ጥበብ ውስጣዊ ስሜትን ፍንትው አድርጎ መግለፅ የሚስችል መንገድ ነው። ጠቢባን ሀሳብና ስሜታቸውን፤ ፈጠራና እይታቸው ለሌላው የሚያደርሱበት መንገድ ደግሞ ይለያያል። ሥነ-ግጥም ከኪነ ጥበብ ዘርፎች ውስጥ ሀሳብን በተዋዛና ዜማዊ በሆነ መልኩ ማቅረብ የሚያስችል፤ ስሜት ከፍ የማድረግ አቅም ያለው ተመራጭ ዘርፍ ነው።
በዛሬው የዘመን ጥበብ አምዳችን በቅርቡ “የወታደር ልጅ ነኝ” በሚል ርዕስ ለህትመት የበቃው የሻለቃ ወይን ሀረግ የግጥም መድብል ይዘትና አጠቃላይ የመፃፉ አንድምታን በሚከተለው መልኩ አይተን ለእናንተ አቀርበናል ፤መልካም ንባብ። ሻለቃ ወይንሀረግ በቀለ ‹‹የወታደር ልጅ ነኝ›› በሚል ርዕስ ያሳተመችው የግጥም መድብል የብዙ መገናኛ ብዙኃን ሲቀባበሉት ነበር።
የግጥም መድብሉ የወታደር ልጅ በመሆኗ ምን ያህል እንደምትኮራ፣ ምን ያህል የአገር ፍቅር ስሜት እንደሰረጸባት ያሳያል። ግጥሞቹን ላጣጣመ ‹‹እኔም የወታደር ልጅ በሆንኩ›› የሚል ስሜት ሳይፈጥርበትም አያልፍ። አሁን ላይ ኢትዮጵያ በገጠማት ፈተና ምክንያት ወታደር መሆን የሁሉም ሰው ድርሻ ሆኖ ‹‹እኔም ወታደር ነኝ›› የሚል ዘመቻ ከተጀመረ ዋል አደር ብሏል። ማንም ሰው ለአገሩ ወታደር ነው። የበለጠ ግን በጦር ግንባር ያለው እና የወታደር ልጅ የሆነ ሊኮራ ይገባል። በነገራችን ላይ በብዙ አጋጣሚዎች ወታደር የነበሩ ሰዎች ሲያወሩ እንደሰማሁት፤ አንድ እንኳን የወታደርነትን ሙያ ያመረረ የለም።
ሰው እንዴት አረንጓዴ የሰራ ውሃ እየጠጣ፣ የደረቅ ብስኩት እየበላ፣ አፈር ለብሶ እያደረ፤ ያ ሕይወት ይናፍቀዋል? ማንም ተንደላቆ ከሚኖረው ባለሙያ በላይ በሙያቸው የሚኮሩ እነዚህ ወታደሮች ናቸው። አንዳንድ ወታደር የነበሩ ሰዎች ደግሞ ‹‹ሁሉም ሰው ትንሽም ቢሆን የውትድርና ሥልጠና ቢወስድ›› የሚል ምክረ ሀሳብ ሲያቀርቡም ይሰማል። ተኳሽ ለመሆን ብቻ አይደለም፤ በውስጡ ያለው የሥነ ምግባር እነጻ እና የአገር ፍቅር ስሜት መስረጽ ነው። የሚገርመው ሲቪል የሆኑ ሰዎች እንኳን ይሄን ሲሉ ይሰማል።
እንግዲህ ይህንን መታደል የታደለችዋ ወታደር ናት ኩራቷን በግጥም የገለጸችው።ይህ የ“ወታደር ልጅ ነኝ” የተሰኘ መድብል እንካችሁ ያለችን ሻለቃ ወይንሀረግ ወታደር ናት፤ አባቷ ወታደር ነበሩ። አባቷ ኢትዮጵያ ሆነዋል፤ ስለዚህ አባቴ ኢትዮጵያ ነው እያለች ነው በኩራት የምትናገረው።
በአባቷ ለአገር መሞት ትኮራለች እንጂ አታለቅስም! ይህን ሀሳብ ለዛ ባለው መልክ የገለፀችበት ‹‹የወታደር ልጅ ነኝ›› ከሚለው መድብሏ የመድብሉ ርዕስ የሆነውን ግጥም እንመልከት። የወታደር ልጅ ነኝ አባቴ ሀገሬን የሚመስለኝ ሀገሬ ነፍሴን የምትመስለኝ ተነካች ሲሉኝ ነፍሴን የሚያመኝ ከሀገር ፈትል የተሸመንኩኝ የሰንደቅ ፍቅር ያሳደገኝ በኢትዮጵያ ጉዳይ ቀልድ የማላውቅ የበረኸኛው ጀግና ልጅ ነኝ አባቷ ኢትዮጵያን ይመስሏታል፤ አባቷም ኢትዮጵያ ናቸው። ኢትዮጵያን ብለው ሞተዋልና ኢትዮጵያ ለሻለቃ ወይንሀረግ አባት ናት፣ ነፍስ ናት።
ከሀገር ፈትል የተሸመነች ስለሆነች፣ በሰንደቅ ፍቅር ስላደገች እነሆ ጀግና ወታደር ሆነች። ኢትዮጵያ ማለት ለእኛ ቤት የነገራችን ማጠንጠኛ የነገራችን መዳረሻ የቤተሰባችን አበይት ጉዳይ የአባታችን ማስታወሻ የማትታይ አባወራ የፀሎታችን ማሳረጊያ አገር ማለት አባታችን አባት ማለት ኢትዮጵያ የሻለቃ ወይንሀረግ ኢትዮጵያ መሆን ቤተሰቡን ስለኢትዮጵያ እንዲያስብ አድርጓታል። የነገራቸው ሁሉ ማጠንጠኛ ነው፣ ቤት ውስጥ የሚወራው ሁሉ ስለኢትዮጵያ ነው ማለት ነው። በዚህ ሁኔታ የሚያድግ ልጅ ጥልቅ የአገር ፍቅር ያለው ነው።
አባቴ ማለት የአገሬ አምሳሌ የማይታይ በአካል መጥቶ በሀሳቤ ብቻ የሚታይ ጠቁሮ የሚያምር እንደ አፈሯ የማልጨብጠው እንደ አየሯ ጠምቶት ሳስበው የምጠማ ምንጮቿ ሥር የሚያውለኝ እርቦት ስስለው በምናቤ ደክሞት ይሆን ወይ ብየ ሳስብ የዛፍ ጥላዋን ለእርሱ የምመኝ አባቴን ከሐገሬ ፀጋ ነጥሎ ማሰብ የተሳነኝ ኢትዮጵያ ሲባል አቤት የምል የጀግና ወታደር ልጅ ነኝ በአገር ፍቅር ስሜት ሌተቀን አገሩንና ሕዝቡን ሲጠብቅ ለሌሎች መስዋዕት ሆኖ እራሱን አሳልፎ የሚሰጠው ወታደር ለገጣሚዋ ልዩ ቦታ አለው። ከራስዋ ሕይወት ጋር እያመሳከረች የኖረችው ማንነት በቃላት ከሽና አቅርባዋለች። ለወታደር ስራው አገር መጠበቅ ሞቱ ለአገር መሰዋዕትነቱ የሕዝብ ሰላም መጠበቅ ነው። ገጣሚዋም ስሜትን እጅኑን በሚኮረኩር መልክ የወታደርን ሕይወት የእሱን መሰዋዕትነት አጉልታ በስንኞችዋ ታመላክታለች።
ገጣሚዋ ቀጥላለች። …. ወጥቶ አዳሪ ነው ከርታታ እረፍት አያውቁም እግሮቹ ድንበሯን ሲቃኙ ያድራሉ አያንቀላፉም አይኖቹ እረፍት አያውቅም ለእረፍቱ አባቴ አሸዋ ልብሱ የምቾቱ ነገር አይገደውም አለት ነው ድንጋይ ትራሱ ምን ቢጎሰቁል አካሉ በርሃብ ቢታጠፍ አንጀቱ ወዙ ጠፍቶ ቢጠወልግ አመዳይ ቢመስል ፊቱ የእግሩ ጣቶች አዝለው ውሃ ጀርባው ቢረሰርስ በላቡ የአገሩን ኪዳን ያኖረበት ሁሌም ታማኝ ነው ጽኑ ልቡ አባቴ አገሬን የሚመስለኝ አገሬ ነፍሴን የምትመስለኝ ተነካች ሲሉኝ ነፍሴን የሚያመኝ ወታደር ለአገሩ ያለው ፍቅር እዚህ ላይ ጎልቶ ይታያል። ያለምቾት ለሌሎች ምቾትና ሰላም ለመፍጠር የሚከፍለው መስዋዕትነት በጉልህ ይንፀባረቃል። ከራሱ በላይ ለሚወዳት ምድሩ ያለስስት የሚያደርገውን ተግባር መዘርዘሩ የግጥሙ ደራሲ ቀጥላለች።እኔ ወታደር ነኝ ብላ የሚሰማትን ስሜት በዚህ መልኩ ታጋባብናለች። …. ከልቤ ምት እኩል የማስባት ከእሷ ውጭ ማሰብ የተሳነኝ በኢትዮጵያ ስም አፍ የፈታሁ የጀግና ወታደር ልጅ ነኝ አባቴ የበረሃው ፈርጥ የኔ አባት የሰውነት ጥግ አገር ነች እምነት ማተቡ ሐቅ ነው ያሳየኝ የእምነት ፈለግ እስከ ሞት የወረደው ዘብ ለቆመላት አገሩ በደም ለለማች አፈሩ በአጥንት ላጠራት ድንበሩ ገጣሚው እጅግ ስሜት ቀስቃሽና ምስል ከሳች በሆነው የቃላት አጠቃቀምና የመግለፅ ከፍ ያለ አቅምዋ ስንኞች የአባቷን ብቻ ሳይሆን የወታደርን ሁሉ ምንነትና ማንነት ነው ያሳየችው።
ምን ሆነው ምን እንደሚያስገኙ ያሳያል። አካላዊ ገጽታቸው ምንም ቢመስል ውስጣቸው ግን የፈካ ነው። ሥጋቸው ተጎሳቁሎ ህሊናቸው ግን የለመለመ ነው። የወታደር ምቾት አገሩን ማድን ነው።
ሺህ ጊዜ ቢሰዋ የሚወድ ቃሉን በተግባር ያጸና የኔ አባት አገር አፍቅሮ ልጁን የረሳኝ ሳተና አባቴ ሰንደቁን ሊያቆም በረሃ የወረደ ጀግና እኔም የአባቴ ልጅ የገባኝ ውትድርና አባቴ ካልሰጠኝ ጊዜ ለአገር በሰጠው የምጽናና በእንቶ ፈንቶ የማልበረግግ ሀቀኝነት ህግ የሆነኝ በኢትዮጵያ ጉዳይ ቀልድ የማላውቅ የጀግና ወታደር ልጅ ነኝ አባቴ አገር ርስቱ ከርታታ አያርፌ እጆቹ ስትናፍቀው እናቴ ስንናፍቀው እኛ ልጆቹ ለአገሩ ይነግራት ይሆናል ከሰንደቋ አርፈው አይኖቹ እንጂማ ደግሞ ደጋግሞ የልጆቹ ውልደት ቢመጣ አባቴ አገር ነውና ወደቤታችን አይመጣ በዓል ዓውደ ዓመት ቢሆንም ገና ፋሲካ ቢከበር አውቃለሁ አባቴ አይመጣም ለምጀው አይለኝም ቅር ተምሬ ስመረቅ ይሁን ወይ ተሞሽሬ ለሰርጌ አባቴን አልጠብቀውም አይመጣም ለወግ ማዕረጌ ይልቅስ ለሰርጌ ድምቀት በተዘረጋው ባንዲራ የአባቴን ምስል እየሳልኩ እቀበላለሁ ምርቃት እረከባለሁ አደራ አዎ! ሰርጓንም፣ ልደቷንም፣ ምርቃቷንም የምታከብረው አባቷ በሥጋ ተገኝተው ሳይሆን ለሚሊዮን ሕዝብ አገር አቁመው ነው። አባቷ ኢትዮጵያ ሆነው ነው። ከኢትዮጵያ በተረከበችው አደራ ነው።
የወታደር ልጅ ነኝና የአባቴን ምስል የሚነግረኝ የሚመርቀኝ ምርቃት ልጄ አገርሽን ውደጃት ከትቢያት በማይመጥ ቀለም ወታደር ለልጁ የሚያወርሰው ከአገር ፍቅር በቀር የለም እንዴት አልወዳት አገሬን የነፍሴን ደማቅ ንቅሳት በሐዘን በደስታዋ ውስጥ የአባቴን እውነት የማይባት አባቴ ማለት አገሬ ኢትዮጵያ ደግሞ የኔ አባት አባቴ አገሬን የሚመስለኝ አገሬ ነፍሴን የምትመስለኝ ሲነኩብኝ ነፍሴን የሚያመኝ ከአገር ፈትል የተሸመንኩ የሰንደቅ ፍቅር ያሳደገኝ በኢትዮጵያ ጉዳይ ቀልድ የማላውቅ የጀግና ወታደር ልጅ ነኝ! የጀግና ወታደር ልጅ እንዲህ ይኮራል።
የእሷም ልጆች ነገ እንዲህ ይኮራሉ። የሁሉም ወታደር ልጆች ይኮራሉ። ውትድርና እንዲህ አገር የኔ ናት ለማለት ያስችላል። የተከፈለው መስዋዕትነት ለሁላችንም ነውና ክብር ለወታደሮቻችን!::
ዋልልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 7/2014