የዛሬ 61 ዓመት ታኅሳስ ወር የመጀመሪያው ሳምንት በኢትዮጵያ የለውጥ አየር ሽው ብሎ ነበር። ይህም የለውጥ አየር በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት ላይ የተካሄደው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ነው። ከ1966 ዓ.ም አብዮት በፊት ዙፋኑን ክፉኛ ያናጋ ተቃውሞ ቢኖር ይሄው ታኀሳስ 4 ቀን 1953 ዓ.ም የተካሄደው መፍንቅለ መንግሥት ሙከራ ነበር።
በወቅቱ ንጉሡ ከብራዚል ፕሬዚዳንት በቀረበላቸው የጉብኘት ጥሪ ወደ ብራዚል ሄደው ነበር። አጋጣሚውን ሲጠባበቁ የነበሩ ከፍተኛ የጦር ባለስልጣናት መፈንቅለ መንግሥት አደረጉ፤ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከረውን ያቀነባበሩት ሁለት ወንድማማቾች መንግስቱ እና ገርማሜ ነዋይ ናቸው።
በተለምዶ የታኅሳስ ግርግር በሚል የሚታወቀው ይህ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ የአንድ ሳምንት እድሜ ብቻ ነበረው። በመፈንቅለ መንግሥቱ በአዲስ አበባ ነዋሪዎች የማይታወቁ በርከት ያሉ የጦር አውሮፕላኖች በከተማዋ ሰማይ ላይ ታይተዋል፤ የተኩስ እሩምታ ከተማውን ፋታ ነስቷታል፤ከጣሊያን ጦርነት በኋላ ለተኩስ እሩምታ እንግዳ የነበሩ ነዋሪዎች ተጨናነቁ፤ ከተወሰኑ ቀናት በኋላ በንጉሡ ዙፋን ደጋፊዎች ድል አድራጊነት የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው ከሸፈ። የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው ቢከሽፍም ለጦር አውሮፕላኖች ጋጋታ ለተኩስ እሩምታ እንግዳ የሆነው ከተሜ ወቅቱን የታኅሳስ ግርግር በሚል ጠራው።
ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ በኢትዮጵያ ታሪክ መጽሐፋቸው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራውን ከ1966ቱ አብዮት በፊት ዙፋኑን ክፉኛ ያናጋ ተቃውሞ ሲሉ ገልጸውታል። ሙከራው ባይሳካም፣ በሀገሪቱ የፖለቲካ ተቃውሞ በታሪክ ወሳኝ የሆነ ምዕራፍ ብለውታል። ሙከራውን ያቀነባበሩት ሁለቱ ወንድማማቾች መንግስቱ እና ገርማሜ ነዋይ ከ1953 በፊትም ሆነ በኋላ የታየውን የተቃውሞውን ሁለት ገጽታዎች ማለትም ወታደራዊና ሲቪላዊ ገጽታዎች የሚያንጸባርቁ ናቸው ሲሉም በመጽሐፋቸው ይገልጹታል።
ብርጋዲየር ጄኔራል መንግሥቱ ንዋይ የጥቁር አንበሳ ድርጅትን መሥርተው በጣልያን ወረራ በአርበኝነት የተፋለሙ ናቸው። ንጉሡ የጣልያን እንቅስቃሴ ስላሰጋቸው በ1927 ዓ.ም የመጀመሪያው ዘመናዊ መደበኛ ወታደራዊ የሆለታ ገነት ጦር ትምህርት ቤት ሲመሠርቱ ከተመራቂዎቹ አንዱ ነበሩ ፤ ሥልጠናውን ባይጨርሱም በነበራቸው ብቃት እሳቸው በመቶ አለቃ ከበደ ገብሬና ሙሉጌታ ቡሊ በሻለቃ ማዕረግ እንደተመረቁ ሰነዶች ያስረዳሉ።
ገርማሜ ንዋይ የተቃውሞ ክብረ ወሰኑ ብዙም የማያጠያይቅ፤ ከጣልያን ወረራ በፊት ከነበሩት ተራ ማጅ ምሁራንና ከ1950ዎቹ ለውጥ ፈላጊ ተማሪዎች መካከል ድልድይ ነበረ ሲሉ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ በመጽሐፋቸው ይጠቅሱታል። በአሜሪካም የመጀመሪያ ዲግሪና 2ኛ ዲግሪውን አግኝቷል።
ገርማሜ ቀደም ካሉት ምሁራን የሚለየው በሁለት ነገሮች ነው። ውጭ አገር ቆይቶ አንዳንድ ነገሮች ቀስሞ መመለስ እንዲሁም ፣መደበኛ ትምህርት ተከታትሎ ለእዚህም ምስክርነት ዲግሪውን ይዞ መመለሱ ነው። በዚህም የወደፊቱን አቅጣጫ የሚተልም ነበር።
አሜሪካ በነበረበት ጊዜ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማህበር ፕሬዚዳንት ከመሆኑም በላይ ከተመለሰም በኋላ የኮተቤን ምሩቃን በስውር አሰባስቦ ማህበር በማቋቋም የዚሁ ማህበር ፕሬዚዳንት ሆኖ ተመርጧል። ዞሮ ዞሮ ግን የቀድሞዎቹ ምሁራን ለውጥ ለማምጣት የተራማጅ መስፍንን ተገን እንደፈለጉ ሁሉ ግርማሜም የወንድሙን ሰራዊት ለዚሁ ተግባር ማዋል ነበረበት።
ወደ አገሩ ሲመለስ በደጃዝማች መስፍን ስለሺ ሥር የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሆኖ ተሾመ። በወቅት ደጃዝማች መስፍን የከፋ አስተዳዳሪ በነበሩባቸው ዓመታት ሠፊ የቡና መሬት በሕገወጥ መንገድ ይዘው፤ ምርቱ ሲደርስ ወኪሎቻቸውን ልከው ቡናውን አዲስ አበባ አስመጥተው በቡና ቦርድ በኩል ይሸጡ ነበር።
ገርማሜ ንዋይ በሕገወጥ ሥራቸው ሀብት ያካበቱትን ሚኒስትር ጠላቸው። የመፈንቅለ መንግሥቱ ጽንሰ ሃሳብ የገርማሜ መሆኑን ይጠቀሳል፤ በተሾመባቸው ቦታዎች በባህርዩ በከፍተኛ ኃላፊነትና በመቆርቆር ስሜት ይሠራ ነበር፤ በዚህም ቦታዎቹን «የፍትሐዊ አስተዳደር ሙከራ ጣቢያ » እንዳደረጋቸው የባህሩ ዘውዴ የኢትዮጵያ ታሪክ መጽሐፍ ይጠቅሳል። መፈንቅለ መንግሥቱ የተጠነሰሰው ህዝቡን በቅንነት ለማገልገል በመሻት መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።
በተመሳሳይ ሀሮልድ ማርኩስ በጻፉት መጽሐፍም ገርማሜ የወላይታ አካባቢ አስተዳዳሪ ሆኖ ሲሾም በባላባቶች የተያዘውን መሬት ነጥቆ ለገበሬው አከፋፈለ። በድርጊቱ ንጉሡ ተቆጡ በአዲስ አበባም ጠርተው አነጋገሩት። እሱም እንደግዛት አስተዳዳሪነቱ መሬት አልባ የሆነውን ጭቁን ገበሬ ችግር መቅረፍ ግዴታ እንዳለበት ተናገረ። ንጉሡ ገርማሜን ወደ የሶማሌን ግዛት እንዲያስተዳድር ወደ ጅጅጋ ላኩት። በሶማሌም የውሃ ጉድጓድ በማስቆፈር ክሊኒኮችን ትምህርት ቤቶችን እና መንገዶች አስገንብቷል። በዚያም በብልሹ አሠራር የተዘፈቁ ሹማምንት ለሕግ ለማቅረብ ብልሹ አሠራርን በማስወገድ ለውጥ አመጣ።
እርምጃው በርካታ ሹማምንትን በማስቀየሙ አዲስ አበባ ተጠርቶ ነበር። በጅጅጋና በወላይታ የነበረውን ሁኔታ የታዘበው ገርማሜ ችግሩ በዘላቂነት የሚወገደው የሥርዓት ለውጥ ሲመጣ ብቻ ነው ሲል ደመደመ።
መፈንቅለ መንግሥቱ ከመካሄዱ ሁለት ዓመታት በፊት አነስተኛ አባላት ያሉት ቡድን አዋቅሮ ነበር። ቡድኑ የክብር ዘበኛ አዛዥ በነበሩት ብ/ጄኔራል መንግሥቱ ንዋይ መኖሪያ ቤት ይሰበሰብ ጀመር ። የንጉሡን ወደ ውጭ መሄድ ተከትሎ ታኅሳስ 4 ቀን 1953 ዋና ዋና ሚኒስትሮችና መሳፍንቱ ለደህንነት በሚል ተጠርተው የተወሰኑ ሚኒስትሮች፣ ንግሥቲቱ፣ አልጋ ወራሹና በርካታ መሳፍንት ተያዙ።
ክስተቱ ላይ አተኩረው የጻፉት የታኀሳስ ግርግር እና መዘዙ እንዲሁም ገድለ መፈንቅለ መንግሥት መጽሐፎችም በማግስቱ አልጋ ወራሸ አስፋወሰን በኢትዮጵያ ሬድዮ ጣቢያ ባደረጉት ንግግር የሥርዓቱን አስከፊነት እና የለውጥ አስፈላጊነትን አስረግጠው ጠቅሰው፣ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ በሚቆረጥልኝ ደመወዝ ብቻ ሀገሬንና የኢትዮጵያን ህዝብ ፍጹም በሆነ ቅን ልቦና ለመሥራት ወስኛለሁ ያሉ ሲሆን ህዝቡ አዲስ ከተቋቋመው መንግሥት ጎን እንዲቆም ጥሪ አስተላለፉ ሲሉ ይጠቅሳሉ። አልጋወራሹ ይህን የተናገሩት ተገደው ነው ፣ በማግባባት የሚሉ መረጃዎችም አሉ።
በዚህም ታኅሳስ 5 በራስ እምሩ ኃይለሥላሴ ጠቅላይ ሚኒስትርነት የሚመራ መንግሥት ሲመሠረት ጄኔራል ሙሉጌታ ቡሊ የጦር ኃይሎች ኤታማዦር ሹም ሆነው ተሰየሙ።
ወንድማማቾቹ ሙከራውን ለህዝብ ሲያስተዋውቁ ለማስተላለፍ የፈለጉት አቢይ መልእክት ኢትዮጵያ በቅርብ ነጻ ከወጡት የአፍሪካ አገሮች ጋር እንኳ ስትነጻጸር ምን ያህል ወደ ኋላ አንደቀረችና የመፈንቅለ መንግሥቱም ሙከራ የአገሪቱን የቀድሞ ዝናና ክብር ለማደስ ነው ሲሉ መግለጻቸውን የፕሮፌሰር ባህሩ መጽሐፍ ያትታል።
እንደ አሜሪካ ያሉትን የቃል ኪዳን ጓደኞች ለማረጋጋትም ይመስላል በውጭ ግንኙነት በኩል ለአገሪቱ ያደረገችውን ስምምነቶች እንደሚያከብሩ የአጼው መንግሥት የሚከተለውን ፖሊሲም እንደሚ ቀጥሉ ማረጋገጫ ሰጥተዋል። የሰፊው ህዝብ ብሶት የቆረቆራቸው መሆኑን በመግለጽም ፋብሪካዎች ለማቋቋምና ትምህርት ቤቶች ለመክፈት ቃል ገቡ። ይሁን እንጂ ሰፊውን ህዝብ ባንደኛ ደረጃ የሚመለከተውን የመሬት ጥያቄ በአግባቡ አላተኮሩበትም።
የዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ተማሪዎችም አማጺያኑን በመደገፍ ሰልፍ ወጡ። በንጉሡ አስተዳደር ድሃው እየተበዘበዘ አድኃሪው ሀብት ማካበቱን በመጥቀስ፤ የተማረው ኃይል አገሪቱን መምራት እንዳለበት አሳሰቡ። ድምጻቸውን ከፍ አድርገው መፈክር እያሰሙ ወደ ቤተመንግሥት አቅጣጫ ተመሙ። ወታደሮች ተማሪዎቹን ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ አዘዙ።
የወታደሮቹ ቁርጠኛ እርምጃ ያሰጋቸው መምህራን (ተማሪዎቹን ለሰልፍ ያነሳሱ ናቸው የሚሉ መረጃዎች አሉ) በማግባባት ተማሪዎቹን አስመለሱ። የተማሪዎቹ መሸነፍ የመፈንቅለ መንግሥቱ መክሸፍ ምሳሌ ነበር ሲል የሀሮልድ ማርክስ መጽሐፍ ያስረዳል።
በዚሁ ቀን ታኅሳስ 6 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዑ ወቅዱስ አቡነ ባስልዩስ መፈንቅለ መንግሥቱን በመቃወም ለህዝቡ መልክታቸውን በማስተላለፍ ድርጊቱን አወገዙ። ህዝቡ የንጉሡን ዘውድ እንዲጠብቅና ከንጉሡ ጎን እንዲቆም የሚጠይቅ ወረቀት በአውሮፕላን አዲስ አበባ ላይ ተበተነ። በዚሁ ቅጽበት አንድ የጦር ጄት በመፈንቅለ መንግሥቱ መሪዎች ይዞታ ላይ ቦምብ ጣለ።
አማጽያኑ ዓላማቸው እንደከሸፈ ተረድተው ከወታደሩ ጋር ለመደራደር ቢጠይቁም፣ ተቀባይነት ሳያገኙ ቀሩ። ድርድሩም ሳይጀመር 15 የሚደርሱ ታጋቾች ታስረውበት በነበረው በያኔው የቀዳማዊ ኃይለስላሴ መኖሪያ ገነተ ልኡል ቤተመንግሥት በመፍንቅለ መንግሥቱ መሪዎች ተረሸኑ።
ታኅሳስ 7 ቀን ጀምሮ በለውጥ ፈላጊ የክቡር ዘበኛ ጦር አባላት እና በአጼ ኃ/ስላሴ ዙፋን ደጋፊ የምድር ጦር አባላት ከፍተኛ ውጊያ በአዲስ አበባ ተደረገ። ውጊያውም በንጉሡ ደጋፊዎች ድል አድራጊነት ተጠናቀቀ። የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራውም ከሸፈ። የመፈንቅለ መንግሥት ዋና ተዋንያንም ዓላማቸው እንደ ተጨናገፈ ሲረዱ ከአዲስ አበባ ለመሰወር ሙከራ አደረጉ።
የመፈንቅለ መንግሥቱ መሪ ሌ/ኮሎኔል ወርቅነህ ገበየሁ ለትንሽ ቀናት በአዲስ አበባ ቀጨኔ መድኃኒዓለም አካባቢ ተደብቀው ነበር፤ በመጨረሻ ለጦር ሠራዊቱ በደረሰው መረጃ በከበባ ስር ዋሉ። እጃቸውን እንዲሰጡ ሲጠየቁ “ቴዎድሮስ እጅ መስጠት አላስተማረንም። ይልቁንም የምላችሁን ስሙ፤ እኛ የተነሳነው እኛ ተበድለን ሳይሆን፤ የሀገራችንን ችግር ለማስወገድ ነበር እኛ ጀምረነዋል፤ እናንተ ጨርሱት”። በማለት በያዙት መሣሪያ ራሳቸውን አጠፉ፤ሲሉ መረጃዎች ያብራራሉ።
ሁለቱ የመፈንቅለ መንግሥት መሪዎች ከከተማው ቢሰወሩም በደብረ ዘይት ዝቋላ አካባቢ ታኅሳስ 15 ተገኙ። እጅ ለመስጠት ፍቃደኛ ባለመሆናቸው በተደረገ የተኩስ ልውውጥ የመፈንቅለ መንግሥቱ ዋና መሪ የነበሩት ብርጋዴዬር ጄኔራል መንግስቱ ንዋይ በከባድ ቆስለው ተያዙ፤ ታናሽ ወንድማቸው ግርማሜ ንዋይ ተገደሉ። ሬሳቸውም ወደ አዲስ አበባ መጥቶ አራዳ ጎዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ፊት ለፊት በሚገኘው አደባባይ ላይ ቀደም ብሎ ከተሰቀለው ሌ/ኮሎኔል ወርቅነህ ገበየሁ ሬሳ ጎን ተሰቀለ። ብ/ጄኔራል መንግስቱ ንዋይ ህክምና ተደርጎላቸው ፍርድ ቤት ቀረቡ፣ ሆኖም ፍርድ ቤቱ በስቀላት እንዲቀጡ ውሳኔ አስተላለፈባቸው።
ለመፈንቅለ መንግሥቱ መክሸፍም በዘመኑ ከእርሳቸው ጋር የሰለጠኑ ሰዎች ድርሻ አለበት። (በኋላ ጄኔራሎች) ዐቢይ አበበ፣ አሰፋ አያና፣ ኢሳይያስ ገብረሥላሴና ከበደ ገብሬ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራውን ካከሸፉት ይጠቀሳሉ። ፕሮፌሰር ባህሩ በበኩላቸው የአመጹ መሪዎች ዐቢይ ስህተት ዋና ዋናዎቹን የጦር ኃይል አካሎች በተለይም የምድር ጦሩንና የአየር ኃይሉን ለማሳተፍ አለመቻላቸው ወይም አለመሞከራቸው አልያም ሳይቀደሙ ቀድመው ከጥቅም ውጭ አለማድረጋቸው ነው ሲሉ ያብራራሉ።
ንጉሡም በአሜሪካ አየር ኃይል በኩል የሬዲዮ መልዕክት አስተላለፉ። ምሽት ላይም አዲስ አበባ በወታደሩ ቁጥጥር ሥር ሆነች፤ንጉሡም አስመራ ደረሱ። ታኀሳስ 9 አዲስ አበባ ገቡ። በኢትዮጵያ ሬዲዮ አለን ወደ ዙፋናችን በሰላም ተመልሰናል የሚል መልዕክት አስተላለፉ።
ንጉሰ ነግስቱም ፍርዱን ከሰጡ በኋላ እፎይ ብለው እንደቀድሞው ለመግዛት ዙፋናቸውን አደላደሉ። በእሳቸው አስተሳሰብ መፍንቅለ መንግሥቱ የጥቂት ውለታ ቢሶች ሴራ እንጂ ማህበራዊ መሰረት ያለው የለውጥ እንቅስቃሴ አልነበረም። ስለዚህም ዋና ተግባር አድርገው ያዩት ዙፋኑን የጠበቁለትን ታማኞች መሾምና መሸለም እንጂ አማጽያኑ የጠቆሟቸውን ፖለቲካዊና ማህበራዊ ችግሮች ለመፍታት አልነበረም።
ንጉሡ ከብራዚል እንደ መጡ ገነተ ልዑል ቤተመንግሥትን ለዩኒቨርሲቲው ሰጡ፤ ግቢውን ሸሽተው ሲኖሩ ከ13 ዓመት በኋላ የግቢው ተማሪዎች አመጽ ተከተላቸው፤ አብዮቱ ፈነዳና ገለበጣቸው።
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 10/2014