አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ወረራ በፈፀመባቸው የአማራና አፋር ክልሎች በመሰረተ ልማት አውታሮች ላይ መጠነ ሰፊ ጉዳት አደርሷል። ቡድኑ ሂሳብ አወራርዳለሁ ብሎ የጥፋት በትሩን ካሳረፈባቸው የመሰረተ ልማት አውታሮች ውስጥም የጤና ተቋማት በዋናነት ይጠቀሳሉ። በዚሁ ወረራ ወቅት አሸባሪ ቡድኑ ከጤና ኬላ እስከ ሆስፒታል ድረስ ያለርህራሄ ከባድ ውድመት ፈፅሟል። በጤና ተቋማት የሚገኙ የህክምና መሳሪያዎችንና መድኃኒቶችንም ዘርፏል። ቁጥሩ ቀላል የማይባል የማህበረሰብ ክፍል የሚገለገልባቸው ጤና ተቋማት በመውደማቸውም ከባድ የጤና አገልግሎት ቀውስ ተፈጥሯል።
በአሁኑ ጊዜ ደግሞ የጤና ተቋማቱ የሚገኙባቸው የሁለቱም ክልሎች በአብዛኛው ከወራሪው ነፃ መሆናቸውን ተከትሎ ተፈናቃዮች ወደ ቀዬአቸው እየተመለሱ በመሆኑ በተለይ የህክምና አገልግሎት በሚፈልጉ ሰዎች ላይ ተጨማሪ ጫና እንደሚያሳድርም ስጋት ጭሯል። የውድመቱ ስፋትና ጥልቀት ከፍተኛ መሆን ደግሞ በዋናነት የድንገተኛ ህክምናና ሌሎች ወሳኝ የህክምና አገልግሎቶችን ለመስጠት አዳጋች አድርጎታል።
ምንም እንኳን ከወረራው አስቀድመው ነፃ በሆኑ የሁለቱ ክልሎች አካባቢዎች በጤና ሚኒስቴርና በክልሎቹ ጤና ቢሮዎች በተደረገ የጋራ ርብርብ ቢያንስ የድንገተኛ ህክምናና ሌሎች የእናቶችና የህፃናት ህክምና አገልግሎት እንዲጀመሩ የተደረገ ቢሆንም በቅርቡ ነፃ በወጡ አካባቢዎች ላይ የወደሙ የጤና ተቋማት ስር ነቀልና አፋጣኝ ጥገናና መልሶ ግንባታ የሚጠይቁ በመሆናቸው የሰፊውን ህዝብ ርብርብ ይጠይቃሉ።
ለዚህም ይመስላል ከሰሞኑ ከፍተኛ ውድመት የደረሰባቸውን የጤና ተቋማትን ለማቋቋምና መልሶ ሥራ ለማስጀመር እንዲቻል ከጤና ሚኒስቴር በኩል ሁሉን አቀፍ የድጋፍ ጥሪ ቀርቧል። የድጋፍ ጥሪውም ከሀገር ውስጥ እስከ ውጭ ሀገር ያሉ ሁሉንም ኢትዮጵያውያን ያካተተ መሆኑም ተነግሮለታል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከጤና ሚኒስቴር ከሰሞኑ በወጡ መረጃዎች መሰረት አሸባሪ ቡድኑ ካደረሰው ሰብዓዊና ሞራላዊ ጥፋት በተጨማሪ ህዝብ የሚገለገልባቸው የጤና አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን፤ የህክምና ግብዓት ማከማቻ መጋዘኖችንና ሌሎች የማህበራዊ ተቋማትን አውድሟል። የህክምና መሳሪያዎችን እና ሌሎች ግብዓቶችንም ጭኖ በመውሰድ ከባድ ዝርፍያ ፈጽሟል።
ቡድኑ በጤና ተቋማት ላይ ያደረሰው ውድመት በተለይ ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች የመሰረታዊ እና ድንገተኛ ህክምና አገልግሎትን ለመስጠት እንዳስተጓጎለም መረጃው ጠቅሷል። እስካሁን ባለው መረጃም ከ2 ሺ 700 በላይ የሚሆኑ የጤና ተቋማት አገልግሎት የማይሰጡ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በመንግሥት ተደራሽ ያልሆኑ አካባቢዎች ሲካተቱ ውድመት የደረሰባቸው የጤና ተቋማት ቁጥር ከዚህም በላይ እንደሚያሻቅብ ተገልጿል።
መረጃው በጤና ተቋማቱ ላይ በተከሰተው መጠነ ሰፊ ወድመት ምክንያት በርካታ ዜጎች ቀደም ሲል የሚያገኙት የጤና አገልግሎት በከፊልና ሙሉ ለሙሉ መስተጓጎሉንም አስታውቋል። በሌላ በኩል ግጭቱ በተከሰተባቸው አካባቢዎች አቅራቢያ አገልግሎት የሚሰጡ ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች እንዲጨናነቁ እና መደበኛ ከሆነው አቅማቸው በላይ አገልግሎት እንዲሰጡ መገደዳቸውን አትቷል።
ይህንንም ተከትሎ ለህብረተሰቡ ቀጣይነት ያለው አገልግሎት ለመስጠት እንዲያስችልና አገልግሎቱን ወደ ነበረበት ለመመለስ ሁሉንም ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ያሳተፈ የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ ጥሪ ማድረግና የመልሶ ማቋቋሚያ ሀብት ማሰባሰብ እጅጉን አስፈላጊ ሆኖ ማግኘቱን ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከባለድርሻ አካላት እና አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን ለዚህ አደጋ ምላሽ ለመስጠት እንዲያግዝ ሁሉን አቀፍ ከግጭት ጋር የተያያዘ ድንገተኛ አደጋ የጤና ምላሽ ስርዓት አቋቁሞ ዘርፈ ብዙ ርብርብ እያደረገ እንደሚገኝም ገልጿል።
በአሁኑ ወቅትም ይህን ፈታኝ የሆነ ተግዳሮት ለመግታት ዝርዝር ተግባር ያለው ስትራቴጂ በመንደፍ ለማስፈጸም እየተንቀሳቀሰ የሚገኝ መሆኑንና ከእነዚህም ውስጥ የመጀመሪያው እና በአሁኑ ጊዜ እየተሰራበት ያለው የተዘረፉ እና ውድመት የደረሰባቸውን ጤና ተቋማት ከተለያዩ በአገር አቀፍ ደረጃ ካሉ የመንግሥት ተቋማት ጋር በመጣመር ተቋማቱን መልሶ የማቋቋም ሥራ ማስጀመር እንደሚገኝበት አስታውቋል።
ከውድመቱ ከፍተኛነትና የጤና ጉዳይ ጊዜ የማይሰጥ ከመሆኑ አንፃር ብሎም ለማህበረሰቡ የሚሰጠውን የጤና አገልግሎት በፍጥነት ማስጀመር እጅግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ የተደራጀ ድጋፍ ከሁሉም አቅጣጫ ማሰባሰብ ከመቼውም ጊዜ በላይና ከሁሉም በፊት ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆኑን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ገልጿል።
የጤና ሚኒስቴር በግጭቱ አካባቢ ፈጣን ዳሰሳ በማካሄድም በአሁኑ ጊዜ የወደሙ የጤና ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም እና ሥራ ለማስጀመር እጅግ ከፍተኛ ገንዘብ የሚያስፈልግ እንደሆነ በዳሰሳው ግኝት አመላክቷል። ይህንን የሃብት ማሰባሰብ እና ድጋፍ ሥራን ለማስተባበር የጤና ሚኒስቴር የባለሙያ ቡድንም ያቋቋመ ሲሆን በግለሰብም ሆነ በቡድን ድጋፍ ማድረግ ለሚፈልጉ ሁሉ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስፈላጊ መረጃ እና ትብብር ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞም በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ ያሉ መላው ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን፤ የኢትዮጵያ ወዳጆች፤ የግሉ ዘርፍ፤ ለጋሽ ድርጅቶች፤ አጋር ድርጅቶች፤ ሲቪክ ማህበራት፤ የሙያ ማህበራት እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት በአሸባሪ ቡድኑ የወደሙ የጤና ተቋማትን ማቋቋምና ሥራ ማስጀመር ጥሪ ተቀብለው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪውን አቅርቧል።
ከዚህ አንፃር የእነዚህን ጤና ተቋማት ግልጋሎት የሚፈልጉ በርካታ ህፃናት፣ ሴቶችና አዛውንቶች አሉና በዳግም መልሶ ግንባታው የሁሉም ህብረተሰብ ክፍል ርብርብ ወሳኝ በመሆኑ ዜጎች ይህንኑ አውቀው ለመልሶ ማቋቋሙ ያልተጠበቀ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
ከሰሞኑ የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል በአሸባሪ ቡድኑ የወደመውን የደሴን ሆስፒታል ለመገንባት የወሰደው እርምጃም ይበል የሚያሰኝና ለሌሎችም አርዓያ የሚሆን ነው። በተመሳሳይ ሌሎችም የሆስፒታሉን አርዓያ ተከትለው የወደሙ ጤና ተቋማትን መልሶ በማቋቋም ሂደት የራሳቸውን አሻራ እንደሚያስቀመጡ አጠያያቂ አይደለም።
በርካታ ባለሃብቶችም ከመንግስት ጎን በመቆም በአሸባሪ ቡድኑ የወደሙ የጤና ተቋማት ዳግም ተገንብተው አገልግሎት እንዲሰጡ አስቀድመው አጋርነታቸውን አሳይተዋል።
ሆኖም እንዲህ አይነቱ ትብብር አሁንም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል። ህብረተሰቡንም በተለያዩ መንገዶች በመልሶ ግንባታው ተሳትፎ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የመንግስት ባለድርሻ አካላት አስፈላጊው ትብበርና ድጋፍ ሁሉ ሊደረግለት ይገባል።
አሸባሪው የህወሓት ቡድን ወረራ በፈፀመባቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች ብቻ በ7 ዞኖችና በ82 ወረዳ እንዲሁም በ1 ከተማ አስተዳደር:- 40 ሆስፒታሎች፣ 453 ጤና ጣቢያዎችን፣ 1 ሺ 850 ጤና ኬላዎችን፣ 466 የግል ጤና ተቋማትና አራት የደም ባንኮች ሙሉ በሙሉ ማውደሙን ከጤና ሚንስቴር የተገኙ መረጃዎች ያሳያሉ። በተመሳሳይ ቡድኑ በአፋር ክልል በፈፀመው ወረራ በግልና በመንግስት ጤና ተቋማት ላይ መጠነ ሰፊ ጉዳት መድረሱን እነዚሁ መረጃዎች ያሳያሉ።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 9/2014