የአንጋፋው ቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበርን የአስተዳደር፣ የማርኬቲንግና ፕሮሞሽን ዘርፍን ለማዘመንና ለማሻሻል የሚያስችል ጥናት ለማስጠናት ስምምነት ተፈራርመዋል። ስምምነቱን ከቀናት በፊት የክለቡ ፕሬዚዳንት አቶ አብነት ገብረመስቀልና የድንቅ ኢትዮጵያ ብራንድ ኮንሰልታንት ኩባንያ ስራ አስኪያጅ አቶ ኤርሚያስ አየለ በስፖርት ማህበሩ መዝናኛ ማእከል በመገኘት ተፈራርመዋል፡፡
ጥናቱ ከዚህ ቀደም የቅዱስ ጊዮርጊስ ይከተል የነበረውን የክለብ የሰው ሃይል አስተዳደርና መዋቅር፣ እንዲሁም በገበያና ፕሮሞሽን ረገድ የአሰራር ስርዓቱን በመቀየር ክለቡን ለማዘመን ከፍ ያለ ጠቀሜታ እንደሚኖረው አቶ አብነት ገብረመስቀል በስነ ስርዓቱ ላይ ገልፀዋል። “ይህ ጥናት መደርደሪያ ላይ የሚቀመጥ ሳይሆን ወደ ተግባር የሚቀየር ነው” ያሉት ፕሬዚዳንቱ “በጥናቱ በሚቀርበው ምክረ ሃሳብ መሰረት በጊዮርጊስ ውስጥ መለወጥ ያለባቸው የአሰራር ስርዓቶች በሙሉ ይቀየራሉ” ሲሉ አስረድተዋል።
የድንቅ ኢትዮጵያ ብራንድ ኮንሰልታንት ኩባንያ ስራ አስኪያጅ አቶ ኤርሚያስ አየለ በበኩላቸው ድርጅታቸው አጠቃላይ ጥናቱን በ9 ወራት ጊዜ ውስጥ አጠናቆ ለክለቡ እንደሚያስረክብ ገልጸዋል። በተጨማሪም ላለፉት ወራት ስለክለቡ አስፈላጊ የሚባሉ መረጃዎችን ለማሰባሰብ ከቦርዱና ከጽህፈት ቤቱ ሰራተኞች ጋር ውይይት መደረጉን ጠቅሰዋል። “ቅዱስ ጊዮርጊስ ከራሱ የሚተርፍ የስፖርት መሰረተ ልማት ባለቤት ነው” ያሉት አቶ ኤርሚያስ ጥናቱ ክለቡ ያለውን አቅም በመጠቀም ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግ እንደሚረዳ አብራርተዋል። በዚህ ጥናት ውስጥም ቅዱስ ጊዮርጊስ ካሉት ደጋፊዎች ባሻገር አዳዲስ ደጋፊዎችን ወደ ክለቡ ለመሳብና ደጋፊዎች ከክለባቸው ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከርም የሚጠቅም እንደሆነ ተገልጿል።
በስምምነት መርሐ-ግብሩ ላይ ስለ ጉዳዩ መግለጫ ከመሰጠቱ ባለፈ ከስፍራው ከተገኙ የብዙሃን መገናኛ አባላት በቅርቡ የተሰናበቱትን ሰርቢያዊ አሠልጣኝ ዝላትኮ ክራምፖቲች ስንብት በተመለከተ አቶ አብነት ገብረመስቀል አስተያየት ሰጥተዋል። “እኛ አገር ትልቅ አሠልጣኝ አይመጣም። ከመጫወቻ ሜዳ ጀምሮ እኛ አገር ያለው ችግር ከባድ ነው። ከዚህ ውጪ እኛ አገር ያሉት ተጫዋቾች ከውጪ ካመጣናቸው አሠልጣኞች ጋር አይግባቡም። ሁሌ ጥል አለ። ሁል ጊዜ ማስታረቅ እና ማግባባት አድካሚ ነው። ይሄ አሠልጣኝ (ክራምፖቲች) ከመጣ በኋላ አምስት እና ስድስቴ ደብረዘይት ለማስማማት ሄደናል።” ያሉት አቶ አብነት አሰልጣኙ ከተጫዋቾች ጋር በተደጋጋሚ በሆነ ባልሆነው ሲጋጩ እንደከረሙ ተናግረዋል።
“እኛ ከሰውዬው የወሰድነው ነገር አለ። ይህም ዲሲፕሊን ነው፣ ይሄንን አስቀምጦልናል። ሜዳም ውስጥ ከሜዳ ውጪም ተጫዋቾቹ የሚኖራቸውን ነገር አስቀምጦልናል። ዲሲፕሊን ሰፊ ቢሆንም ከፀጉር ጀምሮ ያስተካከለልን ሰው ነው። ይሄንን ተጫዋቾቹ አያቁትም። የፕሮፌሽናል ችግር አለ። ከዚህ በተጨማሪም የሥነ- ልቦና ችግር አለ። ምን ያህል ሥነ- ልቦናን የሚያነቃ እና የሚያስተምር ባለሙያ አገራችን አለ የሚለውም ሌላ ጥያቄ ነው።” በማለት አቶ አብነት ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ተሰናባቹ አሰልጣኝ ክራምፖቲች ከተጫዋቾች ጋር የነበራቸውን ዋነኛ ክፍተት በተመለከተ “ዋናው ችግር የቋንቋ ችግር ነው። እንዴት ነው የምናስማማቸው ? ከ23 ተጫዋቾች አራቱ ቋንቋ ከቻሉ ጥሩ ነው። ምክትል አሠልጣኞቹም ጋር የቋንቋ ውስንነት አለ። የሚያስተረጉሙት እነሱ ስለሆነ ሀሳቦች በጥሩ ሁኔታ መድረስ አለባቸው። ብዙ ነገሮች አየር ላይ ይቀራሉ። በአንድ ወቅት ተጫዋቾቹን ለማስተማር ሞከርን። በዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ማታ ማታ እንዲማሩ አደረግን። ግን ከ15 ቀን በኋላ ተንጠባጥበው ጠፉ። በእኛ ቦታ ብትሆኑ የችግሩ ክብደት ይገባችኋል።” በማለት ማብራሪያ ሰጥተዋል። በኋላ ከዚህ በኋላ የውጪ አሠልጣኝ አይመጣም ? ለሚለው ጥያቄ ግን “ተጫዋቾቹን ቋንቋ እናስተምራለን።” በማለት አቶ አብነት አጭር መልስ ሰጥተዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 8 / 2014