መረጃዎች እንደሚጠቁሙትም ካፍ የውድድሩን እጣ ፋንታ በተመለከተ ከፊፋና ከአውሮፓ ክለቦች ማህበር ጋር መነጋገር ጀምሯል።
ካፍ ከአውሮፓ ክለቦች ማህበር ጋር በጉዳዩ ዙሪያ የሚመክረውም ማህበሩና ክለቦች በወረርሽኙ ስጋት አመካኝተው ተጫዋቾችን ለመልቀቅ ፍላጎት እንደሌላቸው እየገለጹ መሆኑን ተከትሎ ነው። በጉዳዩ ዙሪያ ታማኒ ከሆኑ የዜና ምንጮች መካከል አንዱ የሆነው የፈረንሳዩ አርኤምሲ ስፖርት ባለፈው ሳምንት ይፋ ያደረገው መረጃ ካፍ የአፍሪካ ዋንጫው መሰረዙን በመጪው የፈረንጆች ጥር ወር መጀመሪያ ይፋ ሊያደርግ እንደሚችል ጠቁሟል።
በአፍሪካ ዋንጫ ወቅት በርካታ ወሳኝ ተጫዋቾቻቸውን ስለሚያጡ ወትሮውንም ለውድድሩ አሉታዊ አስተሳሰብ ያላቸው የአውሮፓ ክለቦችና አሰልጣኞች የአፍሪካ ዋንጫው እንዲሰረዝ ወይም እንዲራዘም ካፍ ላይ ጫና ለማሳደር አዲሱ ወረርሽኝ ተጨማሪ አቅም ፈጥሮላቸዋል።
በተለይም የእንግሊዝ ክለቦች በእንግሊዝ አዲሱ ወረርሽኝ በስፋት መሰራጨቱን ተከትሎ ተጫዋቾቻቸው ወደ አፍሪካ ዋንጫው ሲሄዱም ይሁን ሲመለሱ በለይቶ ማቆያ ለረጅም ጊዜ ማጣት አለመፈለጋቸውን በመግለጽ ውድድሩ እንዲሰረዝ ጫና እያሳደሩ ይገኛሉ።
የአውሮፓ ክለቦች ማህበር ለካፍና ፊፋ በጻፉት ደብዳቤ ካፍ በአፍሪካ ዋንጫው ወቅት ወረርሽኙን በተመለከተ የሚወስደው የጥንቃቄ ርምጃ አስተማማኝ ባለመሆኑ ተጫዋቾቻቸውን ለመልቀቅ ፍላጎት እንደሌላቸው ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የወረርሽኙ ስጋት በመጪው ጥር በሚከፈተው የተጫዋቾች የዝውውር መስኮትን ሊያውክ እንደሚችል በመጠቆም ለዚህም የአፍሪካ ዋንጫ ችግሩን እንደሚያባብሰው ገልጸው ውድድሩ እንዲሰረዝ ወይም እንዲራዘም በመጎትጎት ላይ ናቸው። የአፍሪካ ታላቁ የስፖርት መድረክ የሆነው የአፍሪካ አዲስ ዘመን ስሰኞ ፖርት ይህ ቦታ ለማስታወቂያ ክፍት ነው! ዋንጫ በምእራብ አፍሪካዊቷ አገር ላይካሄድ እንደሚችል ካለፉት ሳምንታት አንስቶ በስፋት እየተነገረ እንደሚገኝ ይታወቃል።
ካሜሩን ለአህጉሪቱ ትልቅ ውድድር እያደረገች ያለችው ዝግጅት መጓተትና የውድድር ቅድመ ሁኔታን አለማሟላት ለዚህ ምክንያት ተደርጎ የተቀመጠ ሲሆን፣ የአፍሪካ ዋንጫው በካሜሩን የማይደረግ ከሆነ ካፍ ውድድሩን ኳታር ላይ ለማድረግ ቅድመ ዝግጅት እንደሚጀምር ሲነገር ቆይቷል።
የ2022 የአፍሪካ ዋንጫ በዋናነት ሊካሄድ የታሰበው በ2020 ሰኔ ወር ላይ የነበረ ቢሆንም በዚያ ወቅት በካሜሩን ያለው የአየር ጸባይ ምቹ ባለመሆኑ ጥር ላይ እንዲካሄድ ካፍ ከሁለት ዓመት በፊት ውሳኔ ላይ መድረሱ ይታወቃል።
ባለፈው ዓመትም ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስጋት ጋር ተያይዞ ውድድሩ ለሁለተኛ ጊዜ ሊራዘም እንደሚችል ተገልጿል። የካሜሩንን ዝግጅት ለመገምገም በካፍ የተዋቀረው ኮሚቴ አገሪቱ ውድድሩን ለማስተናገድ እያደረገችው የሚገኘው መሰናዶና ውድድሩ ሊካሄድ የቀረው ጊዜ እንደማይጣጣም የተገለጸ ሲሆን ፊፋም ጉዳዩን በቅርበት ለመከታተልና ዝግጅቱን ለማፋጠን ካሜሩን ጊዜያዊ ቢሮ መክፈቱ ታውቋል። ካሜሩን ይህን የአፍሪካ ዋንጫ ለማዘጋጀት ጥያቄ ባቀረበችበት ወቅት በውድድሩ የሚሳተፉ አገራት ቁጥር አስራ ስድስት ነበር።
አሁን ግን በውድድሩ የሚሳተፉ አገራት ቁጥር ወደ ሀያ አራት አድጓል። ይህም ካሜሩንን ተጨማሪ ስቴዲየሞች የመገንባት ግዴታ ውስጥ አስገብቷታል። የተሳታፊ አገራት ቁጥር አስራ ስድስት እያለም የመክፈቻ ጨዋታውን በሚያስተናግደው ስቴዲየም ግንባታ ዙሪያ የተለያዩ ውዝግቦች ሲነሱ እንደነበር ይታወሳል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 11/2014