ተወዳጁ የቦክስ ስፖርት ከኦሊምፒክ ሊሰረዝ እንደሚችል የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ቶማስ ባህ አስጠነቀቁ። ከቦክስ ስፖርት በተጨማሪ የክብደት ማንሳትና ዘመናዊ ፔንታትለን ውድድሮች ከኦሊምፒክ የመሰረዝ አደጋ የተደቀነባቸው ስፖርቶች እንደሆኑ ቶማስ ባህ ሰሞኑን ለመገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።
እነዚህ ስፖርቶች በተለይም የዓለም አቀፉ ቦክስ ስፖርት ማህበር በውስጡ ያለውን ብልሹ አሠራርና የተለያዩ ችግሮች ማስተካከል ካልቻለ እኤአ በ2028 የሎሳንጀለስ ኦሊምፒክ ሊሰረዝ እንደሚችል ባህ አስጠንቅቀዋል።
ባህ ይህን ማስጠንቀቂያ በይፋ የተናገሩት በቅርቡ የወጣ አንድ ምርመራና ክትትል ከአምስት ዓመት በፊት በሪዮ 2016 ኦሊምፒክ በስፖርቶቹ በከፍተኛ ደረጃ ሙስና፣ማጭበርበርና ሆን ብሎ ውጤት የመቀየር ቅሌቶች በተጨባጭ ማስረጃ መጋለጣቸውን ተከትሎ ነው።
ይህንን ቅሌት ተከትሎ የቦክስ ስፖርት ትልቅ የፋይናንስ ቀውስ እንደገጠመው የተጠቆመ ሲሆን፣ ይህን ችግር በቅርቡ ማስተካከል ካልቻለ ከሰባት ዓመት በኋላ በሰሜን አሜሪካ ካሊፎርኒያ ግዛት ሎሳንጀለስ ከተማ በሚካሄደው ኦሊምፒክ ሊሰረዝ የሚችልበት እድል እንዳለ ተጠቁሟል።
‹‹ዓለም አቀፉ የቦክስ ስፖርት ማህበር ውስጡ ያለውን ብልሹ አሠራር መመርመርና ማስተካከል ይኖርበታል፣ ማህበሩ የፋይናንስ ግልጽነትን ጨምሮ የስፖርቱ ገለልተኛነትን ማረጋገጥ አለበት፣ የስፖርቱ ዳኞችንና የዳኝነት ስርዓቱንም መፈተሽ አለበት›› በማለትም ባህ ለዓለም አቀፉ የቦክስ ስፖርት ማህበር ጠንከር ያለ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። ይሁን እንጂ የስፖርቱ አስተዳደር እኤአ እስከ 2023 ችግሮቹን መፍታት ከቻለ የሎሳንጀለሱ ኦሊምፒክ አካል እንደሚሆን ጠቁመዋል።
የክብደት ማንሳትና የዘመናዊ ፔንታትለን ስፖርቶችም ከአበረታች ንጥረነገር ቁጥጥርና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር ያሉባቸውን በርካታ ችግሮች መፍታት እንዳለባቸው ተጠቁሟል። ከዚህ በተጨማሪም በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለይም ወጣቶችን በስፋት ተጠቃሚ በማድረግና በበርካታ አገራት ስፖርቶቹ ተዘውታሪ እንዲሆኑ በማድረግ ረገድ መስራት እንደሚኖርባቸው ባህ ጥሪ አቅርበዋል።
የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከበርካታ ዓለም አቀፍ የስፖርት ማህበራት ጋር ተመሳሳይ ውዝግብ ውስጥ ሲገባ እየተስተዋለ የሚገኝ ሲሆን በዓለም ላይ ትልቅ ተቀባይነት ያለው የእግር ኳስ ስፖርትም በተመሳሳይ ከዓለም አቀፍ ኮሚቴው ጋር ውዝግብ ውስጥ መግባቱ ይታወቃል። ይሁን እንጂ እግር ኳስ በሎሳንጀለስ ኦሊምፒክ መካተቱ ተረጋግጧል።
ዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ግን አሁንም ፊፉ በተለይም የዓለም ዋንጫን በየሁለት ዓመቱ ለማካሄድ ከማሰቡ ጋር ተያይዞ የመርሐግብር መጋጨት አወዛጋቢ በመሆኑ ቁጥጥሮችና ግምገማዎች እንደሚኖሩበት መረጃዎች ያመለክታሉ። የቦክስ ስፖርት ከኦሊምፒክ የመሰረዝ አደጋ እንደተደቀነበት መሰማቱን ተከትሎ ጉዳዩ ስፖርታዊ ሳይሆን ፖለቲካዊ ይዘት እንዳለው የተለያዩ መረጃዎች እየወጡ ይገኛሉ።
ዓለም አቀፉ የቦክስ ስፖርት ማህበር ባለፉት ዓመታት ከሙስና ጋር ተያይዞ ቀውስ ውስጥ መግባቱ የአደባባይ ሚስጥር ከመሆኑ ባሻገር ከዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ጋር ቅራኔ ውስጥ እንዳስገባው ይታወቃል። ከዚህ በዘለለ ግን ሁለቱ ዓለም አቀፍ ተቋማት ሆድና ጀርባ የሆኑት የቦክስ ማህበሩ አዲስ ፕሬዚዳንት መምረጡን ተከትሎ ነው።
ይህም ማህበሩን እኤአ ከ2006 እስከ 2017 የመሩት ዉ ቺንግ ኩዎ ከሙስና ጋር ተያይዞ በቀረበባቸው ክስ ከፕሬዚዳንትነት ተነስተው በምትኩ ጋፉር ራክሂሞቭ በመቀመጣቸው ነው። በዚህም ዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ለቦክስ ማህበሩ የሚሰጠውን የገንዘብ ድጋፍ እንዲዘገይ እስከማድረግ ደርሷል።
ራክሞቪች በፕሬዚዳንትነት ለመወዳደር ብቸኛው እጩ ሆነው መቅረባቸው ዓለም አቀፉን ኦሊምፒክ ኮሚቴ ያስቀየመ ሲሆን እኚህ ግለሰብ በአሜሪካ መንግሥት ከወንጀል ቡድን ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው መፈረጃቸው ይታወቃል።
ኡዝቤኪስታናዊው ራክሞቪች በዚህም የተነሳ ከዓመት በፊት በቦነሳይረስ ተካሂዶ በነበረው የወጣቶች ኦሊምፒክ ጨዋታ ላይ ለመገኘት የአርጀንቲና ቪዛ እንደተከለከሉ ይታወሳል። እኚህ ግለሰብ እኤአ ከ2000 የሲድኒ ኦሊምፒክ አንስቶም የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አባል ለመሆን ከሥነምግባር መርሆች አኳያ አይመጥኑም ተብለው መገለላቸው ይታወቃል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 6/2014