እለተ ዓርብ እንደ ወትሮው ነው..የከሰዓት በኋላው ጥላ አርፎበት ከቀይነት ወደ ጠይምነት ተቀይሯል።ስስ ንፋስ የመስኮቱም መጋረጃ እያውለበለበ ጽሞና የዋጣትን ነፍሷን በኳኳታ አውኳታል፡፡ ቤቱ ውስጥ ትንሿን ቁም ሳጥን ተደግፎ የቆመ አንድ ባለፍሬም ፎቶግራፍ ይታያል፡፡ ከበላዩ በጎለጎታ የራስ ቅል ራሱን ለሰው ልጅ ፍቅር የሰዋው የእየሱስ ክርስቶስ ስዕል ተሰቅሏል፡፡ እየሱስ ክርስቶስን ከባሏ ፎቶ ራስጌ የሰቀለችው እሷ ናት..ጠዋትና ማታ ባሏን ከክርስቶስ አጠገብ ስታየው ውስጧ ያለውን የፍርሀት መንፈስ ይሽርላታል፡፡
ባሏም በቀኙ እንደ ተሰቀለው እንደ በጎው ሰው ጌታ ሆይ በመንግስትህ አስበኝ የሚለው ይመስላታል፡፡ ጠዋት ከእንቅልፏ ስትነሳ፣ ማታም ወደ ማደሪያዋ ስትሄድ ስዕሉ ፊት ቆማ እንዲህ ትላለች..ማንም የማይሰማውን ተማጽኖ ለአምላኳ ታደርሳለች፡፡ ማንም ፈጣሪን እንደዚያ ብሎት አያውቅም፣ የትኛዋም ሴት ስለ ወንድ ልጅ እንደዛ ጸልያ አታውቅም…፡፡ ከንፈሮቿ ጠዋትና ማታ ትንሿ ቁም ሳጥን ላይ ፎቶው ስለተሰቀለው ሰው ፈጣሪን ይማጸናሉ፡፡
ትንሽ ልጇ ከእንቅልፉ ነቃ መሰል ድምጹን ሰማችው፡፡ ዓለም ላይ አንድ ውዳሴ ብቻ አላት እርሱም ልጇ ነው፡፡ ዓለም ላይ አንድ እውነት ብቻ አላት እርሱም ልጇ ነው፡፡ ምድር ላይ አንድ ደስታ ብቻ አላት እርሱም ልጇ ነው…የስምንት ወር ልጇ። ልጇ በዚህ ዓለም ላይ ያለ ብዙ ነገሯ ነው፡፡ ትንሿ ቁም ሳጥን ላይ ፎቶው ያለውን ሰውዬ በልጇ በኩል ነው አካልና ሥጋ ለብሶ የምታየው፡፡ ልጇ ለባከነና ኦና ለቀረው አለሟ መጽናኛዋ ነው፡፡
ደስ እያላት ወደ ልጇ ሄደች…የተስፋዋ ጥግ ልጇ ነው፡፡ በሳቁ ውስጥ ብዙ ደስታ አላት..ከ እስከ የማትለው መባረክ፡፡ ትንሹ ልጇ የእናቱን መምጣት ሲያይ እጆቹን እርስ በርስ እያላተመ..ከጀርባው ለመነሳት በሚመስል ሁኔታ እየተንቀሳቀሰ ጠበቃት..አጠገቡ ደርሳ ጉንጩን እስክትስመው ድረስ ሩቅ ሆኖባት ነበር፡፡ አጠገቡ ደርሳ የማይገባውን ብዙ ነገር አለችው፡፡ ከልጇ ጋር እየተሳሳቀች ትንሽ ቆየች….ከህልሟ አንዱ ከሶስት ነፍሶች ጋር በአንድ ላይ መቆም ነው፡፡ እሷ ልጇና ትንሿ ቁም ሳጥን ላይ ፎቶው ካለው ሰው ጋር ዳግም መገናኘት የነፍሷ ምኞት ነው። በሕይወቷ ውስጥ ዳግም እንዲሆን የምትፈልገው ተዐምር ይሄ ነው..እሷ ልጇና ያ ሰውዬ ያሉበት ተዐምር፡፡
ሊመሻሽ አለ..እለተ ዓርብ ከጠይምነት ወደ ጥቁርነት ተለወጠ፡፡ ሲመሽ ትዝታዋ ብዙ ነው። ሲመሽ ትላንት ይመጣባታል..ሲመሽ ብዙ ነገር ትሆናለች፡፡ ልጇን ትከሻዋ ላይ ጥላ ወደ ሳሎን ወጣች..፡፡ ትንሿ ቁም ሳጥን አናት ላይ የተሰቀለውን ፎቶ ትክ ብላ አየችው፡፡ ጠይም ወጣት፣ ካቆጠቆጠ ጺሙ ጋር ለዘላለም የማትረሳውን ፈገግታውን ይዞ ነፍሷ ላይ ነገሰ፡፡ ካሳ ይባላል…ባሏ ነው፡፡ የልጅነቷ፣ የወጣትነቷም ድርሳን፡፡ የሚገርመው ይሄ አይደለም…በተሞሸሩ በሰልስቱ ነበር የተለያዩት..መለያየት ስላችሁ የመገፋፋት መለያየት አይደለም እናት ሀገር በጠላት ስትወረር ወጣትነቴን ለሀገሬ ብሎ እምነቱንና ፍቅሩን ለአዲሱ ሚስቱ ትቶ ወደ ጦር ሜዳ ዘመተ፡፡ ጫጉላቸውን እሷ ባዶ ቤት እሱ ደግሞ ጦር ሜዳ ነው ያሳለፉት፡፡ በዛ ላይ እርጉዛ ናት፣ በዛ ላይ ሴት ናት፣ በዛ ላይ የኔ የምትለው ማንም አልነበረም በዚህ ሁሉ
ውስጥ አንቺ ሀገሬ ነሽ፣ አንቺ የዚህ ምድር ጉዳዬ ነሽ ይላት ነበር፡፡ ለኔም ላንቺም አዲስ ለሚወለደውም ልጃችን መልካም ሀገር ታስፈልገናለች ይሄ የሚሆነው ደግሞ ኢትዮጵያን ከጠላት ስንታደጋት ብቻ ነው ይላት ነበር፡፡
የመጨረሻ ውሳኔው ዛሬም ድረስ ከእንቅልፏ ያባንናታል፡፡ ለመጨረሻ ጊዜ ምን ነበር ያላት? ይሄን ስታስብ እንባዋ ሳይመጣ ቀርቶ አያውቅም። ይሄን ስታስብ ሆድ ሳይብሳት ቀርቶ አያውቅም፡፡ ይህን ስታስብ ባር ባር ሳይላት ቀርቶ አያውቅም፡፡ አሁንም በብዙ እንባ፣ በብዙ መከፋት ውስጥ ሆና የመጨረሻ ንግግሩን አሰበችው..‹ለሀገሬ ውለታ ለመዋል ትክክለኛው ጊዜ ላይ ነኝ…ታጥቄና ጦር ሜዳ ዘምቼ የሀገሬን ጠላቶች መፋለም አለብኝ› ‹እየቀለድክ ነው አይደል..? መጀመሪያ ቀን እንዲህ ነበር ያለችው፡፡ ‹በአንቺና በኢትዮጵያ ቀልድ አላውቅም፡፡ አንቺ የልቤ ሀገር ነሽ እሷ ደግሞ የነፍሴ፡፡ ልብ ያለነፍስ ምንም ነው..አንቺ እንድትኖሪ እሷ መኖር አለባት፡፡
‹የመውለጃ ወሬ ደርሶ፣ ከተጋባን ሳምንት ሳይሆነን ትተህኝ ልትሄድ? እንደዛ ቀን ልቧ በድንጋጤ መቶ አያውቅም፡፡
‹ተዋበች ትሙት ! ማለላትተዋበች ትሙት ካለ እውነቱን ነው፡፡ በእናቱ ምሎ ውሸት ሆኖ አይታው አታውቅም፡፡ በዚያ ሰዓት የሆነችውን አታስታውሰውም፡፡
‹ብትሞትብኝስ..ያላንተ እንዴት እሆናለሁ? አይኗ እንባ እያቀረረ ጠየቀችው፡፡
እንዲህ ስትለው አሳዘነችው፡፡ ምን ያክል እንደሚወደት፣ ምን ያክል እንደምትወደው ያውቃል። የኢትዮጵያ ነገር ሆኖበት እንጂ ከእሷ መለየት አይፈልግም፡፡ ‹ሞት ለሀገር ሲሆን ክብር ነው..ደሞ አይዞሽ አልሞትም..ዳግም በፍቅር የምንኖርበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም ሲል እያቀፋት፡፡ ለመጨረሻ ጊዜ ያቀፋት ያኔ ይመስላታል፣ ለመጨረሻ ጊዜ ራሷን እቅፉ ውስጥ ያገኘችው ያኔ ይመስላታል፡፡ ከዚያ በኋላ ያለውን ሁሉ ረስታዋለች፡፡
‹አዲሱ ልጃችን አባቴስ ካለኝ ምን ልበለው? እቅፉ ውስጥ እያለች ጠየቀችው፡፡
ይሄን መመለስ ለእሱ ከባድ ነበር…ቢሆንም ግን የሚያምንበት እውነት ሊነግራት ግዱ ነበር። አይኖቹን እንባ የወረሳቸው አይኖቿ ላይ ሰክቶ ‹ካለሁ እመጣለሁ ከሌለሁም በትውልድ ልብ ውስጥ እንዲፈልገኝ ንገሪው፣ በዛ እገኛለሁ ለኢትዮጵያ ሲሉ የሞቱ ሁሉ በትውልድ ልብ ውስጥ አሉ፡፡ ለሀገር መሞት በትውልድ ውስጥ መፈጠር ነው፡፡ ለሀገር መድከም በታሪክ ውስጥ ማረፍ ነው፡፡ እኔ በአባቶቼ መስዋዕትነት እንደቆምኩ መጪው ትውልድም በእኔ መስዋዕትነት እንዲኖር እፈልጋለሁ፡፡ ለልጄ እንድትነግሪው የምፈልገው የአባትነት መልዕክቴ ይሄ ብቻ ነው፡፡
……….
ሁሌም እሷ ልጇና ባሏ ዳግም የሚገናኙበት ቀን ይናፍቃታል፡፡ በሕይወቷ ውስጥ እንዲሆን የምትሻው እውነት ይሄ ነው፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ መሄዱ ቁጭቷት ነበር..የመጨረሻ ንግግሩ ግን ብርታት ሆኗት ዛሬም ድረስ በጽናት አለች፡፡ ይመጣል እያለች በር በር ታያለች…ትንሿ ቁም ሳጥን በላይ ካለው የእየሱስ ክርስቶስ ምስል ፊት ቆማ ታንሾካሹካለች፡፡
ከሞተም በትውልድ ልብ ውስጥ ትፈልገዋለች፣ ካለም ትጠብቀዋለች፡፡ ሀገር ፍቅርና ቃል አይሞቱምና ፡፡
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ታህሳስ 8 / 2014