ዛሬ ሁለት ተቃራኒ ተግባራትን አንስተን ሀሳብ የምንለዋወጥሲሆን፤ በዋናነት “አልሚ” እና “አውዳሚ”ነትን ይዘን፤ መሰረታዊ ችግሩ ድንቁርና መሆኑን እያመለከትንና እያመላከትን እንዘልቃለን።
ጉዳያችን ትምህርት ነውና በተለይ “አውዳሚነት” በትምህርትና ሂደቱ ላይ ያደረሰውንና እያደረሰ ያለውን የከፋ በደል በመረጃዎች እያስደገፍን እንቃኛለን። በሂደቱም የምእራቡን ዓለምና የምስራቁን ዓለም ተቃርኖዎች እንመለከታለን።
ማን ከማን ጎን እንደቆመ፤ ማን ከማን ጀርባ እንደ ተሰለፈም ከመረጃዎቻችን ተነስተን እንጠቁማለን። በአገራችን ላለው፣የዚህ ሁሉ ችግር ባለቤትና የአንበሳውን ድርሻ ወሳጁ የሽብር ቡድኑ መሆኑንም በግልፅ እናሳያለን። ከአወደመውና የወደመው እንጀምር። እንደ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ማተቤ ማንደፍሮ ሰሞንኛ ማብራሪያ በአማራ ክልል የመምህራን ኮሌጆችና የቴክኒክና ሙያ ተቋማትን ጨምሮ 4 ሺህ 107 ትምህርት ቤቶች በአሸባሪው ሕወሓት ቡድን ወድመዋል።
ከአንድ ነጥብ ስምንት ሚሊየን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ተፈናቅለዋል። 11 ሺህ 600 መምህራን ደግሞ ከስራ ውጪ ሆነዋል፡፡ በያዝነው ወር መግቢያ ላይ፣ በሸባሪው ሕወሓትበክልሉ ያወደማቸው የትምህርት ተቋማትን መልሶ ለመገንባት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ አገር አቀፍ ውይይት በባህር ዳር ከተማ በተካሄደበት ወቅት እንደተገለፀው በአማራ ክልል ብቻ በሕወሓት የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ ሥራ ለማስጀመር ከ11 ቢሊየን ብር በላይ ያስፈልጋል።
ይህ እንግዲህ መረጃውን ወቅታዊ ከማድረግ አኳያ ሌላ ተጨማሪ ጥናት የማስፈለጉ ጉዳይ እንዳለ ሆኖ ማለት ነው። ለምሳሌ ከዚህ ይፋዊ መረጃ በኋላ አረመኔው የሽብር ቡድን በወሎ ዩኒቨርሲቲ ላይ የከፋ በደል ፈፅሟል።
ያወደመውን ንብረት ብቻ እንኳን ብንወስድ በትንሹ 10 ቢሊዮን ብር ($200 ሚሊዮን) የሚገመት መሆኑ የሰሞኑ አውራ የዜና ርእስ ሆኖ ሰንብቷል። ሌላም ሌላም …. ይህ ጥሬ መረጃ የአንድ ክልል ብቻ መሆኑን ይዘን፤ መጠኑ ይለያይ እንጂ በሽብር ኃይሉ አማካኝነት የደረሰው የትምህርት ተቋማት ውድመት በሌሎች ክልሎች አልደረሰም ማለት አይደለም። በተለይ በአፋር ክልል፣ ከአማራ ክልል ያልተናነሰ ውድመት በትምህርት ተቋማት ላይ እንደሚደርስ ለማንም ግልፅ ነውና አንዱ ያለማውን ሌላው እያወደመ የት ድረስ አብሮ መሄድ እንደሚቻል ለጊዜው ግልፅ አይደለምና ጉዳዩ ያሳስባል።
(እዚህ ጋ “ከአውዳሚው ጀርባ ማን አለ?” የሚለው ጥያቄ ሁሌም መነሳት አለበት። ካልሆነ ርእሰ ጉዳያችን ይዛባልና አጉል ነው። ጌታቸው ረዳ ሰሞኑን “አሜሪካ ነች እንደዚህ እንድናደርግ ……” ያለውንም ለታሪክ ሲባል ማስታወስ ይገባል።) ይህ ቡድን እንደ አለመታደል ሆኖ፣ አፈር ነህና ወደ አፈር … እንደ ተባለው ተመልሶ ወደ ደደቢት አመራ፤ ተመልሶ እዛው አውዳሚነት ተግባሩ ውስጥ ገባ እንጂ ተቋሞቹን የገነባቸው እሱ እራሱ በዘመነ መንግስቱ ነበር።
የትምህርት ጥራትን፣ ተደራሽነትን ….. ሰማየ ሰማያት አድርሻለሁ በማለት የፖለቲካ ትርፍ ለማጋበስ ሲጠቀምበት ቢኖርም፤ ዞሮ ዞሮ የገነባቸው እሱ ነው። ግን ምን ያደርጋል፣ እራሱን በራሱ አመድ አፋሽ አደረገና አረፈው። ለነገሩ ፀረ ትምህርት ተቋማት መሆን ምንም አይነት ምርምር ሳያስፈልገው፣ ፀረ ትምህርት መሆን ነው። ፀረ ትምህርት መሆን ማለት ደግሞ፣ አሁንም ምንም አይነት ጥናት ሳያስፈልገው፣ አፍቃሪ ድንቁርና መሆን ማለት ነው። አገርን ለባእድ አሳልፎ መስጠትና ከጠላት ጎን በመሰለፍ ወገንን መውጋት፣ ወገንን ማድማት የድንቁርና ሰለባ ከመሆን እንጂ ከሌላ ከየትም ሊመጣ አይችልም።
አሸባሪነትና አውዳሚነት ደግሞ መነሻውም ሆነ መድረሻው፤ ስረመሰረቱ ድንቁርና ነውና እያየን ያለነው ይህንኑ ነው። እዚህ ላይ በቀጥታ ጦርነቱ (ጦርነቱ እጅ አዙር (ባለሙያዎች “ዌስተርን ፕሮክሲ” ይሉታል) አይደለም አልተባለም) ምክንያት የደረሰውን ውድመትና መስተጓጎል አነሳን እንጂ በእነ ሸኔ አይነቱ የሽብር ቡድኑ ተላላኪ በኩል ተመሳሳይ ፀረ ትምህርት ተግባር አልተፈፀመም ማለት አይደለምና ሁሉም በበቂ ሁኔታ ተጠንቶ ሲቀርብ በአጠቃላይ አገሪቱ የደረሰውን ውድመት የምናየው ሆኖ፣ ለጊዜው ግን አንዱ ሲያለማ ሌላው እያወደመ መሆኑ ላይ ተስማምተን እንቀጥል። (እንደገና ለማስታወስ፣ ከማልማቱ ጎን፤ እንዲሁም፣ ከማውደሙ ጀርባ እነማን እንዳሉ ለአፍታም ቢሆን መርሳት አይገባምና ምእራቡን ከምስራቁ እያነፃፀርን እንቀጥል።) በአሜሪካ የሚሾረው የምእራቡ ዓለም ፊቱን በእኛ
ላይ አዞረ ማለት ዓለም በኢትዮጵያ ላይ ፊቱን አዞረ ማለት አይደለም። ከምእራቡ ጨለማ በተሻለ የምስራቁ ብርሀን የወደ ፊቱብሩህ ተስፋነውና ኢትዮጵያ ከወደ ምስራቁ ዓለም ወዳጆች አሏት። ሁሌ መክዳት ልማዱ በሆነው ምእራቡ አለም ስትከዳ የኖረችው ኢትዮጵያ ብርሀኗ ሲፈነጥቅ የኖረው ከምስራቁ በኩል በምትወጣው ፀሀይ ነበርና ምእራቡ የሚያደርገውን ሁሉ ቢያደርግ የባህርይው ነውና አይደንቅም። (በኢትዮ-ሶማሌ ጦርነት እነማን በኢትዮጵያ ላይ፣ እነ ማን ለኢትዮጵያ ….. እንደነበሩ ማስታወሱ ብቻ በቂ ነው።) ወደ ማልማቱ እንምጣ። የታደሉ፣ በግለሰብ ደረጃ እንኳን፣ ቤታቸውን፣ ቦታና ንብረታቸውን ለትምህርት ተቋማት ሲሰጡ እንጂ የተገነባውን ሲያወድሙ አይታዩም ነበር።
ዛሬ ግን፣ የገዛ ወገኑና እወክለዋለሁ የሚለው ክፍል ሁሉ የሚማርባቸውን የትምህርት ተቋማት ቤንዚን አርከፍክፎ አጋያቸው። በታንክ ደመሰሳቸው። የቀሩትንም ዘረፋቸው። ይህ ሁሉ ሲሆን አሜሪካና አሜሪካ መራሹ የምእራቡ ዓለም ከጀርባው አለ። “አለ” ስንል በግምት ሳይሆን በመረጃ፤ መረጃውም የጆ ባይደን አስተዳደር ይህ ሁሉ ሲሆን እያየና እየሰማ የሽብር ቡድኑን የአውዳሚነት ተግባር “ያልተረጋገጠ” (አንኮንፊርምድ) ሲል ማላገጡና ከሕወሓት በላይ ሕወሓት፣ ከአሸባሪው በላይ አሸባሪ ሆኖ መገኘቱ ነው።
ስለ ምእራቡ ማውራታችን ይብቃና ወደ ምስራቁ እንሂድ። ሄደንም ከወዳጆቻችን ቀዳሚ የሆነችውን ቻይናን እናንሳና ከሚወድመውና ከሚያወድመው በተቃራኒ ምን እየሰራች እንደሆን እንመልከት። ማስረጃ ይሆነን ዘንድም የቻይና መንግስትና ተቋማት፣ እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ (በሌሎች የአፍሪካ አገራትም ጭምር) በትምህርቱ ዘርፍ የሰሩትንና እየሰሩ ያሉትን ከተገቢ ምንጮች ጠቅሰን እንመልከት። በኢትየጵያ ሕጋዊ እውቅና አግኝተው የሚንቀሳቀሱ ተቋማትን ከሚመሩ፣ ከሚያስተባብሩና በስራ ላይም ከሚያውሉ ወገኖች (ዝቅ ብለን የምንጠቅሳቸው) ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው የቻይና መንግስትና ተቋማቱ በትምህርቱ ዘርፍ በርካታ አስተዋፅኦ አድርገዋል፤ እያደረጉም ነው። (በርካታ የቻይና መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በተለያዩ ሰብአዊ ተግባራት በመሰማራት የተለያዩ ስራዎችን በማከናወን ላይ መሆናቸውን በተመለከተ በተለያዩ ዝግጅቶቻችን መግለፃችን ይታወሳል።
ከእነዛ ውስጥም የተወሰኑ መረጃዎችን (ዳታ) በዚህ ጽሑፍ ውስጥ መጠቀማችን መግለፅ ተገቢ ነው።) ከተደረጉት ድጋፍና እገዛዎች መካከል የሚከተሉትን መጥቀስ ይቻላል። በ”ኢትዮጵያ ፓንዳ ፓክ ፕሮጀክት” የታቀፈና ላለፉት ሶስት ዙሮች ተግባራዊ ሲደረግ ቆይቶ የተጠናቀቀ ፕሮግራም በድምሩ 118 ሺህ የተማሪ ቦርሳዎችን ማደሉን፤ በ2012 ዓ.ም 43 ሺህ፣ በ2013 ደግሞ 55 ሺህ፤ እንዲሁም ዘንድሮ 2014 የትምህርት ዘመን 20 ሺህ ዘመናዊ ቦርሳዎችን በትምህርት ሚኒስቴር በኩል ለተማሪዎች አድርሷል።
ሲ.ኤፍ.ፒ.ኤ (CFPA) የተባለው ጃንጥላ ድርጅት በስሩ በሚገኙ የተለያዩ ድርጅቶች አማካኝነት እስከ 2020 መጨረሻ ድረስ RMB 24.17 ሚሊዮን (የቻይና ገንዘብ) በጀት መድቦ እየተንቀሳቀሰ ሲሆን፤ በአጠቃለይም 130 ሺህ ዜጎችን ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓል። የቻይና ኮንስትራክሽን ኩባንያ ከሆነው XCMG ጋር በመተባበር እየተከናወነ ያለው ትምህርትና ተማሪዎች ላይ ያተኮረ ፕሮጀክትም ለአራት ዓመታት የሚዘልቅ ሲሆን በአጠቃላይም $16.8 ሚሊዮን በጀት ተይዞለት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።
በሌላ ፕሮግራምም በስፕላሽ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ (Splash International Ethiopia) ፕሮጀክትም በመጀመሪያው ዙር የተማሪዎች በትምህርት ቤት ንፅህና አጠባበቅና ንፁህ ውሀ ተጠቃሚነት ፕሮጀክት (School Wash Project) በአዲስ አበባ የሚገኙ 20 የመንግሥት ትምህርት ቤቶች እድሉን ማግኘታቸውን፤ 23 ሺህ ተማሪዎችም የፕሮጀክቱ ተጠቃሚ አድርጓል። የ”ቻይና ፋውንዴሽን ፎር ፖቨሪቲ አሊቬሽን የኢትዮቢሮው (CFPA Ethiopia office) በኢፌዴሪ ሲቪል ማህበረሰቦች ኤጀንሲ መንግስታዊ ባልሆነ ድርጅት ስም ጁላይ 1 ቀን 2019 (ሰኔ 24 2011) ተመዝግቦ ሕጋዊ እውቅና በማግኘት ወደ ስራ የገባ ሲሆን ከ2016 ጀምሮ በርካታ ስራዎችን እየሰራ ሲሆን፤ በስሩም የተለያዩ (ፓንዳ ፓክ ፕሮጀክት፣ የትምህርት ቤት ምገባ፣ ስኩል ዋሽ ፕሮጀክት፣ የሴቶች ኢኮኖሚያዊ መጎልብ ፕሮግራም እና የመሳሰሉትን) ፕሮጀክቶችን ያካተተ፤ በአይነቱም ለየት ያለ ሲሆን በተለይ እኛ ድርጅቱ ሰፊ ልምድ ያለውና ቻይና ከድህነት የወጣችበትን መንገድ ልንጠቀምበትና ልምዱንም ልንወስድ ይገባል ያሉን በኢትዮጵያ የፕሮግራም ማናጀር አቶ ቢኒያም ወርቁ ናቸው። አቶ ቢኒያም እንደሚሉት በዚህ ፕሮጀክት ኢትዮጵያ ተጠቃሚ እየሆነች ነች። ለምሳሌ ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ ከ100 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል። ቻይናዎቹም ይህንን ሲያደርጉ ደስተኞች ናቸው።
የስፕላሽ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ (Splash International Ethiopia) ካንትሪ ዳይሬክተር አቶ ቀልቤሳ ዳባ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለፁት ፕሮጀክቱ በከተማዋ በሚገኙ ሁሉም የመንግስት ትምህርት ቤቶች የሚከናወንና ከ500 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ አቅዶ የሚሰራ ሲሆን፤ ይህ እንደተጠናቀቀም ፕሮጀክቱ ወደ ሌሎቹ የአገሪቱ ክፍሎች የሚስፋፋ (በአማራ ክልል ተጀምሯል፤ በተፈጠረው ችግር ምክንያት ቢቀዛቀዝም) እና ተማሪዎችንና የየትምህርት ቤቶቹን ማህበረሰብ በሙሉ ተጠቃሚ የሚያደርግ ይሆናል። ከአቶ ቀልቤሳ ዳባ እንደተረዳነው የሁለቱ አገራት ግንኙነት ከምእራቡ ዓለም ይልቅ ከቻይና ጋር ያላት ግንኙነት የተሻለ መሆኑን ያሳያል።
ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ያላት ግንኙነት ከእርዳታ እንድትላቀቅ እንጂ ጠባቂ እንድትሆን እያደረጋት አይደለም ያለው። በመሆኑም “ከቻይና ጋር ያለንን ግንኙነት ጠበቅ ማድረግ ነው ያለብን። ምክንያቱ ደግሞ ከግንኙነቱ ተጠቃሚ መሆናችን ነው።” (እዚህ ላይ የአቶ ቀልቤሳን ሀሳብ እንድንቀበል የሚያደርገን የግራሐም ሐንኮክን “Lords of Poverty” ድንቅ መጽሐፍ ስናስታውስ ነው።) አቶ ቀልቤሳ በዚህ ብቻ አላበቁም። በቅርብ ከሚያውቁትና ከሚከታተሉት ተግባር ተነስተው እንደሚመክሩት ከሆነ መንግስት፣ ትምህርት ቢሮዎች፣ የከተማ ነዋሪዎች፣ ሌሎች የትምህርት ተቋማት፣ አጠቃላይ ማህበረሰቡ ከቻይና በሚገባ መጠቀም ነው ያለበት።
ከልምድ እንደታየው ከእነሱ ብዙ ነገር ማግኘት ይቻላል። የ”ቻይና ፋውንዴሽን ፎር ፖቨሪቲ አሊቬሽን የኢትዮጵያ” ፕሮግራም ማናጀር አቶ ቢኒያም ወርቁም ከዚሁ ከአቶ ቀልቤሳ ጋር ተቀራራቢ የሆነ መልስ ነው የሚሰጡት። አቶ ቢኒያም እንደሚሉት የሁለቱ አገራት ግንኙነት በጣም ጥሩ ሁኔታ ላይ ነው የሚገኘው። ይህ ደግሞ ተጠናክሮ ነው መቀጠል ያለበት። የቻይና እዚህ መምጣትና በተለያዩ ዘርፎች ላይ መሰማራት ኢትዮጵያን በጣም ነው የጠቀማት። የልምድ ልውውጥንና የቴክኖሎጂ ሽግግርን በተመለከተ፣ እኔ ባለሁበት ዘርፍ የአገራችን ተጠቃሚነት ነው ያለው።
የእውቀት ሽግግርም አለ፤ በእርግጥ ውጤቱ ባንዴ ባይታይም ብዙ ልምድ እየወሰድን ነው። ባጠቃላይ ቻይና ከምታደርገው ድጋፍና ትብብር አገርም ሆነ ህዝቡ እየተጠቀመ ነው። በርካታ ፕሮጀክቶችና ብዙ መዋእለ ንዋይም መድበው እየሰሩ ከመሆኑ አኳያ ተጠቃሚዎች ነን። ቻይናዎች ማቀድ፣ ያቀዱትንም ተግባራዊ ማድረግ ላይ ጠንካሮች ናቸው።
ይህንን እኛም ከእነሱ መውሰድ ነው ያለብን። ምናልባት የዛሬ 20 እና 30 ዓመት እንደርስበታለን ብለው ያቀዱትን ላዬ የወደፊቱ የዓለም መነጋገሪያ እንደሚሆን ከወዲሁ የታወቀ ነው። እኛም ከእነሱ በጣም ብዙ ብዙ መማር አለብን። ከእነሱ አገር በበለጠ ብዙ እድሎች ያሉን እኛ ነን። ለምሳሌ እዚህ ዓመቱን ሙሉ መስራት ይቻላል። ሀብት/ሪሶርስ አለ። የምእራቡ ዓለም ሚዲያ የሚያሰራጨውን የሀሰት ፕሮፓጋንዳ በተመለከተ እዚህ ባሉት ቻይናዊያን ዘንድ ምንም የተፈጠረ ብዥታም ሆነ ግርታ የለም። ያለውን አጠቃላይ ሁኔታ ከእኛው እኩል ስለሚያውቁት ምንም አይነት መረበሽ አልታይባቸውም። እርግጥ እዛ፣ ቻይና ባሉት ዘመድ ወዳጆቻቸው ዘንድ ትንሽ የመረበሽ ሁኔታ ነበር ማለት ይቻላል።
ምክንያቱም ወደ እዚህ እየደወሉ “እንዴት ናችሁ?” ይሏቸው ነበር። እሱም ቢሆን ብዙ አልሄደም፤ ከዚህ በሚሰጧቸው መልስ ምክንያት ወዲያው ነው የተረጋጋው። ከዛ ውጪ ሁሉም የምእራቡ ዓለም መሰረት የሌለው ወሬ በሚገባ ገብቷቸዋል፤ በመሆኑም በስራችን ላይ ምንም የፈጠረው መሰናክልም ሆነ እንቅፋት የለም። ስራችን በታቀደው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ነው ሲሄድ የቆየው፤ እየሄደም ያለው። በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዋና ጸሐፊ ኬ ሊዮ በSchool Panda Packs (ለተማሪዎች የቦርሳ ስጦታ) ፕሮግራም ላይ ተገኝተው እንደተናገሩት ቻይና በኢትዮጵያ የምታደርገው ሁሉን አቀፍ ድጋፍም ሆነ ትብብር ከዚህ መለስ ሳይባል የሚቀጥል ነው።
ባጠቃላይ፣ የትምህርቱን ዘርፍ ውጤታማ ለማድረግ ሌት ተቀን የሚለፉ ወገኖች እንዳሉ ሁሉ በዛው ልክ በሽብር ተግባር ላይ ተሰማርተው የትምህርት ተቋማትን ቀዳሚ ታርጌታቸው አድርገው የሚያወድሙ ድኩማኖች እያየን ነው። ምንም ሆነ ምን፣ የትምህርትን ዘርፍ ማልማቱ ይቀጥላል፤ አውዳሚውን ማውደሙም ይቀጥላል።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 11/2014