በጥልቀት መተንፈስ ለብዙዎቻችን እንደተራ ነገር ሊቆጠር ይችላል። በዘርፉ ጥናትና ምርምር ያደረጉ ሳይንቲስቶች ግን በጥልቀት መተንፈስ ለሰዎች የሚሰጣቸው በርካታ የጤና ጠቀሜታዎች እንዳሉ አረጋግጠዋል። በተለይ ሰዎች በተለያዩ ምክንያቶች ጭንቀት ውስጥ ሲገቡ በጥልቀት መተንፈስ ጭንቀትን ተከትሎ ለሚያጋጥማቸው የጤና መቃወስ ፍቱን መድኃኒት ነው ይላሉ። ከዚህ ባለፈ በጥልቀት መተንፈስ የሚከተሉትን ስድስት የጤና ጠቀሜታዎች እንዳሉትም ዘርዝረዋል።
1ኛ፡- የደም ግፊትን ይቀንሳል
ጭንቀት የሚያጋጥማቸው ሰዎች በጥልቀት በመተንፈስ የደም ግፊታቸውን መቀነስ ይችላሉ። ይሁንና ጭንቀታቸውን ስለሚቀሰቅሱባቸው ምክንያቶች ብታወሯቸው የደም ግፊታቸው ዳግም ሊያገረሽ ይችላል። ከዚህ አንፃር የደም ግፊትን ጨምሮ ዘላቂ የጤና ጥቅሞችን ለማግኘት ወጥነት እና መደበኛ በጥልቀት የመተንፈስ ልምምድ ወሳኝ ነው ይላሉ የጤና ባለሙያዎቹ።
በዝግታ የመተንፈስ ልምምድ የደም ግፊትን በመጠኑ እንደሚቀንስ ሁሉ ከዚህ በተቃራኒ በጥልቅ የመተንፈስ ልምምድ በየጊዜው የሚያደርግ ከሆነ የደም ግፊትን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚቀንስም ሳይንቲስቶቹ አረጋግጠዋል። እርስዎም ጭንቀትን ተከትሎ ከፍተኛ የደም ግፊት ካለብዎት በጥልቀት መተንፈስን የዘወትር ልምምድዎ ያድርጉ።
2ኛ፡- አስምና የመተንፈስ ችግሮችን ያቃልላል
በጥልቀት የመተንፈስ ልምምድ ከሳምባ ጋር የተያያዙ የአስምና መሰል ከመተንፈሻ ችግሮች ጋር ከተያያዙ በሽታዎች ለመላቀቅ ጥሩ መንገድ ነው። ከአነስተኛ እስከ መካከለኛ ደረጃ የአስም በሽታ ላለባቸው ሰዎች በጥልቀት የመተንፈስ ልምምድ በጭንቀት ጊዜ የሚከሰትን ከመጠን በላይ የመተንፈስ ምልክቶች እንዳይኖሩ፣ ሳምባ ሥራውን በአግባቡ እንዲያከናውንና ባጠቃላይ የሰዎች የጤና ሁኔታ እንዲሻሻል ያደርጋል።
ከዚህ ባለፈ የመተንፈስ ልምምድ የአስም በሽታ ምልክቶችን በማሻሻል ረገድም ቁልፍ ሚና ይጫወታል። ምንም እንኳን በታሰበ መልኩ የሚከናወነው በጥልቀት የመተንፈስ ልምምድ ቀላል ቢመስልም የአሜሪካው የሳምባ ማህበር ወደ ትክክለኛው መስመር ለመግባት ጊዜ ይፈልጋል ሲል አስቀምጧል። በጥልቀት የመተንፈስ ልምምድ እንዲህ አይነቱን የጤና በረከት የሚያስገኝ ከሆነ እርስዎም ልምዱን ከአሁኑ ለመጀመር እንደማያመነቱ ጥርጥር የለውም።
3ኛ፡- የድብርትና የጭንቀት ምልክቶችን ለመቆጣጠር ያግዛል
ሥር የሰደደ ውጥረት በተለይ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከተከሰተ ወዲህ ይበልጥ እየተስፋፋ የመጣ ችግር ሆኗል። ይህ ውጥረት የተለመደውን ትክክለኛ የአተነፋፈስ ሥርዓትን ሊያዛባና በምላሹም ለጭንቀትና ሌሎች የአእምሮ ጤና ችግሮች ሊያጋልጥ ይችላል።
ከዚህ አኳያ ሰዎች በጥልቀት የመተንፈስ ልምምዶችን ዘወትር በማድረግ የአተነፋፈስ ሥርዓታቸውን ሚዛን መጠበቅ ይችላሉ። ይህም ለአንድ ነገር ያላቸውን ስሜትና አስተሳሰብ ለማሻሻል ይረዳቸዋል።
ለስምንት ሳምንታት የዘለቀ በጥልቀት የመተንፈስ ልምምዶችን ማድረግም የውጥረት ሆርሞን መጠንን በመቀነስ ረገድ ጉልህ አስተዋፅኦ እንዳለው በሳይንቲስቶች ተረጋግጧል። ከዚህ አንፃር ልምምዱ የሚጠቅም እንጂ ጉዳት የማያመጣ በመሆኑ እርስዎም ነገ ዛሬ ሳይሉ አሁኑኑ ይጀምሩ።
4ኛ፡-ውጥረትን ይቀንሳል
በጥልቀት መተንፈስ ዘና ለማለትና የጡንቻዎችን ውጥረት ለመቀነስም ይረዳል። ይህም የራስ ህመም እንዳይኖር ይከላከላል። በትከሻና በአንገት አካባቢ ያለውን ውጥረት በመቀነስ የራስ ህመም እንዳይከሰት በማድረግ ረገድም በጥልቀት መተንፈስ ከፍተኛ ሚና አለው። ከዚህ አንፃር የበለጠ ዘና ባሉ ቁጥር በተሻለ ሁኔታ ማረፍ ይችላሉ። ይህ ደግሞ ጥሩ ስሜት እንዲሰማዎት ይረዳዎታል።
ምንም እንኳን በጭንቅላት መካከል ለሚፈጠር ህመም በጥልቀት መተንፈስ እገዛ ባይኖረውም በጥልቀት መተንፈስን በመደበኛነት ልምምድ ማድረግ ወይም ራስ ምታት በሚመጣበት ቅጽበት፣ በተለይም ከመከላከያ እና አጣዳፊ መድኃኒቶች ጋር ማጣመር ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። ስለሆነም በጥልቀት መተንፈስ ውጥረትን በመቀነስ ራስ ምታት እንዳይፈጠር ትልቅ እገዛ ስለሚኖረው የዘወትር ልምምድዎ ያድርጉ።
5ኛ፡- በሆድ ውስጥ ህመም የሚያስከትል የአንጀት ችግር ምልክቶችን ይቀንሳል
በጥልቀት መተንፈስ በምግብ ልመት ሂደትም የራሱ ተቀሜታ አለው። የዲያፍራም ፊዚዮሎጂያዊ እንቅስቃሴዎች በምግብ መፈጨት ሥርዓት ውስጥ ያለውን ውጥረት ለማስታገስም እገዛቸው ከፍተኛ ነው። ይህም ለውጥ እንደሚያመጣ በጥናትና ምርምር መረጋገጡን ሳይንቲስቶች ተናግረዋል። በጥልቀት የመተንፈስ ልምምድ ባደረጉ ቁጥር ይህንኑ የጤና ጠቀሜታ ስለሚያገኙ ግድ የለም እርስዎም ይሞክሩት።
6ኛ፡- ከወገብ በላይ በድንገት የማተኮስ ስሜትን ይቀንሳል
አንዳንድ ሳይንሳዊ ማረጋገጫዎች እንደሚያሳዩት በጥልቅ መተንፈስ ከወገብ በላይ የሚፈጠሩ ድንገተኛ ትኩሳቶች እንዲቀንሱ በማድረግ ረገድ ፋይዳው የጎላ ነው።
ከወገብ በላይ በድንገት የትኩሳት ስሜት መሰማት ካንሰርን በማከም ሂደት እንደጎንዮሽ ጉዳት ሆኖ ሊከሰት ይችላል። ከዚህ አንፃር በጥልቀት የመተንፈስ ልምምድ ከወገብ በላይ የማተኮስ ኃይለኛ ስሜትንና በተደጋጋሚ መከሰትን የሚቀንስ በመሆኑ በተለይ የካንሰር ታማሚ ከሆኑ ይህንን እንዲያደርጉ የጤና ባለሙያዎች ይመክርዎታል።
ምንጭ፡-ኤቭሪዴይ ሄልዝ
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 9/2014