ኢትዮጵያ ተገዳ በገባችበት የህልውና ጦርነት ከፍተኛ ተጋድሎ በማድረግ ድል እየተቀዳጀች ትገኛለች። ታሪኳን ሊያጠፋ፣ የሕዝቦቿን አንድነት ሊበታትን ከተነሳ ወራሪ ባንዳ ጋር በሚደረገው እልህ አስጨራሽ ትግል ኢትዮጵያውያን ዘርፈ ብዙ የሆነ ተጋድሎ እያደረጉ ድልም ከእነሱ ዘንድ እየቀረበች ትገኛለች። እናፈርሳታለን ላለ ወራሪ ጠላት ‹‹ኢትዮጵያ አትፈርስም›› በማለት ከሰሜን ጫፍ እስከ ደቡብ፤ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ያሉ ውድ ኢትዮጵያውያን በግንባር ጦርነቱን በአካል ተቀላቅለዋል። በገንዘብና በአይነት እንዲሁም የኪነጥበብ ባለሙያዎችን ላይ በመሳተፍ ጭምር በሙያቸው ሠራዊቱን በመደገፍና በማበረታታት ደጀንነታቸውን እያስመሰከሩ ይገኛሉ።
በተለይም በኪነጥበብ ዘርፍ የተሰማሩ ኢትዮጵያውያን አገራዊ አንድነትን፣ ፍቅርና ሰላምን በሚሰብኩ የጥበብ ሥራዎቻቸው ኢትዮጵያን ሲያንቆ ለጳጵሱ ተደምጠዋል። ታድያ ድምጻውያኑ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በአሁኑ ወቅት በሕብረትና በተናጠል በመሆን የተለያዩ መልዕክቶችን የያዙ የሙዚቃ ሥራዎቻቸውን አበርክተዋል። እያበረከቱም ነው። እርግጥ ነው ኪነጥበብ ለተዝናኖት፣ ለኀዘንና ለጾታዊ ፍቅር ከሚውለው ይልቅ ለአገር ፍቅር ስሜት የሚኖረው አበርክቶ እጅጉን ይጎላል። እንደ የዜማው ጥንካሬ ቢለያይም ቅሉ ኢትዮጵያ አገሬን በማለት የተዜሙ ዜማዎች በአብዛኛው አጥንትን ዘልቆ ነብስን የሚያረሰርስ ስሜት አላቸው።
ታድያ በአሁኑ ወቅት ከተዜሙ ዜማዎች መካከል አገራዊ ስሜትን ሚያንጸባርቅና ድሉ የኢትዮጵያውያን ነው የሚል መንፈስ ያለው ዜማ በሲዳምኛ ቋንቋ አዘጋጅቶ ለአድማጭ ተመልካቾቹ ያቀረበው የዛሬው እንግዳችን የመከላከያ ሠራዊት አባል ነው። አብዛኞቹ ዜማዎች በአማርኛና በኦሮሚኛ ቋንቋ የተዜሙ ናቸው። የሚለው እንግዳችን የሲዳማ ክልል ማህበረሰብ በአሁኑ ወቅት ያለውን አገራዊ ሁናቴ መረዳት እንዲችል በራሱ ቋንቋ ዜማና ግጥም ደርሶ ወቅቱን የዋጀ ሙዚቃ አበርክቷል። ይህም ማህበረሰቡን ከማንቃት ባለፈ የአገር ፍቅር ስሜትን በማጋባት ሕዝቡ ደጀንነቱን የበለጠ የሚያጠናክርበትን እድል የሚሰጠው እንደሆነም ይናገራል።
ትምህርቱን አጠናቅቆ ሥራ ማግኘት ባለመቻሉ የአገርን ዳር ድንበር ለመጠበቅ ወስኖ መከላከያ ሠራዊትን የተቀላቀለው የዛሬው እንግዳችን አቶ ስጦታ ቦጋለ ይባላል። አቶ ስጦታ በሲዳማ ክልል ተፈሪ ኬላ ዳራ ኦቲልቾ ወረዳ ተወልዶ ያደገ ሲሆን የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱንም በአካባቢው ተከታትሏል። ወደ ዲላ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ አቅንቶም የሰርቬይንግ ትምህርቱን በመከታተል በ2007 ዓ.ም አጠናቋል። በምርቃቱ ማግስትም 2008 ዓ.ም ወደ መከላከያ ሠራዊት አቅንቷል።
ሁርሶ ማሰልጠኛ ተቋም ውስጥ የነበረው የአራት ወራት ስልጠና አጠናቅቆ ባድሜና ሽራሮ አካባቢ ሽሬ ላይ መከላከያ ሠራዊቱን ተቀላቅሏል። ወታደር ሆኖ የገባው አቶ ስጦታ፤ በአካባቢው ከሶስት ዓመት በላይ ቆይታ ሲያደርግ በሙዚቃ የነበረውን ችሎታ በማሳየት ከማሰልጠኛ ተመርጦ በኪቦርድ ማዕከላዊ ዕዝ ቡድን ውስጥ ገብቷል። በወቅቱ መከላከያ ሠራዊቱ የነበረው ቁመና ምን ይመስል እንደነበር ላነሳንለት ጥያቄ እንደሚከተለው ምላሽ ሰጥቶናል።
‹‹በወቅቱ አዲስ እንደመሆኔ ነገሮችን መረዳት አልቻልኩም እንጂ የአሸባሪው ትህነግ አካል የነበሩ ወታደሮች የነበራቸው አመለካከት ኢትዮጵያዊነትን የተላበሰ አልነበረም›› ያለው አቶ ስጦታ፤ በሂደትም እየተረዳ መምጣቱንና በተለይም ከለውጡ በኋላ ጸረ ኢትዮጵያዊ አመለካከት የነበራቸው የቡድኑ አባላት ፍራቻ ነግሶባቸው እንደነበር ያስታውሳል። ይሁንና በተለያዩ አካባቢዎች የነበረውን ግርግር መነሻ በማድረግም ሰላም ያለው ትግራይ ክልል ብቻ እንደሆነና ወደ ሥልጣን የመጣው መንግሥት ተቀባነት የሌለው በመሆኑ መፍረሱ አይቀርም የሚል ዕምነት ነበራቸው። ከዚህም በላይ መሰል የፕሮፓጋንዳ ተልዕኳቸውን ይፈጽሙ እንደነበር ያነሳል።
ወደ ሥልጣን የመጣው መንግሥት ለትግራይ ክልል ጥሩ አመለካከት የሌለውና ክልሉ በለውጡ መንግሥት እየተገፋ ነው የሚል አስተሳሰብም ያራምዱ ነበር። ለዚህም ቀደም ባለው ጊዜ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ ባለመኖራቸው ምክንያት ነው። እሳቸው በሕይወት በነበሩበት ወቅት እንዲህ ያለ መገፋት አልነበረም በማለት ስለዚህ እሳቸው በሕይወት ቢኖሩ ለትግራይ ክልል መልካም ይሆን ነበር በማለት ለውጡን ይኮንኑ እንደነበር ያስረዱት አቶ ስጦታ፤ ምንም እንኳን ሲዳምኛ ቋንቋ ተናጋሪ ቢሆንም በሽሬ በቆየባቸው ዓመታት ትግርኛ ቋንቋን መስማት በመቻላቸው ሀሳባቸውን እንደቻሉ ይናገራሉ። ታድያ በወቅቱ ኢትዮጵያን የማፍረስ ሀሳባቸውን ወደ አደባባይ አያውጡት እንጂ በወታደሩ መካከል መከፋፈል በመፍጠር ውስጥ ለውስጥ ሲሠራ የነበረው ሴራ እንደነበር እማኝነቱን ገልጿል።
ለውጡን ተከትሎም በ2010 ዓ.ም ወደ ደቡብ የተቀየረው ማዕከላዊ ዕዝ ጉዞውን ወደ ሀዋሳ ሲያቀና ከሽሬ አስቀድሞ በተንቀሳቀሰው ሠራዊት ላይ መንገድ በመዝጋት አግተው የነበረ መሆኑን ያነሳው አቶ ስጦታ፤ በወቅቱ ሕዝቡ መቀሌ መውጫ ላይ ጠብቆ ሠራዊቱ የታጠቀውን መሳሪያ ጨምሮ አጠቃላይ የያዘው ንብረት የትግራይ ክልል ነው በማለት ንብረቱን ጥሎ እንዲወጣ መደረጉን በማስታወስ ቡድኑ ቀደም ሲል ጀምሮ አገርና ሕዝብን ለመበተን ተዘጋጅቶ ነበር ይላል።
በሬ ካራጁ ይውላል እንዲሉ አበው በታሪክ አጋጣሚ ኢትዮጵያን እናፈርሳለን ብለው በህቡ ከተደራጁ ቡድኖች ጋር የነበረውን ቆይታ በወፍ በረር ያጫወተን እንግዳችን፤ መከላከያን የተቀላቀለው በሙዚቀኝነት ሲሆን አንድ ዓመት ባስቆጠረው ጦርነትም ስለአገር ከተዜሙ ዜማዎች መካከል አቶ ስጦታ በሲዳምኛ ቋንቋ ያዜማቸው ሁለት ዜማዎች ተጠቃሽ ናቸው። ከእነዚህም መካከል አንደኛው ‹‹ኦፎሎ›› የሲዳማ ባህልን የሚገልጽ ሲሆን ሁለተኛው ለጠላት መጣሁልህ የሚል መልዕክት ያለው በሲዳምኛ ‹‹ዳሞ›› የሚል ሙዚቃ ነው።
በመከላከያ ሠራዊት ውስጥ ውትድርና ብቻ ሳይሆን ዘርፈ ብዙ የሆኑ ሞያዎች የሚስተናገድበት እንደመሆኑ አቶ ስጦታም ሳያውቀው በውስጡ የነበረውን የሙዚቃ ችሎታና ፍላጎት በተግባር ማሳየት ችሏል። ሠራዊቱ የተለያየ ፍላጎቱን ማውጣት የሚችልበት ዕድል የተመቻቸለት በመሆኑ የሙዚቃ ሥራውን አጠናክሮ ቀጥሏል። አጠናክሮ የቀጠለው ግልጋሎትም በተለየ ሁኔታ በዚህ ወቅት ጊዜውን የዋጀ ሙዚቃ መሥራት አስችሎታል። ኢትዮጵያን ለመበተን የተዘጋጀው ጠላት ከሩቅ ያልመጣና በቅርብ ከሚያውቃቸው አካላት መሆናቸውም አስቆጭቶታል። በመሆኑም የክልሉ ማኅበረሰብ ወቅታዊ አገራዊ ሁኔታውን መረዳት እንዲችል በሚል በሲዳምኛ ቋንቋ ሙዚቃ በማዘጋጀት አሻራውን ማሳረፍ ችሏል።
በተለይም ሁለተኛው ሙዚቃ ሙሉ በሙሉ ወታደሩን የሚገልጽ፣ የሚያነቃቃና የሚያበረታታ ከመሆኑም በላይ “አገሬ በመነካቷ ዝም ማለት አልቻልኩም” የሚል ይዘት ያለውና ሕዝቡም መልዕክቱን ተረድቶ ምላሽ መስጠት የሚያስችለው እንደሆነና በቁጭት የተሠራ ሙዚቃ ስለመሆኑ አቶ ስጦታ ይናገራል።
‹‹በመከላከያ ሠራዊት ውስጥ ለመግባትም ሆነ የሙዚቃውን ዓለም እቀላቀላለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም›› የሚለው አቶ ስጦታ፤ ግንባር ላይ ተሰልፎ የአገሩን ዳር ድንበር ከሚጠብቀው መከላከያ ሠራዊት እኩል በርካታ የኪነጥበብ ባለሙያዎች በጥበብ ሥራቸው ለአገር ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን እና እርሱም አሻራውን ማሳረፍ በመቻሉ ደስተኛ እንደሆነ ይናገራል። ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት ሠራዊቱ ከፍተኛ መስዋዕትነት እየከፈለ ያለ ሲሆን ግንባር ላይ ካለው ወታደር በተጨማሪ በተለያዩ አካባቢዎችና በከተሞች የሚገኙ ወታደሮች አቶ ስጦታን ጨምሮ በየጊዜው ግዳጅ በመውጣት የተለያዩ ተግባራትን ይፈጽማሉ።
አማርኛ ቋንቋ ለማይሰማው የሲዳማ ሕዝብ በቋንቋው ወቅታዊ የሆነ ሙዚቃ መጫወት መቻሌ አንድ ነገር ያበረከትኩ ያህል ይሰማኛል። የሚለው አቶ ስጦታ፤ ኢትዮጵያ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች የሚገኙባት እንደመሆኗ መሰል ሥራዎች አስፈላጊ ናቸው ይላል። እነዚህን ሥራዎችም መከላከያ ሠራዊቱ በሚገኝባቸው የተለያዩ አካባቢዎች በመጓዝ ሲያቀርቡ እንደነበርና ለሰራዊቱም ከፍተኛ መነቃቃትን ከመፍጠር ባለፈ ወታደሩ ለአገር ፍቅር ያለውን ስሜት በቀላሉ መረዳት ያስችላል። የሙዚቃ ሥራዎችን ባቀረቡበት ቦታ ሁሉም ወታደር ሆነውም በእንባ እየተራጩ እንደሚሠሩ ያስታውሳል።
‹‹ስለአገር ያዜመ ማንኛውም ድምጻዊ ለእኔ አንድ ነው›› የሚለው አቶ ስጦታ፤ ዜማና ግጥሞቹ ቢለያዩም ሁሉም አንድ እንደሆኑ ይናገራል። በተለይም በመከላከያ ውስጥ ሆነው ኪነ-ጥበብን የተቀላቀሉ አባላት የአገር ፍቅር ስሜትን በሚቀሰቅስ መልኩ የተለያዩ የሙዚቃ ሥራዎችን ያቀርባሉ። ከዚህም ባለፈ አጠቃላይ ሠራዊቱ በአንድ አመለካከትና አስተሳሰብ ሆኖ አገሩን በተለያየ ዘርፍ ሲያገለግል መመልከት አስደሳች እንደሆነ ይናገራል። ለአብነትም እርሱ ወደ መከላከያ ከመግባቱ አስቀድሞ ለአገር የነበረው አመለካከትና አሁን ካለው በፍጹም የተለየ መሆኑን መታዘቡንና አሁን ጤናማ አስተሳሰብ እንዳገኘ ያስረዳል።
ለዚህም ሲባል ታድያ ሁሉም ሰው መከላከያ ገብቶ ቢወጣ በአገሪቷ ከሚስተዋሉ ችግሮች መካከል ቀዳሚ የሆነው የዘረኝነት አስተሳሰብ ይወገዳል የሚል ዕምነት ያለው መሆኑን አቶ ስጦታ ይናገራል። በመከላከያ ዓለም ውስጥ መግባት ስለ ክልል ሳይሆን ስለታላቋ አገር ኢትዮጵያ እንድናስብ ያደርጋል። ይህም ሲባል በመከላከያ ሠራዊት ውስጥ ያለው ሠራዊት ከሁሉም የአገሪቷ ክልሎች የተውጣጡ በመሆናቸው ሁሉም እንደ ወንድም ነው። በጦርነት ወቅትም ይሁን በሌላ አንድ ጉዳት ሲደርስ የሚያነሳው አጠገቡ ያለው ሠራዊት ነው። ይህ አብሮነት ደግሞ ከዘረኝነት አስተሳሰብ የወጣ አገራዊ ስሜት የሚያጎናጽፍ ነው።
በቀጣይም አገራዊ ስሜት ያላቸውን የሙዚቃ ሥራዎች ለማዘጋጀት ዕቅድ ያለው አቶ ስጦታ፤ ዕቅዱን ለማሳካትም በመከላከያ ሠራዊት ውስጥ የተፈጠሩለት ምቹ ሁኔታዎች ስለመኖራቸው አንስቷል። እስካሁን የሰራቸው የሙዚቃ ሥራዎችም አድማጭ ተመልካቾች ጋር ለማድረስ በዩቲዩብ ላይ መጫኑን እንዲሁም ሀዋሳ ከተማ ውስጥ በፋና ኤፍ ኤም ላይ እየተለቀቀ ስለመሆኑ መረጃው ደርሶታል። ከዚህ ባለፈ ግን የሙዚቃ ሥራው በምን ያህል መጠን እየተደመጠ ስለመሆኑ በቂ መረጃ ለማግኘት ወቅቱ በስፋት ግዳጅ የሚወጣበት በመሆኑ ማወቅ እንዳልቻለም ይናገራል። ይሁንና በማገኘው አጋጣሚ ሁሉ አገራዊ አንድነትን የሚገልጹ የሙዚቃ ሥራዎችን በቀጣይነት እሠራለሁ የሚለው አቶ ስጦታ፤ ግጥምና ዜማም ይደርሳል።
ለውጡን ተከትሎ አገሪቷን ለማፍረስ የተነሳውን አሸባሪ ቡድን ለመከላከል እየተወሰደ ያለው እርምጃ እጅግ የሚያኮራ ስለመሆኑ ያነሳው አቶ ስጦታ፤ በተለይም ለመከላከያ ሠራዊት እየተደረገ ያለው ድጋፍ አስደሳች በመሆኑ ‹‹እንኳንም ወታደር ሆንኩ›› በማለት ወታደር በመሆኑ የሚሰማውን ኩራት ገልጿል። እርግጥ ነው ወታደር መሆን ወጥቶ መቅረት እንዳለ ቢታሰብም ቅሉ አሁን ያለው አስተሳሰብ ግን ወላጆችን ጨምሮ ማንኛውም ነገር የሚያምረው በአገር እንደሆነ በማመን የአገርን ዳር ድንበር ለማስከበር ልጆቻቸውን ወደ ግንባር ይልካሉ። ወጣቱም ለአገር ያለው አስተሳሰብ የጠራ በመሆኑ ለአገሩ ዋጋ እየከፈለ ይገኛል። ይህ አስተሳሰብና ግንዛቤ የመጣውም በይበልጥ ከለውጡ ወዲህ ነው። በማለት ለአገር ሲባል የትኛውንም አይነት መስዋዕትነት መክፈል የግድ እንደሆነ አስረድቷል።
‹‹በኢትዮጵያ ሰሜን ክልል ተጀምሮ አንድ ዓመት ባስቆጠረው ጦርነት የኢትዮጵያ ሠራዊት ተገቢውን ምላሽ በመስጠት ስኬታማ በመሆኑና እኔም ከሠራዊቱ አባል አንዱ መሆኔ በእጅጉ ያኮራኛል›› የሚለው አቶ ስጦታ፤ በአሁን ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ ስድስት ኪሎ አካባቢ በሚገኘው የመከላከያ ኪነ-ጥበባት ሥራዎች ማርሽ ባንድ ቡድን፣ የሙዚቃ ትምህርትና ሥልጠና ቡድን እንዲሁም የመከላከያ ክብር ሰልፍ ቡድን በሚገኝበት ቅጥር ግቢ ውስጥ ሆኖ የሙዚቃ ሥራውን ይሰራል። በዋናነትም ቤዝ ጊታር ይጫወታል። ግጥምና ዜማ ይደርሳል። ከዚህ በተጨማሪም በማንኛውም ጊዜና ሰዓት የተለያዩ ግዳጆች ሲሰጡት ተልዕኮውን እየፈጸመ ይገኛል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 9/2014